Tuesday, July 23, 2024

መንግሥት አሁንም የሕዝቡን የልብ ትርታ ያዳምጥ!

ሕዝብ ለመንግሥት ያቀረባቸው በርካታ ጥያቄዎች አሉት፡፡ ቅደም ተከተላቸው ተጠብቆ የቀረቡት ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የቀረቡ አቤቱታዎች ሰሚ ባለማግኘታቸው በተፈጠረው አመፅ፣ በአገሪቱ ምን ዓይነት ሰቆቃ ተከስቶ እንደነበር መቼም አይዘነጋም፡፡ ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ ሆነው ሊደማመጡ ባለመቻላቸው የበርካቶች ሕይወት ተቀጥፏል፡፡ በርካቶች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ በብዙዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ልቦና ቀውስ ተፈጥሯል፡፡ የአገርና የሕዝብ ህልውና ለአደጋ ተጋልጦ ነበር፡፡ በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት የስድስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ ታውጆ ችግሮች ለጊዜው ቢረግቡም፣ ለዘላቂ ሰላም የሚበጁ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመምከር ሁነኛ መፍትሔ መፈለግ ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት ሕዝብ ምን እንደሚፈልግ በግልጽ መስማት አለበት፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት የሕዝብን የከተማቹ ጥያቄዎች መመለስ ባለመቻሉ ምክንያት የተፈጠረው ቀውስ ለአገር ህልውና ጠንቅ ሊሆን የቻለው፣ በሕገ መንግሥቱ ሳይቀር የመንግሥት አሠራርን ለሕዝብ ግልጽ የማድረግና ተጠያቂነት እንዳለበት የተደነገገው ጭምር በመጣሱ ነው፡፡ ራሳቸውን ከሕግ በላይ ያደረጉ ግለሰቦችና ቡድኖች ሕዝብን ንቀው ነበር፡፡ ጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ተገብቶ ያለፉትን 15 ዓመታት ለመገምገም ዘመቻ የተጀመረው የተፈጸሙ ጥፋቶች ከሚገመቱት በላይ በመሆናቸው እንደሆነ ማን ይክዳል? የፓርቲና የመንግሥት ሥራን በመቀላቀል ሕገወጥ ተግባራት መፈጸም፣ በኔትወርክ በመቧደን የአገር ሀብት መዝረፍ፣ የግዥና የጨረታ ሕጎችን እየጣሱ ራስንና ቢጤዎችን ማበልፀግ፣ የሕዝቡን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች መጣስ፣ መብታቸውን ለማስከበር የሚንቀሳቀሱ ዜጎችን ማንገላታት፣ ሕጋዊ ተቋማዊ ፓርቲዎችን ማዳከምና የመሳሰሉት ተግባራት ከተሃድሶም በላይ አሁንም በአደባባይ ይቅርታ የሚያስጠይቁ ናቸው፡፡

ሕዝብና መንግሥት በተመሳሳይ መንገድ ላይ ሁሌም መጓዝ አለባቸው ተብሎ መደምደም ባይቻልም፣ ቢያንስ በበርካታ አገራዊ ጉዳዮች መግባባት አለባቸው፡፡ ለአገር ልማት ሲባል ይዞታን መልቀቅ የአንድ ዜጋ የተቀደሰ ኃላፊነት ቢሆንም፣ እዚህ ግባ በማይባል ካሳና በሚገባ ባልተዘጋጀ ሥፍራ ላይ በማፍሰስ በሕዝብ ላይ የተፈጸመው ሰቆቃ መቼም ቢሆን በአሳዛኝ ድርጊት አስተማሪነት ሊታሰብ ይገባል፡፡ የአገሪቱ ልማት ባለቤት ሕዝብ መሆን ሲገባው፣ በተለይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማትና አመራሮች በጭፍን ሲወስዱት የነበረው የመረረ ዕርምጃ የፈጠረው ቀውስ እንዴት ይዘነጋል? ሕፃናት፣ አቅመ ደካሞችና አዛውንቶች ሳይቀሩ ከኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለው ሜዳ ላይ የተጣሉበት ሌላው ቢቀር የጥፋት መጥፎ ማስተማሪያ ሆኖ ሊታወስ ይገባል፡፡ በማዘጋጃ ቤቶችና በተለያዩ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት የዜግነት መብታቸው ተገፎ ለእንግልት የተዳረጉና በገንዘባቸው ፍትሕ እንዲገዙ የተገደዱ ዜጎች ጉዳይም አይዘነጋም፡፡ ሕዝብና መንግሥትን ያጋጩ መሰል ሌሎች በርካታ ጉዳዮችም አሉ፡፡ አሁንም የሚያጋጩ አሉ፡፡

የኢሕአዴግም ሆነ የአባል ፓርቲዎቹ አመራሮች የድርጅት የልደት ቀናቸውን ሲያከብሩ ሁሌም ሲናገሩ በረሃ የወጡት፣ የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት በትግል ብቻ እንደነበር አምነው እንደሆነ ነው፡፡ ይህ ትግል በጠረጴዛ ዙሪያ የሚደረግ የሐሳብ ፍጭት ሳይሆን፣ እሳት የሚተፉ የተለያዩ ዓይነት የጦር መሣሪያዎችን በመተኮስ ሕይወት የሚገበርበት፣ ደም እንደ ውኃ የሚፈስበትና ዘግናኝ የሆኑ የአካል ጉዳቶች የሚደርሱበት ነበር፡፡ በወቅቱ የሕዝብ ብሶትን አንግበው በረሃ ገብተው ሲዋጉ መስዋዕት የሆኑት የዚያን ጊዜዎቹ ወጣቶች ዛሬ በሕይወት ባይኖሩም፣ ጓደኞቻቸው ግን ዓላማቸውን አሳክተው ለሥልጣን በቅተዋል፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት በሰላማዊ ምኅዳር ውስጥ በእነሱ አመራር በርካታ ውጣ ውረዶች ታልፈዋል፡፡ በተለይ የነኮተው የአገሪቱ ኢኮኖሚ አንሰራርቶ ተስፋ ሰጪ በርካታ ነገሮች ታይተዋል፡፡ በትምህርትና በጤና ዘርፍ አሁንም ችግሮች ቢኖሩ አመርቂ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ነገር ግን ራስን በራስ የማስተዳደርና የማንነት ጥያቄዎች ተመልሰዋል ቢባልም፣ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ አላገኙም፡፡ በተደጋጋሚ በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ደረጃ ሳይቀር ችግሩ ቢታመንም፣ ሕዝብ የሚያረካ ቀጥተኛ ተግባራዊ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም፡፡

ሕዝብ በገዛ አገሩ የባይተዋርነት ስሜት እየተሰማው፣ ከዝቅተኛው እስከ ከፍተኛው ሹም ድረስ ግልምጫ እየደረሰበት፣ በየደረሰበት ቦታ ሁሉ ጉቦ እንዲከፍል እየተገደደ፣ የአገልግሎት መስተጓጎል ወይም መቋረጥ ሲያጋጥመው እንኳን ይቅርታ የሚጠይቀው ስለተፈጠረው ችግር የሚነግረው ሲያጣ፣ በሰው ሠራሽ የዋጋ ግሽበት ምክንያት ኑሮው ሲመሰቃቀል፣ የቤት ኪራይ ዋጋ ከአቅም በላይ ሆኖበት መከራውን ሲያይ፣ ፍትሕ በገንዘብ እየተሸጠበት ምሬቱ ጣሪያ ሲነካ፣ ወዘተ ተደላድለው የተቀመጡ ቅንጡዎች ምንም አይሰማቸውም ነበር፡፡ በደሉና ሰቆቃው ሞልቶ ግድቡን ሲጥስ ግን የተከሰተው አደገኛ ጥፋት ነበር፡፡ መቼም ቢሆን ሊተካ የማይችል የዜጎች ሞት፡፡ አሁንም በተለይ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ባሉ መገናኛ ብዙኃን የሚስተዋሉ አላስፈላጊ ግርግሮች ያንን ክፉ ጊዜ ያስታውሳሉ፡፡ አገሪቱ አሁንም በተሟላ ዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ግስጋሴ ውስጥ እንዳለች ብቻ የሚተርኩ ዝባዝንኬዎች ይሰማሉ፡፡ አፍጥጠው የሚታዩ ችግሮችን እያድበሰበሱ በጥልቅ ተሃድሶው ሁሉም ነገር በሰላም የተጠናቀቀ ያህል ይሰብካሉ፡፡ ብልጣ ብልጦችም ያለኃፍረት ወጣ ገባ እያሉ ይህንኑ ያስተጋባሉ፡፡ ሕዝብ ግን አሁንም ትዕግሥቱ እስኪያልቅ እየታዘበ ነው፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

በእርግጥ ሁሉም ችግሮች በአንድ ጊዜ መፍትሔ አያገኙም፡፡ ሁሉም ጥያቄዎች ምላሽ ሊገኝላቸው አይችልም፡፡ ነገር ግን በጣም መሠረታዊ የሚባሉ ጥያቄዎች ግን ምላሽ ይጠብቃሉ፡፡ ቅደም ተከተል ስላላቸው በዚያ መሠረት መልስ ማግኘት አለባቸው፡፡ ሕዝብ የልማቱ ባለቤት የሚሆነው በጥረቱም ሆነ በውጤቱ ውስጥ ፍትሐዊ የሆነ ተሳትፎ ሲኖረው ነው፡፡ ለምግባረ ብልሹ አመራሮች ቅርብ የሆኑ ሁሉንም ነገር ሲያፍሱና ጥቂቶች ያላግባብ ሀብት ሲያካብቱ፣ ልማቱ በሕዝብ ዘንድ ትርጉም የለውም፡፡ ይልቁንም የጥፋት ዒላማ ይሆናል፡፡ በዜጎች መካከል ፍፁም ልዩነት ሳይፈጠር ተሳትፎም ሆነ ተጠቃሚነት ለሁሉም በፍትሕዊነት ሊዳረስ ይገባል፡፡ ያኔ ልማቱ በእርግጥም የሕዝብ ባለቤትነት ያገኛል፡፡ ከሥራ ሥምሪት ጀምሮ መሬት፣ የባንክ ብድር፣ የውጭ ምንዛሪ፣ ማዘጋጃ ቤታዊና አስተዳደራዊ አገልግሎቶች፣ የሕግ ከለላና ጥበቃ የመሳሰሉት ሁሉ በእኩልነት ሊከናወኑ ይገባል፡፡ ግድ ነው፡፡

 በፖለቲካው መስክ ነፃና ፍትሐዊ የውድድር ሜዳ መኖሩ መረጋገጥ አለበት፡፡ በሕጉ መሠረት የመደራጀትና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብቶች መከበር አለባቸው፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር የሚመራ የምርጫ ሥርዓት መኖር አለበት፡፡ ያኔ ማንም ሰው ወይም ቡድን ከሕግ በላይ መሆን ስለማይችል ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ጉዞ ይሰምራል፡፡ የሥልጣኑ ባለቤት የሆነው ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ የመወሰን መብቱ ይረጋገጣል፡፡ ሕዝብ የአገሩ ባለቤት ይሆናል፡፡ በሕዝብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ ማጭበርበር ለታሪክ ሰነድነት ይቀመጣል፡፡ ሥልጣን በኃይል ሳይሆን በሕዝብ ድምፅ ብቻ ይያዛል፡፡ የጥላቻና የጽንፈኝነት ፖለቲካ ጡረታ ይወጣል፡፡ ትምክህተኝነትና ጠባብነት ያበቃላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ከልዩነታቸው በላይ አንድነታቸው እንደሚበልጥባቸው ስለሚያውቁ፣ ለዘረኝነትና ለጽንፈኝነት ቦታ አይሰጡም፡፡ በዚህ መንፈስ መጓዝ ሲቻል ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ጫፍ የኢትዮጵያ ምድር ሰላም ይሆናል፡፡ ብልፅግና ይሰፍናል፡፡ ሕዝብ ይህንን ስለሚፈልግ መንግሥት አሁንም የልብ ትርታውን ያዳምጥ! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...