Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርእንናገራለን የሚሰማን የለም

እንናገራለን የሚሰማን የለም

ቀን:

በውብሸት ተክሌ

ይህን አስተያየት ለመጻፍ ስዘጋጅ ሐሳብን በነፃ የመግለጽ ዴሞክራሲያዊ መብት ሞልቶ ሊፈስ የደረሰ በመሆኑ ሳይሆን ሰው ሆኜ በመፈጠሬ በተቀዳጀሁት ሰብዓዊ መብት በመጠቀም መሆኑ ይታወቅልኝ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በየጊዜው በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሊቪዥን የሚሰጡትን መግለጫ ሳዳምጥ መንፈሴ በቅሬታ ይሞላል፡፡ ንግግራቸው በነፃ ሚዲያው ሲብጠለጠል እየሰሙ በሠለጠነ መንገድ ማስተባበያ ከመስጠት ይልቅ ውግዘት ያስቀድማሉ፡፡ አባባሌን እውነት የሚያደርገው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ማኅበራዊ ሚዲያው ጥቅም እንዳልሰጠ ለማሳመን መሞከራቸው የሚሰማ ጆሮ ማጣቱ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሚወክሏት አገር ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በአውሮፓ ኅብረት፣ በዓለም የምጣኔ ሀብት ሸንጎ፣ በአፍሪካ ኅብረትና በኢትዮጵያ ፓርላማ ጭምር እየተገኙ ንግግር ያደርጋሉ፡፡ የሚያነሷቸው ነጥቦች አገሪቷ የገጠማትን ችግሮች የሚፈቱ ከመሆን ይልቅ ባሉበት ቀጥለዋል፡፡ እስቲ ጥቂቶቹን ላብራራ፡፡

በምግብ ራስን አለመቻል

እያንዳንዱ የከተማ ነዋሪ በመቶ ሺሕ የሚገመቱ ዜጎች በየድልድዩ ሥር ካርቶን አንጥፈው ድሪቶ ደርበው፣ እንደ ጦር በሚወጋ ቅዝቃዜ የተቆራመዱ ዱር ቤቴዎች በየጊዜው ሲመለከት ሐዘኑ የከፋ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡ በግምትም ቢሆን የተጠቀሰው አኃዝ ገና ለዓይን ያዝ ሲል ጀምሮ ምግብ ፍለጋ በየቆሻሻ ገንዳው የሚንጦለጦለውን ምስኪን አያካትትም፡፡ በመሠረቱ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የቻለችበት ጊዜ አይታወቅም፡፡ በምኒልክ ዘመነ መንግሥት በ1881 ዓ.ም. ተከስቶ የነበረው አስከፊና ዘግናኝ ድርቅ ባስከተለው ረሃብ አንሳሮ ውስጥ አንዲት ሴት ሰባት ሕፃናትን፣ አንዲት እናትም የገዛ ልጇን መብላታቸውን ጳውሎስ ኞኞ ‹‹አጤ ምኒልክ›› በሚባለው መጽሐፉ ገልጦታል፡፡ ከዚያም ወዲህ በኢያሱም ሆነ በዘውዲቱ፣ በንጉሡም ሆነ በደርግ ረሃብ ተለይቶን አያውቅም፡፡ ዛሬም በኢሕአዴግ መንግሥት በደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል ብቻ 8.5 ሚሊዮን ሕዝብ በረሃብ እየተጠበሰ የለጋሽ አገሮችን ዕርዳታ ይጠብቃል፡፡ ከ1881 እስከ 2010 ዓ.ም. ባሉት 129 ዓመታት እኛና ረሃብ ሳንወድ በግድ አንድም ሁለትም ሆነን ለመኖር ተገደናል፡፡

የብሔራዊ ሚትዮሮሎጂን የአንድ ወቅት ትንበያ እንደ መነሻ በመቁጠር ድርቅ በየአሥር ዓመቱ ይከሰታል፡፡ ይህ ማለት 13 ጊዜ በመመለስ ደቁሶናል፣ ወደፊትም የሚሆነውን አናውቅም፡፡ የሚያስገርመው ነገር በሚፈሱ ወንዞች ባለፀጋ ሆነን በመስኖ እርሻ ላይ ከማተኮር ይልቅ ውኃ በማቆር የእንቁራሪት መፈልፈያ ማድረጋችን ነው፡፡ አንድ ጥያቄ ለማንሳት ይፈቀድልኝ፡፡ ለመሆኑ በምግብ ራሳችንን ከቻልን ወጣቱ ለምን ይሰደዳል? ባህር ውስጥ እየሰመጠ፣ በኮንቴይነር ውስጥ እየታፈነ ለምን ይሞታል? ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንደ ነገሩን የአገር ጉዳይ የሚወስኑት በሌላቸው መረጃ ሰዎች በሚያቀብሏቸው ወሬ ከሆነ፣ እውነታም የማይፈታ ችግር ውስጥ መውደቃችንን እንረዳለን፡፡ በነገራችን ላይ ክብርት ቀዳማዊ እመቤት ሮማን ተስፋዬ፣ ቁርስና ምሳ ማግኘት ባለመቻላቸው በየትምህርት ቤቱ የሚወድቁ ታዳጊዎችን በመመገብ ያሳዩት ሰብዓዊነት የተላበሰ ድርጊታቸው የላቀ ዕውቅናና ከበሬታ ሊቸራቸው ይገባል፡፡

ወርቅ በሰፌድ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በትግራይና በደቡብ ክልሎች የወርቅ ክምችት መኖሩን ካብራሩ በኋላ ማዕድናቱ በሚገኙበት አካባቢ ቁፋሮ በማካሄድ ወርቅ በሰፌድ በማበጠር መለየት እንደሚቻል ነግረውናል፡፡ ይሁን እንጂ በቁፋሮው ለመሳተፍ የዜጎች መነሳሳት አለመኖር ሳይሆን ከተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ሚኒስቴር ፈቃድ ማግኘትና የመገልገያ መሣሪያዎችን የማሟላት አቅም ይጠይቃል፡፡ የቢሮክራሲው ውጣ ውረድ እንዳለ ሆኖ አንዲት ግራም ወርቅ ለማውጣት ከሚወስደው ጊዜና ከሚባክነው የሰው ጉልበት አንፃር አዋጭ ባለመሆኑ ከችግር አያላቅቅም፡፡ ቢሞከር እንኳን ሌሎች ምክንያቶችን ታሳቢ ማድረግ ይጠይቃል፡፡

ሁሉም ዜጋ በጎሳ ስልቻ ተከፋፍሎ እኛና እነሱ በሚባልበት በዚህ ወቅት፣ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላኛው ክልል ተዘዋውሮ ወርቅ ማውጣት የሚሞከር አይሆንም፡፡ በየጊዜው እያየን ያሉት አሰቃቂ ግጭቶች የጫት ንግድና የጥቁር ገበያ የፈጠረው ያለመግባባት ሳይሆን፣ የብሔር ፖለቲካ የተከለብን ጠንቅ በመሆኑ ብዙ ማስረጃዎችን መደርደር ይቻላል፡፡ የበደኖው እልቂት፣ የጉራፈርዳ አማሮች ስደት የፀፀት ትዝታዎቻችን ሆነው ይኖራሉ፡፡ ግራ ተጋብተው ግራ የሚያጋቡን ብሔረተኛ ፖለቲከኞች ልዩነታችን ውበታችን ነው ቢሉንም፣ አይተነውና ሰምተነው የማናውቀው ብሔር ተኮር ግጭቶች በተስፋፋበት አገር ቀዬውን ትቶ ወርቅ ፍለጋ የሚዘምት ዜጋ ይኖራል ብሎ ማሰብ የሚቻል አይመስለኝም፡፡

ስለሙስና

በአንድ ወቅት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‹‹የመንግሥት ሌቦች እጃችንን አስረው አላሠራ ብለውናል፡፡ አንዳንዶቹ በውሾቻቸው ስም አካውንት ከፍተዋል፤›› በሚል ንግግራቸው ስንገረም፣ ከጊዜ በኋላ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ማስረጃ የለንም ማለታቸውን ተከትሎ ተሸብሮ የነበረው የሙሰኞች ሠራዊት በተረጋጋ መንፈስ ወደ ምሽጉ ተመልሷል፡፡ የሁለቱን ጠቅላይ ሚኒስትሮች የሐሳብ ተቃርኖ ታሳቢ በማድረግ ሙስና የቱን ያህል ሥር እንደ ሰደደ ዋናው ኦዲተር (አቶ ገመቹ) በፓርላማው ፊት ቀርበው ያሰሙትን ሪፖርት ማንሳት እንችላለን፡፡ በተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና አገር ተረካቢ ወጣቶችን በማፍራት አገራዊ ግዴታቸውን ይወጣሉ በተባሉ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ከ5.2 ቢሊዮን ብር በላይ መዘረፉን ይፋ አድርገዋል፡፡

አንዳንድ የፓርላማ አባላት በቁጭት ተነሳስተው ክቡር አፈ ጉባዔ በሪፖርቱ መሠረት ዕርምጃ ባይወሰድ የመረጠን ሕዝብ ይታዘበናል ሲሉ ቢደመጡም፣ ከተለመደው ጫጫታ ያለፈ ነገር አላመጡም፡፡ ኦዲተሩ የምዝበራውን ሒደት ግልጽ በሆነና ሙያዊ ብቃት በታየበት መንገድ በማቅረባቸው ያለኝ አድናቆት እንዳለ ሆኖ ነገር ግን ሰሚ በማጣት ተስፋ እንዳይቆርጡ እሠጋለሁ፡፡ ሁሉም ዜጋ ለሙያው ይቆም ዘንድ ምሳሌ ሆነውናል፡፡ የተመዘበረው ገንዘብ ለጤና አገልግሎት፣ ለትምህርት ተደራሽነትና ለቤቶች ግንባታ ቢውል ኖሮ ታክስ ከፋዩን ኅብረተሰብ ተጠቃሚ ያደርገው እንደነበር ለሚያስብ ሰው ያስቆጫል፡፡ ይሁን እንጂ በእኛ ፍላጎት የሚሆን ነገር የለም በሚል ቸልተኝነት ዝምታን አንመርጥም፡፡

ሁለተኛው የሙስና ድራማ የተደራጁ ቡድኖች በጋምቤላ ክልል በሚገኙ ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች እንዲያለሙ ለማበረታታት በሚመስል መልኩ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያለ በቂ የዕዳ ዋስትና (Collateral) የተበደሩትን በሚሊዮን የሚቆጠር የሕዝብ ገንዘብ ሳይመልሱ ከፊሎቹ ከአገር ሲወጡ፣ ከፊሎቹ ደግሞ በእርሻው አካባቢ ድርሽ ሳይሉና አካፋና ዶማ እንኳን ሳያስቀምጡ በዋና ዋና ከተሞች ፎቅ ገንብተውበታል፡፡ እጅግ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤትና የመኪና ግዥ ፈጽመውበታል፡፡ ጥቂቶች አሮጌ ትራክተሮች ሲንቀሳቀሱ በካሜራ እንዲቀረፁ ካደረጉ በኋላ ዘወትር እንጨት እንጨት በሚል ዘገባው የምናውቀው ኢቢሲ ዘግቦታል፡፡ ቀደም ሲል የባንኩ ፕሬዚዳንት የነበሩት ግለሰብ ከኃላፊነታቸው የተነሱት በሹመት ወይም በዝውውር እንዳልሆነ መረጃው በደረሰን ጥቂት ወራት ውስጥ በሕጋዊ መንገድ ከአገር መውጣታቸው አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

የጉዳዩ ስፋትና ጥልቀት ትኩረት የሳበ ቢሆንም ‹‹መርፌ ከለገመ ቅቤ አይወጋም›› እንዲሉ፣ በመንግሥት በኩል ሙስናን የሚያፀዳ ዕርምጃ ሲወሰድ አልሰማንም፡፡ ከ97 ምርጫ ማግሥት በአዲስ አበባ ያሉ ባዶ ቦታዎች በዝርዝር እንዲታወቁ ከተደረገ በኋላ አግባብ ባልሆነ መንገድ ለእነ ማን እንደተቸበቸቡ የምናውቅ የከተማው ነዋሪዎች ትዝታው ሳይወጣልን፣ አሁን ደግሞ ከላይ የገለጽኳቸው ከሙስና ያለፈ ዘረፋ የተፈጸመባቸው የሕዝብ ንብረቶች የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከተጠያቂነት አይድኑም፡፡ አልሚ ተብዬዎቹ ዛሬም ቢሆን ብድር ካልተሰጠን በሚል ከተራ ስድብ እስከ ማስፈራራት መድረሳቸውን እናውቃለን፡፡

ስለ ሁለት አኃዝ ዕድገት

የሕዝቡን የነፍስ ወከፍ ገቢ ታሳቢ ያላደረገ ዕድገት በዓለም ላይ ስለመኖሩ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በሕክምና ዕጦት በየሆስፒታሉ ኮሪደር እየተኛ ተራ የሚጠብቅ ዜጋ፣ በትራንስፖርት ችግር ሠልፍ የለመደ ሕዝብ፣ የመብራት ተጠቃሚ መሆን ባልተቻለበት አገር ዕድገትን በምኞት ከማሰብ በስተቀር ያየነው ነገር የለም፡፡ የዓለም የገንዘብ ተቋማት እንደሚገልጹት ከሆነ አገሪቷ 26 ቢሊዮን ዶላር ብድር እንዳለበት እየታወቀ የባቡር መስመር መዘርጋት፣ የመንገድ ግንባታ ማስፋፋትና የሕንፃዎች ብዛት ዕድገት አመላካች ቢመስሉም ብድሩ ተከፍሎ እስኪያልቅ ድረስ ባቡሩ አገልግሎቱን ይጨርሳል፣ መንገዶችም ውኃ ማቆር ይጀምራሉ፡፡ መጪው ትውልድ ራሱን ከመቻልና አገርን ከማገልገል ይልቅ ብድር ከፋይ ሆኖ ሕይወቱን ይገፋል፡፡ ብድር በኢኮኖሚስቶች ጥልቅ ጥናት ታግዞ ለረዥም ጊዜ ከሚሰጠው ጥቅም አኳያ ካልታየ በስተቀር፣ የሚያስከትለውን ቀውስ ከአውሮፓዊቷ አገር ግሪክ ተሞክሮ መውሰድ ብልህነት ይመስለኛል፡፡

ጥልቅ ተሃድሶ

የትምህርት ደረጃ፣ የሥራ ልምድና ብቃት እንደ መሥፈርት ሳይቆጠር በየመሥሪያ ቤቱ ጥቅማ ጥቅም (መኪናና ወፍራም ደመወዝ) የሚያስገኙ ቦታዎች በካድሬዎች መሞላት፣ ሕዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች በቂ ምላሽ መስጠት አልተቻለም፡፡ ጥልቅ ተሃድሶው የመልካም አስተዳደር ችግሩን ይፈታል በሚል ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ የብዙዎችን ጥቅም የሚያሳጣ ሆኖ በመገኘቱ ተኮላሽቶ ቀርቷል፡፡ ወደፊት ሕዝቡ ብልሹ አሠራሮችን ሳይፈራና ሳይሸማቀቅ እንዲናገር ዋስትና የሚሰጥ መድረክ ተዘጋጅቶ በሚገኘው ግብዓት መሠረት ዕርምጃ መውሰድ ካልተቻለ በስተቀር፣ ችግሮቹ ሞልተው መፍሰሳቸው አይቀርም፡፡ እርሳስና እስክርቢቶ ላልገዙላቸው አገሮች የሚያገለግሉ ምሁራን አመለካከታቸው ሳይነካ የሚመለሱበት ሁኔታ ቢመቻች፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል መታመን ይኖርበታል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...