ማክሰኞ የካቲት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ነው፡፡ ቦታው ከአትላስ ሆቴል ወደ ቺቺኒያ የሚወስደው ጎዳና ጫፍ ላይ ነው፡፡ ‹‹ቀስ እያልክ፣ ቀዩን መስመር ሳትረግጥ፣ የፈንጂ ወረዳውን ለመሻገር እየተጠነቀቅህ. . .›› እያለ አንድ በሰላሳዎቹ መጨረሻ ዕድሜ ላይ የሚገኝ የሚመስል ሰው ድምፁን ጎላ አድርጎ ይጮሃል፡፡ ሙሉ ልብስ ከነ ከረባቱ ለብሶ፣ ፀዳ ያለ ጫማና ባለ ክፈፍ ክብ ባርኔጣ አድርጎ ጀነን እያለ የሚራመደው ይህ ሰው ሲያዩት ረጋ ያለና ጤናማ ይመስላል፡፡ ነገር ግን፣ ‹‹ቀስ እያልክ፣ ቀዩን መስመር ሳትረግጥ፣ የፈንጂ ወረዳውን ለመሻገር እየተጠነቀቅህ. . .›› እያለ በተደጋጋሚ በከፍተኛ ድምፅ ሲናገር ደግሞ ንክ ይመስላል፡፡
በዚያ ሰዓት የቀጠርኩትን ሰው ለመጠበቅ መኪናዬን ተደግፌ ወጪ ወራጁን ስታዘብ ይህ ሰው ድምፁ ጎልቶ ይሰማኛል፡፡ ሰውየው አጠገቤ ደርሶ ከቆመ በኋላ ያንኑ ንግግር ደገመው፡፡ በሁኔታው በመገረም ከላይ እስከ ታች ሳየው፣ ‹‹ወንድም እኔን ማየቱን ትተህ ስለምን እየተናገርኩ እንደሆነ አትጠይቀኝም?›› አለኝ፡፡ ደንገጥ እንደማለት ካልኩ በኋላ ጉሮሮዬን አፀዳድቼ፣ ‹‹ጤነኛ ትሁን ወፈፌ እንዴት አውቄ ልጠይቅህ?›› በማለት ጥያቄውን በጥያቄ መለስኩለት፡፡ ዓይኖቹን አጉረጥርጦ አፍጥጦ ካየኝ በኋላ ከት ብሎ ስቆ፣ ‹‹ጤነኛና ወፈፌ ልዩነታቸው ምን ይሆን?›› እስኪ የእኛ ሊቅ አስረዳኛ. . .›› እያለ እንደኔ መኪናውን ተደግፎ ቆመ፡፡
ወዲያው ከኪሱ የሲጋራ ፓኮና ክብሪት ካወጣ በኋላ ሲጋራውን መዞ አውጥቶ ለኮሰና በረጂሙ ወደ ውስጥ ሳበው፡፡ ከዚያም፣ ‹‹ምነው ግራ ገባህ አስረዳኝ ነው እኮ ያልኩት?›› ብሎ ፊቱን ወደ እኔ አዞረ፡፡ እኔም፣ ‹‹ጤነኛ ሰው ማለት ሰዎችን በሥነ ሥርዓት ቀርቦ በማናገር የሚፈልገውን የሚጠይቅ ሲሆን፣ ወፈፌ ደግሞ ልክ እንዳንተ ድንገት እንደ ጎርፍ ደርሶ መያዣ መጨበጫ የሌለው ነገር የሚያወራና ግራ የሚያጋቡ ጥያቄዎችን የሚደረድር ነው፤›› ብዬው ካቀረከርኩበት ቀና ስል በተመስጦ አንገቱን እያወዛወዘ ይሰማኝ ነበር፡፡ ለአንድ ደቂቃ ያህል ሲጋራውን እያቦነነ ካጨሰ በኋላ ትርኳሹን መሬት ላይ ጥሎ እየደፈጠጠ፣ ‹‹ይኼ የምታወራው ዝባዝንኬ አይጠቅምህም፡፡ ዓለም በዚህ ዘመን እንዳተ ዓይነቶቹ የሚያወሩትን የሚሰማበት ጆሮ የለውም፡፡ የዋሆችና ቂላቂሎች ስለሞራል፣ ሥነ ምግባር፣ ሥርዓት፣ ምናምንቴ ነገር ስታወሩ ሌሎች ይስቁባችኋል፣ ይሳለቁባችኋል፡፡ ዓይንህን ገልጠህ ዙሪያህን ተመልከት፡፡ ጊዜው የወፈፌዎች ነው. . .›› እያለ ሳቀብኝ፡፡
ይህን ሰው አላውቀውም፡፡ የተገናኘነው በአጋጣሚ ነው፡፡ ከየት እንደመጣና ወዴት እንደሚሄድም አላውቅም፡፡ በራሴ የሕይወት ፍልስፍና መሠረት ከማላውቀው ሰው ጋር መነጋገር አልነበረብኝም፡፡ ስለዚህ ዝም አልኩ፡፡ ሰውየው ቀጠለ፡፡ ‹‹ሰማህ ወንድም፡፡ ጤነኛና ወፈፌ የሚባሉት ተምታተውብሃል፡፡ ሁላችንም ወፈፌዎች ነን፡፡ በቀን ስንት ጊዜ ወፈፍ እንደሚያደርገን የምናውቀው እኛ ራሳችን ነን፡፡ አንዱ ምን ሆነ መሰለህ? ከመንግሥት ቤት የቀናውን ያህል ዘርፎ ከወጣ በኋላ ሆቴል ይከፍታል፡፡ ከመጣ ከሄደው ጋር ማንጫለጥ ለምዶ የአልኮል ሱሰኛ ይሆናል፡፡ ሚስቱ በአማላጅ ብዛት ሆቴሉን አዘግታ የተሽከርካሪዎችና የማሽኖች ኪራይ ቢዝነስ ይጀምራል፡፡ ለካ በኬክ ቤትና በስቴሽነሪ የተለመደው አጉል መንጋጋት እዚያም ተባብሶ ቀጥሎ ይከስርና ይወጣል፡፡ ያዋጣል ሲሉት የኅትመት ሥራ ይጀምራል፡፡ እሱም አልቀናውም፡፡ በመጨረሻ ድለላ ጀምሮ እሱ ተሻለው፡፡ በኮሚሽን የሚያገኘው ገንዘብ ቢጣፍጠውም፣ ደላላ የሚባለው ስያሜ እያበገነው ይኖራል፡፡ ይኼ ሰው ጤነኛ ነው ወይስ ወፈፌ?›› ሲለኝ ሳላስበው ከት ብዬ ሳቅኩ፡፡
ሰውየው አሳሳቄ አስገርሞት ነው መሰል ቀጠለ፡፡ ‹‹እስኪ መንግሥትን ተመልከት፡፡ በዚህ ዘመን የመንግሥት ሹመት ምን ይጠቅማል? በቪኤይት ብትሄድ፣ ፅዱ ቪላ ውስጥ ብትኖር፣ በጥበቃ አጀብ ውስጥ ብትሆን፣ ምርጥ ምርጥ ምግቦች ብትበላ፣ የተለያዩ አገሮች ብትንሸራሸር ምን ዋጋ አለው? ሁልጊዜ አጥር ውስጥ ነህ፡፡ የፈለግከው ቦታ አትሄድም፡፡ የፈለግከው ምግብ ቤት ወይም መጠጥ ቤት መግባት አይፈቀድም፡፡ ሕዝብ በነፃነት የሚዝናናባቸው ቦታዎች ድርሽ አትልም፡፡ የቀልድ ፏፏቴ ያለበት ሥፍራ ከቶም እንደናፈቀህ ይቀራል፡፡ ቆነጃጅትን በዓይንህ ሙሉ ማየት ብርቅ ይሆንብሃል፡፡ በስብሰባና በግምገማ ልብህ እየጠፋ ትኖራለህ፡፡ ሌላው ቀርቶ የምትሰርቀውን ታከማቻለህ እንጂ አትበላውም፡፡ ምን ደግ ብትሠራ ምሥጋና የለም፡፡ እና አንተ ጤነኛ ነህ ወፈፌ?›› ሲል በመገረም አየሁት፡፡ ሲጋራውን ለኩሶ በረጂሙ ሲምገው በሐሳብ ጭልጥ ብሎ ነው፡፡
በዚህ መሀል፣ ‹‹ቅድም ስለጥንቃቄ፣ ቀይ መስመርና የፈንጂ ወረዳ በጩኸት ስትናገር የነበረው ምን ሆነህ ነው?›› ስለው፣ አሁንም ሲጋራውን በረጂሙ ምጎ መሬት ላይ ከጣለው በኋላ በእግሩ ደፈጠጠና፣ ‹‹ከቦሌ ጀምረህ እስከ መሳለሚያ፣ ከእንጦጦ ጀምረህ እስከ ቃሊቲ የምታየው ሁሉ ተጠንቀቅ አያሰኝም?›› አለኝ፡፡ ‹‹አሃ! ስለዚህ ጥንቃቄ ላይ የምታተኩር ከሆነ ጤነኛ ነህ ማለት ነው. . .›› ብዬው መልሱን መጠበቅ ጀመርኩ፡፡ ‹‹አትሳሳት! እኔ እየተነጋገርኩ የነበርኩት ከራሴ ጋር ነው፡፡ እየነገርኩ የነበርኩት ለራሴ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ከጤነኝነት ጋር አይገናኝም. . .›› እያለ ሲለፈልፍ ጓደኛዬ ደረሰ፡፡ ጓደኛዬ ሰላምታ አቅርቦልኝ፣ ‹‹ከአጅሬው ጋር እያወራሁ ነበር እንዳትለኝ ብቻ. . .›› ከማለቱ፣ ‹‹ኧረ ብዙ ነገር ተወያይተናል. . .›› ስለው በሳቅ ፍርስ አለ፡፡ ‹‹ምን ሆነሃል?›› ስለው፣ ‹‹ይኼ እኮ እህ ካልከው እኮ በወሬ አፍዝዞ አቁሞ ያሳድርሃል. . .›› ሲለኝ ሰውዬው ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹እግዜር ይይልህ ደህና መደበሪያዬን አባነንክብኝ. . .›› እያለ ከት ብሎ ሳቀ፡፡ ‹‹ምንድነው ነገሩ?›› በማለት ወደ ጓደኛዬ ስዞር፣ ‹‹በየቀኑ እየመረቀነ የወሬ ርዕስ ይፈጥርና ተወዛግቦ ማወዛገብ ነው ሥራው. . .›› ሲለኝ በራሴ አዘንኩ፡፡ ሳላውቀው ለካ ‹የምርቃና ጨብሲ› ሆኛለሁ፡፡
- (ሰለሞን ዕዝራ፣ ከባልደራስ ኮንዶሚኒየም)