Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮጵያ ግብርና ቀዳሚ የሆነው የጤፍ እርሻ በሜካናይዜሽን ሊደገፍ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የግብርና ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ ለማስገባት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ይጠበቃል

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ለአርሶ አደሩ አድካሚ ሆኖ የቆየውን የጤፍ እርሻ ሥራ በሜካናይዜሽን እንዲታገዝ ለማድረግ፣ ለመጀመርያ ጊዜ ጤፍ የሚያጭዱና የሚወቁ ማሽኖችን ከቻይና አስገባ፡፡

ሚኒስቴሩ ለእርሻ ሥራ የሚሆኑ የግብርና ማሽኖች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጥያቄ ማቅረቡም ታውቋል፡፡

ጤፍ የሚያጭድና የሚወቃ ማሽን ለማግኘት ቢሞከርም ሊገኝ ባለመቻሉ፣ መንግሥት ከቻይና ኩባንያ ጋር በመነጋገር እንዲመረት መደረጉ ታውቋል፡፡ በዚህ መሠረት ለመጀመርያ ጊዜ ለጤፍ እርሻ ሥራ እንዲሆኑ ተደርገው የተመረቱ ስምንት ማሽኖች ጂቡቲ ወደብ መድረሳቸው  ተመልክቷል፡፡

ባለፈው ሳምንት ኅዳር 14 ቀን 2010 ዓ.ም. በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሶ ሊበን ወረዳ በተካሄደው የሜካናይዜሽን ቀን ላይ፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ እያሱ አብርሃ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ጤፍ 50 ሚሊዮን ሕዝብ በቋሚነት የሚመገበው ሰብል ነው፡፡ ሦስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ጤፍ ይለማበታል፡፡ ነገር ግን የጤፍ እርሻ ሥራ በሜካናይዜሽን ሳይደገፍ በመቆየቱ አድካሚና የምርት ብክነት የሚታይበት ነው፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት መንግሥት ከቻይና ጤፍ አጭደው የሚወቁ ስምንት ማሽኖች እያስገባ ነው፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ማሽኖቹ በዚህ ሳምንት ጤፍ አምራች በሆነው ምሥራቅ ጎጃም ዞን አገልግሎት ላይ ይውላሉ ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ ጤፍን በመስመር መዝራት እጅግ ምርታማ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለማምረት አግሮ ኬሚካል መጠቀምና አጨዳውና የመውቃቱ ሥራ በሜካናይዜሽን መካሄድ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ጤፍ በማምረት አርሶ አደሩ ከሰባት ላላነሱ ጊዜያት በተደጋጋሚ መሬቱን ማረስ የሚጠበቅበት ሲሆን፣ አጨዳውም ሆነ ውቅያው የሚካሄደው በሰው ጉልበት ላይ በመመሥረት ነው፡፡ ይኼንን አሠራር ለመቀየር የተለያዩ ሙከራዎች ቢደረጉም ውጤታማ ባለመሆናቸው፣ መንግሥት ከቻይና ጋር በመነጋገር እነዚህን ማሽኖች አስመርቷል፡፡ መንግሥት ከዚህም በጥልቀት በመሄድ የአገሪቱን የግብርና ዘርፍ በሜካናይዜሸን የታገዘ እንዲሆን ዕቅድ አውጥቷል፡፡

ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፣ በዓለም አቀፍ መሥፈርት መሠረት በአሥር ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ መኖር የሚገባቸው 66 ትራክተሮች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የጎረቤት አገሮች ደረጃ ሲታይ በኬንያ 26.3 ትራክተሮች፣ በሱዳን ደግሞ 9.6 ትራክተሮች ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ 2.2 ትራክተሮች ብቻ የሚገኝ በመሆኑ አገሪቱ በሜካናይዜሽን ኋላ እንደቀረች ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ መዋቅራዊ ለውጥ ለማድረግ ያቀደች እንደ መሆኑ፣ ለግብርና ሥራ የሚውሉ ማሽኖች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ሚኒስቴሩ አቋም ይዟል፡፡ በዚህ መሠረት ሚኒስቴሩ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች