Saturday, September 30, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በሕዝብ ስም መነገድ ይቁም!

የአገር ውሎና አዳር ጤነኝነት ከሚረጋገጥባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሕዝብ ደኅንነት ነው፡፡ የሕዝብ ደኅንነት በሰላም ወጥቶ ከመግባት በተጨማሪ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ መስኮች እርካታ ማግኘትን ያጠቃልላል፡፡ ሕዝብ የአገሪቱ የሥልጣን የመጨረሻው ሉዓላዊ ባለቤት እንደ መሆኑ መጠን፣ በምርጫ አማካይነት ተወዳድረው ሥልጣን የሚይዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጠሪነታቸው ለእሱ ብቻ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም የሚገነባው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በሕዝብ ስም እየነገዱ ‹ሕዝባዊ ነን› ማለት ጊዜ ያለፈበትና ለዘመኑ የማይመጥን ድርቅና ነው፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ገዥውን ፓርቲ ኢሕአዴግ ጨምሮ፣ በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አለን የሚሉ ኃይሎች ራሳቸውን ሊፈትሹ ይገባል፡፡ በሕዝብ ስም እየነገዱ በፀረ ሕዝብ ተግባር ውስጥ መሰማራት መቆም አለበት፡፡ ለሕግ የበላይነት የሚገዛ አስተሳሰብ ሳይኖር በሕዝብ ስም መቆመር ፋይዳ የለውም፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የአገሪቱን ሥልጣን ከተቆጣጠረ ጊዜ ጀምሮ በሕዝብ ስም ብዙ ብሏል፡፡ ምንም እንኳ በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የሚታዩ በርካታ ለውጦች ቢኖሩም፣ ከ26 ዓመታት በኋላ አገሪቱን ቋፍ ውስጥ የከተቱ በርካታ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡ በኢሕአዴግ ጓዳ ውስጥ ከሚካሄደው ሽኩቻ ጀምሮ በርካታ የሚብላሉ ነገሮች አሉ፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱን ጥያቄ ውስጥ የከተቱና የአገሪቱን ህልውና የሚፈታተኑ ችግሮችን ለመፍታት ባለመቻሉ፣ ከዛሬ ነገ ምን ይመጣ ይሆን የሚለው የብዙዎች ሥጋት ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የግለሰቦች ግጭት የብሔር ገጽታ እየተላበሰ የዜጎች ሕይወት ይቀጠፋል፣ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ይወድማል፡፡ አንፃራዊ የነበረው ሰላምና መረጋጋት ይደፈርሳል፡፡ በአገሪቱ ሕዝብ መካከል አንዳችም ዓይነት ቁርሾና ጥላቻ ሳይኖር፣ አገሪቱን ለውድመት የሚያጋልጡ አሳዛኝ ድርጊቶች ይፈጸማሉ፡፡ በሕዝብ ስም እየተነገደ አገር መቀመቅ ትገባለች፡፡ የወጣቱን ትውልድ መሠረታዊ ችግርች በመፍታት መረጋጋት መፍጠር ሲገባ፣ የበለጠ ትርምስ የሚፈጥሩ እንካ ሰላንቲያዎች ይሰማሉ፡፡ እርስ በርስ በመናቆር መደማመጥ እየጠፋ አገር ትታመሳለች፡፡

ማባሪያ ከሌላቸው ስብሰባዎች፣ ግምገማዎችና ተሃድሶዎች በኋላ የሚሰማው ሁሉ ማድበስበስ ነው፡፡ የአገሪቱ መሠረታዊ ችግር እየታወቀ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ የቡድን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል ብቻ፣ ‹እውነቱ ተነጋግሮ የመሸበት ማደር› ብርቅ ሆኗል፡፡ ትናንት ያለ እኛ ሕዝባዊ የለም ሲሉ የነበሩ ስማቸው የሙስና ጥላሸት ተቀብቶ ሲብጠለጠሉ፣ በመረጃና በማስረጃ ታግዘው ራሳቸውን ሲከላከሉ ማየት አልተቻለም፡፡ የውስጥ ችግሮችን ውጫዊ ገጽታ እያላበሱ ‹ፀረ ሰላምና ፀረ ሕዝብ ኃይሎች› ከሚለው ኩነኔ መውጣት አልታቻለም፡፡ ሕዝብ ብዙ ነገሮችን እያወቀ እንዳላዋቂ መታየቱ ሳያንስ፣ በስሙ የሚሰበሰቡና ውሳኔ የሚያሳልፉ ወገኖች በቁስሉ ላይ እንጨት ይሰዱበታል፡፡ ለዓመታት የተጠራቀሙ ብሶቶች ምክንያታቸው ምን እንደሆነ በግልጽ እየታወቀ፣ ዙሪያ ጥምጥም እየተኬደ ሕዝቡ ያልበላውን እንዲያክ ይደረጋል፡፡ ዋናው ጉዳይ እንደ ዘበት እየታለፈ እዚህ ግባ የማይባሉ ትርኪ ምርኪ ነገሮች ላይ መንጠላጠል ያተረፈው ተዓማኒነት ማጣት ነው፣ ከመጠን ያለፈ ጥላቻ ነው፣ ከዚያ አልፎ ተርፎ ተስፋ መቁረጥ የወለደው ውድመት ነው፡፡ ሕዝብን አክብሮ ለፍላጎቱ ተገዥ መሆን አለመቻል ሰላምን ያደፈርሳል፡፡ አገርን ላላስፈላጊ ትርምስ ይዳርጋል፡፡ ይህ በፍጥነት መቆም አለበት፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‹ትምክህተኛ›፣ ‹ጠባብ›፣ ‹ኮንትሮባንዲስት›፣ ‹ኪራይ ሰብሳቢ›፣ ወዘተ. በሚባሉ የቃላት ጦርነት መወነጃጀሎች በስፋት ይሰማሉ፡፡ እነዚህ ውንጀላዎች በተገኘው አጋጣሚ እርስ በርስ ለመላተም የሚያገለግሉ ሥውር መሣሪያዎች ሆነዋል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ በእነዚህ ቃላት ለመወነጃጀል የሚያስችል የተፈጠረ ችግር እንዳለ ሆኖ፣ በእነዚህ መጠሪያዎች መሰየም ያለባቸው በግልጽ እነማን ናቸው? ማስረጃዎቹስ ምን ያህል አሳማኝ ናቸው? እነዚህ ጥያቄዎች እየቀረቡ ያሉት በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ አገር እያስተዳደሩ ላሉ አካላት ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አገር በሕግ የበላይነት ሥር የምትተዳደር ከሆነ አጥፊ ለሕግ ይቀርባል እንጂ፣ ጊዜ ባለፈበት የፕሮፓጋንዳ ልፈፋ ምንድነው የሚገኘው? በሌላ በኩል ሕዝብን በማጋጨት ለሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ አካላትን በሕጉ መሠረት ለፍትሕ ማቅረብ ሲገባ፣ ለውዝግብ መነሻ የሆኑ አላስፈላጊ የቃላት ጨዋታ ውስጥ ለምን ይገባል? ሕዝብስ ከእንዲህ ዓይነቱ ፋይዳ ቢስ ገመድ ጉተታ የሚያተርፈው ምንድነው? የቃላት ጦርቱን በዚህ መንገድ በመቀጠል አገርን ማፍረስ ይሻላል? ወይስ ወደ ቀልብ ተመልሶ ለሕግ የበላይነት መገዛት? በሕዝብ ስም እየነገዱ አገርን መመለሻ የሌለው ችግር ውስጥ መክተት ሊያበቃ ይገባል፡፡ የቃላት ጦርነት የመጨረሻ ግቡ መጠፋፋት ነው፡፡

በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊ ነን የሚሉ ኃይሎችም ወደ ቀልባቸው መመለስ አለባቸው፡፡ ለአዲሱ ዘመን ትውልድ ከማይመጥንና ጊዜ ካለፈበት የመጠፋፋት አባዜ በመውጣት፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በሚመጥን አቋም ላይ መገኘት የጊዜው ጥያቄ ነው፡፡ የረባ አጀንዳ ሳይኖራቸው በድጎማ ለሚገኝ ገንዘብ ከሚራኮቱ ፓርቲ ተብዬዎች ጀምሮ፣ ከፖለቲካ ሥልጣን በላይ የአገር ጉዳይ በጭንቀት የማያሳስባቸው ከሴራና ከአሻጥር አረንቋ ውስጥ ሊወጡ ይገባል፡፡ ይልቁንም በኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ እንዲጀመር የሕዝብ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤትነት በስፋት እንዲስተጋባ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ ‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው› የሚባለው የደካሞችና የግዴለሾች ልፍስፍስ አስተሳሰብ በዚህች የተከበረች አገር ውስጥ ሥፍራ እንዳይኖረው መታገል ይኖርባቸዋል፡፡ ሥልጣን የሕዝብ ነው እያሉ ሕዝብ ላይ ለመፈናጠጥ መሞከር እንደማያዋጣ በተግባር እየታየ ነውና ለሥልጡን የሰጥቶ መቀበል መርህ ራሳቸውን በማስገዛት፣ በሕግ የበላይነት ሥር የሚተዳደር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን መታገል የሕዝብን ልብ ለማማለል ይረዳል፡፡ ሥልጣን የሚያዘው በሕዝብ ፈቃድ ብቻ መሆኑን ከልብ መቀበል ይጠቅማል፡፡ በሕዝብ ስም እየነገዱ ፀረ ሕዝብ ተግባር ውስጥ መሰማራት ለአገር አይጠቅምም፡፡

ኩሩውና አስተዋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ መከበር አለበት፡፡ ይህ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ወንድሞቹ ታላቅ አርዓያ የሆነ ሕዝብ በገዛ አገሩ በክብር መኖር ይገባዋል፡፡ የሚወዳት አገሩ ሰላም ሰፍኖባት በብልፅግና ጎዳና መራመድ የምትችለው፣ ትውልድ በነፃነት እየኖረባት ሲቀጥል ነው፡፡ የትውልድ ቅብብሎሹ ውጤታማ ሆኖ ከከፍታው ማማ መድረስ የሚቻለው ደግሞ አገር በሕግ የበላይነት ሥር ስትመራ ነው፡፡ በሕዝብ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ መንግሥት ኃላፊነትም ይህ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ማንም እየተነሳ ጉልበተኛ ሲሆን፣ የአገር ሀብት ሲዘርፍ፣ ሕዝብን እያጋጨ ደም ሲያፈስና አገርን መከራ ውስጥ ሲጥል ዝም ማለት በትውልድም በታሪክም ያስጠይቃል፡፡ ሕዝብ በመንግሥት ውሳኔዎች ላይ ያለው ተሳትፎ ወደ ጎን እየተገፋ ግለሰቦችና ቡድኖች የሚያብጡበት ሥርዓት አገር ያጠፋል፡፡ በሕዝብ ስም እየተነገደ ከሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ መንጎድ ለበለጠ ትርምስ በር ይከፍታል፡፡ ከዚህ ይልቅ የተበላሸውን የፖለቲካ ምኅዳር አስተካክሎ ለሕዝብ ፈቃድ የሚገዛ ሥርዓት ለመመሥረት መነሳት ያስከብራል፡፡ አገርም ትውልድም በዘለቄታዊነት መቀጠል የሚችሉት በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም በሕዝብ ስም መነገድ ይብቃ መባል አለበት!

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...

ማን በማን ላይ ተስፋ ይኑረው?

በአንድነት ኃይሉ ችግሮቻችንን ለይተን ካወቅን መፍትሔውንና ተስፋ የምናደርግበትን ማወቅ እንችላለን፡፡...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...