Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ አዲስ የባንኮች የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምና አስተዳደር መመርያ አወጣ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሁሉም የአገሪቱ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምና አስተዳደራቸውን በጥብቅ ለመቆጣጠር ያስችላል ያለውን አዲስ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምና አስተዳደር መመርያ አወጣ፡፡ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄያቸው በቅድሚያ መስተናገድ ይገባል ያላቸውን የገቢ ምርቶችም ይፋ አድርጓል፡፡ አዲሱ መመርያ ቁጥር 51/2017 ይባላል፡፡

ብሔራዊ ባንክ የአገሪቱ ባንኮች ከሰኞ ኅዳር 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ያወጣው ይህ መመርያ፣ ውስን የሆነውን የውጭ ምንዛሪ በአግባቡና በጥንቃቄ ማስተዳደር እንዲቻል ከዚህ ቀደም በሥራ ላይ የነበረውን መመርያ ቁጥር 46/2016 የሚተካ ነው፡፡ ተዓማኒነት ያለው የአሠራር ሒደት መከተል እንደሚገባ የሚያሳስበው አዲሱ መመርያ፣ የውጭ ምንዛሪ ለሕገወጥ አሠራር በር ሳይከፈት ቅድሚያ በሚሰጣቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች ሥራ ላይ መዋል እንዳለበት በመግቢያው ላይ ተመልክቷል፡፡

ይህ መመርያ ቁጥጥሩን ያጠብቃሉ የተባሉ ድንጋጌዎች ታክለውበታል፡፡ በአዲሱ መመርያ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባሉ ተብለው በዝርዝር ለተቀመጡት ገቢ ዕቃዎች የሚውለው የውጭ ምንዛሪ መጠን ላይ ገደብ መኖሩ ደግሞ፣ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ላይ አዲስ አሠራር ተግባራዊ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና አስተዳደርን ብቻ ሳይሆን፣ ባንኮች በአመዳደብ ቅድሚያ ሊሰጠዋቸው ይገባሉ ያላቸውን ምርቶችና ሸቀጣ ሸቀጦች በዝርዝር ያስቀመጠ ነው፡፡ ባንኮቹም በዚህ መሠረት አገልግሎት እንዲሰጡ ይደነግጋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ብሎ በዝርዝር ካስቀመጣቸው ምርቶች ውስጥ ነዳጅ፣ ሞተር ዘይት፣ የሲሊንደር ጋዝ፣ ማዳበሪያ፣ የሕክምና መሣሪያዎች፣ የእርሻ መሣሪያዎችና መለዋወጫዎች፣ እንዲሁም የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችና መለዋወጫዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

መመርያው ለነዳጅ፣ ለሲሊንደር፣ ለማዳበሪያና ለመሳሰሉት ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ላላቸው ምርቶች ግዥ ባንኮች በጠቅላላው ከሚሰጡት የውጭ ምንዛሪ መጠን ውስጥ ከ40 በመቶ በታች መስጠት እንደሌለባቸው ይደነግጋል፡፡ መመርያው ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ምርቶችም ቢሆንም መጀመሪያ ለመጣ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ሁሉም የንግድ ባንኮች ብሔራዊ ባንክ የሚጠይቃቸውን መሥፈርቶች ተከትለው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር፣ ደንብና የማስፈጸሚያ መመርያዎችን አውጥተው በግልጽነት እንዲያከናውኑ የቦርድ ዳይሬክተሮች፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ሠራተኞች ሊፈጽሟቸው ይገባል ያላቸውን ድንጋጌዎች መመርያው አካቷል፡፡

ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተገናኘ ሥራ የሚያከናውኑ የባንክ ሠራተኞች በተጠያቂነትና በግልጽነት ሥራቸውን ማከናወን እንደሚገባቸው በመመርያው ተጠቅሷል፡፡

በአዲሱ መመርያ የሁሉም ባንኮች የዳይሬክተሮች ቦርዶች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን መመርያ በመከተል የውጭ ምንዛሪ የአሠራር መመርያ አዘጋጅተው ሥራ ላይ የማዋል ግዴታ እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የእያንዳንዱ ባንክ የዳይሬክተር ቦርድ ቢያንስ በየወሩ የባንኩን የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ይዘት ከተቀመጠው የአሠራር ደንብ ጋር ተገናዝቦ እየተሠራ መሆኑን የመፈተሽና የመመርመር ግዴታ እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡ በተለይ የውጭ ምንዛሪ በበቂ ሁኔታ መኖሩን፣ ይህም በአግባቡ መተግበሩን መፈተሽ እንደ ግዴታ ተቀምጧል፡፡ በመመርያው ቦርዱ የተጣለበት ሌላው ኃላፊነት ተግባራዊ እንዲሆኑ የተዘጋጁ የአሠራር ይዘቶችን ለመከታተል የሚያስችለውን ሥልት ማስፈንና ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ መንገድ መተግበር ነው፡፡

በተመሳሳይ የዋናው ማኔጅመንት አባላት ደግሞ በማንኛውም ጊዜ ለብሔራዊ ባንክ በሚቀርብላቸው ጥያቄ መሠረት የሪከርድ አያያዝ፣ የመረጃና የዶክመንቴሽን አሠራርን ማሻሻል አለባቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዙ ዕለታዊ የቢዝነስ እንቅስቃሴያችንን የሚያሳይ መረጃ ሊኖራቸው ይገባል፡፡

 በሌላ በኩል ዋናው ማኔጅመንት በዋና ጽሕፈት ቤትና በቅርንጫፍ ባንኮቹ መካከል ያለው የሪፖርት አሠራር በአግባቡ እየተከናወነ መሆኑን የመከታተል ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡

ከውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ጋር በተያያዘ ዋናው ማኔጅመንት ሊከውኗቸው ይገባል ተብሎ በግዴታነት ከተቀመጡት ውስጥ፣ ቢያንስ በየወሩ የሚቀርበውን የውጭ ምንዛሪ አስተዳደርና አሠራር በመመርያው መሠረት መተግበሩን ማረጋገጥ ተጠቃሽ ነው፡፡

በሌላም በኩል ዋናው ማኔጅመንት መረጃ የመለዋወጫ ሥልቱን ማጠናከርና ብሎም በሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባ የሚጠቁመው ይህ መመርያ፣ ይህንንም የመከታተልና የመቆጣጠር፣ የባንኩን ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ዝውውርን ሪፖርት ለባንኩ ቦርድና ከፍተኛ የማኔጅመንት ኃላፊዎች የማቅረብ ግዴታንም ይጥልበታል፡፡

የባንኩን ጠቅላላ የውጭ ምንዛሪ ሥራን በአግባቡ መቆጣጠር የሚያስችል ውስጣዊ አሠራር ተግባራዊ ማድረግም የዋናው ማኔጅመንት ግዴታ ሲሆን፣ በተቀመጠለት የአሠራር ይዘት መከናወኑን የማረጋገጥ ግዴታም ተጥሎበታል፡፡ በተለይ የውጭ ምንዛሪ ምጣኔን የሚያሳይ ወቅታዊ የዳታ ቤዝ ሥራን ማከናወን ጨምሮ፣ የውጭ ምንዛሪ ለመግዛት ጥያቄ ያቀረቡና የወሰዱትን የስም ዝርዝርና እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ለደንበኞች የሚፈቀደው ኮሚቴ ቃለ ጉባዔ እንዲኖረው ማድረግም አለበት፡፡

መመርያው የየባንኮቹ የውስጥ ኦዲተሮችም ሊያከውኗቸው የሚገቡ ሥራዎችን አስፍሯል፡፡ የየባንኮቹ የውስጥ ኦዲተሮች ከተጣለባቸው ግዴታ ውስጥ ቢያንስ በግማሽ ዓመት አንድ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ዝውውርና እንቅስቃሴያቸውን ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው መመርያ መሠረት መፈጸሙን ማረጋገጥ ተጠቃሽ ነው፡፡

የውስጥ ኦዲተሮች የኦዲት ግኝታቸውን ሪፖርት ለየባንካቸው ቦርድና ከፍተኛ የማኔጅመንት አመራሮች ማቅረብ የሚኖርባቸው ሲሆን፣ ያቀረቡትንም ሪፖርት ቅጂ በግልባጭ ለብሔራዊ ባንክ የማቅረብ ግዴታም አለባቸው፡፡  

በአዲሱ የብሔራዊ ባንክ መመርያ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀማቸውን በተመለከተ በየሳምንቱ ሪፖርት የማድረግ ግዴታ የሚጥልባቸው ሲሆን፣ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምን የተመለከተውና ለብሔራዊ ባንክ መቅረብ ያለበት ሳምንታዊ ሪፖርት ደግሞ በየባንኩ ለቦታው በተመደበ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ወይም በየባንኩ ዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ዲፓርትመንት በኩል ይቀርባል፡፡

የሪፖርት አቀራረቡም ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ያለውን የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም የሚያሳይ ሆኖ፣ ለውጭ ምንዛሪና ክምችት ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት ቀጣዩ ማክሰኞ ሳያልፍ ለብሔራዊ ባንክ መላክ እንዳለበትም በመመርያው ተመልክቷል፡፡ ሪፖርቱ ተቀባይነት ካገኘበት ፎርማት እንዲሁም ከፕሮፎርማ ኢንቮይስ ጋር ተያይዞ ብሔራዊ ባንክ ለባንኮቹ በሚያሳውቀው ሚስጥራዊ የኢሜይል አድራሻ፣ በየሳምንቱ መላክ እንደሚኖርበትም በመመርያው ተጠቅሷል፡፡

ማንኛውም ባንክ ወይም ግለሰብ ይህንን መመርያ የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት የሚጠቁመው አዲሱ መመርያ፣ ይህንንም ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ ክትትል የሚያደርግበት መሆኑን ይገልጻል፡፡

ይህ መመርያ አስመጪዎችንም ግዴታ ውስጥ የሚከት አንቀጽ ያካተተ ነው፡፡ አስመጪዎች የውጭ ምንዛሪ ጥያቄያቸውን ከአንድ ባንክ በላይ መጠየቅ የሌለባቸው መሆኑን በመግለጽ ክልከላ ያደርጋል፡፡ አስመጪዎች ይህንን ግዴታቸውን የማይፈጽሙና ከመመርያው በተቃርኖ የሚገኙ ከሆነ ከስድስት ወራት እስከ ሁለት ዓመታት ድረስ ጥቁር መዝገብ ውስጥ ይገባሉ፡፡

በተመሳሳይ በዚህ መመርያ በተቀመጡት አሠራሮች መሠረት ኃላፊነቱን መወጣት ያልቻለ ማንኛውም ባንክ፣ ከመመርያው ውጪ በየእንዳንዱ ጥፋት አሥር ሺሕ ብር እንደሚቀጣም ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም በ2000 ዓ.ም. በተሻሻለው የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ 591 መሠረት ተጠያቂ እንደሚሆንም በመመርያው ተገልጿል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች