Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትአትሌቶች ለሕገወጥ ዝውውር እየተዳረጉ ነው

አትሌቶች ለሕገወጥ ዝውውር እየተዳረጉ ነው

ቀን:

–  ቻይና ዋነኛ መዳረሻ ሆናለች ተባለ

የኢትዮጵያ አትሌቲክስና አትሌቶች በሕገወጥ ደላሎች ምክንያት ለሕገወጥ  ዝውውር እየተዳረጉ መሆኑን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ይፋ አደረገ፡፡ የፌዴሬሽኑ አዲሱ አመራር ሐሙስ የካቲት 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ከአትሌት ማናጀሮች፣ ከተወካዮቻቸውና ከአትሌቶች ጋር በብሔራዊ ሆቴል ባደረገው ውይይት፣ በአትሌቶች የግል ብቃትና ውጤት ብዙ ነገሩ ተሸፍኖለት የቆየው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በበርካታ ችግሮች የተተበተበ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የፌዴሬሽኑ አመራሮች፣ የአትሌት ማናጀሮች፣ አሠልጣኞችና የችግሩ ሰለባ እየሆኑ የሚገኙት አትሌቶች በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአትሌቲክሱና በአትሌቶች ህልውና ላይ እያንዣበበ ነው ተብሎ በሚታማው የሕገወጥ ሰዎች እንቅስቃሴ ከወዲሁ መፍትሔ ካልተበጀለት አደገኛ እየሆነ መምጣቱን ሲናገሩ ተደምጧል፡፡

መድረኩን የመራው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ የችግሩን አሳሳቢነት አጉልቷል፡፡ ‹‹ጉዳዩ ፌዴሬሽኑን እያስቸገረ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ጉዳይ እጃቸውን ያስገቡ አካላት ከድርጊታቸው ዛሬ ነገ ሳይሉ ሊታቀቡ ይገባል፤›› ብሎ ሰዎችን መቅጣትና ማገድ በጣም ቀላሉ ነገር እንደሆነና አሁን ባለው ሁኔታ ግን ፌዴሬሽኑ ‹‹ቀላል መስሎ ከባዱን›› ነገር ዕውን ለማድረግ የሚገደድበት ደረጃ ላይ መድረሱን ጭምር በግልጽ አስረድቷል፡፡

የችግሩ መነሻ

እያንዳንዱ የአትሌት ማናጀር፣ አሠልጣኞችና አትሌቶች እንዲሁም ሕገወጥ ደላሎች እነማንና ምን እንደሆኑ ‹‹እንተዋወቃለን›› በማለት የችግሩ መነሻ ‹‹አወቅኩሽ ናቅኩሽ›› ካልሆነ ሌላ ምንም ሊሆን እንደማይችል ኃይሌ ተናግሯል፡፡ ይኽም በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ከአትሌት ማናጀሮች ጋር በመግባባት አብሮ ለመሥራት ፍላጎቱና ተነሳሽነቱ ቢኖረውም፣ በተፈጻሚነቱ ላይ ግን ጥርጣሬ እንዲያድርበት ምክንያት መሆኑንም ሳይናገር አላለፈም፡፡

ለዚህ ሁሉ ዋናውና ትልቁ መንስኤ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሚያወጣቸው ደንቦችና መመርያዎች ተፈጻሚ ባለመሆናቸው አትሌቱን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ አካላት የ‹‹ዲሲፕሊንን› ትርጉም ችላ እንዲሉት ማድረጉንና ከእንግዲህም አትሌቱም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የቱንም ያህል ብቃቱም ሆነ ችሎታው ቢኖራቸው ዲሲፕሊን ከሌላቸው ተቋሙ ተሸክሞ የሚሄድበት አግባብ እንደሌለም ተናግሯል፡፡

‹‹አንዳንድ ሰዎች ይህ የፌዴሬሽኑ ውሳኔ ከግትርነትና አምባገነንነት የመነጨ አድርገው የሚመለከቱት እንደሚኖሩ ይገባኛል፤›› በማለት ማብራሪያውን የቀጠለው ኃይሌ፣ ከሦስትና አራት ዓመታት ላላነሰ ጊዜ አሜሪካንን ጨምሮ በሌሎችም አገሮች በኢትዮጵያ ስም የሚሮጡ እንዳሉ፣ ነገር ግን ስለነዚያ አትሌቶች ኢትዮጵያም ሆነች ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ምንም የሚያውቁት ነገር ሳይኖር ‹‹አበበ›› ወይም ‹‹አየለ›› የተባለ ኢትዮጵያዊ በአበረታች ንጥረ ነገር ‹‹ተጠርጥሯል›› በሚል አገሪቱ ለዕገዳና መሰል ችግሮች የምትዳረግበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ነው ያስረዳው፡፡

እስካሁን በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) የመረጃ ቋት ውስጥ የሚታወቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች 62 ብቻ መሆናቸውን የገለጸው ኃይሌ፣ በኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ ግን በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ አትሌቶች ቢገኙም፣ የተሟላ መረጃ እንደሌለ ጠቁሟል፡፡ ለዚህ ከፍተት በአገሪቱ የሚገኙ አትሌቶች መሮጣቸውን ካልሆነ እነማን በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ መቆጣጠሪያ ሥርዓቱ በተደራጀ አግባብ አለመዘጋጀቱ እንደሆነም አስረድቷል፡፡

አይኤኤኤፍ በዚህ በተበታተነ አግባብ ያለውን የአትሌቶችን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አትሌቲክሱን እያጠቃ ለሚገኘው አበረታች ንጥረ ነገሮች ኢትዮጵያ የችግሩ ተጠቂ ከሆኑ አገሮች ተጠቃሽ እንድትሆን መነሻ እንደሆነውም አስረድቷል፡፡

ሕገወጥ ደላሎችና አትሌቲክሱ

ለወትሮው ኢትዮጵያውያን አትሌቶችና አትሌቲክስ የባንዲራና የክብር ጉዳይ ካልሆነ በአትሌቶችና ማናጀሮች እንዲሁም ከፌዴሬሽኑና ከሌሎችም አካላት ጋር እንዲህ እንደ አሁኑ ሥር የሰደደ አለመግባባት አይስተዋልም ነበር፡፡ ይሁንና ስፖርቱ በጊዜ ሒደት እያበረከተ ባለው ልዩ ልዩ ፋይዳው እየጎለበተ መምጣቱ ነገሮች በነበሩበት እንዳይቀጥሉ ምክንያት ስለመሆኑም የሚናገሩ አሉ፡፡ የእነዚህ ነገሮች ድምር ውጤት በተለይም በማደግ ላይ ለሚገኙ እንደ ኢትዮጵያ ለመሰሉ አገሮችና አትሌቶች አሁን ለሚገኙበት ውስብስብ ችግር ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት መሆኑን በውይይት መድረኩ ጉልህ መከራከሪያ ሆኖ ቀርቧል፡፡

የአትሌት ማናጀሮች፣ በፌዴሬሽኑ ዕውቅና ያላቸውም ሆኑ የሌላቸው ከአትሌቶቻቸው ጋር የሚያደርጓቸው ስምምነቶች በአብዛኛው በሕግ ፊት ትርጉም የሌላቸው እየሆኑ አትሌቶችን ለከፋ እንግልትና ጉዳት እየዳረጉ መሆኑ በውይይቱ ተደምጧል፡፡ ሕገወጥ ደላሎችና መሰሎቻቸው ደግሞ ክፍተቱን በመጠቀም በተለይም አዳዲስና ወጣት አትሌቶችን በማይጨበጥ ‹‹ረብጣ ዶላር›› እያማለሉ ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲዳረጉ እየሆነ እንደሚገኝም ተነግሯል፡፡ የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ አመራሮችና የሥራ ኃላፊዎች ከተቋሙ የዕለት ተዕለት ሥራ ይልቅ በአትሌቶችና በማናጀሮች መካከል የሚፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ጊዜያቸውን እያጠፉ ስለመሆኑም ኃይሌ ተናግሯል፡፡ በተለይም ከሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር ተያይዞ ቻይና ዋነኛ መዳረሻ ስለመሆኗ ጭምር ተናግሯል፡፡

እንደ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚደንት ከሆነ በአትሌቶችና በማናጀሮች መካከል የሚደረጉ ውሎች በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ሆነ በአይኤኤኤፍ የሚታወቁ ናቸው፡፡ በሁለቱ አካላት መካከል ውል በሚፈጸምበት ወቅት እንዴትና በምን ዓይነት አግባብ እንደሚከወን ግልጽና የማያሻማ መስፈርት ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን ትልቁ ችግር አትሌቶች ከማንኛውም ማናጀር ጋር ውል በሚዋዋሉበት ጊዜ የውሉን ዓይነትና ዝርዝሩን በውል ሳይረዱ ውድድሮችን ከተሳተፉ በኋላ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ሲጠይቁ ያልጠበቁት መልስና ገንዘብ ሲሰጣቸው ነው የሚረዱት፡፡ ጉዳዩን በሕግ አግባብ ለመፍታት በሚታሰብበት ጊዜ ደግሞ አትሌቱ በቃል የሚነገረውና ውሉ ላይ የተቀመጠው ለየቅል መሆኑ ለፍትሕ አሰጣጡ አስቸጋሪ እየሆነ ስለመምጣቱም በውይይቱ ተነስቷል፡፡

በፌዴሬሽኑ በኩል ያለውን የመፍትሔ አቅጣጫ በተመለከተ ውሎች በማስረጃ የተደገፉ ሆነው እንዲቀርቡ የፌዴሬሽኑ ፍላጎት ቢሆንም እስከዛሬ የነበረው ከዚህ በተቃራኒ በመሆኑ በተለይ አትሌቱ እንዲጎዳ ማድረጉን ኃይሌ ተናግሯል፡፡ ከእንግዲህ ግን የነበረው ይቀጥላል ማለት እንዳልሆነ ያከለው ኃይሌ፣ በማናጀሮችና በአትሌቶች መካከል የሚደረጉ ውሎች በተቻለ መጠን አትሌቶች በሚረዱት ቋንቋ በአማርኛም ጭምር እንዲሆን ይሞከራል፡፡ ለዚህ ተፈጻሚነት ዋናው ሚና መጫወት የሚኖርባቸው ደግሞ አትሌቶች መሆናቸውንም አስረድቷል፡፡ ምክንያቱም ውል ከመዋዋላቸው አስቀድሞ ፌዴሬሽኑ ጉዳዩን እንዲያውቀው ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውና ፌዴሬሽኑም ራሱን የቻለ ደንብና መመርያ የሚያዘጋጅ መሆኑንም ተናግሯል፡፡

ኢትዮጵያ አበረታች ንጥረ ነገሮች ከተጠረጠሩ አምስት አገሮች አንዷ ልትሆን እንዴት ቻለች?

      ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በየትኛውም ክፍለ ዓለም የሚገኙ አትሌቶች በተለይም አይኤኤኤፍ በሚያውቃቸው ውድድሮች የሚሳተፉ አትሌቶች በየሦስት ወሩ የትና በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የሚያስረዳ ፎርም እንዲሞሉ የሚደረግበት አሠራር መኖሩ ይታወቃል፡፡ አትሌቱ በአስገዳጅ ችግር ምክንያት የአድራሻና የመኖሪያ ቦታ ቢቀይር እንኳ ለአይኤኤኤም ሆነ ለዋዳ የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት፣ ካልሆነ ግን በተሞላው ፎርም መሠረት ሁልጊዜ ዝግጁ ሆኖ መገኘት የግድ እንደሚል ያስገድዳል፡፡

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ ባለሙያ ወ/ት ቅድስት ታደሰ ገለጻ ከሆነ፣ አትሌቶቻችን ለሚሞሉት ፎርም ተገቢውን ክትትል አያደርጉም፡፡ ብዙዎቹ በየሦስት ወሩ የሚሞላውን የአትሌቶችን መገኛ አድራሻ ሲሞሉ ያለውን ጥቅምና ጉዳት በውል አውቀውት እንዳልሆነ ጭምር ተናግረዋል፡፡ የባለሙያዋን አስተያየት በማጠናከር በጉዳዩ ማብራሪያ እንደሰጠው ኃይሌ አገላለጽ፣ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች እስካሁን  ድረስ ትልቅ ችግር ሆኖ የሚገኘው የዚህ ፎርም አሞላል ነው፡፡

በፎርሙ መሠረት እያንዳንዱ አትሌት ቀንና ሰዓቱን አክብሮ በቦታው መገኘት ይጠበቅበታል፡፡ በቅርቡም 22 አትሌቶች ቀኑ ‹‹ማክሰኞ›› ወይም ‹‹ዓርብ›› ሊሆን ይችላል፣ በሞሉት ፎርም መሠረት የደምና የሽንት ናሙናቸውን ለመውሰድ ዓለም አቀፍ ኤጀንቶች አዲስ አበባ ስታዲየም በድንገት ቢመጡም፣ በወቅቱ ቦታው ላይ ልምምዱን ሲያደርግ የተገኘው አንድ አትሌት ብቻ ነበር፡፡  በቦታው 21ዱ አትሌቶች በአዲስ አበባ ስታዲየም ዝግጅት እንደሚኖራቸው ፎርሙ ላይ በሞሉት መሠረት ግን አልተገኙም ሆኖም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ለእያንዳንዳቸው ስልክ ተደውሎ ከፊሉ ጃንሜዳ ከፊሉ ደግሞ እንጦጦ መሆናቸውን መግለጻቸውን ኃይሌ በማሳያነት አመልክቷል፡፡ ለዚህ ጉዳይ የሚመጡት ኤጀንቶች አትሌቶች በሞሉት ፎርም መሠረት የማይገኙ ከሆነ በሪፖርታቸው የሚያካትቱት ‹‹አልተገኙም›› ብለው መሆኑንና ይህ ደግሞ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማኅበርና ዋዳ የበለጠ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገቡ እንደሚያደርጋቸውም ተናግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...