Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ባንክ በስድስት ወራት 7.8 ቢሊዮን ብር አተረፍኩ አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  ከ2.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ተገኝቷል ብሏል

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2009 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከታክስ በፊት 7.8 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡ ባንኩ ዓርብ የካቲት 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በበጀት ዓመቱ የስድስት ወራት አፈጻጸም ከታክስ በፊት 15.5 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገልጿል፡፡ በግማሽ ዓመቱም የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 414.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን ጠቁሟል፡፡

የስድስት ወራት የአፈጻጸም ግምገማ የባንኩ የበላይ ሥራ አመራር በተገኘበት ከጥር 18 እስከ ጥር 20 ቀን 2009 ዓ.ም. በሐዋሳ መካሄዱን የገለጸው የባንኩ መግለጫ፣ በአመዛኙ መልካም ውጤት ተመዝግቧል ብሏል፡፡

በግማሽ ዓመቱ አፈጻጸም መሠረት ከ31.8 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉን፣ ይህም ክንውን የንግድ ባንክን ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ከነበረበት 288.5 ቢሊዮን ብር ወደ 320.2 ቢሊዮን ብር እንዳሳደገው ተገልጿል፡፡

ከተቀማጭ ገንዘብና ከብድር አሰባሰብ የተገኘውን ገንዘብ መልሶ ለተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች በብድር ማቅረብ ሌላው ዓብይ ተግባሩ እንደሆነ የገለጸው ንግድ ባንክ፣ በግማሽ ዓመቱ 28.2 ቢሊዮን ብር ከብድር ተመላሽ መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል 40.4 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር በማቅረብ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን መደገፉን ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ከ2.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ ከወጪ ንግድ የተገኘው 332.5 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን፣ ወደ አገር ውስጥ ከተላከው ሃዋላ ደግሞ 1.9 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቱን ጠቁሟል፡፡

በግማሽ ዓመቱ በርካታ ቅርንጫፎችን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች መክፈቱን ያስታወቀው ባንኩ፣ የቅርንጫፎቹን ብዛት ከ1,500 በላይ ማድረሱን በመግለጫው ጠቅሷል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት 266 የኤቲኤምና 239 የፖስ ማሽኖችን ሥራ ላይ በማዋል፣ የኤቲኤምና የፖስ ማሽኖችን ቁጥር እንደ ቅደም ተከተላቸው 1,155 እና 6,508 ማድረስ መቻሉን ገልጿል፡፡

በስድስት ወራት 807,831 የባንክ ካርዶችን ለደንበኞች በማሠራጨት የተጠቃሚዎችን ቁጥር 3,298,826 ማድረሱን ገልጾ፣ ይህ ክንውን ኅብረተሰቡን ከዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ጋር ይበልጥ ማስተዋወቁን አስረድቷል፡፡ የሞባይል ባንክ ተጠቃሚዎች ቁጥር 1,262,399 መድረሱን፣ የኢንተርኔት ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር ደግሞ 19,114 እንደደረሰ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች