ለዘመናት ትልልቅና አይረሴ ግጥሚያዎችንና ውድድሮች አስተናግዷል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፈርጦች በተለያዩ ጊዜያት እንደ ከዋክብት የፈነጠቁባቸው፣ ደጋፊዎች በስሜትና በሲቃ ያዜመላቸውን በርካታ ባለድሎች ያስተናገደው የአዲስ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም ማንነቱን የሚፈታተኑ የህልውና ጥያቄዎች ተደቅነውበታል፡፡
የስታዲየሙ የሳንቴሽንና የሐይጅን ይዘት፣ የንፅህናው አጠባበቅ የተመልካቾችን ደኅንነትና የመሳሰሉትን ፈተናዎች ማለፍ እየተሳነው መንገዳገድ ጀምሯል፡፡ ለዚህ ደግሞ በዋናነት የብሔራዊ ስታዲየሙ ባለቤትና አስተዳዳሪ ማንነት በውል አለመታወቁ እንደሆነ የሚናገሩ በርካታ ናቸው፡፡
ገበናው አደባባይ የወጣው ይህ ታሪካዊ የስፖርት ሜዳ፣ በመፀዳጃ ቤቶች ንፅህና እጦት ክስ ቀርቦበታል፡፡ ባለፈው እሑድ የካቲት 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ለአፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመከላከያንና የካሜሩን ዮንግ ስፖርትስ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ኡጋንዳዊው የዕለቱ የጨዋታ ታዛቢ ዳኛ ከሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አስቀድሞ ጨዋታውን እንዲያስተናግድ የተመረጠው የአዲስ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም፣ ከንፅህና ቤቶቹ ጀምሮ የተጨዋቾች ልብስ መቀየሪያ ክፍሎች ድረስ ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ ደረጃውን የጠበቀ ነው? አይደለም? የሚለውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ይሁንና ኡጋንዳዊው የጨዋታው ታዛቢ ዳኛ የአዲስ አበባ ስታዲየም መፀዳጃና የተጨዋቾች ልብስ መቀየሪያ ክፍሎች መስፈርቱን እንደማያሟላ በመግለጽ ጨዋታ በተከናወነ ማግስት ለካፍ ሪፖርት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የካፍ ብቃት ማረጋገጫ ዲፓርትመንት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማስጠንቀቂያ መጻፉም ተሰምቷል፡፡
ዓመታትን ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ዝግጅቶች፣ ኮንሰርቶችና በርካታ የተለያዩ ዝግጅቶችን በማስተናገድ ይታወቃል፡፡ በካፍና በፊፋ ድንጋጌዎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቋል ተብሎ የሚወሰድ አንድ ስታዲየም፣ በማንኛውም ሁኔታ አህጉራዊውም ይሁን ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን የሚያስተናግድ ከሆነ ቢያንስ ለ48 ሰዓታት ያህል ስታዲየሙ ከማንኛውም ዝግጅት ነፃ ይሆናል፡፡
ለዚህ ያልታደለው የአዲስ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም አይደለም 48 ሰዓታት ቀርቶ በተመሳሳይ ሰዓትና ጊዜ ሁለትና ከዚያም በላይ ዝግጀቶችን የሚያስተናግድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮችም በዋናነት የስታዲየሙን የባለቤትነት ጉዳይ ምክንያት መሆኑን ያስረዱት፡፡