‹‹ባሳለፍነው ዓመት የገጠመን አገራዊ ችግር በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች ሁከትና ግጭት መቀስቀስና አንፃራዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት መታየቱ ነበር፡፡ ይህን የመሰለው ችግር በየአካባቢው እንዲቀሰቀስ ምክንያት የሆኑ ወቅታዊ ችግሮች እንደነበሩ ባይካድም፣ ከተከሰተበት ሁኔታና ከደረሰው የሕይወትና የንብረት ጉዳት በመነሳት መሠረታዊ ምክንያቶቹን በውል ማስቀመጥ ይገባል፤›› ይህንን ያሉት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶችን የ2009 ዓ.ም. የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ በንግግር በከፈቱበት ወቅት ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር ተከትሎ መደበኛ የሥራ ዘመኑን ኃላፊነቶች መወጣት የጀመረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ጥር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ለአንድ ወር የዕረፍት ጊዜ ተበትኗል፡፡
ፓርላማው ለዕረፍት ከመበተኑ አስቀድሞ በነበሩት አራት ወራት ውስጥ 16 መደበኛ ጉባዔዎችን አካሂዷል፡፡ በእነዚህ መደበኛ ጉባዔዎች ካከናወናቸው ተግባራት መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የቀረበውን የካቢኔ ሹም ሽር ተወያይቶ ማፅደቅ ሲሆን፣ ከሁሉም በላይ ግን ሹም ሽሩን ተከትሎ ያፀደቀው የስድስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተለየና በበርካቶች ዘንድ አይረሴ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በመላ አገሪቱ ላይ የተጣለ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመሆኑ ነው፡፡ ፓርላማውም የዚህ ታሪካዊ ውሳኔ አካል በመሆኑ የተለየ ያደርገዋል፡፡
ፓርላማው ከዚህ ባለፈም የተለያዩ አዋጆችንና የብድር ስምምነቶችን አፅድቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የተለያዩ ሚኒስትሮችን በመጥራት የፓርላማ አባላት ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚዎችን የሥራ ክንውን ሪፖርት አዳምጧል፡፡ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎችም በተናጠል የሚከታተሏቸውን አስፈጻሚ አካላት ሪፖርት አዳምጠዋል፡፡ በተለይ የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተለያዩ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶችን በመጥራት በተገኘባቸው የኦዲት ውጤት ችግሮቻቸውን በተመለከተና የወሰዱትን የመፍትሔ ዕርምጃ አስመልክቶ ክትትል አድርጓል፡፡
የፕሬዚዳንቱ ንግግር ማጠንጠኛና የፓርላማው ተግባራት
ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ የሁለቱ ምክር ቤቶችን የጋራ ጉባዔ በንግግር በመክፈት፣ መንግሥት በ2009 ዓ.ም. ቅድሚያ ሊጣቸው ይገባል ያሏቸውን መሠረታዊ ነጥቦች ይፋ አድርገዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ያነሷቸው መሠረታዊ ነጥቦች በጥቅሉ ያጠነጠኑት አገሪቱ በ2008 ዓ.ም. በገጠማት የፖለቲካ አለመረጋጋት ላይ ነው፡፡ አገሪቱ ለገጠማት የፖለቲካ ቀውስ መሠረታዊ ምክንያቶች ናቸው ካሏቸው ውስጥ፣ በመንግሥት አመራር አካላት ዘንድ የሚታይ ምግባረ ብልሹነት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ምግባረ ብልሹነቱ ደግሞ በመንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የተቀመጡ ሰዎች የተረከቡትን ሕዝባዊ አደራ ለኅብረተሰባዊ ለውጥ መጠቀሚያነት ከማዋል ይልቅ፣ የግል ኑሯቸውን ማበልፀጊያ መሣሪያ አድርገው እየተጠቀመበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ፓርላማው ሥራውን በሚጀምርበት ወቅት የፌዴራል መንግሥትን የአመራር ሥርዓት በአዲስ መልክ እንዲቃኝ ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የሥራ አስፈጻሚው ሰብሳቢ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ያቀረቡትን የካቢኔ ሹም ሽር ፓርላማው ተቀብሎ አፅድቆታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቀረቡት አዲስ ካቢኔ ውስጥ ዘጠኝ ነባር የአመራር አባላትን በነበሩበት ቦታ እንዲቆዩ ያደረጉ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 21 ሚኒስትሮችና ከፍተኛ አመራሮች ላይ ሹም ሽር አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው የፓርቲ አባል እንዳልሆኑም ይነገራል፡፡
ፓርላማው ሥራ ከመጀመሩ አስቀድሞ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅንም ፓርላማው በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ማፅደቁ አይዘነጋም፡፡
‹‹ለማንም ግልጽ እንደሚሆነው ባሳለፍነው 2008 ዓ.ም. በተከሰቱት ግጭቶች ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የነበሩት የአገራችን ወጣቶች ነበሩ፡፡ ይህ እውነታ ወጣቶቻችን የሚገኙበትን ሁኔታ በትክክል መገንዘብና ለችግራቸውና ለጥያቄያቸው የሚመጥን መሠረታዊ መፍትሔ ማቅረብ አጣዳፊ ሆኖ ይገኛል፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡
መንግሥት ከዚህ ቀደም የነበሩ የወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄዎችን ለመመለስ በርካታ ተግባራትን እንዳከናወነ ያስታወሱት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ፣ እያደገ ከመጣው የወጣት ቁጥርና ፍላጎት ጋር ሲነፃፀር በመንግሥት የተከናውኑ ተግባራት ተመጣጣኝ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የተከሰቱት ችግሮች በመሠረቱ ከኢኮኖሚ ፍላጎትና ተጠቃሚነት ጋር የተያያዙ በመሆናቸው፣ እነዚህን ችግሮች ወጣቶችን በሚያሳትፍ አኳኋን መፍታት ጊዜ የማይሰጠው ተግባር መሆኑን አሳስበው ነበር፡፡
በፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ መሠረት በማድረግም ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ አሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ እንዲቋቋም ለፓርላማው ጥያቄ አቅርቧል፡፡ የቀረበውን የፈንዱ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ለዕረፍት ከመበተኑ አስቀድሞ አፅድቆታል፡፡
በዚህ አዋጅ መሠረት መንግሥት ለሥራ ፈጠራ የመደበውን ፈንድ የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲሆን፣ ከ18 ዓመት እስከ 35 ዓመት ያሉ የአገሪቱ ወጣቶች ምንም ዓይነት ማስያዣ ሳያቀርቡ መበደር የሚቻልበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ሌላው ያነሱት ነጥብ የአገሪቱ የዴሞክራሲያዊሥርዓት ብዝኃነትን እንዲያስተናግድ የማድረግ አስፈላጊነት አንዱ ነው፡፡ አገሪቱ በምትከተለው የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ላለፉት ሃያ አራት ዓመታት በድምሩ ለአሥር ጊዜ አገራዊ፣ ክልላዊና አካባቢያዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ በእነዚህ ምርጫዎች የብዙ ፓርቲዎች ተሳትፎ የነበረ በመሆኑ፣ በተለይ ባለፉት ሁለት ምርጫዎች ግን የገዥው ፓርቲ ሙሉ በሙሉ የበላይነት የታየባቸው ሁኔታዎች መስተዋላቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህም ተቃዋሚዎችን የመረጡ የኅብረተሰብ ክፍል ድምፆች እንዳይደመጡ ማድረጉን የተናገሩት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ፣ በዚህም ሳቢያ ሥርዓቱ ተረጋጋቶ እንዳይቀጥል አድርጓል ማለታቸው ይታወሳል፡፡ በመፍትሔነትም ልዩ ልዩ መድረኮችን በመክፈት የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ረገድም ፓርላማው ሁለተኛውን የሰብዓዊ መብት ድርጊቶች መርሐ ግብር ከማፅደቁ አስቀድሞ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማወያየት በርካታ ግብዓቶች እንዲካተቱ አድርጓል፡፡ ይህ ቢሆንም ተቃዋሚዎችን ያሳዘነ ጠቃሚ ሊባሉ የሚችሉ ወሳኝ ግብዓቶችንም ሳያካትት አልፏል፡፡
ፕሬዚዳንት ሙላቱ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን አስመልክቶ ሌላው በመፍትሔነት ያስቀመጡት ገዥው ፓርቲ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በመደራደር የምርጫ ሕጉን የማሻሻል ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡
ይህንንም በተመለከተ ፓርላማው በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በቅርቡ የተጀመረውን ውይይትና ድርድር በጽሕፈት ቤቱ አማካይነት በገለልተኝነት የመምራትና የማስተባበር ሥራ ማከናወን ጀምሯል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ሌላው ያነሱት ጉዳይ ለግጭት መነሻ ከሆኑት ነጥቦች አንዱ የሆነው የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ሕገ መንግሥታዊ የተጠቃሚነት መብት እንዲከበር የሚለው ይገኝበታል፡፡ ከዚህም አኳያ ፓርላማው ዘንድሮ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ፓርላማው መደንገግ እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል፡፡
ይህ ኃላፊነት ፓርላማው ለዕረፍት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በረቅቅነትም አልቀረበም፡፡ በመሆኑም በቀጣይ የግማሽ ዓመት የሥራ ዘመኑ ተግባራዊ እንደሚሆን ይበጠቃል፡፡
ጉድለቶቹ
ፓርላማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማፅደቁና የራሱን መርማሪ ቦርድ ማቋቋሙ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ መርማሪ ቦርድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም በተመለከተ ያለውን አስተያየት የአስቸኳይ ጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት የማቅረብ ኃላፊነት ቢኖረውም፣ ፓርላማው ግን በራሱ መንገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸምና ለአገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውሶች ምክንያት የሆኑ መነሻዎች ምላሽ እያገኙ ስለመሆናቸውና ሌሎች ለሕዝብ ቅሬታ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፈተሽ አልሞከረም፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ፓርላማው በመንግሥት ላይ የሚያደርገው ቁጥጥርና ክትትል ወጥነት የሌለውና በፖለቲካ የተቃኘ ይመስላል፡፡ ለአብነት ያህል ለፓርላማው ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርጉት ቋሚ ኮሚቴዎች መንግሥት ካቢኔውን በምሁራን እንዳደራጀው ሁሉ፣ ከሚከታተሏቸው ተቋማት ጋር የቀረበ ልምድና ዕውቀት ባላቸው የምክር ቤት አባላት እንዲመሩ ማድረግ አልቻለም፡፡
ይህንንም አስመልክቶ ከአንዳንድ የምክር ቤት አባላት ጥያቄ ተነስቶ የነበረ ቢሆንም በቂ ምላሽ ማግኘት አልቻለም፡፡
በሌላ በኩል ቋሚ ኮሚቴዎች በመንግሥት ላይ የሚያደርጉት ክትትልና ቁጥጥር በምንም ዓይነት ሁኔታ ለጋዜጠኞች ዝግ መሆን የሌለበት ነው፡፡ የፓርላማው የአሠራርና የአባላት ሥነ ሥርዓት ደንብ በዝግ ሊካሄዱ የሚችሉ የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባዎች አስመልክቶ የሚደነግገው ከአገር ደኅንነት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የቋሚ ኮሚቴ የክትትልና የቁጥጥር ስብሰባዎች ዝግ ስለሚሆኑበት ሁኔታ የሚለው ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ ችግር እንዳለባቸው የሚታወቁ መሥሪያ ቤቶች ላይ ጋዜጠኞችን በማስወጣት በዝግ ሪፖርታቸውን አዳምጧል፡፡
ከእነዚህም መሥሪያ ቤቶች መካከል የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ኬሚካል ኮርፖሬሽን ይገኙበታል፡፡ ሁለቱ መሥሪያ ቤቶች የያዟቸው የስኳር ፕሮጀክቶችና የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ መጠናቀቅ ባለመቻላቸው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በመንግሥት ላይ ቅሬታ እያቀረቡ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
በመሆኑም ፓርላማው በእነዚህ መሥሪያ ቤቶች ላይ በሚያደርገው ቁጥጥር በሩን ለጋዜጠኞች ዝግ አድርጎ ማካሄዱ፣ የመንግሥትን ጉድለቶች የመደበቅ አዝማሚያ እንዳለው ማሳያ እየመሰለ ነው፡፡