ከትውልድ ቀዬዋ የወጣችው በለጋ ዕድሜዋ ነበር፡፡ ለቤተሰቧ አራተኛ ልጅ የሆነችው ታዳጊ የሥጋ ደዌ ተጠቂ በመሆኗ በአካባቢዋ እንደሌላው ማኅበረሰብ መኖር አልቻለችም፡፡
ወይንእሸት ሁርጌሳ የተወለደችው ከአዲስ አበባ 150 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው አምቦ ከተማ ነበር፡፡ ከቤተሰቦቿ መካከል የሥጋ ደዌ ተጠቂ በመሆኗ ከአካባቢው መራቅን መረጠች፡፡ ከአምቦ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ እስከምትገኘው ሆለታ ድረስ በእግሯ እንደመጣች ትናገራለች፡፡
በ1993 ዓ.ም. በሆለታ ከቤተ ክርስቲያን በልመና በሰበሰበችው ገንዘብ በአዲስ አበባ አለርት ማዕከል መጥታ ሕክምናውን እንዳገኘች ትገልጻለች፡፡ ሕክምናውንም ካጠናቀቀች በኋላ በሻሸመኔ ወደሚገኘው ኩየራ የሥጋ ደዌ ጣቢያ አምርታ ኑሮዋን ጀመረች፡፡
ሥጋ ደዌ ተጠቂዎች በማኅበረሰቡ የተዛባ አመለካከት ምክንያት ሲገለሉ ቆይተዋል፡፡ በሽታውም ከቁጣና ከመዓት ጋር የተያያዘ ነው የሚል አመለካከት ስላለ ከመደበኛ ሕክምና ይልቅ የባህልና የእምነት ፈውሶችን የመሻት ዝንባሌ በሰፊው እንደሚታይ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡
በአዲስ አበባ በ1935 ዓ.ም. እንዲሰፍሩበት ከተደረገውና ከአለርት ማዕከል አጠገብ ከሚገኘው ገብረ ክርስቶስ አካባቢ በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ ኩየራ በ1960 ዓ.ም. ተመሥርቶ በሚገኘው መንደር፣ ከ5000 በላይ ቀጥተኛ ተጠቂዎችና ከ25,000 በላይ ቤተሰቦቻቸው ይገኛሉ፡፡
ከተለያዩ ክልል ተውጣጥተው በመንግሥትና በተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች እየተደገፉ ኑሮዋቸውን በኩየራ ያደረጉ እንደ ወይንሸት የሉ የበሽታው ተጠቂዎች ጥቂት አልነበሩም፡፡
በ1944 ዓ.ም. ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባመቻቹላቸው የመኖሪያ ሥፍራ የሚኖሩት የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ዕርዳታ በመጠባበቅ ሕይወታቸውን ሲመሩ የቆዩ ቢሆንም አሁን ነገሮች ተቀይረዋል፡፡
ወይንእሸትም ኩየራ የሥጋ ደዌ ጣቢያን ከተቀላቀለችበት ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ ራሷን ለመቻል ብዙ ጥራለች፡፡ በ1996 ዓ.ም. ኩየራ ከሚገኘው የሥጋ ደዌ ማኅበር 300 ብር በመበደር ሁለት በጎች ገዝታ ሥራዋን ሀ ብላ መጀመሯ የዛሬ ስኬቷ መሠረት መሆኑን ትናገራለች፡፡
‹‹ከማኅበሩ ባገኘሁት ብድር ሥራዬን በማስፋፋት ያለብኝን ዕዳ መልሻለሁ፡፡ በቆጠብኩት ገንዘብ የከብት ሥራ ውስጥ ተሰማርቻለሁ›› በማለት የስኬቷን ሂደት ታስረዳለች፡፡
ከኅብረተሰቡ የሚደርስባትን መገለል በመቋቋም ትኩረቷን ሥራዋ ላይ ያደረገችው ወይንእሸት፣ ከማኅበሩ ጋር በቅርበት መሥራቷ እንደረዳት ትገልጻለች፡፡ በኢትዮጵያ ግብርናው ዘርፍ ካለፉት 25 ዓመታት ወዲህ የቴክኖሎጂ ድጋፍ እየሰጠ ከሚገኘው ሳሳካዋ ግሎባል ለማኅበሩ ካደረገው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ የተለያዩ ሥልጠናዎች መስጠቱ ለበሽታው ተጠቂዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡
በአካባቢው በማኅበሩ ታቅፈው ከሚገኙት 1000 የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች 400 ያህሉን በተለያዩ የግብርናና የከብት ዕርባታ ሥራዎች ውስጥ እንዲሰማሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ድጋፍ ሲያደርግላቸው እንደቆየ የሻሸመኔ የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ማኅበር አስተባባሪ አቶ ተመስገን አብርሃም ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
ከእነዚህ ተጠቂዎች ውስጥ አንዷ የሆነችው ወይንእሸት በሥልጠናው በመታገዝ ኑሮዋን ከብት በማርባት ከበፊቱ በማሻሻል ሁለት ልጆቿን እያስተማረች ትገኛለች፡፡
ወይንእሸትን ጨምሮ መሬት የሌላቸው 19 የሥጋ ደዌ ተጠቂዎችና የማኅበሩ አባላት ከብት በማደለብ ሥራ ላይ ተሰማርተው አቅማቸውን ከፍ ማደረግ እንደቻሉ አቶ ተመስገን ይናገራሉ፡፡
የ67 ዓመቷ ወ/ሮ ደምባቤ ሞጎሮ ወደ አካባቢው ካመሩ 40 ዓመታትን አሳልፈዋል፡፡ ቀድሞ በየወሩ በዕርዳታ ከሚያገኙት 60 ኪሎ በቆሎ አረቄ በማውጣት አራት ልጆቻቸውን ያስተዳድሩ ነበር፡፡ አንድ ጥማድ መሬት ቢኖራቸውም መሬቱን የእኩል ሲያሳርሱ እንደበር ይናገራሉ፡፡
መሬቱን ለማረስ በቀን 150 ብር ለበሬ የመክፈል አቅም የተሳናቸው ወ/ሮ ደምባቤ ከማኅበሩ ጋር በቅርበት ተወያይተው ወደ እርሻ ሥራው ገቡ፡፡
ከዚህ ቀደም ማሳው ላይ ብዙ ጊዜ ቢዘሩም ከአራት ኩንታል በላይ ማግኘት አያስችላቸውም ነበር፡፡ እሱንም የእኩል በማካፈል ከዕለት ጉርሻቸውና ከዘር በስተቀር እምብዛም እንደማያገኙበት ያስረዳሉ፡፡
በሳሳካዋ ግሎባል አማካይነት ለገበሬዎች የተሰጠውን አዲስ የእህል ዘርና የተለያዩ አዳዲስ የእርሻ ዘዴዎች ሥልጠና በመውሰድ በአንድ ጥማድ መሬት ላይ አሥር ኩንታል ስንዴ ማግኘት ችለዋል፡፡
መሬቱን ለልጃቸው በኃላፊነት ሰጥተው ከመሬት አዘገጃጀት ጀምሮ የዘር አጠቃቀም እንዲሁም ማዳበሪያና አረምን በተመለከተ በወሰዱት ሥልጠና በመታገዝ የተሻለ ምርት በማምረት ላይ እንደሚገኙ ያስረዳሉ፡፡
‹‹ቀድሞ ተረስተን ነበር፡፡ ከጉድጓድ ውስጥ ነው የወጣነው፡፡ ዛሬ የራሳችንን ሥራ እየሠራን ከዕርዳታና መገለል መውጣታችን ትልቅ ክብር ነው፤›› ይላሉ፡፡
የሥጋ ደዌ በዘር ይተላለፋል የሚለው የኅብረተሰቡ አስተሳሰብ ተጠቂዎችን ከቤተሰቦቻቸውና ከማኅበረሰቡ እንዲርቁ አድርጓል፡፡ ወ/ሮ ደምባቤ የአራት ልጆች እናት ሲሆኑ ልጆቻቸው ከትምህርት ቤት መልስ ለዕለት ጉርሳቸው ስለሚሯሯጡ በትምህርቱ እምብዛም እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡
በመስመር መዝራት፣ ምርጥ ዘርን መጠቀም የሚባሉት ነገሮች እንግዳ የሆነባቸው ወ/ሮ ደምባቤ በግብረ ሰናይ ድርጅቱ ከተሰጣቸው ሥልጠና በኋላ አዲስ የኑሮ ምዕራፍ እንደተከፈተላቸው ያወሳሉ፡፡
ቀደም ብሎ አረቄ እያወጡና በቀያቸው የግጦሽ ሳር በመሸጥ ይተዳደሩ የነበሩት አዛውንቷ፣ ቤት ውስጥ ተገልለው የሚኖሩት ከጓዳቸው ወጥተው በሥራ እንዲሳተፉ ምኞታቸው ነው፡፡
የሥጋ ደዌ ማኅበሩ ከሳሳካዋ ሁለት ሺሕ ግሎባል ጋር ለአምስት ዓመታት ለመቀጠል ውል የሚፈራረም ሲሆን፣ በቀጣይም ተጠቃሚ የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው የማኅበሩ አስተባባሪ አቶ ተመስገን ተናግረዋል፡፡
በዓለም 225,000 ሰዎች በሥጋ ደዌ በየዓመቱ ይጠቃሉ፡፡ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በዓለም ላይ የሥጋ ደዌ በሽታ 90 በመቶ የቀነሰ ቢሆንም፣ በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካና በታዳጊ አገሮች ጉዳት እያስከተለ ነው፡፡