Wednesday, May 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፈረንሣዩ አኮር ኩባንያ በኢትዮጵያ የሚያስተዳድራቸው ብራንድ ሆቴሎች አምስት ደረሱ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የሦስት ሆቴሎች ስምምነት ተፈረመ

በዓለም ስማቸው ከሚጠራ ትልልቅ ብራንድ ሆቴሎችን ከሚያስተዳድሩ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው አኮር ሆቴልስ ግሩፕ፣ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ እንዲከፈቱ ከተስማማባቸው በተጨማሪ ሦስት አዳዲስ ብራንዶችን ለማምጣት ተስማማ፡፡

አኮር ሆቴልስ ሰሞኑን ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር ስምምነት ያደረገባቸው ሦስት ሆቴሎች እ.ኤ.አ. ከ2019 እስከ 2021 ባለው ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት ይበቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኩባንያው ይፋ አድርጓል፡፡ በአዲስ አበባ በተካሄደ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ሦስት አገር በቀል ኩባንያዎች ከአኮር ግሩፕ ጋር ስምምነት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡ በዚህ መሠረት ቲሃት ኢንቨስትመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ 162 ክፍሎች ያሉትንና ሜሪኩዩር የተባለውን ብራንድ ሆቴል ለመገንባት ስምምነት አድርጓል፡፡ ከሦስት ዓመታት በኋላ ሥራ እንደሚጀምር የሚጠበቀው ይህ ሆቴል፣ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አካባቢ ይገነባል ተብሏል፡፡ ቲሃት በብረታ ብረት ንግድ ዘርፍ የተሰማራ ኩባንያ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

አይቢስ ስታይልስ የሚባለውን ብራንድ ሆቴል ለማስተዳደር የተስማማው አኮር ኩባንያ ሜትሮ ሆስፒታሊቲ ሰርቪስስ የተባለው አገር በቀል ኩባንያ ጋር በመደራደር ስምምነቱን መቋጨቱን ይፋ አድርጓል፡፡ የሜትሮ ኩባንያ ንብረት የሚሆነው ሆቴል የሚገነባውም እዚያው ካዛንቺስ አካባቢ ሲሆን፣ 135 ክፍሎች የሚኖሩትና ከሁለት ዓመታት በኋላ ሥራ እንደሚጀምር የሚጠበቅ ነው፡፡ ከሦስቱ ሆቴሎች በክፍሎቹ ብዛት ትልቁ የሆነው አይቢስ የተባለውን ብራንድ የሚይዘው ሆቴል ሲሆን፣ 230 ክፍሎች እንደሚኖሩት ይጠበቃል፡፡

ዓባይ ቴክኒክ ትሬዲንግ የተባለውና ከባድ ተሽከርካሪዎችን የሚያስመጣውና የሥራ ተሽከርካሪዎችን መገጣጠም የጀመረው ይህ ኩባንያ፣ አይቢስ የተባለውን ሆቴል ከአራት ዓመታት በኋላ ዕውን እንደሚያደርግ ሲገለጽ፣ በአፍሪካ ኅብረት ጽሕፈት ቤት አካባቢ የሚገነባው ይህ ሆቴልም ባለ 22 ፎቅ እንደሚሆን ታውቋል፡፡

ሪፖርተር የሦስቱንም ሆቴሎች ባለንብረቶች ስለፕሮጀክቶቻቸው ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ይሁንና የአኮር ሆቴልስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስቴቨን ዴይንስ እንዲሁም የኩባንያው የኦፕሬሽን ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሊቪዬ ግራነት ከባለሀብቶቹ ጋር ካደረጉት ስምምነት በኋላ እንደገለጹት፣ የሦስቱ ሆቴሎች መምጣት ከ500 በላይ ክፍሎች እንደሚያስገኙ ይጠበቃል፡፡

ከዚህ ቀደም አኮር ግሩፕ ከእንይ ጄነራል ቢዝነስ ኩባንያ ጋር (የእንይ ሪል ስቴት እህት ኩባንያ) ባደረገው ስምምነት ፑልማን የተባለውን የአኮር ብራንድ ሥራ እንደሚያስጀምሩ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡ የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ በተደረገው ስምምነት ወቅት ፑልማን ሆቴል 330 ክፍሎች እንደሚኖሩት ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ለዚህ ሆቴል የ20 ሚሊዮን ዶላር ፋይናንስ ያቀረበው የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የንግድና ልማት ባንክ በማለት ስሙን የቀየረው ፒቲኤ ባንክ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ኖቮቴል የተባለውን ብራንድ ለማምጣት ንብራስ ሆቴል ከተባለው ኩባንያ ጋር ስምምነት ያደረገው ካቻምና  ነበር፡፡ ለዚህ ሆቴል ግንባታ 25 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

አኮር ሆቴልስ በአምስቱ ሆቴሎች አማካይነት ከ1,000 በላይ ክፍሎችን እንደሚያስተዳድር ይጠበቃል፡፡ በመላው አፍሪካ ከ19,000 በላይ ክፍሎች ያሏቸውን 111 ሆቴሎች በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ይህ የፈረንሣይ ኩባንያ፣ አምስቱንም ሆቴሎች ለማስተዳደር ድርድር ያካሄደው ካሊብራ ሆስፒታሊቲ በተባለው አማካሪ ድርጅት በኩል እንደሆነ ታውቋል፡፡ ካሊብራ ከዚህ ቀደም ራማዳ፣ ቤስት ዌስተርን የተባሉትን ጨምሮ፣ ከደቡብ አፍሪካ ስፐር ኮርፖሬሽን የሚታወቅበትን ስፐር ስቴክ የተባለውን ሬስቶራንት በማደራደር ከግሬት አቢሲንያ ኩባንያ ባለንብረቶች ጋር በማስማማት የቤሰተብ ሬስቶራንቱ ሥራ እንዲጀምር አስችሏል፡፡ በቦሌ አከባቢ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ፣ አቢሲንያ ፕላዛ ላይ የሚገኘው ስፐር ሬስቶራንት አገልግሎት የጀመረ ሲሆን፣ ከሚታወቅባቸው ምግቦች መካከልም ስቴክ ተጠቃሽ ምግብ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች