የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለከተማዋና በአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ነዋሪዎች ንፁህ የመጠጥ ውኃ ለማቅረብ፣ የነደፈውን ግዙፍ ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ ዓለም አቀፍ ጨረታ አወጣ፡፡
ከንቲባ ድሪባ ኩማ ከጥቂት ወራት በፊት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ አስተዳደሩ በራሱ ወጪ በርካታ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቱን ተናግረው ነበር፡፡ በዚህም መሠረት የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችና የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን፣ ሥራውን የበለጠ ለማስፋፋት ደግሞ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ውይይት እያካሄደ መሆኑን ጠቁመውም ነበር፡፡
በዚህም መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን 27 ጥልቅ የመጠጥ ውኃ ጉድጓዶቹን በአዲስ አበባና በበርካታ የኦሮሚያ ልዩ ዞን አካባባቢዎች ለመቆፈርና ግንባታውን ለማካሄድ፣ ዓለም አቀፍ ጨረታ ሰሞኑን አውጥቷል፡፡ ፕሮጀክቶቹ የሚከናወኑት በአራት ቦታዎች ተከፍለው እንደሚሆን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ በዚሁ መሠረት በመጀመርያው ቦታ ሰባት የጥልቅ የመጠጥ ውኃ ጉድጓዶች ቁፋሮና ግንባታ ይከናወናል፡፡
በመጀመሪያው ፕሮጀክት ሥር የተያዙት ፕሮጀክቶች የሚከናወኑት የኦሮሚያ ልዩ ዞን አካል በሆኑት አካባቢዎች ነው፡፡ በቡራዩ፣ በሱሉልታና ሰበታ በእያንዳንዳቸው ሁለት ጥልቅ ጉድጓዶች፣ እንዲሁም በገላን የአንድ ጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮና ግንባታ ተካቷል፡፡ በሁለተኛው ቦታ በተመሳሳይ ሰባት የጥልቅ ጉድጓዶች ቁፋሮና የግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ታቅዷል፡፡ በዚህም መሠረት በለገጣፎና በአቃቂ አካባቢዎች እንደ ቅደም ተከተላቸው ሁለትና አንድ ጥልቅ የመጠጥ ውኃ ጉድጓዶች ቁፋሮና ግንባታ ለማከናወን ሲታቀድ፣ በለገዳዲና ኩዬ አካባቢዎች ሁለት ተለዋጭ የመጠጥ ውኃ ጉድጓዶች፣ እንዲሁም በለገዳዲ አንድ መጠባበቂያ ጥልቅ የመጠጥ ውኃ ጉድጓድ መቆፈርና የግንባታ ሥራዎችን እንደሚከናወኑ ተዘርዝሯል፡፡
በሦስተኛው ፕሮጀክት ሥር ሦስት መጠባበቂያ ጥልቅ የመጠጥ ውኃ ጉድጓዶችን በአቃቂ አካባቢ፣ እንዲሁም አራት አዳዲስ ጥልቅ የመጠጥ ውኃ ጉድጓዶችን በሰበታና በሆለታ አካባቢዎች መቆፈርና የግንባታ ሥራዎችን ማከናወን ተለይተዋል፡፡ በአራተኛው ፕሮጀክት ሥር ስድስት አዳዲስ ጥልቅ የመጠጥ ውኃ ጉድጓዶችን በሰበታና በሆለታ አካባቢዎች መቆፈርና የግንባታ ሥራዎችን ማከናወን ይገኙበታል፡፡
በዘርፉ ልምድ ያላቸው የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት የጨረታ ሰነዱን ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ በመግዛት ፍላጎታቸውን እ.ኤ.አ. እስከ ዲሴምበር 27 ቀን 2017 ድረስ እንዲገልጹ የጊዜ ሰሌዳ የወጣ ሲሆን፣ ዲሴምበር 27 ቀን ጠዋት ጨረታው ተዘግቶ ከቀትር በኋላ ጨረታውን የመክፈት ፕሮግራም ተይዟል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አወቀ ኃይለ ማርያም በቅርቡ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የመጀመሪያዎቹን የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ለማሳካት 660 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ የሚሆኑ የኦሮሚያ ልዩ ዞን አካባቢዎችንም ገልጸው ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በመጀመሪያ ዙር ውኃ የሚቀርብላቸው የአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ገላን፣ በኬ፣ ድሬ፣ ሰንዳፋና በረህ ናቸው፡፡ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ቡራዩ፣ ሰበታ፣ ሱሉልታ፣ ሆለታ፣ ለገጣፎና ለገዳዲ ናቸው፡፡ እነዚህን ከተሞች ውኃ የሚያጠጡ አሥር ጥልቅ ጉድጓዶች እንደሚቆፈሩ በዕቅድ ተይዟል፡፡