Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎችን ግጭት ሲከታተል የነበረው ግብረ ኃይል አዲስ ውሳኔ ማስተላለፉ ታወቀ

የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎችን ግጭት ሲከታተል የነበረው ግብረ ኃይል አዲስ ውሳኔ ማስተላለፉ ታወቀ

ቀን:

ከወራት በፊት በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት ሲከታተል የነበረው ግብረ ኃይል፣ አዲስ ውሳኔ ማስተላለፉ ታወቀ፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራው የፌዴራል ግብረ ኃይል ቅዳሜ ኅዳር 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ የሶማሌ ክልል በግጭቱ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋል ባለመቻሉ፣ ተባባሪ ያልነበሩ አመራሮች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ውሳኔ ማስተላለፉ ታውቋል፡፡ ከዚህ በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ውሳኔ የሶማሌ ክልል አንዳንድ የፀጥታ አካላትና አመራሮች ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ሳቢያ፣ በግጭቱ ተሳታፊ የነበሩ አካላትን በቁጥጥር ሥር ማዋል እንዳልተቻለ ታውቋል፡፡

የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት አገሪቱ ያለችበትን ፀጥታ በተመለከተ ከክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮችና ከፀጥታ አካላት ጋር በቅርቡ ውይይት ባደረገበት ወቅት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁለቱም ክልሎች አመራሮች በግጭቱ እጃቸው ያለባቸውንና የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር እንዲያውሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ የሶማሌ ክልል ውስን አመራሮች ይህንን ተግባራዊ ባለማድረጋቸው የሁለቱ ክልሎች የሕዝብ ለሕዝብ ኮንፈረንስ ማካሄድ እንዳልተቻለ ተጠቁሟል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ስማቸው እንዳይጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የኦሮሚያ ክልል በግጭቱ እጃቸው አለበት የተባሉትን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ቢያውልም የሶማሌ ክልል ተባባሪ አልሆነም፡፡

የሶማሌ ክልል አመራሮችና የፀጥታ አካላት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ለግብረ ኃይሉ ሪፖርት መቅረቡም ታውቋል፡፡ ግብረ ኃይሉ የፌዴራል ፖሊስ ያቀረበውን ሪፖርት ካዳመጠ በኋላ የተጠረጠሩትን በሕግ ጥላ ሥር ለማዋል በተደረገው ጥረት፣ ተባባሪ ያልነበሩ የክልሉ አመራሮች ተጠያቂ እንዲሆኑ መመርያ መተላለፉን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) እሑድ ኅዳር 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት በጉጂ፣ በባሌና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች አዲስ ግጭቶች ተከስተው ከ20 በላይ ዜጎች ሕይወት አልፏል፣ በርካቶች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ግብረ ኃይሉም ይህንን መገምገሙን አስረድተዋል፡፡

እንደ አዲስ በተቀሰቀሰው ግጭትም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ዜጎች ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ የፌዴራል የአደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ለግብረ ኃይሉ ባቀረበው ሪፖርትም፣ ከዚህ በፊት ተፈናቅለው የነበሩና በመጠለያ ካምፖች የሚኖሩ ዜጎች የሥነ ልቦና ችግር እየደረሰባቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ተፈናቃዮችም ከመጠለያ ካምፖች መውጣትና ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ እንደሚፈልጉ መገለጹን ጠቅሰዋል፡፡

ሚኒስትሩ ሕግን ከማስከበር አኳያ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል በተመሳሳይ መጠን እየተሠራ እንዳልሆነ መገምገሙንም አስረድተዋል፡፡ ‹‹በኦሮሚያ ክልል በተለይም በአወዳይ በነበረው ግጭት እንደተሳተፉ የተጠረጠሩ 54 ሰዎችን የክልሉ መንግሥት በቁጥጥር ሥር አውሏል፤›› ብለዋል፡፡  

የፌዴራል ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ባደረገው ጥረት የኦሮሚያ ክልል ጥሩ ትብብር እያደረገለት መሆኑን ሪፖርት እንዳቀረበ አስረድተዋል፡፡ 44 ተጠርጣሪዎችም በፌዴራል የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው እየተመረመረ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ በአጠቃላይ 98 ተጠርጣሪዎች በክልሉ በሕግ ጥላ ሥር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

በሶማሌ ክልል ሕግን ከማስከበር አኳያ በፌዴራል ፖሊስ አማካይነቱ 38 ተጠርጣሪዎች እንደተለዩ፣ ከእነዚህ መካከል በዘጠኙ ላይ አሁንም ማጣራት እንደሚያስፈልግ፣ 29 ተጠርጣሪዎች ግን የእስር ትዕዛዝ ወጥቶባቸው በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየተሠራ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ እስካሁን ድረስ አምስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ አስረድተዋል፡፡

ሰላሳ ስምንቱ ተጠርጣሪዎች በፌዴራል ፖሊስና በመከላከያ መለየታቸውንና ቁጥራቸው ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ግብረ ኃይሉ መገምገሙን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ የሶማሌ ክልል ተመሳሳይ ዕርምጃ እንዲወስድ ቅሬታ እያቀረበ እንደሆነም ግብረ ኃይሉ መገምገሙን አክለዋል፡፡  

ሕግን ከማስከበር አኳያ የሶማሌ ክልል ተባባሪ እንዲሆን ግብረ ኃይሉ እንዳሳሰበና ተባባሪ በማይሆኑ አካላት ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ መወሰኑንም አስረድተዋል፡፡

ከሁለቱ ክልሎች የአገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ኅዳር 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ሊካሄድ የነበረው የሰላም ኮንፈረንስ በተለያዩ ምክንያቶች ማካሄድ እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡ በምክንያትነት ከቀረቡ ጉዳዮች መካከልም የኦሮሚያ ክልል በሕግ ማስከበር ላይ ጥያቄ በማቅረቡ ነው ብለዋል፡፡

ከሁለት ሳምንታት በፊት የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ዓብዲ መሐመድ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ፣ ‹‹ጥፋተኛ የሆኑ አካላትን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየሠራን ነው፤›› ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ በክልሉ ላይ እየቀረበ ያለው ቅሬታ ግን ከሰጡት አስተያየት  ተቃራኒ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከ2010 ዓ.ም. መግቢያ ጀምሮ እየተከሰተ ባለው ግጭት የበርካቶች ሕይወት እንደጠፋና በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩት ደግሞ ከመኖሪያ ቀዬአቸው እንደተፈናቀሉ የሚታወስ ሲሆን፣ ግጭቱ እስካሁን እንዳልቆመ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡   

በጉዳዩ ላይ የሶማሌ ክልል የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊን በስልክ ለማነጋገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...