Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርኢትዮ ቴሌኮምን ምነው ሃይ የሚለው ጠፋ?

ኢትዮ ቴሌኮምን ምነው ሃይ የሚለው ጠፋ?

ቀን:

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኅብረተሰቡን ፍላጎትና ፈቃድ ባላገናዘበ ሁኔታ ኢትዮ ቴሌኮም በየመንደሩ እየገባ፣ ነዋሪው ሕዝብ ሳይሰስትና ሳይሳሳ ገንዘቡን አዋጥቶ የሠራውን የኮብልስቶን መንገድ ኬብል እንቀብራለን የሚሉ ቆፋሪዎቹን አሰማርቶ በመቆፋፈር በጥሩ ደረጃ የተሠራውን መንገድ ፈነቃቅሎ አበላሽቶታል፡፡

ኬብሉን ከቀየረ በኋላ አፈሩንና ድንጋዩን እንዲሁም ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት መልክ ይዞ የነበረውን ኮብልስቶን ከፊሉን ከአፈር ደባልቆ በመቅበር፣ ቀሪውን የትም በመበታተን እንዳልሆነ አድርጎታል፡፡ የኢትዮ ቴሎኮም ቆፋሪዎች ለምን እንደነበር አታስተካክሉትም ነበር ሲባሉ ቀበሌ መጥቶ ይሠራዋል የሚል አጉል ምላሽ በመስጠት ያበላሹትን ሳያስተካክሉ ሔደዋል፡፡ ቀበሌውም ቢሆን የተበላሸውን መንገድ ዘወር ብሎ አላየውም፡፡ አይፈረድበትም፡፡ በየትኛው አቅሙና በጀቱ ነው በየመንደሩ እየገባ የሚያስተካክለው?

የኢትዮ ቴሌኮም ጥፋት ይኼ ብቻ አይደለም፡፡ ዋናው መንገድም እንደዚሁ ዳርዳሩን  በመቆፈር ኬብሉን ከቀበረ በኋላ አፈሩንና ድንጋዩን እንዳለ ዘርግፎት ሄዷል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ ለማን አቤት እንበል በማለት መንደርተኛው ዝምታን መርጦ በመታዘብ ላይ ይገኛል፡፡

ይባስ ብሎም እንደፈራነው የካቲት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ሌሊት የዘነበው ዝናብ መንገዱን ሁሉ ጭቃ በጭቃ በማድረግ እንኳንና ለእግረኛ ለመኪናም አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲፈጠር አስገድዷል፡፡ ከአሁኑ አስቸኳይ ዕርምጃ በመውሰድ ያበላሸው ክፍል ማለትም ኢትዮ ቴሌኮም መጥቶ እንደበር ካላስተካከለው ዋናው ክረምት ሲመጣ ምን እንደሚውጠን ፈጣሪ ይወቅ፡፡ ስለዚህ በቅርብ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ሃይ በማለት መፍትሔ እንዲሰጠንና መንገዱም በአስቸኳይ እንዲስተካከልን ያደርግ ዘንድ እናመለክታለን፡፡

(ከአዲስ አበባ፣ የመጠለያ ነዋሪዎች)

***************

ለመገናኛ አደባባይ ጭንቅንቅ አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልጋል

አብዛኛውን ጊዜ በማዘወትርበት የመገናኛ አደባባይን በተመለከተ በጣም ያሳሰበኝን ነገር ነው ዛሬ ለመጻፍ የወሰንኩት፡፡

የመገናኛ አደባባይ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ፈርሶ መገንባቱ የሚታወስ ነው፡፡ ግንባታውን ለማካሄድ ከዲዛይኑ ጀምሮ እስከ ማጠነቃቀቂያው ድረስ ባለው ሒደት የተሳተፉት ሁሉ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡ አሁን የቀረው ነገር ቢኖር የአደባባዩን ዙሪያ በተዋቡ ሕንፃዎችና ባማሩ አትክልቶች በመከለል ለቱሪስትና ለነዋሪው ሕዝብ መስህብ እንዲሆኑ የማድረጉ ተግባር ነው፡፡

ነገር ግን ይህ አደባባይ አሁንም በሕዝብና በተሽከርካሪ እንደተጨናነቀ ነው፡፡ አደባባዩ ላይ ሌላ ተጨማሪ መንገድ መገንባት የሚታሰብ አይደለም፡፡ በእኔ እምነት ይህንን አደባባይ ከመጨናነቅ ሊያድነው የሚችል መንገድ ያለ ይመስለኛል፡፡ ይህንን አደባባይ ተጠቅሞ ወደ ሲኤምሲ፣ ሰሚት አካባቢ የሚጓዘው የኅብረተሰብ ክፍል አሁንም ወደፊትም በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደሚሄድ ለሁላችንም ግልጽ ይመስለኛል፡፡ በቅርቡ ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት የሚውሉ ቤቶች በመቶ ሺዎች ወይም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ስለሚይዙ፣ በርካቶች ከመሐል ከተማ ወደ እነዚህ አካባቢዎች መዛወራቸው የማይቀር ነው፡፡ በመሆኑም መጨናነቁ በከፍተኛ ደረጃ መቀጠሉ አይቀርም፡፡

ገርጂ ጊዮርጊስ ተብሎ በሚጠራው ቦታና በጐሮ አደባባይ በኩል ያለው ርቀት ከሁለት ኪሎ ሜትር የሚያንስ ሲሆን፣ በዚህ አካባቢ በሚያልፈው ወንዝ ላይ ምንም ዓይነት ድልድይ ካለመኖሩም ባሻገር የተገነባ መንገድም የለም፡፡ በመሆኑም በመብራት ኃይል ሰፈር ወይም በመገናኛ ለመጓጓዝ በሚራወጡ መንገደኞችና እግረኞች ከላይ የተጠቀሰው ትንቅንቅ የተፈጠረ ይመስለኛል፡፡

ይህንን ድልድይ ለመሥራት በእርግጥ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ከሚፈጥረው ጥቅም አኳያ ግን ምንም ወጪ ቢወጣ ግንባታው ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ከቦሌ ብራስና ከኢምፔሪያል አካባቢ የሚመጣው ትራፊክ በዚህ አቋራጭ መጠቀም ከቻለ፣ በመገናኛ የሚያልፈው ትራፊክ በእኔ እምነት በግማሽ የሚቀንስ ይመስለኛል፡፡

መገናኛ አካባቢ ለሚገኘው አነስተኛ የመንገድ ሥርጭት የሰው ብዛት የፈጠረው መጨናነቅ ሳያንስ፣ ሁለት የክፍለ ከተማ ሕንፃዎች በቦታው መገንባታቸው በእውነቱ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ሕንፃዎቹ በተለያየ አካባቢ መገንባት ነበረባቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አሁን እየተገነባ ያለው ትልቁ ስታዲየም ሲያልቅ ተመልካቹ ሁሉ ከስታዲየም ወጥቶ ወደ ቤቱ ሲያቀና የሚኖረውን ትርምስ ለማስተናገድ ይህ የገርጂ ጊዮርጊስ አቋራጭ መንገድ ወሳኝ መፍትሔ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡

ይህ አቋራጭ መንገድ ከመገናኛ ሰሚት ያለው መንገድ ላይ ሊኖር የሚችለውን ጭንቅንቅ በመቀነስ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ከስታዲየሙ በቀለበት መንገድ በኩል በድልድይ አልፎ ወደ ገርጂ ጊዮርጊስ የሚሄድ ደረጃውን የጠበቀ የመንገድ ግንባታም ከዚህ ድልድይ ጋር አብሮ ቢታሰብበት መልካም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

በመጨረሻም ማሳሰብ የምፈልገው ነገር ሲኤምሲ አካባቢ መኖሪያ ቤት የሚበዛበት በመሆኑ፣ አብዛኛው ነዋሪም መሥሪያ ቤቱ የሚገኘው መሀል ከተማ  ከመሆኑ አኳያ፣ እንዲህ ያለውን የተራዘመና የተጨናነቀ የትራፊክ ፍሰትን ለመቀነስ መንግሥት መሥሪያ ቤቶቹን ወደ ሲኤምሲ አካባቢ ቢያዛውር የመገናኛን ጭንቅንቅ ለማቃለል ሌላው አማራጭ ይሆናል፡፡

(መታሰቢያ መላኩ፣ ከአዲስ አበባ)

                          * * * * * * *       

መልካም የመሥራት ምርጫ

ከዚህ በታች የሚነበበውን አነስተኛ ጽሑፍ ያገኘሁት ‹‹ቪቭ ኬራ›› የተባሉ ደራሲ “You can win” የሚለው መጽሐፋቸውን ማህሌት ጥላሁንና ዳኜ መላኩ የተባሉ ተርጓሚዎች በ2001 ዓ.ም. ‹‹ለአሸናፊነት መገዛት›› በሚል ርዕስ ካወጡት መጽሐፍ  ነው፡፡ ለአንባቢያን የሚጠቅም ሆኖ ስለታየኝ በሪፖርተር ጋዜጣ ይጠቅማል ብዬ ልኬዋለሁ፡፡ እንዲህ ይላል፡፡

ሕይወት በምርጫዎች የተሞላችው እንዴት ነው?

‹‹ምግብ አብዝተን ስንበላ ወፍራም የመሆንና ጤናን የማጣት ምርጫን መረጥን ማለት ነው፡፡ መጠጥ አብዝተን ስንጠጣ በነጋታው ጠዋት ራስ ምታት እንዲይዘንና ቀስ በቀስ የጤና መታወክ እንዲደርስብን መረ­ጥን ማለት ነው፡፡ ጠጥተን ካሽከረከርን በሚፈጠረው አደጋ የመሞት አሊያም ሰው የመግደል ምርጫን መረጥን ማለት ነው፡፡ ሰዎችን በሕመማቸው ጊዜ ካስታመምናቸው እኛም ስንታመም ተመሳሳዩን አገልግሎት ለማግኘት መረጥን ማለት ነው፡፡ ለሌሎች ማሰብ ካቆምን ሌሎችም እንዳያስቡልን መረጥን ማለት ነው፡፡ ምርጫዎች ሁሉ የራሳቸው ጣጣ አላቸው፡፡ ምርጫዎችን ለመምረጥ ነፃ ብንሆንም ቅሉ ከዚያ በኋላ ምርጫችን እኛኑ ይቆጣጠረናል፡፡ እኩል ያለመሆን እኩል ዕድል ነው ያለን፡፡ መምረጡ የእኛ ፈንታ ነው ሕይወት የፈለገውን ዓይነት ቅርጽ እየሠራ ከሚኖር ሸክላ ሠሪ ጋር ትነጻጸራለች፡፡ እኛም ሕይወታችን የፈለግነውን ቅርጽ እንዲይዝ መምረጥ እንችላለን፤›› ይላል፡፡ ስለዚህ ጤናማ አስተሳሰብ ይኑረን፡፡

(ተክልዬ ጀማነህ፣ ከምሥራቅ አዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...