Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዲስ አበባ ከስድስት ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የፍሳሽ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማን የፍሳሽ ቆሻሻ በመስመር የማንሳት አቅም አሁን ካለበት አሥር በመቶ ሽፋን፣ ወደ 64 በመቶ ከፍ የሚያደርጉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ከስድስት ቢሊዮን ብር በበለጠ ወጪ እየተካሄደ ነው፡፡

ግንባታዎቹ በአሁኑ ወቅት በአማካይ 70 በመቶ የደረሱ ሲሆን፣ የተለየ ችግር ካላጋጠመ በስተቀር በ2010 ዓ.ም. የመጀመሪያዎች ወራት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አወቀ ኃይለ ማርያም ገልጸዋል፡፡ ረቡዕ የካቲት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. የፕሮጀክት ሳይቶቹ በተጎበኙበት ወቅት አቶ አወቀ እንደገለጹት፣ በአጠቃላይ እነዚህ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የአዲስ አበባ ከተማ አብዛኛው ክፍል በዘመናዊ መንገድ የፍሳሽ ቆሻሻዎችን ማስወገድ ይቻላል፡፡

የአዲስ አበባ ፍሳሽ ቆሻሻዎች በሁለት መንገድ ይሰበስባሉ፡፡ የመጀመሪያው በፍሳሽ ቆሻሻ ተሽከርካሪ (ቦቴ)፣ ሁለተኛው ደግሞ በመስመር (ቱቦ) አማካይነት ነው፡፡ የከተማው ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በርካታ የፍሳሽ ማስወገጃ ተሽከርካሪዎች በማሠማራትና እስከ ስምንት ጊዜ ምልልስ በማድረግ የከተማውን ፍሳሽ ቆሻሻ እንደሚያነሳ ቀሪው ደግሞ አሥር በመቶ ብቻ ሽፋን ባለው መስመር እንደሚወገድ ተገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ ፍሳሽ የማንሳት ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ቢኖረውም፣ አንድ ዘመናዊ ከተማ ሊኖረው የሚገባው የፈሳሽ ማስወገጃ አውታር ባለመዘርጋቱ ቅሬታዎች ሲቀርቡ ነበር፡፡

በዚህ መሠረት የከተማው አስተዳደር ለፍሳሽ ማስወገጃ ፕሮጀክቶች ግንባታ ትኩረት በማድረግ፣ የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያና ፍሻስ መስመር ግንባታ ፕሮጀክት ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ ታውቋል፡፡

ግዙፉ የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክት በቀን 100 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ የማጣራት አቅም አለው፡፡ ይኼ ፕሮጀክት ዕውን ሲሆን ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ፣ ቂርቆስ፣ ልደታ፣ አራዳና ጉለሌ ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል፡፡

ይህ ፕሮጀክት በ2010 ዓ.ም. ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ለፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚያስፈልገው አጠቃላይ በጀት 2.9 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ የማጣሪያ ጣቢያው ግንባታና የ18 ኪሎ ሜትር የፍሳሽ መስመር ዝርጋታ ሥራ፣ ሙሉ በሙሉ በዓለም ባንክ ብድር የሚሸፈን መሆኑን ባለሥልጣኑ አስረድቷል፡፡ የ80 ኪሎ ሜትር የመለስተኛና የ28 ኪሎ ሜትር የዋና ፍሳሽ መስመር ዕቃ አቅርቦትና ዝርጋታ ሥራዎች ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት በጀት ይሸፈናሉ፡፡

ግንባታውን የግሪክ ኩባንያ በሆነው ኦክቶር፣ የዋና ፍሳሽ መስመር ዝርጋታ ሥራውን ደግሞ የቤልጂየም ኩባንያ በሆነው ዴኒስ ኮንስትራክሽን እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ከዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት በተጨማሪ በአቃቂ ፍሳሽ ተፋሰስ የጨፌ ክፍል አንድ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያና የፍሳሽ መስመር ግንባታ ፕሮጀክት ግንባታ እየተካሄደ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት በቀን 12,500 ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ የማጣራት አቅም አለው፡፡ ከ50 ሺሕ በላይ ቤቶች በተገነቡበት ኮዬ ፈጬ ያልተማከለ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያን ጨምሮ በቦሌ ቡልቡላ፣ መካኒሳ፣ ቆጣሪ፣ ደግነት፣ ካራ ቆሬ ሳይቶች አገልግሎት የሚሰጠው የኮንቴይነር ያልተማከለ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ግንባታ ፕሮጀክት ጋር በድምሩ በቀን 60 ሺሕ ሜትር ኪዩብ የማጣራት አቅም ያላቸው ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ ነው፡፡ አቶ አወቀ እንደገለጹት የእነዚህ ፕሮጀክት ግንባታ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች