Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እንጠንቀቅ ወይስ እንተናነቅ?

ሰላም!  ሰላም! ሰው ‹በፍቅር ቀን› አብዶ አሳበደን እኮ። ያብዛልን ነው። ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ቀን የሩኒና የሮናልዶን ጫማ ቁጥር በምንሰበክበት አገር ለፍቅር አንድ ቀን መመደቡ በራሱ ያበሳጫቸው አጋጥመውኛል። ዘንድሮ ግጥሚያና አጋጣሚው ለጉድ ነው። ያጋጣሚን ነገር ካነሳሁ አንዱ ሾካካ፣ ‹‹አንበርብር ከአንዲት መጠጥ ያለች ሴት ጋር ቆሞ ስልክ ቁጥር ሲለዋወጥ አየሁት፤›› ብሎ ለማንጥግቦሽ መናገር። በለጠፈና ባለጠፈ መሀል ‘ቫላንታይንስ ደይ’ እኩል እንደማይሠራ ልንገራችሁ ብዬ እኮ ነው። ታርጋ አውጥታችሁ ስትከራርሙ ፍቅርና ነገር መሳ ለመሳ ይረማመዱባችኋል። እናስ? ማንጠግቦሽ አኮረፈች። ይታያችሁ እንግዲህ። እኔ ደላላ ነኝ። ስልክ ስሰጥና ስቀበል ነው የምውለው። ወሬ አነፍናፊ ግን የሚታየው ሌላ ነው። እውነቴን እኮ ነው።

መቼ ዕለት ከባሻዬ ልጅ ጋር ስናወራ የሆነውን ብነግረው፣ ‹‹ዓለም እኮ ዝም ብሎ ነው አልበርት አንስታይንን ስም የሰጠው፤›› አለኝ። ‹‹እንዴት?›› እለዋለሁ፣ ‹‹ወሬን የመሰለ ኃይድሮጂን ቦምብ ፈልሳፊዎች እያሉ ምን ወደ ሌላ የኢነርጂ ቀመር ፈልሳፊ ያስኬዳል?›› አለኝ። የደረሰብኝ አንገብግቦኛልና ‘ኧረ ልክ ነህ ብዬ’ በልቤ አጨበጨብኩለት። በልቡ የሚያማን ሳታሙ በልብ እንዴት ይጨበጨባል የምትሉት እናንተስ ብትሆኑ ምን ለማለት ነው? ጉዳዩ እኮ ‘ሲሪየስ’ ነው። (መቼስ በእንግሊዝኛ ካላሴረስነው እንደ ቁምነገር የምንቆጥረው ነገር እያደር አንሷል) የታላቁ የፍቅር ፀር ነገር እንደሆነ አጣችሁትና ነው? የነገር አምራቹ ደግሞ የወሬ ሊቅ ነው። ይኼው ታዲያ በወሬ ሱስና በወሬ ፍተላ የስንቱ ቤት ሲፈርስ ዝም እየተባለ፣ ማስታወቂያው ሁሉ ‘ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች . . . ክልክል ነው’ እያለ በጎን ሌላ ጨዋታ ይጫወታል። ኧረ መቼ ይሆን ወሬና ወሬኛ የሚዛትበት? ናፈቀኝ!

የፍቅርን ነገር ካነሳሁ ታዲያ ያኔ በደጉ ጊዜ ይኼውላችሁ እኔና ማንጠግቦሽ ስንጣበስ፣ ‹‹ደብዳቤ ቢጽፉት እንደቃል አይሆንም፣ እንገናኝና ልንገርህ ሁሉንም፤›› ብላ ትልክብኝ ነበር። ሴቶች መቼም ከወደዱ እኮ ሙሴ ቀይ ባህርን ከከፈለው በላይ ፓስፊክን ካላደረቅን ባዮች ናቸው። የደረሰበት ያውቀዋል። ሳይፈልጉም ታዲያ የዚያኑ ያህል ናቸው። ‹‹ምነው ባደረገኝ የደጅሽን አፈር፣ አንቺ ስትረግጭኝ እኔ እንድንፈራፈር፤›› ያለው ሙሉቀን መለሰ በጤናው አይመስለኝም። አሁን የእኔንና የማንጠግቦሽን ታሪክ ያነሳሁት ሰሞኑን ከምሰማው አጓጉል ነገር በተለይ ከፆታዊ ትንኮሳና ወንጀል ጋር ቅር ያለኝ ነገር ስለበዛ ነው። ማን አለኝ? እናንተው ናችሁ ቅሬታዬን የምታንቃርሩ። የአገሪቷ ቅሬታ ሰሚ ቢሮዎች እንደሆኑ ባልሰሙዋቸው ቅሬታዎች ላይ ቅሬታ ሊያሰሙ፣ ሌላ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ለማቋቋም ስብሰባ እየያዙ አስቸግረዋል።

‹‹እኔስ ይኼ ስብሰባ የሚባል ነገር እስኪያልቅ ላልተወሰነ ጊዜ ለምን ‘ቫኬሽን’ ውጡ እንደማይሉን አይገባኝ?›› የሚለኝ የባሻዬ ልጅ ነው። የዘንድሮ ልጅ ታውቁት የለ ገና ሳያድግ እያረጀ ቶሎ ቶሎ ይደክመዋል። እኔማ አንዳንዴ ላንጋኖና ሶደሬ እንደ አዲስ አበባ መንገዶችና ቤቶች መልሶ ማልማትና ማስፋት ዕቅድ ውስጥ ካልገቡ፣ ለ‘ቫኬሽን’ የሚዝተውን ሕዝብ ለማስተናገድ የሚችሉ እየመሰለኝ አይደለም። ቀላል የሚዝተው በዝቷል እንዴ? እ . . .  ምን እያልኩ ነበር? ጉድ ፈላ እንደ አፍሪካ መሪዎች እያወራሁ እንቅልፍ ይዞኝ ይሄድ ጀመር? ‹‹የጉድ ቀን ቶሎ አይመሽ›› አለ ያገሬ ሰው። ኧረ ይኼን ያገሬን ሰው ምን አባቴ ላድርገው ዛሬ። እውነት የጉድ ቀንና የጉድ ዘመን እኮ ሲንጀላጀል ጥሩ ማሳያ እንደ እኛ የሚሆን የለም!

ስለፈቃድ ነበር የማወራው አይደል? የንግድ ፈቃድ አላልኩም። በፍቅር መፈቃቀድ፣ መዋደድ ነው ያልኩት። ምንም እንኳን ዛሬ በፍቅር ስም ብዙ ነጋዴ ቢበዛም። ዘመኑ የልማት ነው ብለን እንለፈው ተውት። እና ይገርማችኋል የእኔና የማንጠግቦሽ ፍቅር ልዩ ነበር። እንዳሁኑ የቅፅበታዊ ስሜት ጉጉት እየገባ አይበጠብጠው፣ የቴሌ ጣጣ ንፋስ ሆኖ አይገባብን፣ የታክሲ ችግር ቀጠሮ አያስረፍደኝ አያስረፍዳት (ኧረ ማን ወያላ ነው በበሞቴ በነፃ ላሳፍራችሁ ብሎ ያለመነን? እስኪ የሎተሪ ዕጣ ብቻ ከምትፍቁ የዘመን ሎተሪም ፈልጋችሁ ቁረጡና ከደረሳችሁ በእኛ ጊዜ ተወለዱ)፣ ዛሬ ግን የምሰማው ነገር ያስደንቀኛል። ስንት መግባቢያ ቴክኒክና ታክቲክ ባለበት ዘመን፣ ቢቆራረጥና ቢዘገይም ኢንተርኔት እያለ፣ ስንት ወሬ ማስጀመሪያ ተናግሮ ማናገሪያ ርዕስ እያለ ለምሳሌ ‹‹የቁጠባ ቤቶች ዕጣ እንዲህ በአጭር ጊዜ የሚወጣልን ይመስልሻል?›› ቢሏት የሆዷን አውግታ ቡና ካልጠጣን የምትል እንስት በማትጠፋበት ዘመን መጥለፍና ማስገደድን እንስሳት እንኳ ትተዋል።

የምሬን ነው! እንስሳት እንኳ ትተዋል! ካላመናችሁ እንግሊዝ አገር አንድ ውሻ ዓይኑን የጣለባትን እንስት ውሻ ለማግኘት የተጠቀመውን አማላይ ቴክኒክ ‘ሰርች’ አድርጉ። ምነው እናንተ የፖለቲካ ሸረኞችን ዜና ስትሸሹ ስንት ነገር እኮ እያመለጠጣችሁ ነው! ‹‹መቼም ሠልጥኖ የማይሠለጥንን ዓለም የሽብር ዜና ከመቁጠር፣ በደመነፍስ የሚመሩት እንስሳት የሚሠሩትን ሥራ ‘ስንት ነገር’ ብሎ ማጨብጨብ እፎይ ማስባል ብቻ ሳይሆን ሳያፀድቅም አይቀር፤›› ይሉኛል ከባሻዬ ጋር ስናወራ። ‹‹ሰው ግን ሰው ነውና፣ ቢነግሩት ቢመክሩት እሺ ማለት ከቶ አይቀናውምና፣ አለ ከመሞቱ ከሽረቱ ጋራ!›› ያለው ማን ነበር እናንተ! ዳሩ ማንም ቢለው የሚፈለገው መባሉ ነው! ለመስማት ለመሰማማቱማ አልተፈጠረም እያልኳችሁ? እንዴ በእሑድ ምድር እንኳ ስለካሽ ሬጂስተር ማሽናችሁ መጨነቅ ለአፍታ አቁማችሁ ብትከታተሉኝ ምን አለበት? የወሬ ያለህ ያሰኛችሁ!

ዛሬ እንዲህ ስለሥራ ውጣ ውረድ በየመሀሉ ጣልቃ ሳላስገባ የባጥ የቆጡን የምቀደው ለካ ምን ሆኜ እንደሰነበትኩ አልነገርኳችሁም? የእኔ ነገር! የሚያዝል፣ የሚያዞር፣ ካልጋ ከወረዱ የሚጥል ወረርሺኝ (ደግሞ ይኼንንም በዓለም አንደኛና ብቸኛ ካላስባለን እንዳንል እንጂ) ጉንፋን አሞሃል ተብዬ እንዲቺው የሰነበትኩት አልጋዬ ላይ ነው። ያው ስልኩ ስላለ አንዳንዴ ሲሻለኝ በስልክ የምሸቅለው ሽቀላ እንዳለ ነው። ታዲያ ልምከራችሁ? ምንም ቢሆን በዚህ ጊዜ መያዝ የለባችሁም። እኔ በፖሊስ አላልኩም በበሽታ ነው! ኧረ እባካችሁ እያጣራችሁ ስሙ። ምርጫ በማጣራት የዛሉት አንሷቸው ወሬ አጣሩልን ብለን አውሮፓ ኅብረትን ማስቸገር እኮ ነው የቀረን። ታዲያላችሁ አንድ ወዳጄ ደውሎ፣ ‹‹ያንን ቤት ላሳይልህ ሰዎች አግኝቻለሁ፤›› አለኝ። ባለሁለት ፎቅ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ነው። ‹‹ጥሩ አሳያቸውና መልሰህ ደውል፤›› ብዬው እኔ በቴሌቪዢን የአሜሪካን ጉድ እኮመኩማለሁ።

ለካ እዚያም ሰው ይቆጣል። አይ ጊዜ። እነሱም ወግ ደረሳቸውና ይኼው መከፋፈልን እየቀመሷት ነው። እሰይ ባይባልም መቼስ አንዳንዱን ነገር ካላዩት አይረዱትምና ሰሞኑን ያለቅጥ የትራምፕ ደጋፊ ሆኛለሁ። በሁለት አፍ ማውራትና የቋንቋ መደበላለቅ በእትዬ አሜሪካ እልፍኝ ተቀጣጥሎ ሳይ የአፍሪካ አምላክ እላለሁ። ለካ የእነሱም ዴሞክራሲ የጭንቅ ቀን ለገላጋይ ይከብዳል? እነዚህ ሰዎች በመረጡት ፕሬዚዳንት ያውም ገና በወር ዕድሜያቸው እንዲህ ከሆኑ እንደኛ ሳምንት ሁለት ሳምንት ውኃ ቢሄድባቸው፣ ሙስና ቢደቁሳቸው፣ በየሄዱበት ቢሮ ስብሰባ ላይ ናቸው ቢባሉ አሜሪካ የምትባል አገር ከዓለም ካርታ ላይ ልትጠፋ እንደምትችል አሰብኩ። ‹‹አወይ ሥልጣኔ! እውነት የምር የሠለጠነችው ሥልጣኔ፣ ከግጭትና ከሁከት በላይ ክንፍ አውጥቶ የበረረ ሕዝብ ያዘለችው ሥልጣኔ መገኛዋ የት ይሆን?›› ስል ማንጠግቦሽ ሰማችኝ፡፡ ‹‹አርፈህ ጉንፋንህን አታስታምም? በሰው ፀብ ምን ጥልቅ አደረገህ?›› ብላ ተቆጣችኝ። ስልኬ አልጠራም። ወዲያው ጭልጥ አድርጎ እንቅልፍ ወሰደኝ። ማንጠግቦሽ ‘አያገባህም’ ብላ ዝም ብታስብለኝም በህልሜ ጭራሽ ‘ቪዛ’ ሳይመታልኝ ብጥብጡ መሀል ድንጋይ እወረውራለሁ። መቼም ድንጋይ መወርወር ሲሳይ ነው እንዳትሉኝና እንዳንጣላ!

በሉ እንሰነባበት። ሰሞነኛው ወሬ በዝቶብኝ ግራ ገብቶኛል። በተለይ በጃፓንና በሃይቲ ያሽሟጠጥነው ሽሙጥ ወደኛ ሊመጣ ይሆን እያልኩ በሚንተከተከው የአፋሩ እሳተ ጎሞራ ወሬ ጉልበቴ ከድቶኛል። ‹‹ከላይ እሳት ከታች እሳት ሆኖብን ምን ልንሆን ነው?›› የሚለኝ የባሻዬ ልጅ ነው። ባሻዬ ደግሞ በበኩላቸው፣ ‹‹እንግዲህ ዘመኑ ቀርቧል። በልዩ ልዩ ሥፍራ የመሬት መናወጥ ይሆናል ይላል ቃሉ። አርፋችሁ በጊዜ ንስሐ ግቡ፤›› ይሉናል። ማንጠግቦሽ በፈንታዋ፣ ‹‹እሱ ካመጣው ምን ልታደርግ ነው? እሳት እንደ ውኃ አይገደብ?›› ትለኛለች። በየአቅጣጫው አስተያየቱ ሲበዛብኝ ብቻዬን ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪ እጓዝና እቆዝማለሁ። እዚያም አመሻሽቶ ሰው ሞቅ ሲለው የሚያወራው ስለዚሁ ነው። አንዱ እንዲህ ይላል ‹‹እኔ በጣም የማዝነው ግን ይህንን የመሰለ ታላቅ ክስተት እየተከናወነ እኛ ግን ልባችን ያለው የባርሴሎና ቀጣይ አሠልጣኝ ማን ይሆናል የሚለው ላይ ነው፤›› ይላል። ሌላው ቀጠል አድርጎ፣ ‹‹ታዲያ ከዚህ በላይ ምን እንድናስብ ፈለግክ? በሰው አገር ቡድን የሰው አገር መሪ ምርጫ ላይ ልባችንን በማሳረፋችን መሰለኝ ይችን ታክል የሰነበትነው፤›› ይለዋል። የኤርታሌው ጎሞራ ሲገርመኝ ደግሞ በዚህ በኩል ሌላ የነገር ጎሞራ ሲፈነዳብኝ ሒሳቤን ከፍዬ ውልቅ። ወዲያ ግራ ያጋባ ፍቅር፣ ወዲህ እሳተ ጎመራ፡፡ እንጠንቀቅ ወይስ እንተናነቅ? መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት