Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ብራናዎቹን ማን ይታደጋቸው?

ኢትዮጵያ የዓለም ቅርስ ከሆኑት እነዚህ ጥንታውያን መጻሕፍት ባሻገር  የበርካታ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች ባለቤት ናት፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ መስጊዶችና ሌሎችም ተቋሞች የቅርሶቹ ቀዳሚ መገኛ ሥፍራ ናቸው፡፡ ጥንታውያኑ መጻሕፍት አገር በቀል ዕውቀትን አምቀው እንደመያዛቸው ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው መረጃ የሚሸጋገርባቸው ድልድዮችም ናቸው፡፡ ድርሳናት እንደሚጠቁሙት፣ በጥንታውያን ገዳማትና መስጊዶች የሚገኙ የጽሑፍ ቅርሶች ምን ዓይነት ይዘት ያላቸው መጻሕፍት፣ በምን ያህል መጠን፣ በየትኛው ተቋም፣ እንደሚገኙ በቅጡ አለመታወቁ ቅርሶቹ ለስርቆት ከሚዳረጉባቸው ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳል፡፡ ለጉብኝት፣ ለጥናትና ምርምርና ሌሎችም ምክንያቶች ወደ አገሪቱ የሚመጡ ግለሰቦች ለስርቆቱ ቀዳሚ ተጠያቂ ሲሆኑ፣ ዜጎችም የቅርስን ዋጋ ባለመገንዘብና በገንዘብ በመደለል ይተባበራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ጽሑፋዊ ቅርሶችን በባህላዊ ቤተ መዛግብቷ፣ በዋሻና በከርሰ ምድር ውስጥ ከወራሪዎች ዘረፋ ደብቃና ጠብቃ አኑራለች፡፡ ሆኖም የባህልና ታሪክ እንዲሁም የማንነት መገለጫ የሆኑት የመረጃ ሀብቶች ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ እየተደረገላቸው ባለመሆኑ ለሕገወጥ ዝውውርና ዘረፋ መጋለጣቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከሚፈጸሙ ስርቆቶች በተጨማሪ ቅርሶችን በሕገወጥ መንገድ ከአገር ለማስወጣት ሲሞክሩ የተያዙም አሉ፡፡ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው ብራናዎቹ 2007 እስከ 2009 .. በሦስት ግለሰቦች እጅ የነበሩና ወደ ውጭ ሊወጡ ሲሉ በፌዴራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ናቸው። 100ዎቹ ብራናዎቹ በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቡድን አስፈላጊው የማጣራት ሥራ ሲደረግባቸው ቆይተው ለሚመለከተው አካል እንዲሰጡ በፍርድ ቤት ብይን በማግኘታቸው መሰንበቻውን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ተረክቧል፡፡ ቅርሶቹን ያስረከቡት የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የልዩ ልዩ ወንጀል ምርመራ ዲቪዥን ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ሞላ አናጋው እንዳስታወቁት፣ ብራናዎቹ በተለያዩ መደብሮችና ቤቶች ውስጥ ሊያዙ የቻሉበት አጋጣሚ የተፈጠረው አንድ ቻይናዊ ከአገር ለመውጣት በሚያደርገው ሙከራ በእጁ ላይ በያዘው አምባር ከየት እንዳመጣ ፖሊስ በሚያጣራበት ወቅት ነው። የተለያየ መጠን ያላቸው ብራናዎቹን የተረከቡት የቅርስ ምዝገባ፣ ቁጥጥርና ደረጃ ማውጣት ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ አበባው ሲሆኑ፤ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታን ጨምሮ የቅርሶቹን መመለስ አስመልክቶ በወቅቱ ለሪፖርተርና ለሌሎች ሚዲያ ጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ ሔኖክ ያሬድ መግለጫውንና ምልልሱን እንደሚከተለው ቀምሮታል፡፡

  • ስለቅርሶቹ መመለስ የባለሥልጣኑ ዕይታ

አቶ ደሳለኝ፡-  ብራናዎቹን በአግባቡ ተንከባክቦ ለጥናትና ምርምር እንዲውሉና ለቀጣዩ ትውልድ መተላለፍ ወደሚችለበት ቤታቸው መመለሳቸው ደስተኞች ነን፡፡ በሌላ በኩል  በጥቂት ግለሰቦች ብዛት ያላቸው ቅርሶቻችንን በሕገ ወጥ መንገድ ይዘው መገኘታቸው ያሳዝናል፡፡ የብራና ቅርሶቻችንን ዛሬም ቢሠሩ በፊትም ቢሠሩ ከአገር መውጣት አይችሉም፡፡ በቅርስ ጥናትና አጠባበቅ አዋጅ ቁጥር 209/1992 መሠረት፣ ከቅርሶቹ ጋር በተያያዘ ሁለት አካላት ትኩረት ያሻቸዋል፡፡ የመጀመሪያው የቅርሱ ጠባቂ የሆኑ የእምነት ተቋማት በአግባብ የመጠበቅ፣ የመንከባከብና ከአደጋ መጠበቅ አለባቸው፡፡ ቅርሶቹ እየወጡ ያሉት ከነርሱ በመሆኑ ሁለተኛው የስጦታ ዕቃ መደብሮች ከስጦታዎች ጋር ብራናዎች ቀላቅለው ይታዩበታል፡፡ ብራናዎቹ ከፍተኛ ዕውቀት የያዙ ከሥነ ከዋክብት ከፍልስፍና ከታሪክ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡

 አቶ ዮናስ፡- የአገራችን የቅርስ አጠባበቅ አዋጅ አንቀጽ 8 መሠረት የብራና ጽሑፍ ከሚንቀሳቀስ ቅርስ ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ የብራና መጽሐፍ ከአገር ወጥቶ ሊዘዋወር ባለቤትነቱ ለሌላ ሊሸጋገር አይችልም፡፡ ይህ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡ አገራችንን ለማስተዋወቅ በልዩ ሁኔታ ሕግና ሥርዓትን ተከትለው ለጊዜያዊ ኤግዚቢሽኖች ቅርሶች ከአገር ሊወጡ ይችላሉ፡፡ ከዚያ በመለስ ግን በባለቤትነት ለሌላ ማስተላለፍ አይቻልም፡፡ የቅርስ ባለይዞታነት በግለሰቦች፣ በሃይማኖት ተቋማት፣ በድርጅቶች በመንግሥትም ሊሆን ይችላል፡፡ የቅርስነት እሴታቸውን እስኪጠበቁ ቅርስነትን ይላበሳሉ፡፡ ባለይዞታው ቅርሱ የሚሸከመው ነገር የሕዝብ ስለሆነ የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፡፡

      በአገር አቀፍ ደረጃ የመረጃ ዳታ ቤዛችን ውስጥ ሊገቡ የሚገባቸው ቅርሶች በየቦታው እንዳሉ ይታመናል፡፡ ብራናዎቹ ይዘታቸው ብዙ ነው፡፡ ማንኛውም መጽሐፍ መቅደሙን ካላነበብነው አንረዳውም፡፡ ከተረዳነውም ምናልባት በተዛቢ መልኩ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ የብራና መጻሕፍት ውስጥ ያሉት ዕውቀቶች በኢትዮጵያዊነታቸው ላይ የመቅድም ገጾች ናቸው፡፡ ስለዚህ በውስጣቸው ያሉትን ዕውቀቶች በትክክል ካልተገነዘብን ልንገነባት የምንመኛትን አገር የተሟላ አድርገን መሄዱ አስቸጋሪ ይሆንብናል፡፡ አገር በቀል ዕውቀቶች በብራና የተደጎሱ መጻሕፍት ስለሆኑ ብቻ አይደለም፤ የያዙት ዕውቀት ኢትዮጵያዊነታችንን በደንብ የሚያንፀባርቁ፣ አዲስ ትውልድ ስንገነባ እንዲሁ የምነሳ ሳይሆን ከትናንትናው በመነሳት ነው፡፡ ኅብረተሰቡ እነዚህ ሀብቶች ሀብቶቼ ናቸው፣ የማንነታችን የውስጥ ገጾች ናቸው የሚል ግንዛቤ ፈጥረን እንዲጠብቃቸው ካላደረግን በቀር በር ላይ ሊወጡ ሲሉ የምንጠብቅበት አካሄድ ሩቅ መንገድ ይዞን አይሄድም፡፡ ያንን ሀብቶች በየደረጃው የኢንቬነተሪ ሥራ መከናወን ይገባዋል፡፡ ከባለቤቶቹ ተቀምጠው ግን ምዝገባ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሊወጡ የሚችሉባቸው አካባቢው ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ሌላው ተግባር ነው፡፡ በሌላ በኩል ቱሪስቶች በሚንቀሳቀሱበት ቦታ የሚዘዋወሩ ደላሎች አዳዲስ የስጦታ ዕቃዎች በማስመሰል ቅርሶችን እንዲዘዋወሩ፣ እንዲሸጡ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሌላው ተግባር ይፈጽማሉ፡፡

       ከሚመጡት ቱሪስቶች (ሁሉንም ማለት አይደለም) ጋር ተቀላቅለው የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ ደላሎች አሉ፡፡ ስለዚህ በስጦታ ዕቃ መሸጫ መደብር የሚሠሩ በጥንቃቄ ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ መሥራት አለባቸው፡፡ የሚያሳዝነው ቅርሶችን ያዘዋወሩ አካላት የተቀመጡት ከአንድ እሰከ አራት ዓመት በሚደርስ እስራትና ከአንድ ሺሕ እስከ አራት ሺህ ብር ብቻ ነው፡፡

  • ብራናዎቹ እንዴት ሊያዙ ቻሉ? ከየትስ መጡ?

ምክትል ኢንስፔክተር ሞላ፡- ብራናዎቹን ልናገኝ የቻልነው አንድ ቻይናዊ ወደ አገሩ ለመሄድ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ሲደርስ በእጁ በዝሆን ጥርስ የተሠራ አምባር ይዞ በመገኘቱ የተፈጠረ አጋጣሚ ነው፡፡ ያመጣውም ቸርችል ጎዳና አካባቢ በሚገኝ የስጦታ ዕቃ መደብር መሆኑን በገለጸው መሠረት፣ በፍርድ ቤት ትዕዘዝ መደብሩን ስንፈትሽ የተወሰኑ የብራና መጻሕፍትና የተለያዩ የዱር እንስሳት ውጤቶች አገኘን፡፡ በልደታና ቤቴል አካባቢዎች በሚገኙ መኖሪያ ቤቶችም ያስቀመጣቸውንም በጠቅላላው 65 ብራናዎችን አግኝተናል፡፡ ምርመራችንን አካሂደን በፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡ ብራናዎቹ ከገዳማት፣ ከቤተ ክርስቲያናት የተወሰዱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ምርመራችን የሚያሳየው በሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን አካባቢ ከሚገኙ ገዳማት እንደሆነ ነው፡፡

  • ስለተያዙት ብራናዎች ይዘትና  ስለሚቀመጡበት ሥፍራ

አቶ ደሳለኝ፡- የብራና መጻሕፍቱን ይዘት ገና ወደፊት በባለሙያዎች የምናስጠናው ይሆናል፡፡ ከአቀማመጣቸው ጋር በተያያዘ ምንም ችግር የለም፡፡ ከብራና ጽሑፎች ጋር በተያያዘ የራሱ ባለሙያ የተደራጀ ቤተ መጻሕፍት አለው፡፡ ቅርሶች በዓይነታቸው የሚመዘገቡ ሲሆን ከሰባት ዓይነቱ አንዱ የብራናው ክፍል ነው፡፡ ሰብስቦ ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን ለጥናትና ምርምር ምቹ ማድረግንም ይይዛል፡፡ የመመዝገቡ፣ ዲጂታላይዝ ማድረጉ የተያያዘ ሥራ ነው፡፡ መሥሪያ ቤታችን በየጊዜው የግንዛቤ ማስጨበጫ ቤተክህነትን ጨምሮ ለተለያዩ አካላት ይሰጣል፡፡ ለስጦታ ዕቃዎች መደብሮችም ጭምር፤ ከሌሎች አካላት ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋርም እንዲሁ፡፡ በሕግ ማዕቀፍ በመግባቢያ ሰነድ ጭምር የታገዘ የቅርስን ምንነት በሚያስገነዝብ መልኩ ይከናወናል፡፡

  • ቅርስን ስለሚጠብቀው ሕግ ጥንካሬ

አቶ ደሳለኝ፡- በእርግጥ ሕጉ ጥንካሬ አለው ማለት ያዳግታል፡፡ እነዚህን ትላልቅ ሀብቶቻችን የወሰደ ሰው ቅጣቱ እስርና 4,000 ብር ብቻ ነው፡፡ እንደ መሥሪያ ቤታችን እነዚህ ቅጣቶች በቂ ናቸው ብለን አናምንም፡፡ ምናልባት በሒደት ጠንከር የሚልበትና የሚሻሻልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡

አቶ ዮናስ፡- ቅርስን በመጠበቅ በኩል ቅንጅቱን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ቅርስን አንድ ባለይዞታ መያዝ፣ ማውረስ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል የግል ይዞታቸውን የሚያበረክቱ እንዳሉ ለእነሱም ምስጋና ያቀረብንበት ሌሎችም ሊከተሉት የሚገባ ነው፡፡ ፖሊስ በፍርድ ቤት ሒደት ለቅጣት ውሳኔ ይመች ዘንድ የተያዘው ብራና የዋጋው ግምቱን ስጡን ይለናል፡፡ እስቲ እግዜር ያሳያችሁ [ባለማህደሩን ብራና እያሳዩ] ይሄን ቅርስ ማነው ይህን ያህል ዋጋ አለው ብሎ የሚገምተው? ቅርስ ከማንኛውም ገንዘብ ዋጋ በላይ ነው፡፡ ሕጉ ያስቀመጣቸው ቅጣቶች ምን ያህል ናቸው? የመከለስ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ ሕጉ በሚከለስበት ጊዜ የራሳችን ግብአት እንደተጠበቀ ሆኖ ከሁሉም በላይ ግን እንደ ዜጋ የሚያሳፍር ሥራ ሊሆን ይገባል የሚለውን መውሰድ አለብን፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የቆመው የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ፋውንዴሽን

የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት አባላት ለአገራቸው የሕይወት መስዋዕትን ለመክፈል የወደዱ፣ ለአገራቸው ክብር ዘብ የቆሙና ውለታን የዋሉ ናቸው፡፡ እነኚህ የአገር ጌጦች በአገሪቱ በተከሰተው የሥርዓት ለውጥ...

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...