Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዕውቁ የታሪክ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ሥርዓተ ቀብር ነገ ይፈጸማል

የዕውቁ የታሪክ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ሥርዓተ ቀብር ነገ ይፈጸማል

ቀን:

በኢትዮጵያ የታሪክና ማኅበራዊ ጥናት ሁነኛ ሥፍራ የነበራቸው ዕውቁ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ሥርዓተ ቀብር፣ ሰኞ የካቲት 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ይፈጸማል፡፡ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ያረፉት ባለፈው ሐሙስ የካቲት 9 ቀን ነበር፡፡

ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ከአስተማሪነት እስከ ተመራማሪነት እንዲሁም በኃላፊነት ያገለገሉት ፕሮፌሰር ፓንክረስት፣ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋምን ከመሠረቱት አንዱና የመጀመሪያው ዋና ዳይሬክተር ነበሩ፡፡ ቤተ መጻሕፍቱን፣ ሙዚየሙንና የሥነ ጥበብ ጋለሪውን በማደራጀትና በማስፋፋት ይጠቀሳሉ፡፡

በኢጣሊያ (ሮም) የተጀመረውና ሁለት ጊዜ በውጭ አገሮች የተካሄደው የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ፣ በ1958 ዓ.ም. በአዲስ አበባ 3ኛው እንዲካሄድ በማድረግ የነበራቸው ሚናም ይወሳል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በተቋሙ የሚታተመው ‹‹የኢትዮጵያ ጥናት መጽሔት›› (Journal of Ethiopian Studies) በ1948 ዓ.ም. (1956) ካቋቋሙት አንዱና ኤዲተርም ሆነው እስከ 1966 ዓ.ም. (1974) አገልግለዋል፡፡ በመጀመሪያዎቹ ሁለት አሠርታት አካዴሚያዊ ጉዞዋቸው የኢትዮጵያን የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ታሪክ በተመለከተ እ.ኤ.አ. በ1961 ‹‹ኢንትሮዳክሽን ቱ ዘ ኢኮኖሚክ ሂስትሪ ኦፍ ኢትዮጵያ›› (Introduction to the Economic History of Ethiopia)፣ በ1965 ‹‹ስቴት ኤንድ ላንድ ኢን ኢትዮጵያን ሂስትሪ›› (State and Land in Ethiopia History)፣ በ1968 ‹‹ኢኮኖሚክ ሂስትሪ ኦፍ ኢትዮጵያ 1800-1935›› (Economic History of Ethiopia 1800-1935) አሳትመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በ1965 ዓ.ም. ፓንክረስት ለኢትዮጵያ ጥናት ያደረጉትን ተግባር በማክበር ስመ ጥር የሆነው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማትን ሸልሟቸዋል፡፡

የዘውዳዊው ሥርዓቱ መገርሰስና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኅልፈትን ተከትሎ በ1968 ዓ.ም.  ወደ አገራቸው እንግሊዝ ያመሩት ፕሮፌሰር ፓንክረስት በ1979 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ በመመለስ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋምን ሲቀላቀሉ በተከታታይ ዓመታት በርካታ ኢትዮጵያ ተኮር መጻሕፍትን በግልና በጋራ አዘጋጅተዋል፡፡ የኅትመት ትሩፋታቸው ከ25 በላይ መጻሕፍት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ መጣጥፎችና ሐቲቶችንም ያካተተ ነው፡፡ የነፃ ፕሬስ መባትን ተከትሎ በኢትዮጵያ ታሪካዊና ባህላዊ ጉዳዮች ላይ ሥሉጥ ግንዛቤን ለአንባቢያን ለመፍጠር የሚያስችሉ ጽሑፎችን በጋዜጦችና በመጽሔቶች ላይ በዐምደኝነት ጽፈዋል፡፡

ጤናቸው ‹‹በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ›› እስከተያዘበት ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ በመደበኛነት ከመሳተፋቸውም በላይ፣ የመድበለ ጥናቶች (ፕሮሲዲንግስ) ተባባሪ አዘጋጅ ሆነው ሠርተዋል፡፡ በርካታ ምሁራን በተሳተፉበት ለባለ ስድስት ቅጹ ‹‹ኢንሳይክሎፔዲያ ኢትዮፒካ›› (Encyclopaedia Aethiopica) በርካታ ጽሑፎችን አበርክተዋል፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1996 ዓ.ም. የክብር ዶክትሬት ዲግሪን፣ የብሪታንያ ዘውዳዊ መንግሥትም በኢትዮጵያ ጥናት ላከናወኑት ላቅ ያለ ተግባር ‹‹የብሪቲሽ ኦርዶር›› ሜዳይ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ50 ዓመታት በላይ ለሰጡት አገልግሎትም የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በብር የተሠራ የአክሱም ሐውልት ምሥል ሰጥቷቸዋል፡፡

በፋሺስት ኢጣሊያ ተዘርፎ የሄደው የአክሱም ሐውልት ወደ እናት ምድሩ እንዲመጣ በተደረገው ትግል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ የሚነገርላቸው ፕሮፌሰር ፓንክረስት፣ በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ዘመን በመቅደላ ወረራ እንግሊዞች የዘረፉትን ቅርስ ለማስመለስ በተቋቋመው ‹‹አፍሮሜት›› (The Association for the Return of Magdala Ethiopian Treasures) ምክትል ሊቀመንበር ሆነው አገልግለዋል፡፡ የሥነ ጥበብ ውጤቶች፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት፣ መስቀሎች፣ ምሥሎችና መጻሕፍት እንዲመለሱ የተደራጀ ዘመቻ በመከፈት የታገሉ ሲሆን፣ በቀላሉ የማይገመቱ ቅርሶች ከእነዚህም የአፄ ቴዎድሮስ ክታብ፣ ጋሻና ጎራዴ ይልቁንም የመድኃኔዓለም ታቦተ ሕግ ተመላሽ እንዲሆን አድርገዋል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ድምፁ የማይሰማው የኢትዮጵያ ጥናት ወዳጆች ማኅበር (ሶፊ)፣ ለበርካታ ዓመታት ንቁ ተሳታፊና ሊቀመንበር በመሆን በሰጡት አገልግሎት የተቋሙ ሙዚየምና ቤተ መጻሕፍት ስብስቦቹ በጥንታዊ ቅርሶች የተሞላ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ በባሕር ማዶ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶች ከሽያጭ ለማዳን ገቢ ማሰባሰቢያ በማዘጋጀት ምሥሎችን፣ ሥዕሎችን፣ መስቀሎችና የሥነ ጥበብ ውጤቶች የማስመለሱን  ዘመቻ መርተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በቅጥር ግቢው እያሠራ ያለው አዲሱን ቤተ መጻሕፍት በስማቸው ከመሰየም ባሻገር፣ ከባለቤታቸው ሪታ ፓንክረስት ጋር በመሆን ላበረከቱት አገልግሎትም የክብር መገለጫ እንዲሆን ከስድስት ዓመት በፊት የታተመው የኢትዮጵያ ጥናት መጽሔትን የመታሰቢያ ዕትም አድርጎላቸዋል፡፡

ኅዳር 23 ቀን 1920 ዓ.ም. የተወለዱት ፓንክረስት ገጸ ታሪካቸው እንደሚያወሳው፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚ ታሪክ፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በፖለቲካል ሳይንስ አግኝተዋል፡፡ እናታቸው ሲልቪያ ፓንክረስት የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራን (1928-1933) በመቃወምና በለንደን የተቃውሞ ሠልፍ በማስተባበር ለዘመቻው ድጋፍ ገቢ ማሰባሰቢያ ሲፈጥሩ ከጎናቸው አልተለዩም፡፡ ‹‹ኒው ታይምስ ኤንድ ኢትዮጵያ ኒውስ›› የተሰኘው ጋዜጣቸውን ከ20 ዓመታት በላይ በአርትዖት ያግዙ ነበር፡፡

 ከ1948 ዓ.ም. (1956) ጀምሮ መኖሪያቸውን ከእናታቸው ሲልቪያና ከባለቤታቸው ሪታ ጋር በአዲስ አበባ ያደረጉት ፓንክረስት ያረፉት በ89 ዓመታቸው ሲሆን፣ ሁለት ወንድና ሴት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ አራት የልጅ ልጆችንም አይተዋል፡፡ ዜና ዕረፍታቸውን ተከትሎ የውጭ ጉዳይና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሮች ሐዘናቸውን መግለጻቸው ታውቋል፡፡

እንደ እናታቸው ሁሉ የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ሥርዓተ ቀብር የሚፈጸመው በኢትዮጵያ መሬት ነው፡፡ ሲልቪያ ፓንክረስት በመንግሥታዊ ክብር ሥርዓተ ቀብራቸው የተፈጸመው በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሲሆን፣ ለኅትመት ዓርብ እኩለ ሌሊት እስከገባንበት ድረስ የፕሮፌሰር ፓንክረስት ሥርዓተ ቀብር ሰኞ የካቲት 13 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደሚፈጸም ከመታወቁ በቀር ቦታው የት እንደሆነ ማወቅ አልተቻለም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...