Friday, December 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገርጨለማው አይነጋም ብንል እንኳ ዓይን ያስፈልገናል

  ጨለማው አይነጋም ብንል እንኳ ዓይን ያስፈልገናል

  ቀን:

  በሳሙኤል ረጋሳ

  የሰው ልጆች ሁልጊዜ ለመኖር ካለን ጉጉት የተነሳ የዛሬ እንቅስቃሴያችን ሁሉ ለነገ ያበቃናል በሚል ታሳቢ የሚተገበር ነው፡፡ መሥራት፣ መመገብና ማሰብን የመሳሰሉት የዘወትር እንቅስቃሴዎች ሁሉ ለዕለት ውሎ ብቻ ሳይሆን ከበስተጀርባው ያለው ሚስጥር ለነገ መብቃት ነው፡፡ ነገ ደግሞ ሌላ ተስፋ ይዞ ይመጣል፡፡ ዛሬን ለነገ የማመቻቸት ጉዳይ በጽሑፍ ታቅዶና ተመክሮበት ብቻ ሳይሆን፣ የግለሰቦች ዕለታዊ የደመነፍስ ተግባርም ነው፡፡ ራስን ዛሬን አውሎ ለነገ ማብቃት ቀላል ጉዳይ ነው፡፡ ቀበሌያችንን ሲገፋም ወረዳችንን በሰላም ለነገ ማብቃት ግን የደመነፍስ ጉዳይ ሳይሆን፣ ወሰብሰብ ያለ በመሆኑ የብዙ ሰዎች የጋራ ጉዳይ ነው፡፡ በአገር ደረጃ ስንወስደው ግን ለነገ ለመብቃት በውጭም በውስጥም መሥራት የሚያፈልጉ በርካታ ጉዳዮች ስላሉ፣ ለእነዚህ ሥራዎች ኃላፊነት የሚወስድ የበቃ መንግሥትና የበቃ ማኅበረሰብ ያስፈልጋል፡፡

  በተለይ አገርን በተመለከተ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለቀሪው ዓለም ምሳሌ የሚሆኑበትና በታሪክ ሒደት ውስጥ ጎልተው የወጡባቸው ጉዳዮች በርካታ ናቸው፡፡ እነሱ በነበሩበት ዘመን አገራቸውን በክብር ሊኖሩባት፣ ነገ ደግሞ ልጆቻቸው ከእነሱ ተረክበው የሚያኖሯት የታፈረችና የተከበረች አገር እንዲኖራቸው ያደረጉት መስዋዕትነት ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ለዛሬ መጠቀሚያና መኖሪያ ብቻ ሳይሆን ለዘለዓለም እንድትሆን ታስቦ ነው መሠረቷ  የተጣለው፡፡ ከኢሉአባቦር ጫፍ ተነስቶ ስንቁን በትከሻው ተሸክሞ ያለበቂ መሣሪያ፣ ረሃብና ጥም ሳያግደው ባለዘመናዊ መሣሪያ ጠላትን ገሎ ለመሞት ዓደዋ ድረስ በእግሩ ተገዞ አገርን በነፃነት ለማቆየት መሥዋዕትነት የከፈለ ከኢትዮጵያውያን በስተቀር ሌላው ዓለም ላይ ስለመኖሩ መናገር  አይቻልም፡፡ 2,000 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀትን በባዶ እግር ያለስንቅ ጉዞ መጀመሩ እንኳን ለጦርነት ለሽልማትም ቢሆን በአሁኑ ጊዜ የሚታሰብ አይደለም፡፡ የሄዱበትን ጦርነት ተዋግተው ግዳጃቸውን ሲያበቁ በለስ ከቀናቸው በተመሳሳይ የአደጋ ጉዞ የመመለስ ተስፋም ከአድማስ ወዲያ ማዶ እንደሚጠብቃቸው ያውቃሉ፡፡ የዚህ ዓይነት ጉዞና መስዋዕትነት ለመከራ ሳይሆን በሰላም ጊዜ መልዕክት አድርሶ ለመመለስ እንኳ የሚታሰብ አይደለም፡፡ አባቶቻችን ግን ማድረግ የማይቻለውን ነገር አድርገውታል፡፡ የማይሞከረውን ሞክረው ተሳክቶላቸዋል፡፡ ሌሎች ያልሞከሩትን እነሱ ሞክረው ነው ኢትዮጵያ የቆመችው፡፡

  የሚገርመው ነገር ኢትጵያውያን በዚህ ዓይነት መስዋዕትነት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተው ከአደጋ የተከላከሉዋትና ለዚህ ያበቋት አገር፣ ለእነዚህ ጀግኖች የከፈለችው ውለታ የለም፡፡ ከውጭ ወራሪዎች ግን አድነዋታል፡፡ ልጆቻቸው በአባቶቻችን ደምና አጥንት የቆየች ነፃ አገር አለኝ፣ የቅኝ ገዥ ቀንበር አለተጫነብኝም፣ አይጫንብኝምም እያለ አንገቱን ቀና አድርጎ በዓለም ፊት በኩራት የሚራመድ ትውልድ ፈጥረዋል፡፡ ይኼ ታሪክ የተወሰነ የኢትዮጵያ ክፍል ታሪክ አይደለም:: ሁሉም ኢትዮጵያውያን በጋራ ስለሠሩት ብቻ ነው ሊሳካና ሊደምቅ የቻለው፡፡

  በአገሪቷ ላይ በየጊዜው የተፈራረቁት ገዥ መደቦች ይኼንን ጀግና፣ አስተዋይና ኩሩ ሕዝብ አስከፍተውታል፡፡ አስረውታል፣ ገርፈውታል፣ ገለውታል፡፡ ሕዝቡም የአገር ማዳን ግዴታውን እየተወጣ ወቅቱና የጊዜው ሁኔታ በሚፈቅደው ልክም እየታገላቸው ይኼው ለዚህ በቅተናል፡፡ በግልጽም ይሁን በአሻጥር አገሩን አሳልፎ የሰጠበት ወቅት አልነበረም፡፡

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዱ የኅብረተሰብ ክፍል ለሚያልፍ ነገር በሌላው ላይ እያቄመ በሚወስደው ዕርምጃ፣ የመሰነጣጠቅ አደጋን ሊፈጥር የሚችል አደገኛ ሁኔታ በመፍጠር ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው መሠረት ጠንካራ በመሆኑና እንደተባለው የሠርገኛ ጤፍ በመሆናችን በቀላሉ አልፈረስንም፡፡ ነገር ግን አደጋዎች እየመጡ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ሳይሆን እርግጠኛ ለመሆን የሚቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ በእርግጥ የመጨቆን፣ የመገፋትና የመበዝበዝ የመጨረሻ ጫፍ የሚያስከትለው ብሶት ወደ ተስፋ መቀረጥ ያመራል፡፡ ተስፋ መቁረጥ ደግሞ በሰዎች ተፈጥሮ ውስጥ የመጨረሻውን አደጋ ያስከትላል፡፡ አጥፍቶ ጠፊዎች አዕምሮአቸው የሚቃኘውና በዚህ ዓለም ላይ ለመኖር የቀራቸው ምንም ነገር እንደሌለ ተደርጎ ነው በሌሎች የሚሠራው፡፡ ተስፋቸው ባዶ እንዲሆን፡፡

  መገንጠል፣ መሰደድ፣ ራስን ማጥፋት አደገኛ ዕርምጃዎችና ውሳኔዎች በአብዛኛው የተስፋ መቁረጥ ውጤቶች ናቸው፡፡ ወደፊትም ቢሆን ዓለም የምትጠፋ ከሆነ የምትጠፋው ተስፋ በቆረጡ ሰዎችና አገር ነው፡፡ ይኼ ትውልድ አሁን ባለበት ሁኔታ የመበታተን፣ የመፈራራት፣ እርስ በርስ የመጠራጠርና ያለመተማመን በውስጡ እንደ ተፈጠረ በገሀድ ይታያል፡፡ አንዱ በሌላው ላይ ተስፋ ካጣና የጋራ የሆነ ነገር የለኝም ብሎ ካመነ፣ ሊከተል የሚችለው አደጋ እጅግ የከፋ ነው የሚሆነው፡፡ ነገር ግን አዕምሮአችን ሁልጊዜ ከጥላቻ ይልቅ በጎ ነገርን እንዲያመጣም እናስገድደው፡፡ ከላይ የጠቅሰናቸው አያቶቻችን ስንት መከራ አልፈው ለዚህ እንዳደረሱን እናስብ፡፡ የዛሬ ሁኔታዎች ምንም ከባድ መስለው ቢታዩንና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳ ብንሆን ተስፋ አንቁረጥ፡፡ የደብረ ሲናን ዋሻ ደፍረን የምንገባበት በሌላው ጫፍ በኩል መውጫ መኖሩን የሚያሳይ የብርሃን ጭላንጭል ስለሚታየን ነው፡፡ እያንዳንዱ የጨለማ ሌሊት ሲመጣ የብርሃን ጨረር ከኋላው ተከትሎ እንደሚመጣ አንርሳ፡፡

  በተረት ዓለም ውስጥ ስለተፈጠሩ ሰዎች ወሬ ልንገራችሁ፡፡ ተረት ነው፡፡ ቀኑ አልፎ ጨለማ በሆነ ጊዜ በዓለም ላይ የተፈጠሩ አዲስ ሰዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሰዎች የተፈጠሩትና ራሳቸውን ያገኙት በጨለማ ጊዜ ስለሆነ፣ ስለራሳቸው ለማወቅ የሰውነት ክፍላቸውን በመዳሰስ የእያንዳንዱን ክፍል ጥቅም ለማወቅ ሞከሩ፡፡ እጃቸውን ይይዙበታል፡፡ እግራቸውን ይራመዱበታል፡፡ ጆሮዎቻቸውን ይሰሙበታል፡፡ አፋቸውን ይናገሩበታል . . .፡፡ በዚህ ዓይነት በዳበሳው ሒደት የሁሉንም አካሎቻቸውን ክፍሎች ጠቀሜታ አወቁት፡፡

  ነገር ግን በወቅቱ ምንም ጥቅም የሌለ እንደ ልብ ለመዳበስና ለመነካካት እንኳ ምቹ ሆኖ አስፈላጊ ያልሆነ ትርፍ ነገር አውጥተን እንጣለው የሚል ሐሳብ ተነሳና ብዙዎች ሲደግፉት፣ በጣም ጥቂት ሰዎች ምናልባት አንድ ቀን ያስፈልገን ይሆናል ብለው በተቃውሞ ክርክራቸውን ገፋበት፡፡ የክርክሩ ሒደት ረዥም ጊዜ እየወሰደ በመሄዱ ጨለማው እየለቀቀ ብርሃን እየተተካ መጣ፡፡ ብርሃን ሲመጣ ደግሞ የመጀመሪያው አስፈላጊ ነገር ማን እንደሆነ ታወቀ፡፡

  እንግዲህ እነዚህ ሰዎች የብርሃንን መተካት ሳያውቁ ዓይናቸውን አውጥተው ጥለው ቢሆን ኖሮ፣ በብርሃነ ዘመን ምን መፅናኛ ይገኝላቸው ነበር? አሁን በምናውቀውና ባለ ሁኔታ ላይ ተመሥርተን የምንወስደው አቋም አደጋው የሚታየን ካለፈ በኋላ ነው፡፡ አንዴ ካመለጡን በሌላ ጊዜ መፅናኛ የማናገኝላቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች ውስጥ የአገር ጉዳይ አንዱና ዋናው ነው፡፡ ዛሬ ያልተመቸችኝ አገር፣ መብቴን ያሳጣችኝ አገር፣ የደኸየሁባት አገር የኔ አይደለችም ብሎ ከውስጣችን በሚንቀሳቀስ ስሜት የምንወስነው ውሳኔና የሚፈጠረው ችግር አገሪቱን አደጋ ላይ ከጣላት የብርሃን ዘመን ሲመጣ መፅናኛ እናጣለን፡፡

  ዛሬ ብሔር ብሔረሰቦች በተከለሉባት አገራችን የአስተዳደር ክልሎች በትምህርት፣  በባህል በአስተዳደራዊ ጉዳዮች . . . ወዘተ የራሳቸውን መብት አስከብረው በጋራ አገሪቱን ይጠብቋታል ተብሎ ይገመታል፡፡ ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ በክልሎች መካከል የሚፈጠሩ የፖለቲካ ሽኩቻዎች ከአንድነት ይልቅ ልዩነቱን የሚያጎሉ ክስተቶች ሆነዋል፡፡ በክልሎች መሀል ያለው ልዩነት እንዳለ ሆኖ መንግሥት መከወን ያቃተው፣ ለምሬት የሚዳርጉ፣ ኢኮኖሚውን በፅኑ የሚፈታተኑ ጉዳዮችም ተስተውለዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ የሞባይል ካርድ፣ ስኳርና ዘይት የመሳሰሉትን መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን በተገቢው መንገድ ማቅረብ አልተቻለም፡፡ መንግሥት በውጭ ምንዛሪ እጥረት ተሰንጎ በተያዘበት በዚህ ወቅት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮች በግለሰቦች በየጊዜው በድብቅ ወደ ውጭ ይኮበልላሉ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ ኮንትሮባንድ ነጋዴ ባለሥልጣናት መፈናፈኛ አሳጥተውት ሕዝቡንም አስመርረውታል፡፡ ከሁሉ በላይ የተወሰኑ አካላት አንዱ ብሔር በሌላው ላይ እንዲነሳና ሕዝቡ አደጋ ላይ እንዲወድቅ የመፈለጋቸው አደገኛ አዝማሚያ በጣም ያስፈራል፡፡ እነዚሁ ሁሉ ነጥቦች በመንግሥት የተነገሩ ናቸው፡፡

  አሁን አገራችን በጨለማ ውስጥ ናት፡፡ ብርሃን የማይመጣልን መስሎን በተረት ዓለም እንዳየናቸው ሰዎች ዓይናችንን አውጥተን ለመጣል አንሞክር፡፡ ብርሃንን በተስፋ እንጠብቅ፡፡ ሁለጊዜ ከጨለማ ጀርባ የብርሃን ጮራ እንዳለ እንወቅ፡፡ አሁን አገራችንን ለመታደግ በተለያየ ጎራ ቆመን ክርክር ጀምረናል፡፡ ክርክሩ በግድ ዛሬውን በአንዱ አሸናፊነትና በሌላው ተሸናፊነት የማያበቃ ሊሆን ይችላል፡፡ ክርክሩን በሚገባ የሚመራልንና ብቁ ተከራካሪዎች ያስፈልጉናል፡፡ ባለ ብሩህ ራዕይ መሪዎችን፣ መብቱንና ግዴታውን የሚያውቅ ሠራተኛ፣ ሕዝብና ሕዝብን ከዕልቂት ጎዳና የሚመልስ ጎበዝ አስተማሪ ዛሬ አገሪቱ ትፈልጋለች፡፡ ይኼ ከሆነ ያለ ጥርጥር የችኮላና የግብታዊ ስሜታዊነትን ተቆጣጥረን በምናደርገው ክርክርና በምናሳየው የመቻቻል ባህሪ፣ ጨለማውን አልፈን የብርሃን ዘመን ላይ የምንደርስበት የደስታ ጊዜ ይመጣል፡፡

  በየክልሎችንና በየብሔረሰቦቻችን ላይ የደረሰውን ጭቆና እያውጠነጥን፣ እውነተኛም ሆነ ምንም መረጃ የሌላቸው የቀድሞ ታሪኮቻችንን እያነበነብን፣ ለድህነታችንና ለኋላ ቀርነታችን ምክንያት መስለው የሚታዩትን ወይም የሆኑትን ለመበቀል እየፎከርን፣ አሁን ከእኛ ጋር ያሉትን ችግሮቻችን በድሮ ሚዛን እየመዘንን፣ የታወቀውን ነገር ሁሉ ካልተወቀ ነገር ጋር በማመዛዘን አቋራጭ መፍትሔ የምንፈልግ ከሆነ ምንጊዜም እውነትን ለማግኘት ወይም ችግራችንን ለመፍታት አንችልም፡፡ ጨለማው ያለመንጋቱን ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ የምናምን ከሆነ ዓይናችንን አውጥተን ለመጣል ወደ ኋላ አንልም፡፡ ያ ደግሞ የሁሉም ነገራችን መጨረሻ ነው፡፡ ከላይ ያየነው የአያቶቻችን መስዋዕትነት ሁሉ ውኃ በላው ማለት ነወ፡፡ ይህችን አገር በትዕግሥትና በመቻቻል የማዳኑን ጉዳይ የዛሬው ትውልድ ለደቂቃም ቢሆንም ሊዘነጋው አይገባም፡፡

  ከሰሞኑ የኦሮሚያና የአማራ ክልል የጀመሩት የፖለቲካ ሥራ አጀማመሩ ከጥርጣሬ ጋር ለኢትዮጵያ ህልውና ተስፋ የጫረባቸው በርካቶች ናቸው፡፡ ሁለቱም ክልሎችና ኢትዮጵያ ከሁለቱም በኩል በመጡ የአገር ሽማግሌዎች ተመርቀዋል፡፡ ሁሉም አገሩን በጋራ ከልብ ከመረቀ የተስፋ ዘመን ለመሰነቁ ምልክት ነው፡፡ ምሁራን ስለአንድነት ታሪካችን ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ መሪዎቻችንም በአንድነት አገሪቱን በቀድሞው መልክና በሰላም ለመቀጠል ያለውን ተስፋ አብራርተዋል፡፡ የኦሮሚያን ፎሌዎች ጣና ውስጥ አይተናቸውዋል፡፡ ዱሮም የጠፋው መሪ እንጂ አገሪቱና ሕዝቡማ እኛው የድሮዎቹ ነን፡፡

  ከሩቅ ሆነን ስናይ ይኼን የፖለቲካ ተነሳሽነት የወሰዱት አቶ ለማ መገርሳ ይመስለሉ፡፡ ይኼ ለአገሪቱ በጎ ጅምር ሳይሆን አይቀርም፡፡ ለጊዜው ላመስግናቸው አልፈልግም፡፡ ላለማመስገን ከሳቸው ንግግር ውስጥ የተማርኩት ነገር አለ፡፡ አቶ ለማ በአማራ ክልል ውስጥ ስለተደረገላቸው አቀባበል ለተለያዩ የክልል አካላት ምሥጋና ካቀረቡ በኋላ፣ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ለጊዜው እንደማያመሰግኗቸው ገልጸዋል፡፡ ምክንያንም ሲገልጹ በመጀመሪያ ደረጃ መሪዎቹ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ብቻ እየሠሩ ከመሆኑም በላይ፣ የአሁኑ ሥራ ጅምር በመሆኑ የመጨረሻውን ግብ ካዩ በኋላ እንደሚያመሰግኑ ነው ያሳወቁት፡፡ ስለዚህም ‹ለጊዜው ምሥጋና ይቆይልን› ብለው ነው ቁርጠኝነታቸውን ያሳወቁት፡፡

  አቶ ለማ ወጣቱና ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ በእርስዎ አመራር ዘመን አገሪቱን ከጥፋት ለመታደግ ፍንጭ በማሳየታቸው፣ የክልሎዎችን ሕዝብና ወጣቶች ለማመስገን እወዳለሁ፡፡ ለእርስዎ የማቀርበው ምሥጋና ነበረኝ፡፡ ግን ለጊዜው ይቆይልኝ፡፡ ሁሉም ነገር ሲሳካና አገሪቱን አሁን ካለችበት ጨለማ በሚያወጣው የብርሃን ጎዳና እስከ መጨረሻው ተጉዘን ሰላማችን አስተማማኝ ሲሆን፣ በሕዝቡ ውስጥ የአንድነት መንፈስ ሲሰፍን ባርኔጣዬን አንስቼ አመሰግንዎታለሁ፡፡

  አሁን አንዳንድ ሰዎች በሁለቱም ክልሎች በተለይም በኦሮሚያ እየተተገበረ ያለው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ የመንግሥት የማዘናጊያ ታክቲክ አድርገው ነው የሚጠራጠሩት፡፡ ይኼ ሐሳብ በምንም መመዘኛ ተቀባይነት ሊኖረው የሚገባ መሆን የለበትም፡፡ ነገሮችን ሁሉ በክፉ እየተረጎምን ኑሮን አንጉዳ፡፡ ኢሕአዴግም ቢሆን ስህተት ናቸው ብሎ ሕዝብ ያመነበትን ጉድለት ለማረም ከተነሳ ባይሆን እናመስግነው እንጂ፣ ዕድሉን ልንከለክለው አይገባም፡፡ ዋናው ቁምነገር ለበጎ ጅምር ድጋፍ እየሰጠንና እየተከታተልን መጨረሻውን ማየት ተገቢ ነው፡፡ አንድን ነገር ጅምሩን ከወደድነው ፍፃሜው አደጋ አለበት ብሎ ማሰብ ወይ ከጨለምተኝነት፣ ወይ ከተስፋ መቁረጥ፣ ወይ ከክፉ ልቦና የሚመነጭ ነው፡፡ እኛም የድርጊቱን ፈጻሚ ማንነት ብቻ ሳይሆን የሐሳቡን ይዘት እያየን ፍፃሜውን እንጠብቅ፡፡ መጀመሪያውንና መጨረሻውን በአንድ ጊዜ ማየት እንደማንችል እርግጠኛ እንሁን፡፡ ሁለቱንም ዛሬውኑ ካላየሁ ማለት ከጉጉትም ከችኮላም በላይ ነው፡፡ አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ከአንድ የወንዝ መነሻና መዳረሻ ውኃ ሊቀዳ አይችልም፡፡ የተወሰኑ የፖለቲካ ቆማሪዎች ደግሞ ይኼ የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ ሁልጊዜ በኢሕአዴግ ላይ አለን የሚሉት ዋናው መቃወሚያ ስለሆነ፣ የመጫወቻ ካርዳቸውን ላለማስነጠቅ የሚደረግ ጥረት መሆኑን አንርሳ፡፡

  አገሪቱን ለማዳንና ሳናስበው ከገባንበት ጨለማ ለመውጣት የሚያስፈልጉን፣ ቢሮዎቻቸውን ከተሰጣቸው ሥልጣን በላይ አሳምረው ያለሥራ ለመዋያነት የሚገለገሉበትን አይደሉም፡፡ ሌቱንም ቀኑንም ስለአገራቸው የሚያስቡ፣ የሚያቅዱ፣ አዳዲስ ሐሳቦችን የሚያመነጩ፣ የሕዝብ የልብ ትርታ እያዳመጡ መፍትሔ መስጠት የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡ ሕዝቡ ከጨለማ ለመውጣት እነሱ በሚመሩት ልክ ነው እየተራመደ የሚጓዘው፡፡

  ለማንኛውም ጨለማው የሚነጋ መስሎን ወይም የጨለማውን ሌሊት የሚያሳልፈን ሰው አጥተን በተረት ዓለም እንደተጠቁት፣ በጠንካራ ሁኔታ ሳንታገልና ሳንከራከር በቀላሉ ዓይናችንን እኛው እንዳናወጣው፡፡ ዓይናችንን አውጥተን መጣል የለብንም የሚሉ ሰዎች ምንም ጥቂቶች ቢሆኑ ያሸንፋሉ፡፡ ዓይንን ዘላቂ ጨለማ ውስጥ ከማኖርም  በላይ ከፍተኛ ሕመም እንዳለው አንርሳ፡፡

  ሰላማችንን ችግር እንዳይገጥመው ፖለቲካዊ መፍትሔዎች ለመስቀመጥ መንግሥትና ሕዝብ ተገናኝተው መወያየት እንዳለባቸው፣ ችግራቸውንም ያለ ፍርኃት በዴሞክራሲያዊ አግባብ እንዲፈቱ የሚል ሐሳብ ሲቀርብ ኖሯል፡፡ ነገር ግን መንግሥት የዚህን ዓይነት ውይይት ባለመፈለጉ ነገሮች አሁን ያሉበት ደረጃ ደርሰዋል፡፡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች መሀል ለናሙና ያህልም ቢሆን የተጀመረው ግንኙነት ወሳኝ ጅማሮ ነው፡፡

  የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች በአገሪቱ ውስጥ ካለው የሕዝብ ቁጥር አንፃር አብዛኛውን የሚያጠቃልሉ ናቸው፡፡ በመሆኑም የእነሱ ፍቅርና ስምምነት ፈር ቀዳጅ ከመሆኑም  በላይ፣ በሌሎችም ላይ ለተመሳሳይ አዎንታዊ ዕርምጃ አብነቱና ጫናው ከፍ ያለ ነው፡፡

  ሌላው ከዚህ አንፃር መታየት የሚገባው በተደጋጋሚ በኦሮሚያ ውስጥ የሚከሰተው ሁከትና ረብሻ ነው፡፡ ዋና ከተማይቱ አዲስ አበባ የኦሮሚያ አካል እንደ መሆኗና ክልሉ ካለው ጂኦግራፊያዊ ማዕከልነቱ በተጨማሪ፣ ካለው የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሀብት አንፃር ሁሉም ክልሎች ከኦሮሚያ የሚያገኙት ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማኅበረሰባዊ ጥቅም ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ካለበት አጠቃላይ ኃላፊነት አንፃር የኦሮሚያን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የመፍታትና ጥቅሞቹን የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ሰላም ሲጠፋ ለሁሉም የአደጋ ደወል ነው፡፡

  እስካሁን ድረስ ችግሮቹ እየተወሳሰቡና እየተበለሻሹ የመጡት መንግሥት ትንንሾቹን ችግሮች ሁሉ መፍታት እያቃተው ወይም ባለመፈለጉ፣ ችግሮች በላይ በላይ እየተደራረቡ አደገኛውን የቆሼ ተራራ ፈጠሩ፡፡ እንግዲህ መንግሥት ይኼን ተራራ እንዴት እንደሚንደው ለማየት ጓጉተናል፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው ጭፍጨፋና ሥጋቱ

  ኦሮሚያ ክልል ከቀውስ አዙሪት መላቀቅ ያቃተው ይመስላል፡፡ ከ200 በላይ...

  እናት ባንክ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

  መጠባበቂያን ሳይጨምር የባንኩ የተጣራ ትረፍ 182 ሚሊዮን ብር ሆኗል እናት...

  ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር ቻለ

  ቡና ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን ለመጀመርያ...