በወርቅ ቅብ የተንቆጠቆጠውና ለሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ ድምቀትን የሚፈነጥቀው ባለ አምስት ኮከብ ሪትዝ ካርልተን ሆቴል፣ ዛሬ እንደ ቀድሞው ለሀብታሞች የቅንጦት መስተንግዶ እየሰጠ አይደለም፡፡
ለዓይን የሚማርኩ አዳራሾቹ፣ የዋና ሥፍራው፣ መኝታ ቤቶቹና ሌሎችም አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎቹ የልዑላን ዓይነት መስተንግዶ ፈልገው ከሳዑዲም ሆነ ከውጭ የሚመጡ እንግዶችን ማስተናገድ ካቆሙም ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ ለከርሞው የስፖርታዊ እንቅስቃሴ፣ የሠርግና የውበት ሳሎን አገልግሎት የሚሰጡትም ክፍሎች ለእንግዶች በራቸውን ዘግተዋል፡፡
በሪያድ ከሚገኙ ሆቴሎች ሁሉ ግርማ ሞገስ የተላበሰ ገጽታ አለው የሚባለውን ሪትዝ ካርልተን ሆቴል የሚያስተዳድረው አካልም፣ ሥልጣኑን ለ32 ዓመቱ የአገሪቱ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢል ሰልማን ካስረከበ 25 ቀናት ተቆጥረዋል፡፡
ሆቴሉ የሀብታሞችና የዝነኞች መዝናኛ መሆኑ ቀርቶም 11 ልዑላንን ጨምሮ 201 የሳዑዲ ቱጃሮች እስር ቤት ሆኗል፡፡ ለቱጃሮቹ እስር ምክንያት የሆነው ሙስና ቢሆንም የፖለቲካ አንድምታ አለው ተብሎም በፖለቲካ ተንታኞች ተነግሯል፡፡
ቱጃሮቹና ልዑላን በታሰሩበት ሪትዝ ካርልተን ሆቴል በሳዑዲ መንግሥት ከተፈቀደላቸው ባለሥልጣናት፣ ጠበቆች፣ መርማሪ ቡድኖችና ቤተሰቦች በስተቀር መግባት የተከለከለ ነው፡፡ እስካሁንም ዓለም አቀፍም ሆኑ የሳዑዲ መገናኛ ብዙኃን ሲዘግቡ የቆዩት ከውጭ የሚባለውን እንጂ ከሆቴሉ ዘልቀው የታዘቡትን አልነበረም፡፡ ቢቢሲ ግን ባለፈው ሳምንት ተሳክቶለት ባገኘው ፈቃድ መሠረት በሆቴሉ ያለውን ድባብ ለመዘገብ የመጀመርያ ሆኗል፡፡ የቢቢሲ ዓለም አቀፍ ዘጋቢዋ ሊዚ ዱሴት ከባልደረባዋ ፊሊፕ ጉድዊን ጋር በመሆን በወርቃማው እስር ቤት ውስጥ ምን እየተከናወነ እንደሆነ እንዲህ ትገልጸዋለች፡፡
‹‹ማንም ሰው ከመንግሥት ፈቃድ ካልተሰጠው በስተቀር የሆቴሉን ተሽከርካሪ ጥቁር የብረት በር አልፎ መዝለቅ አይችልም፡፡ እኔና የሥራ ባልደረባዬ ፊሊፕ ጉድዊን ባገኘነው ፈቃድ መሠረት በፖሊስ ታጅበን በወርቃማ መብራት ወዳሸበረቀው ሆቴል ገባን፡፡ ከውስጥ እንደ ደረስን የአምስት ኮከብ መስተንግዶ የሚሰጡ ሠራተኞች ተቀበሉን፡፡ ሆኖም የሳዑዲ ባለሥልጣናት አቀባበል ጠንካራና ጥብቅ ነበር፡፡
‹‹የታሳሪዎችን ፊት መቅረፅም ሆነ ቃላቸውን መቅዳት አልተፈቀደም፡፡ ለጥቂት ሰዓታት ከባለሥልጣናት ጋር በነበረን ቆይታ ሙሉ መረጃ ባናገኝም፣ በሆቴሉ ውስጥ የታሳሪዎች ሕይወት ምን እንደሚመስል ፍንጭ አግኝተናል፡፡
‹‹ባህላዊውን ነጭ ጀለቢያ እንዲሁም ቀይና ነጭ መስመር ያለውን የራስ መጎናፀፊያ የለበሱ በርካታ ወንዶች ይታያሉ፡፡ ከአንዱ በረንዳ ጥግ ሆነው የሚያወሩትም በሹክሹክታ ነው፡፡ ሁሉም ዓይናቸውን ሰብረዋል፡፡ አልፎ አልፎ በሥፍራው ያለውን ፀጥታ የሚሰብረው፣ የሻይ ስኒው ውስጥ ያለው ትኩስ መጠጥ በብርማ ማንኪያ ሲማሰል የሚፈጥረው ድምፅ ብቻ ነው፡፡››
የሆቴሉ ልዩ እንግዶች እነማን ናቸው?
‹‹ልዑላኑ፣ ባለሀብቶቹና ባለሥልጣናት ወደ እስር ቤትነት ከተቀየረው ባለአምስት ሲደመር ኮከብ ሆቴል ከመግባታቸው በፊት ከነበራቸው ስሜት የአሁኑ የተለየ ለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በሳዑዲ አልጋ ወራሽ መሐመድ ሰልማን የሚመራው የፀረ ሙስና ዘመቻ ኮሚቴ አባል የሆኑ ባለሥልጣን ለጋዜጠኞቹ እንዳሉት፣ የታሰሩት ባለሀብቶችና ባለሥልጣናት የተፈጠረውን አላመኑም፡፡ የሚያስቡት ለታይታ ተብሎ ለአጭር ጊዜ የተወሰደ ዕርምጃ እንደሆነ ነው፡፡
‹‹ታሳሪዎቹ ተበሳጭተዋል፡፡ አንድን ሰው አንተ ሌባ ነህ ብትይው ይበሳጫል‘ ሲሉም እኚሁ ባለሥልጣን ተናግረዋል፤›› የማንንም ስም ጠቅሰው እንዳይጽፉ የተነገራቸው የቢቢሲ ጋዜጠኞች እንዳሰፈሩት፣ ከ200 በላይ የሚሆኑት ልዑላን፣ ባለሀብቶችና ባለሥልጣናት በሆቴሉ እንዲታሰሩ የተደረገው ሊያመልጡ ይችላሉ ከሚል ሥጋት መሆኑንም በዚያው ያገኙት ዓቃቤ ሕግ ነግሯቸዋል፡፡
የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት የታሳሪዎችን ማንነት ባይገልጽም፣ ታዋቂው ቱጃር ልዑል አልዋሊድ ቢን ታላል፣ የአልጋ ወራሹ ዘመድና የብሔራዊ ዘቡ መሪ ሚቴብ ቢን አብደላህ በሪትዝ ካርልተን ሆቴል ከታሰሩት መካከል እንደሚገኙ፣ ቀደም ብሎ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተነግሯል፡፡
በንጉሣዊ ቤተሰብ ተቀናቃኞችና የአገሪቱን ፖለቲካ በሚተቹት ላይ ብቻ እስራት መፈጸሙ የሳዑዲን መንግሥት ያስወቀሰና ያስተቸ ቢሆንም፣ ቢቢሲ በሆቴሉ በነበረው ቆይታ ሁሉም ታሳሪዎች በሕግ የሚያስጠይቅ ጉዳይ እንዳላቸው፣ የሁሉም ጉዳይም በማስረጃ የተደገፈ መሆኑን ከዓቃቤ ሕግ መረዳት ችሏል፡፡
መረጃ የማሰባሰብ ሒደቱ ሁለት ዓመታት የፈጀ ሲሆን፣ አንዳንድ ማስረጃዎችም ከአሥር ዓመታት በፊት ጀምሮ በሚስጥር ሲጠናቀሩ የቆዩ ናቸው፡፡
የፀረ ሙስና ኮሚቴው ከተዋቀረ በኋላ የተያዙት ባለሀብቶች እየተጠየቁ ሲሆን፣ ሒደቱም የሳዑዲን ሕግ የተከተለና ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉም ነፃነት የሰጠ ነው ተብሏል፡፡ ታሳሪዎችም በቅድመ ምርመራ ሒደት ላይ ሲሆኑ፣ ገንዘብ የወሰዱ እንዲመልሱ ተጠይቀዋል፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚቴው ባለሥልጣንም፣ ‹‹የምርመራ ሒደቱ የወዳጅነት ዓይነት ነው፣ መረጃ እናሳያለን፣ ችግሩን እንፈታለን፤›› ብለዋል፡፡
በሆቴሉ ከሚገኙት አብዛኞቹ ከእስር ቶሎ መለቀቅን የሚሹ ናቸው፡፡ በሆቴሉ የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ 500 ያህል ሰዎች ሲኖሩ፣ ወጪውም በሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት የሚሸፈን ነው፡፡
ሰባት እስረኞች በሕግ የተሰናበቱ መሆኑን፣ በሆቴሉ ታስረዋል ከሚባሉት 201 ሰዎች ውስጥም 95 በመቶ ያህሉ በድርድር ለመውጣት ፈቃደኛነታቸውን ማሳየታቸው፣ አራት በመቶው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይ የሚፈለጉ መሆናቸውን ጋዜጠኛዋ ዘግባለች፡፡
በድርድር ለመውጣት የሚፈልጉ ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ከሚገኝ ሀብታቸው አብዛኛውን ማለትም 70 በመቶ ያህሉን ወደ ሳዑዲ ግምጃ ቤት ለማስገባትና ከእስር ነፃ ለመውጣት ፈቃደኞች መሆናቸው በዘገባው ተገልጿል፡፡
በሪያድ የሚገኝ ነጋዴን ጠቅሶ ቢቢሲ እንዳሰፈረው፣ 1,900 የባንክ ሒሳቦች እንዳይንቀሳቀሱ ታግደዋል፡፡ ከእነዚህ አንዱ ተጠርጥረው ከታሰሩ ባለሀብቶች ቤተሰብ ውስጥ ነው፡፡ በአጠቃላይ የታገደውም 800 ቢሊዮን ዶላር ነው ይባላል፡፡ ይህንን በተመለከተ የፀረ ሙስና ኮሚቴው አባል እንደሚሉት፣ አገሪቷ 100 ቢሊዮን ዶላር ማስመለስ ከቻለች መልካም ነው፡፡
የሸመገሉ፣ የስኳር፣ የልብና ሌሎች ሕመሞች ያሉባቸው ታሳሪዎችም አሉ፡፡ ሆኖም በሆቴሉ ለሕሙማን ያለው ክብካቤ ያነሰ ነው ተብሎ ይታማል፡፡ ይህንን በተመለከተ ዘጋቢዎቹ ያገኙት መረጃ፣ በሆቴሉ በእያንዳንዱ ክፍል ዶክተሮችና ነርሶች የሕክምና ክትትል እንደሚያደርጉና ልዩ ልዩ መድኃኒቶችም ከታሳሪዎች ቤት ይመጣሉ ተብሏል፡፡
‹‹በባለ አምስት ኮከቡ ሆቴል ለሚገኙ ታሳሪዎች አስፈላጊው ሁሉ የሚቀርብላቸው ቢሆንም፣ የእያንዳንዱን ፍላጎት ግን ማሟላት አለመቻሉ ተገልጿል፡፡ አንዳንዶቹ የሩሲያ ካቪያር እንዲቀርብላቸው ሲፈልጉ፣ የግል ፀጉር ቆራጫቸውና ወጌሻቸው እንዲጠራላቸው የሚያዙም አሉ፡፡ ሆኖም ከልዩ አገር ልዩ ምግብ ልናመጣ አንችልም፤›› አንድ ባለሥልጣን ማለታቸው በቢቢሲ ዘገባ ተካቷል፡፡
ታሳሪዎቹ ተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው በመወሰዳቸው ቅሬታ ያሰሙ ቢሆንም፣ የመኝታ ቤት የመስመር ስልክ እንዲጠቀሙ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ጠበቆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ሊደውሉላቸውም ይችላሉ ተብሏል፡፡ የየኩባንያዎቻቸው ሥራዎች እንዳይደናቀፉ የድርጅቶቻቸው ባለሥልጣናት በስልክ መወያየትም ሆነ ሆቴሉ ድረስ መጎብኘት እንደተፈቀደላቸው፣ ኢሜይል መጠቀምም እንደሚችሉ ተዘግቧል፡፡
የቢቢሲ ጋዜጠኞች በአጃቢያቸው አማካይነት አንድ ባለሀብት ለማናገር ችለውም ነበር፡፡ ታሳሪው፣ ‹‹ብዙውን ሰዓት በክፍሌ ውስጥ ከጠበቃዬ ጋር አሳልፋለሁ፡፡ ትኩረቴ ጉዳዬ ላይ ነው፡፡ ከቤተሰቦቼ ጋር በስልክ በየቀኑ እገናኛለሁ፡፡ ሆኖም እዚህ መጥተው እንዲጎበኙኝ አልፈልግም፤›› ብለዋል፡፡
አጃቢው ከዚህ በላይ ስለክስ ጉዳዩ እንዲጠይቁ አልፈቀደላቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት ተሰናብተው ሲወጡ ከይቅርታ ፈገግታ ጋር፣ ‹‹ይቅርታ ባህላችንን ረሳሁ›› የሚል ድምፅ የሰሙት የቢቢሲ ጋዜጠኞች እንዳሰፈሩት፣ እኚህ ታሳሪ እንደ ባህላቸው፣ ወጋቸውና ልማዳቸው የሚጠጣ ወይም የሚበላ ነገር ባለመጋበዛቸው ይቅርታ ጠይቀዋቸዋል፡፡
በዚሁ የሆቴል ቆይታቸውን አጠናቀው የወጡት ጋዜጠኞች፣ እስረኞቹ በአዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት መጀመርያ ወይም በአሮጌው ዓመት ማብቂያ ሊፈቱ እንደሚችሉ ባለሥልጣናት እንደነገራቸው አስፍረዋል፡፡
‹‹አልጋ ወራሹ ጉዳዩን ቶሎ መቋጨት አለባቸው፡፡ ነገሮች በተጓተቱ ቁጥር ጥያቄዎች እየበዙ ይመጣሉ፤›› ሲል አንድ የሳዑዲ ባለሀብት እንደ ነገራቸው በዘገባቸው ሰፍሯል፡፡
(ጥንቅር በምሕረት ሞገስ)