Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹የበረሃ መርከብ›› ፌስቲቫል

‹‹የበረሃ መርከብ›› ፌስቲቫል

ቀን:

ፀሐይ ወደ መጥለቋ ነውና ሰማዩ ቀላ ማለት ጀምሯል፡፡ በነጩ የዳሎል የጨው ሜዳ ነፋሻ አየርና ወበቅ ይፈራረቃሉ፡፡ ቢጓዙበት የማያልቅ በሚመስለው የጨው መሬት ከአንድ አቅጣጫ ረዥም መስመር ሲንቀሳቀስ ይታያል፡፡ አንዳችም ዝንፍ ያላለው መስመር ወደ ምንቆምበት ቦታ እየቀረበ መጣና ተከታትለው የሚሄዱ ግመሎች ታዩ፡፡ በግመል ሰንሰለቱ ከአሥር በላይና በታችም የሆኑ ግመሎች በአንድ ቡድን ይገኙበታል፡፡ ከየቡድኑ ፊት ለፊት ደግሞ ግመሎቹን የሚመሩ ሰዎች ይጓዛሉ፡፡ ከነዚህ መሪዎች አንዱ አቶ ገብረሥላሴ አብርሃ የ37 ዓመት ጎልማሳ ሲሆኑ፣ ተወልደው ባደጉበት ሐውዜን ወረዳ ከባለቤታቸውና ከአራት ልጆቻቸው ጋር ይኖራሉ፡፡ ስድስት ግመል ያላቸው አቶ ገብረሥላሴ፣ ጨው በግመል በማጓጓዝ ሥራ ተሰማርተዋል፡፡ ከትውልድ ቀዬአቸው ተነስተው ጨው በግመሎቻቸው ይጭኑና በረሃውን አቆራርጠው ለሽያጭ ያቀርባሉ፡፡

ጎልማሳው ጨው ለሚፈነቅሉ ሰዎች በቀን 25 ብር፣ ለሚቆርጡ አምስት ብርና አጠቃላይ ቀረጥ 38 ብር ከፍለው ጨው ይወስዳሉ፡፡ በአንድ ወር ቢያንስ ሦስት ቀን ጨው አስጭነው የሚጓጓዙ ሲሆን፣ የበረሃው ጉዞ ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹እንጀራ ስለሆነብኝ ነው እንጂ ሕይወትን ሙሉ በረሃ እያቆራረጡ መሥራት ከባድ ነው፤›› ይላሉ፡፡ እሳቸውና ስድስቱ ግመሎቻቸው በዛ በረሃ በየጊዜው ሲጓጓዙ የሚገጥማቸውን ፈተና ቀለል የሚያደርግላቸው ቤተሰባቸውን ማስተዳደር መቻላቸው የሚሰጣቸው ደስታ ነው፡፡ ይህን ዕውን ላደረጉላቸው ግመሎቻቸው ያላቸውን ፍቅር መግለጽም ይከብዳቸዋል፡፡

‹‹ፀጋ፣ ሲሳይ፣ ፀሊም (ጥቁር) እና ሙሉ ለግመሎቼ ከሰጠኋቸው ስሞች መካከል ናቸው፡፡ ጨው በማጓጓዝ በማገኘው ገቢ ወፍጮ ቤት መክፈት እፈልጋለሁ፤›› ይላሉ አቶ ገብረሥላሴ፡፡ ዕቅዳቸው ይሳካ ዘንድ እንደ አጋር የሚያዩዋቸው ግመሎች ያላቸውን ሚናም ያስረዳሉ፡፡ ከግመሎቻቸው ጋር በረሃውን ሲያቋርጡ የሚያገኟቸው ቱሪስቶች ፎቶ አንስተዋቸው የሚሰጧቸውን መጠነኛ ገንዘብ እንደ ተጨማሪ ገቢ ያዩታል፡፡ በአካባቢው እንደ ጎልማሳው ሁሉ የብዙዎች የእንጀራ ገመድ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከግመሎችና ከጨው ጋር ይገናኛል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የ40 ዓመቱ አቶ ደስታ ታደሰን ማንሳት ይቻላል፡፡ የአምስት ልጆች አባት ሲሆኑ፣ ጨው በማጓጓዝ ሥራ ያሰማሯቸው አምስት ግመሎች አሏቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ በአንድ ግመል የሚጭኗቸውን 28 የጨው ክፋዮች እያንዳንዱን በ25 ብር ይሸጣሉ፡፡ ጨው ከሚሸጡበት በርሀሌ ከተማ ለመድረስ አምስት ቀን ይወስድባቸዋል፡፡ ከ20 ዓመታት በላይ በዚህ ሙያ የተሰማሩት አቶ ደስታ፣ ‹‹ሙያው ስለተለመደ ነው እንጂ ገቢው እምብዛም አይደለም፤›› ይላሉ፡፡

ማዕዳችንን ከማጣፈጥ በተጨማሪ ለሰውነት የሚጠቅሙ ንጥረ ነገሮችን በውስጡ ያመቀው ጨው፣ ዳሎል አካባቢ ሜዳ ሠርቶ የተራራ ክምር ሆኖም ይታያል፡፡ የጨው ሀብቱ ገበያ ላይ ውሎ የአገሬውን ምግብ መከሸን ደረጃ ከመድረሱ አስቀድሞ የበርካቶች የገቢ ምንጭ ነው፡፡ ጨውን ቆፍሮ በማውጣት፣ በመጥረብ፣ በመጫንና በማጓጓዝ ሥራ ተሰማርተው ሕይወታቸውን የሚገፉ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ አሞሌ ጨው የአገሪቱ መገበያያ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮና እስከ ዛሬም ድረስ የአካባቢው የጨው ሀብት የገቢ ምንጫቸው የሆነ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በአፋር ክልል ዕውቅ ከሆኑ ባህላዊ ሥርዓቶች  ጨው ቆፍሮ ከማውጣት በግመል እስከ መጫን ያለው ሒደት ይጠቀሳል፡፡ በተመሳሳይም ጨው በግመል ከተጫነ በኋላ በረሃውን በማቆራረጥ የሚደረገው ጉዞ (በአፋርኛ አረሆ በአማርኛ ቅፍለት የሚባለው) በአካባቢው ማኅበረሰብ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡

በአረሆ የግመሎቹ ባለቤት ወይም መሪ ከፊት ለፊት ይሆንና ግመሎቹን እርስ በርስ በማስተሳሰር ይጓዛሉ፡፡ ጉዞውን የሚያከናውነው አንድ ባለ ግመል ብቻ ሳይሆን በርካቶች ሲሆኑ፣ ሁሉም በተመሳሳይ መንገድ ተከታትለው ይሄዳሉ፡፡ በተለይም ጨው በማጓጓዝ ሥራ የተሰማሩ ሰዎች በረሃው ሳይበግራቸው ከግመሎቻቸው ጋር ረዥም ርቀት መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የአህመድ ኤላ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሁሴን መሀመድ እንደገለጹልን፣ በአፋር እስከ የካቲት ወር ድረስ አረሆ ተጠናክሮ ይታያል፡፡ ሙቀቱ ከፍተኛ በሚሆንበት ወቅት እንቅስቃሴው ይቀንሳል፡፡ ‹‹አፋር የሚወዳቸው ሦስት ነገሮች መሬቱ፣ ሚስቱና ግመሉ ናቸው፤›› የሚሉት አቶ ሁሴን፣ በአረሆ ረዥም ርቀት የሚጓዙ የአካባቢው ነዋሪዎች በርካታ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ አቶ ገብረሥላሴና አቶ ደስታን ያገናኛቸው መደበኛ ጉዞ በሚያደርጉበት ቦታ  ጉዟቸው ዕውቅና እንዲያገኝ በሚል  በተዘጋጀ ፌስቲቫል ነበር፡፡

የግመል አረሆ ለነዚህ ሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ሲሆን፣ ከዚያም በላይ የቱሪስት መስህብ ሆኖ ገቢ ማግኛም እንዲሆን በሚል ነበር ዓመታዊ ፌስቲቫሉ የተዘጋጀው፡፡ ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ የተዘጋጀውን የግመል ቅፍለት (በእንግሊዝኛው ካሜል ካራቫን) ፌስቲቫል ያዘጋጀችው ኒም ፕሮሞሽን የተሰኘ የማስታወቂያ ድርጅት ያላት ኒም ሐጎስ እንደ ቤት እንስሳ ሆኖ የሚያገለግለው ግመል ከአፋር ክልል ሕዝብ ጋር ያለውን ልዩ ቁርኝት ለማሳየት ፌስቲቫሉ መሰናዳቱን ትገልጻለች፡፡ ‹‹የበረሃ መርከብ›› የሚባሉት ግመሎች ለሕዝቡ ለሚሰጡት ዓይነተኛ አገልግሎት ምሥጋና ለማቅረብ እንደተፈለገም ትናገራለች፡፡

በአዘጋጇ ገለጻ፣ የግመል ቅፍለት የሚታይበት ፌስቲቫል መኖሩ የቱሪስቶችን ቁጥር ሊጨምር ይችላል፡፡ ለወደፊት ከጉዞው በተጨማሪ ሌሎችም ግመልን ያማከሉ ክንውኖች በማካተት በስፋት የሚታወቅ ፌስቲቫል እንደሚሆንም ታምናለች፡፡ ‹‹አረሆውን ከመመልከት ጎን ለጎን ስለ ግመል የፓናል ውይይቶች ይኖራሉ፡፡ የግመል ወተት፣ ሥጋና ቆዳ ስላለው ጥቅም እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ላይ ያተኩራል፤›› ስትል ትገልጻለች፡፡

ወደ 55 ኪሎ ሜትር የሚሆነውን በረሃማ መንገድ የሚያቆራርጡት ግመሎች ከ500 እስከ 3,000 የሚደርሱበት ጊዜ እንዳለ ኒም ትናገራለች፡፡ ጉዞው በየጊዜው በንጋትና አመሻሽ ላይ ስለሚካሄድ አንዱን ወቅትና ቀን መርጦ በተዋቀረ ሁኔታ ጎብኚዎች የሚታደሙት ማድረግም ይቻላል፡፡ በተያያዥም የግመሎቹ ባለቤቶች እንዲሁም ጨው በማውጣት ሥራ የተሰማሩትም የሚጠቀሙበት መሆን እንዳለበት ታክላለች፡፡

አረሆን ፌስቲቫል የማድረግ ሐሳብ በአፋር ክልል የተጠነሰሰው በቅርቡ ይሁን እንጂ፣ በተቀረው ዓለም ዕውቅናን ያተረፈ ክንውን ነው፡፡ በሰሜን አፍሪካ፣ በዓረብ አገሮችና በሌሎችም በረሃማ የዓለም ክፍሎች ለዓመታት የግመል ፌስቲቫሎች ተካሂደዋል፡፡ ለምሳሌ በዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ በሚካሄደው የግመል ፌስቲቫል ከ15,000 በላይ ግመሎች ይሳተፋሉ፡፡ በተለያዩ አገሮች የሚካሄዱ ፌስቲቫሎች እንደየባህሉ የግመል ስፖርታዊ ውድድሮች፣ የግመል አልባሳትና ጌጣ ጌጥ ትዕይንትና ሌሎች ክንውኖችንም ያካትታል፡፡ በዚህ ረገድ የአፋር ክልል እንቅስቃሴ ገና በጅማሮ ይገኛል፡፡

የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ማስፋፊያና ፓርኮች ልማት ሥራ ሒደት ባለቤት አቶ አህመድ አብዱልቃድር እንደሚሉት፣ ጎብኚዎች ባህላዊ የጨው አወጣጥን ከተመለከቱ በኋላ አረሆን እንዲያዩ የፌስቲቫሉ መጀመር መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡ ‹‹ግመል በጣም ልዩ እንስሳ ነው፡፡ በአፋርኛ አረሆ የሚባለው ግመል ተሳስሮ የሚሄድበት ጉዞ ከፍተኛ የቱሪስት መስህብ ይሆናል፡፡ ሒደቱ የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜም ያራዝማል፤›› ይላሉ፡፡ ከአህመድ ኤላ የሚነሱትና ጨው ጭነው የሚሄዱት ከ1,000 በላይ ግመሎች ሲተላለፉ ያለው ሒደት ማራኪ በመሆኑ የብዙዎችን ቀልብ እንደሚስብም እምነታቸው ነው፡፡

ጉዞው ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች ስለ አንዱ የገለጹልን የበርሀሌ ወረዳ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሳ አሊ፣ አሞሌ ጨው የሚወጣበት ባህላዊ ሥርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ ያለውን ለውጥ ለማሳየት አውጪዎቹ የሚገለገሉባቸው ቁሳቁሶች በክልሉ ሙዝየም ለዕይታ እንደቀረቡ ይገልጻሉ፡፡ ሰመራ ከተማ የሚገኘውን ሙዝየም የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁሳቁሶቹ በተግባር ሲውሉ እንዲያዩና ጨው ከወጣ በኋላ ያለውን ጉዞ እንዲመለከቱም ለማድረግ ፌስቲቫሉ ይረዳል ይላሉ፡፡

ፌስቲቫሉ የአገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎችንም ያማከለ ሲሆን፣ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ከአፋር ሕዝብ ታሪክ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ‹‹አፋር በታሪክ ዐምድ›› በተሰኘው ጥናት እንደተመለከተው፣ የሕዝቡ የኢኮኖሚ ታሪክ ከክልሉ የቀይ ባህር ድንበርነቱና ከማዕከላዊ የኢትዮጵያ የንግድ መስመርነቱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በጥናቱ፣ ‹‹የአፋር ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ በግመልና በሌሎች አጋሰሶች ቅፍለት ጨው፣ የውጭ ሸቀጣ ሸቀጦችን ወደ ትግራይ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ሸዋ፣ ወሎ፣ ጅማ፣ ሲዳማ፣ ባሌና አርሲ እየወሰደ ሲሸጥ በምትኩም ጥራጥሬ፣ የዝሆን ጥርስ፣ የነብርና የዝሆን ቆዳዎች፣ ዕጣን፣ ከርቤ፣ ዝባድ፣ ቅመማ ቅመሞችን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ወደ ሩቅ ምሥራቅ፣ ወደ አውሮፓና ወደ ሰሜን አፍሪካ ይልክ እንደነበር ይታወቃል፤›› በማለት ተገልጿል፡፡

የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ማርኬቲንግ ባለሙያ አቶ አብዲ አህመድ፣ አረሆ የሚካሄደው በየጊዜው ቢሆንም፣ ከጉዞው አንዱን ቀን እንደ ፌስቲቫል በማድረግ በአካባቢው ግመል ስለሚሰጠው ትልቅ ቦታ ማሳየት እንደሚቻል ይገልጻል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች የቱሪስት መስህቦችን በመንከባከብ ረገድ ያላቸውን ሚና ለማሳደግና መንግሥትም ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጥ ለማድረግ ፌስቲቫሉ እንደሚያነሳሳ ይናገራል፡፡ በተጨማሪም ከግመልና ከማኅበረሰቡ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች የውይይት መድረኮች ይዘጋጃሉ ይላል፡፡ ለምሳሌ በዘንድሮው ፌስቲቫል በተካሄደው ውይይት ከኤልኒኖ ጋር በተያያዘ በአካባቢው በተሰከተው ድርቅ ሳቢያ ግመሎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት ተነስቷል፡፡ በአካባቢው የብዙ ግመሎች ባለቤት የሆኑ ዕውቅ ግለሰቦች ተገኝተውም ለግመል ስለሚደረገው እንክብካቤ ተነጋግረዋል፡፡

አቶ አብዲ እንደሚለው፣ የአፋር ሕዝብ ለግመሎቹ ካለው ፍቅር የተነሳ ግመሎቹን የሚያወድስበት ሥርዓት (ጋሊሳሬ የሚባል) አለው፡፡ ከክልሉ ሕዝብ ወደ 86.6 በመቶ የሚሆነው የሚኖረው በገጠራማ አካባቢ ሲሆን፣ ግመል የሀብት መገለጫ፣ የምግብ ምንጭ፣ መጓጓዣና ብዙ ብዙም ነው፡፡ ግመሎች ስለ አገልግሎታቸው ውዳሴ ሲንቆረቆርላቸው ጆሯቸውን ቆም አድርገው እንደሚሰሙም ይነገራል፡፡ ‹‹የሰው ሀብቱ የሚለካው ባለው ግመል ልክ ነው፡፡ ብዙ ግመል ያለው ሰው በራሱም ይተማመናል፡፡ ቤተሰቡ ቢታመም ወይም ጉዳት ቢደርስበት የሚጓጓዝበት ነው፡፡ ግመል እንደ ባንክ አካውንት ነውና በጣም ሲቸገር ተሽጦም በገንዘቡ ይጠቀማል፤›› ይላል፡፡

ግመሎች በቀለማቸውና በተለያየ ምክንያት የሚሰጣቸውን ስያሜ ይዘው ከቤተሰብ ወደ ልጅ መተላለፋቸው ማኅበረሰቡ የሚሰጣቸውን ክብር እንደሚያመላክት የሚገልጸው ባለሙያው፣ ብዙ መቶ ዓመታትን ያስቆጠረው አረሆ፣ በዳሎል፣ በርሀሌና በሌሎችም የአፋር አካባቢዎች የኢኮኖሚ መሠረት መሆኑን ያስረዳል፡፡ አሞሌ ጨውን ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ በዋነኛነት የአፋር ክልል ነዋሪዎች ቢሆንም፣ ከሌሎች አካባቢዎች ወደ ሥፍራው ለሥራ የሚሄዱም አሉ፡፡

ተጓዞች ከበርሀሌ ተነስተው ሰባ የተባለ ቦታ አርፈው አህመድ ኤላ ይደርሳሉ፡፡ ጨው የሚመረትበት ቦታ በነጋታው ደርሰው ጨው ጭነው ከወጡ በኋላ አረፍ እያሉ ተጉዘው ከአራት ቀን በኋላ ወደ ገበያው ይደርሳሉ፡፡ በአካባቢው መተዳደሪያ ከሆኑ ሥራዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው አርብቶ አደርነት ሲሆን፣ አረሆም ሌላው ገቢ ማግኛ ነው፡፡ አረሆ ከአንድ አካባቢ ሲነሳ አንድ ሰው አርሆት አባ (የአርሆዎች መሪ እንደማለት) መሪ ይሆንና ሌሎች ባለግመሎች ይከተሉታል፡፡ በጉዟቸው ወቅት የሚያርፉበትን ቦታ የመምረጥና አጠቃላይ ሒደቱን የመቆጣጠር ኃላፊነት ይወሰዳል፡፡

አብዲ እንደሚለው፣ አሳይታ ውስጥ ወደ 500 ግመሎች ያሉት ሰው ያለ ሲሆን፣ እንደየሰው አቅም አንድ ግመል ብቻ ያለውም አለ፡፡ የአንድ ሰው የግመል ሀብት የሚፈለገው ደረጃ ሲያደርስ ሰቡ በሚባል ሥርዓት በግመል ወተት ይታጠባል፡፡ እሱ ኑሮውን ከተማ ካደረገ በኋላ ግመሎቹን የሚንከባከብለት ሰው ባያገኝም 20 ግመሎቹ ከገበያ ዕቃ የማመላለስ፣ ውኃ የማጓጓዝና ሌላም አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ግመል በቀን በአማካይ እስከ 13 ሊትር ወተት ስለምትታለብ በወተቱም ተጠቃሚ ነው፡፡ የግመል ቆዳ በባህላዊ መንገድ ምንጣፍና ጫማ ለመሥሪያነት (አፈርከቤላ የሚባል) ይውላል፡፡ ቆዳው እንደ ኬኬና ሆራ ላሉ ጭፈራዎች ማጀቢያ የሚሆን ከበሮም ይሠራበታል፡፡ በአሁን ወቅት የአንድ የግመል ዋጋ ወደ 28,000 ብር የደረሰ ሲሆን፣ ለአረሆ የሚሆኑ ግመሎች ከባለቤታቸው ጋር ለዓመታት የኖሩ ናቸው፡፡

‹‹የአፋር ብሔረሰብ ባህላዊ እሴቶች›› የተሰኘው ጥናት እንደሚያስነብበው፣ አርብቶ አደሩ የቤት እንስሳቱን በሚገባ ስለሚንከባከብ ጥንካሬያቸውን ለማሳየት የከብቶችና ግመሎች ውድድር ይካሄዳል፡፡ አሁን አሁን እየቀረ እንደመጣ የሚገለጸው ከዩ ባህላዊ የግመል ግልቢያ ውድድር ሲሆን፣ የተወዳዳሪዎችን ግመል ቁመናና ብርታት እንዲሁም የጋላቢውን ብቃት ለማሳየት ይካሄዳል፡፡ ውድድሩ መኖና ውኃ እንደልብ በሚገኝበት ወቅት የሚደረግ ሲሆን፣ ከአምስት እስከ አሥር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መሆኑም ይነገራል፡፡ ውድድሩን በግለሰቦች መካከል ወይም አንዱ ጎሳ ከሌላው ጋር በመፎካከር ሊያከናውነው ይችላል፡፡

ይህን መሰል ግመልን ያማከሉ ክንውኖች በሌሎች አገሮች ሲካሄዱ፣ ዓለም አቀፍ ትኩረት ይስባሉ፡፡ ክንውኖቹን ለመመልከት ከሚሄዱ ጎብኚዎች በተጨማሪ መገናኛ ብዙኃንም ይታደማሉ፡፡ በፓኪስታኑ የግመል ፌስቲቫል የአካባው ነዋሪዎች በባህላዊ አልባሳት ተውበው፣ ግመሎቻቸውም በጌጣ ጌጥ ደምቀው፣ የግመል ዳንስና ልዩ ልዩ ትርዒት ይቀርባል፡፡

በተመሳሳይ በህንድና አቡዳቢ የሚካሄደው ፌስቲቫልም ትኩረት ሳቢ ነው፡፡ በአቡዳቢው ፌስቲቫል የግመል የቁንጅና ውድድር ተካሂዶ፣ አሸናፊዎቹ ከከፍተኛ ኃላፊዎች ሽልማት ያገኛሉ፡፡ በየአገሩ ያሉ ፌስቲቫሎች የሚያካትቷቸው ክንውኖች ሚሊዮኖች የሚወጣባቸውና በዚያው ልክ ገቢ የሚያስገኙም ናቸው፡፡ በአገራችን ግን ከግመል ጋር የተያያዙ ክንውኖች ከአንድ አካባቢ ሲያልፉ አይስተዋልም፡፡ አረሆን ፌስቲቫል የማድረግ ጅማሮ ብዙ ርቀት ቢቀረውም ተስፋ ሊጣልበት ይችላል፡፡ በስፋት ከተሠራበት እንደ አቶ ገብረሥላሴና አቶ ደስታ ለዓመታት ጨው ያጓጓዙ ግለሰቦች የሚጠቀሙበትም ይሆናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...