Friday, February 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ብርሃን አልባ ጎዳናዎች

ለአዲስ አበባ ብርቅዬ የሚባል ተደራራቢና ተሻጋሪ መንገዶች እየተገነቡላት፣ ከተማዋም የእነኚህ ዘመናዊ መንገዶች ባለቤት እየሆነች ነው፡፡ ከከተማዋ ዕድገትና ፍላጎት ጋር የተጣጣመ ዘመናዊ መንገዶች እንዲኖሯት ግድ የሚልበት ወቅት ነው፡፡ አዲስ አበባ እንደ ስፋቷና እንዳመቀችው ሕዝብ ብዛት በርካታ መንገዶችን የምትሻ ቢሆንም፣ በአቅም መጠን እየተገነባ ነው የሚለውም ያስማማናል፡፡ በአገርና በሕዝብ አቅም መጠን እየተሠሩ ያሉ መንገዶች የከተማዋን የመንገድ ሽፋን በመጠንም ቢሆን ከፍ ስለማድረጋቸው ቢነገርም፣ ከፍላጎቱ አንፃር ብዙ የሚቀራት ከተማ ነች፡፡ በአንፃሩ ግን በተለይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ መስፋፋት ለከተማዋ የመንገድ ሽፋን ዕድገት አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ መገንዘብ ይችላል፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታዎች ለአዲስ አበባ አዳዲስ መንገዶች እንዲፈጠሩላት ማድረጋቸው የሚታመን ነው፡፡ ጥራቱና በተያዘለት የጊዜ ገደብ መሠራቱ ላይ የምናቀርበው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንገድ ያልነበራቸው የከተማዋ ክፍሎች የመንገድ ባለቤት እየሆኑ መምጣታቸው ሐቅ ነው፡፡

እስካሁን እየተገለገልንባቸው ስላሉት መንገዶች ካወራን ግን ለብዙዎቻችን እንቆቅልሽ እየሆነ ያለ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም ከመንገድ ግንባታ ጋር ፈጽሞ መነጣጠል የማይችለውና ከመንገድ ግንባታው ጋር አብረው መዘርጋት የነበረባቸው የመንገድ ዳር የኤሌክትሪክ መብራት ምሰሶዎች ሥራ ነው፡፡

መንገድ ሲገነባ ወይም ለመንገድ ግንባታ ዲዛይን ሲሠራ ለተሽከርካሪና ለመንገዶች መጠቀሚያ የሚሆነውን ሥፍራ ከልሎ መገንባትን ብቻም ሳይሆን ከመንገዱ ግራና ቀኝ እንደ መንገዱ ዲዛይን በምሽት ብርሃን የሚሰጡ አምፖል ተሸካሚ ምሰሶዎችን መትከል የግድ ነው፡፡ ምሰሶዎቹ የሚያንጠለጥሏቸው አምፖሎችም በተገቢው መጠን ብርሃን መፈንጠቅ አለባቸው፡፡ በተለይ በከተሞች ትራፊክ በሚዛበት ምሽት ይህ የግዴታ መሟላት ይኖርበታል፡፡

አዳዲሶቹ የመንገድ ግንባታዎች ግን አብረዋቸው መተከል ያለባቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል ምሰሶዎች ሳያካትቱ ብቅ የማለታቸው ነገር ግልጽ አይደለም፡፡ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች በአዳዲስ ጎዳናዎች ላይ አለመታየታቸው ብቻም ሳይሆን ዘመናዊና የተሻለ አገልግሎት የሚሰጡ የከተማውን መንገዶች ተከትለው አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ የጎዳና መብራቶች፣ ብርሃን አልባ መሆን ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

እንደውም በአሁኑ ጊዜ ከሚገነቡ መንገዶች ዘመናዊነት ጋር የተመጣጠነ ዓይነ ግቡ የመንገድ መብራት ምሰሶዎች የተገነባላቸው መንገዶች፣ ምሰሶዎቻቸው የመንገድ ጌጥ ሆነዋል፡፡ በቅርብ ከተገነቡ ዘመናዊ መንገዶች ግራና ቀኝ ከተተከሉት ውስጥ ከአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ጋር ተያያዥ ሆነው የተሠሩትን መንታ መንገዶች መጥቀስ ይቻላል፡፡ በእነዚህ መንገዶች መሳ ለመሳ ቄንጠኛ የመንገድ መብራት ምሰሶዎች ቢተከሉም ብርሃን አልባ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ከዕለት ወደ ዕለት መብራት አልባ እየሆኑ መምጣታቸው፣ የከተማዋን ገጽታ ከማጉደሉም ባሻገር ለማኅበራዊ ችግሮች ምንጭ እየሆኑ ነው፡፡ በምሽት ወንጀል እንዲፈጸም አጋዥና ተገን መሆናቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ የክልል ክተሞች ጎዳናዎች ዕጣ ፈንታም በተመሳሳይ የሚታይ ሲሆን፣ ነገሩ እየተበራከተ መምጣቱም የጎዳና መብራቶች አስፈላጊነት ብዙም እየታሰበበት እንዳልሆነ ያሳያል፡፡

በእርግጥ ለመኖሪያና ለሥራ ቦታዎች የሚያስፈልገን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን እየተቆራረጠና እያነሰ፣ የመንገድ መብራት እንዲለቀቅልን መጠበቅ ቅንጦት ሊመስል ይችላል፡፡ ግን አይደለም፡፡ የጎዳና መብራቶች ከሚሰጡት ጠቀሜታ አንፃር በመኖሪያ ቤት ሊኖረን የሚገባውን ያህል ያስፈልጉናል፡፡

 በአዲስ አበባ ከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ በምሽት ብርሃን ይሰጡ የነበሩ መብራቶች አስታዋሽ አጥተው ከመጥፋታቸው ባሻገር አምፖሎቹ ሲቃጠሉና ሲበላሹ እየተከታተሉ ይቀይሩ የነበሩ ሠራተኞችም እንደቀድሞ እምብዛም አይታዩም፡፡

እርግጥ እንደ አፍሪካ ኅብረት ያሉ ስብሰባዎች አሉ ሲባል አንዳንድ ጎዳናዎች ብርሃን እንዲበራባቸው ይደረጋል፡፡ በአብዛኛው የከተማው ጎዳና ላይ በተለይ ከዋናው  ወደ ውስጥ የሚገቡ መንገዶች ላይ ቀድመው የነበሩ መብራቶች አገልግሎት መስተጓጎልና ይህ የአገልግሎት ዘርፍ ትኩረት ማጣቱ በአዲስ አበባ በብዛት ይታያል፡፡ ይህ ከተማዋን የሚገልጽ አይደለም፡፡ የከተማ መብራቶችን እያንቦገቦጉ ማደር አስፈላጊ አይደለም ብሎ ሙግት የሚገጥም ይኖራል ብዬ ባላስብም፣ የአዲስ አበባ ጉዳይ ግን ያሳስባል፡፡ ይባስ ተብሎ ስንት ወጪ የወጣባቸው ቄንጠኛ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ብርሃን የማይሰጡ ከሆኑ ቀድሞውንስ ለምን ተተከሉ?

 የጎዳና መብራቶች ጉዳይ በቅጡ ይታሰበበት፡፡ መብራት አልባ ጎዳናዎች እየበዙ በመጡ ቁጥር ለወንጀል ድርጊትና ለአደጋ መበራከት ምክንያት መሆናቸው  አያጠራጥርም፡፡ የጎዳና መብራቶች ጉዳይ ይታሰብበት ብቻ ሳይሆን ጎዳናዎቻችንን ብርሃን አናሳጣቸው፡፡ ብርሃን አልባ ጎዳናዎቻችንም ብራሃናቸው በሰው ሁሉ ፊት ይብራ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት