Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየሠራዊቱ ቀን ሲከበር መታወስ ያለባቸው ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች

የሠራዊቱ ቀን ሲከበር መታወስ ያለባቸው ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች

ቀን:

በውብሸት ሙላት

በዚህ ሳምንት ከተከናወኑት አገራዊ ክዋኔዎች ውስጥ አንዱ አምስተኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን በጅግጅጋ መከበሩ ነው፡፡ ይህ በዓል ሲከበር የሠራዊቱ የስኬት መለኪያ ሆነው ማገልገል ያለባቸው ሕገ መንግሥታዊዎቹ መሥፈርቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም በዋናነት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 87 ላይ የተቀመጡትን የመከላከያ መርሆች በመመንዘር እንዲሁም ሌሎች የሕግ ድንጋጌዎችን መነሻ በማድረግ በአገሪቱና በዙሪያዋ በተከሰቱና ሊከሰቱ የሚችሉ ሁኔታዎች ላይ መጠነኛ የሕግ ትንተናና የፖሊሲ ጉዳዮችን ያነሳል፡፡

የሠራዊቱ የብሔር ተዋጽኦ

ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች በየትኛውም እርከን ውስጥ ባሉ መንግሥታዊ መዋቅሮች ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የመወከል መብት እንዳላቸው ተገልጿል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ትኩረት ከሰጠባቸው መንግሥታዊ መዋቅሮች አንዱ መከላከያ ሠራዊቱ ነው፡፡ ጉዳዩ ከአንቀጽ 39 በተጨማሪ 87 ላይ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ስብጥር ከግምት ያስገባ መሆን እንዳለበት በማከል አስፍሯል፡፡

በየትም አገር ቢሆን መከላከያ ሠራዊቱ የአገሪቱ ሕዝቦች ስሜትና ፍላጎት ነፀብራቅ መሆን አለበት፡፡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ስብጥሮች ካሉም የዚያው መገለጫ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ብዙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ አካባቢ፣ እንዲሁም ሃይማኖቶች ካሉም እነዚህን ልዩነቶች ከግምት ማስገባት አለበት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ብዙም ኅቡዕ አይደለም፡፡

መከላከያ ሠራዊቱ ወደ አንድ ወገን ወይም ቡድን እንዲያጋድል ወይም ወገንተኛ እንዲሆን ተደርጎ ከተዋቀረ ቀን ያበደ ለታ (ክፉ ቀን ሲመጣ) ያው ወደ ወገኑ ማዘንበሉ አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪክ ህያው ምስክር ነው፡፡

ከታሪካችን ልንማር የምንችለው ቁም ነገር ቢኖር ሠራዊቱ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም ሃይማኖቶች ሚዛናዊ ውክልና መኖር እንዳለበት ነው፡፡ ከተራ ወታደር እስከ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና  ካውንስሉ (ጉባዔው) ድረስ ስብጥሩ ተመጣጣኝ መሆን አለበት፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ ሚዛናዊ ውክልና መኖሩ ወይም የተወሰኑ መኮንኖች ከብዙ የኅብረተሰብ ክፍሎች መወከላቸው ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡

መከላከያ ሠራዊቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሙሉ ነፀብራቅ መሆን አለበት ብለናል፡፡ የአንዱ ወይም የጥቂቱ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ ውትድርና አገራዊ የዜጎች ግዴታ ባልሆነበትና በፈቃደኝነት ብቻ ምልመላ በሚከናወንባቸው በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ባለብዙ ብሔር አገሮች ምጥጥኑን ማምጣት ከባድ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ሙሉ በሙሉ ጠንካራ ወታደራዊ ዲሲፕሊንን መፍጠርም አታካች ነው፡፡ የአታካችነቱ ምክንያቶችም የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተመጣጣኝ ሁኔታ የትምህርት ሽፋን ባለመኖሩ ዝቅተኛውን የትምህርት መሥፈርት በተመሳሳይ መልኩ የሚያሟሉ ዕጩ ማጣት፣ ውትድርና የድሆችና የሥራ አጦች ምርጫ መሆኑ፣ ከ1987 ዓ.ም. በፊት የመከላከያ ሠራዊቱ ወደ አንድ ብሔር ብቻ ያደላ መሆኑና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

አሁን ያለው የመከላከያ ሠራዊት የብሔር ስብጥር ሲታይ በቁጥር አማራ እንደሚበልጥ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን መብለጥ የነበረበት ኦሮሞ ነበር፡፡ በመኮንኖችም ቁጥር ቢሆን እንደዚሁ፡፡ የማመጣጠኛ ወይም ሚዛናዊ ውክልና መፍጠሪያ የማይለዋወጥ ሒሳባዊ ቀመር ሊኖር እንደማይችል ሃቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀ ጀምሮ ሃያ ሁለት ዓመታት ቢሆነውም እነዚህ ጊዜያት ደግሞ የአንድ ትውልድ ዕድሜ ናቸውና ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንደ ቡድን ካላቸው መብቶች አንዱና የደኅንነት ዋስትና እንዳላቸው እንዲሰማቸውና የሚያረጋግጡበት በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ ተወክለው ማየታቸው በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

በተለይም በቁጥራቸው አናሳ የሆኑ ብሔረሰቦች በኮሎኔልነትና ጄነራልነት የተወከለ ፊት አለማየት፣ የድሮውን በመውቀስ ነገር ግን ያንኑ በመድገም ባለንበት ከመሄድና ከአፋዊ ትርክት (Rhetoric) ወደ ተግባር መሸጋገር ግድ ይላል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱ ቀን ሲከበር የሚኒስቴሩ ስኬት አንዱ መለኪያ ይህ ነው፤ በአንቀጽ 87(1) መርህ ሆኖ ተቀምጧልና!

ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ ዓቢይ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ

በ2008 ዓ.ም. ከመከላከያ ሠራዊቱ ግዴታና ተልዕኮ ጋር በተገናኘ ከተከሰቱት ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ በጋምቤላ ክልል የሚገኙ ነባር ብሔረሰቦችን ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ጎሳዎች ልጆቻቸውንና ከብቶቻቸውን መውሰድ፣ እንዲሁም ዜጎች ላይ ያደረሱት ግድያ አንዱ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከኤርትራ በመነሳት አንድም በትግራይ፣ በሌላ ጊዜም በሱዳን በመዞር በአማራ ክልል በኩል ታጣቂዎች ገብተው ነገር ግን በዋናነት በሚሊሻና በነዋሪው አማካይነት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ሌላው ክስተት ነው፡፡ ስለዚሁ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚዲያ የሕዝቡን አድራጎት ሲያደንቁም ተሰምተዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የግልገል ጊቤ ሦስት ግድብ ከተመረቀ በኋላ በደቡብ ኦሞ ዞንና በአካባቢው የሚገኙ ዜጎችን ሲያወያዩ ከተወያዮቹ ከቀረበላቸው ጥያቄዎች አንዱ ከግብርና ሙያቸው የሚያፈናቅሏቸው ከኬንያ በኩል የሚመጡ ጥቃቶች ስላሉ እነሱን መፍትሔ እንዲያበጁላቸው ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም መፍትሔ እንደሚሹለትም ቃል መግባታቸውን በሚዲያ ሰምተናል፡፡

የድንበር ጥበቃ ለገበሬውም ይሁን አርብቶ አደሩ የሚተው ጉዳይ አይደለምም፤ መሆን የለበትም፡፡ ድንበርን በማለፍ በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ሉዓላዊነት ላይ የሚደረጉ ጥቃቶች ስለመሆናቸው አያጠራጥርም፡፡ ጠረፍ ጠባቂ ወታደር (Frontier Army) በሌለበት ሁኔታ ከውጭ የሚነሱ አነስተኛ ጥቃቶች፣ ኮንትሮባንድ፣ እንዲሁም ገደብ አልባ የስደተኞች ፍሰትን መቆጣጠር የመከላከያ ሠራዊቱ ድርሻ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ የመከላከያ ሠራዊት ቀን ሲከበርም ስኬቱ ከእንዲህ ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ አንፃርም ጭምር መታየት አለበት፡፡

በሌላ ጎኑ ደግሞ በአካባቢው መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ምክንያት የፖለቲካ ጉዳይንም ከግምት ማስገባት ተገቢ ነው፡፡ በባብኤል ወንደብና በቀይ ባህር ዙሪያ ያለው የተባበሩት ዓረብ ኢሜሬትስና የሳዑዲ ዓረቢያ፣ የመን ላይ በተከሰተው ቀውስ ሰበብ አጭር ለማይባል ጊዜ አሰብን ከኤርትራ መከራየታቸው አንዱ የሥጋት ምንጭ ነው፡፡ ከአሜሪካ፣ ከጃፓንና ከቻይና በተጨማሪ ግብፅም፣ ጂቡቲ ላይ የባህር ኃይል ቦታ ለመከራየት የምታደርገው ድርድር፣ የተባበሩት የዓረብ ኢሜሬትስ ሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት፣ የደቡብ ሱዳንና የግብፅ ወዳጅነት መጠናከር እንዲሁም የኤርትራ የባህር ኃይል እያደር መጠናከርና አገሪቱ በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነትና ሌሎች በቀጠናው ላይ ከሚከናወኑ ተግባራት አንፃር የመከላከያ ሠራዊቱ የአገሪቱን ሉዓላዊነት እንዳይደፈር የማድረግ አቅሙን መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ከአድዋ ድል በኋላ ጣሊያን በአገሪቱ ውስጥ በርካታ ቆንስላዎችን በመክፈት ከፍተኛ ወታደራዊ ጠቀሜታ ያለውን ሥራ ካከናወነች በኋላ ጦር እንደከፈተችው ሁሉ ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶችም በዙሪያዋ በመመሸግ፣ ወደብ ባለበት አካባቢ ወታደራዊ ሠፈር በመገንባት ከተደላደሉ በኋላ ማስታወስ ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል የመቻሉ ጉዳይ ጣሊያን በ1928 እንዲሁም ኤርትራ ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ ያጋጠመንን ችግርና ያስከፈለንን ዋጋ ማስታወስ ይበቃል፡፡ የዓለም አቀፍ ሕግ ጉልበት በሌላቸው አገሮች ዘንድ የተፈጻሚነቱ ሁኔታ የሚያወላዳና የሚያስተማምን አይደለም፡፡ ጥሩ ማሳያው አሁንም ቢሆን ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ የነበረውና የባድመ ሁኔታ ነው፡፡ በመሆኑም፣ ኢትዮጵያ ካለችበት ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ አንጻር ወታደራዊ የበላይነቷ እንዳይኮሰምን መሥራት አለባት፡፡

የባህር ኃይል ማቋቋምንም እንደ አማራጭ መውሰድ አለባት፡፡ የባህር በር ሳይኖራቸው በወንዞቻቸው፣ በሐይቆቻቸውና አንዳንዶቹም ከሁለቱም ሳይኖራቸው ነገር ግን የባህር ኃይል የገነቡ አሉ፡፡ አዘርባጃን፣ ቱርኬምስታን፣ ካዛኪስታን፣ ቦሊቪያ፣ ላኦስ፣ ፓራጓይ፣ ሞንጎሊያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ሀንጋሪ፣ ማላዊ፣ ማሊና መካከለኛው አፍሪካ ጥሩ ምሳሌ ናቸው፡፡ ኤርትራ ከተገነጠለች በኋላ ከአራት ዓመታት ላላነሰ ጊዜ ኢትዮጵያ የባህር ኃይሏ አልፈረሰም ነበር፡፡ በዙሪያችን የሚንቀሳቀሱ አገሮች ጋር የሚኖረን የውጭ ግንኙነት የጥሩ ጎረቤት ዓይነት ሆኖ እንዲቀጥል በሌሎች ተፅዕኖ ምክንያት ጎረቤቶቻችን እንዳይከዱንና ሉዓላዊነታችን አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ቀድሞ ሁኔታዎችን ከግምት ያስገባ መከላከያ ሠራዊት ግንባታ ማስፈለጉ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ነው፡፡

እዚህ ላይ ሌላው ልብ ሊባል የሚገባው ቁምነገር ከእስራኤል ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የፀጥታና ደኅንነት እርዳታን ከአሜሪካ የምታገኘው ግብፅ መሆኗ ነው፡፡ የግብፅ እጅ በደቡብ ሱዳን፣ በኤርትራ፣ አሁን ደግሞ በጂቡቲ በኩል እየረዘመ መሄዱ እንዲሁም በዓረብ ሊግ በኩል የሚኖራት ተፅዕኖን በማሰብ ሊሆን ይገባል የመከላከያ ቀን አከባበርና ስኬት፡፡

ለጠባቂው ጠባቂ ማበጀት

መከላከያ ሠራዊት ዋና ተልዕኮው አገርን መጠበቅ ነው፡፡ ሲቋቋምም ጥቃትን ለመከላከል ወይም ጥቃት ለመፈጸም ስለሚሆን ይህንን መፈጸም የሚያስችል አቅም እንዲኖረው ይጠበቃል፡፡ ይህ አቅም ያለው አካል ደግሞ በአገር ውስጥ በቀላሉ ሌላ ጥቃት መፈጸም የሚያስችለው አቅም ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም ራሱ የመካላከያ ሠራዊቱ ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዳያፈርስ፣ መፈንቅለ መንግሥት እንዳይፈጽም፣ የዜጎችን መብት እንዳይጥስ ማን ይጠብቀው? ወይም እንዴት ይጠበቅ? የሚለው ጥያቄ ለዘመናት እንደቀጠለ ነው፡፡ ሊጠብቅው የሚገባውን ሕዝብ ራሱ ማጥቃት ወይም ማጥፋት የለበትም፡፡ ጥያቄውን የዘርፉ ባለሙያዎች የሲቪልና የወታደሩ ግንኙነት እንዴት ይሁን በማለት ያስቀምጡታል፡፡ ሲቪሉ የማኅበረሰብ ክፍል ከወታደር ውጭ ያለውን ሁሉ ቢያካትትም እንኳን የዚህ ጽሑፍ ትኩረት የመከላከያ ሚኒስትር፣ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር ያለውን ወይም የሚኖረውን ግንኙነት ብቻ ነው፡፡

በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሠራዊቱ እንደተቋም ሁልጊዜም ለፖለቲከኞች መገዛትና መታዘዝ አለበት፡፡ ሕዝብ በመረጣቸው ተወካዮቹ አማካይነት የሚሾሙ ባለሥልጣናት የውክልና ሌላ ውክልና ስለሚኖራቸውና ሕዝብ በተዘዋዋሪ መንገድ ስለሚቆጣጠራቸው በእነሱ አማካይነት መከላከያው ሊተዳደር ይገባዋል፡፡ ሠራዊቱ፣ ሕዝቡ ላይ እንኳን ጉዳት ባያደርስም የፖለቲካ ሹመኞቹ የሚሰጡትን ትዕዛዝ ተቀብሎ መፈጸም አለበት፡፡ ፖለቲካዊ ውሳኔዎቹ ውስጥ ራሱ ሳይገባ ነገር ግን የሚሰጠውን ተልዕኮ መፈጸም የተቋሙ ተፈጥሯዊ ግዴታው አድርጎ መውሰድ አለበት፡፡ ወታደሩ ሥጋትን፣ አደጋን ይመረምራል፤ ለሲቪሉ ያቀርባል፣ ሲቪሉ ግን ይወስናል፡፡ የሥጋቱን ሁኔታና መጠን ወታደሩ ይገልጻል፤ ሲቪል ምን መደረግ እንዳለበት ይወስናል፡፡ እንደ ባለሙያ ትንታኔ ወታደሩ ያቀርባል፣ ሲቪሉ ግን ውሳኔ ያሳልፋል፡፡ እንዲህ እያለ ለሲቪሉ ሥልጣን ይሰጣል፡፡

ከዚህ አንፃር ሕገ መንግሥቱን ለማፅደቅ በተደረገው ውይይት ላይ ስለመከላከያ መርሆች ጉዳይ ቃለ ጉባዔው እንደሚያሳው የመከላከያ ሚኒስትሩ ተግባር፣ ፖሊሲ ላይ እንደሚያተኩር፣ ሙያዊ የሆነውን ግን የጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ እንደሚሆን ያሳያል፡፡ በመሆኑም የመከላከያ ሠራዊቱ ግብና ተልዕኮ የሚወስነው ደግሞ በሚኒስትሩ በኩል ነው ማለት ነው፡፡ የአስፈጻሚውን ሥልጣንና ኃላፊነት ለመወሰን ከወጣው አዋጅ መረዳት እንደሚቻለው የመከላከያ ሠራዊቱን ማቋቋም፣ ማስታጠቅ፣ የውጊያ ብቃቱን ማረጋገጥ፣ መቆጣጠርና ሌሎች ተግባራት መከናወናቸውንም ይከታተላል፤ ያስፈጽማል፡፡ በጀቱንም ይሁን ሌሎች የገቢ ማስገኛ ዘዴዎች መቆጣጠርም ማስፈጸምም አለበት፡፡ በመሆኑም በእነዚህና በሌሎች አሠራሮች በኩል መከላከያ ሚኒስትሩ ወታደራዊ ተቋሙን ይቆጣጠራል፡፡

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑ፣ የጦርነት አዋጅ ማወጅ የሚችለው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለሕዝብ ተወካዮች በማቅረብ በማፀደቅ እንጂ በመከላከያ ሠራዊቱ በራሱ ፍላጎት አለመሆኑ አንዱ የመቆጣጠሪያ ዘዴ ነው፡፡ የሠራዊቱን አደራጃጀት የሚወስነውም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑም ሌላው ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ግር የሚያሰኝ ነገርን ማንሳት ይገባል፡፡ እሱም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዡ፣ ማለትም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ምንድን እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ የኢታማዦር ሹሙና የመከላከያ ሚኒስትሩ ተግባራትና ኃላፊነት በሕግ ተደንግጓል፡፡ በሌሎች አገሮች የጠቅላይ አዛዡ ሥልጣንም በግልጽ ይታወቃል፡፡ ሥልጣኑ የአለመታወቁ ብዥታ ለተለያዩ ስህተቶች ሊዳርግ መቻሉ እሙን ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በተከሰተው አመፅ ምክንያት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመታወጁ በፊት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድሩ ለፀጥታ ሠራተኞች የሰጡትን መመርያ ዓይነት እንዲሰጡ ያደርጋል፡፡ አመፁን ለማስቆም ተገቢውን ዕርምጃ እንዲወስዱ ለፀጥታ ሠራተኞች፣ የሠራዊቱ አባላትንም ጨምሮ፣ በራሳቸው ስም መመርያ የሰጡት ማለት ነው፡፡

የግንኙነቱ ሁኔታ ምን ይመስላል፣ መጠኑስ ምን ያህል መሆን አለበት? ግንኙነታቸውን ለማሻሻልስ በቀጣይ ምን መደረግ አለበት? የሚሉት ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ የፖሊሲ ጉዳዮች ናቸው፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች በቅጡ ማጤን መፈንቅለ መንግሥትን ለመቆጣጠር፣ ወታደሩ ሲቪሉ ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ለመቀነስ (የሥራ ክፍፍልን ተገንዝቦ በትክክል ለመፈጸም)፣ በሁለቱ መካከል ሊነሳ የሚችልን ፍጭት ለማለስለስና ለመግራት፣ መከላከያው ሲቪሉ የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎች በተገቢው ሁኔታ መፈጸም እንዲችል ወይም ሲቪሉ ከሚሰጠው የራሱን ወደ መምረጥ ማዘንበሉን እንዲተው፣ እንዲሁም የቁጥጥር ተግባርን ለማስፈጸም ይቻላል፡፡ መረን የለቀቀ መከላከያ መገንባት የለበትም፡፡

የቁጥጥር ዘዴዎቹ ደግሞ በሕገ መንግሥታዊና በአስተዳዳራዊ ለሲቪሉ ታማኝ እንዲሆኑ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱ በሲቪል አስተዳደሩ ላይ የፈረጠመ ክንድ ሊኖረው አይገባም፡፡ የመከላከያ ሠራዊት ቀን ሲከበር ይህ የሲቪልና የሠራዊቱ ግንኙነት እንደ አንድ መለኪያ በመንግሥት በኩል ሊወሰድ ይገባል፡፡

ፖለቲካዊ ወገንተኛ አለመሆን

“ፖለቲካዊ ኃይል አቆጥቁጣ የምታድገው ከጥይት ክምር ላይ ሆና ነው፤” እንዲል የወታደራዊ አባባል ማንም ሥልጣን/ኃይል አለኝ የሚል የፖለቲካ ቡድን ባለነፍጡን የመከላከያ ሠራዊት በእጁ ሳያደርግ ወይም በበቂ ሁኔታ የሠለጠነና የታጠቀ ወታደር ከሌለው ዋጋ የለውም፡፡ ቁምነገሩ ያለው ነፍጥና ብር (Sword and Purse) ጋር ነውና!

ከላይ ከተገለጸው በተጨማሪ መከላከያ ሠራዊቱ ከፖለቲካዊ ወገንተኛነት ነፃ መሆን አለበት፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ተቆናጣጭ የፖለቲካ ድርጅቶች ቢቀያየሩም ሠራዊቱ ግን እንዳለ መቀጠል አለበት፡፡ በመሆኑም ወታደራዊ ተቋማቱ ነፃ ሆነው ለሕገ መንግሥቱ ብቻ በመታመን መቀጠል አለባቸው፡፡

ስለዚህ ጉዳይ በ1993 ዓ.ም. በተከሰተው የሕወኃት ውስጣዊ ክፍፍል ወቅት አቶ ስዬ አብርሃ ሠራዊቱ ፖለቲካው ውስጥ መግባት ሕገ መንግሥቱ ቢከለክልም የነመለስ ዜናዊ ቡድን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌውን ወደ ጎን በመተው የተወሰኑ መኮንኖችን የመቀሌው ስብሰባ ላይ እንዲቀላቀሉ አድርገዋል በማለት ይከሳሉ፡፡ የእነ ሌተናል ጀነራል ፃድቃን ገብረ ትንሳኤ ከኃላፊነታቸው የመነሳታቸው ምክንያት ገለልተኛ መሆናቸው ነው ይላሉ፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱን ገለልተኛ የመሆኑን ምክንያት ሲገልጹ “ሠራዊት አንዴ ፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ከገባ መሪዎች በመረጡለት የጨዋታ ዓይነት ብቻ ሳይወሰን ይበጀኛል ያለውን የፖለቲካ ጨዋታ መጫወቱ አይቀርም፤’’ ይላሉ፡፡ ከምርጫ 1997 በኋላ ስንት ጀነራሎች  በእንዲህ ዓይነት ጨዋታ እንደኮበለሉና እንደተገፉ የመከላከያ ሚኒስቴር መዝገብ ይወቀው ይላሉ፡፡

በእርግጥ ሠራዊቱ ከፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኝነት ነፃ የመሆን ቁመና ላይ እንዳልደረሰ አቶ በረከት ስምዖንም ምርጫ 97ን ተከትሎ ስለተከሰተው ቀውስ እነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን መክረውበት ከነበረው ዓረፍተ ነገሮቻቸው መረዳት አያዳግትም፡፡ “አጉል ድፍረት ሲሰማቸውም (ቅንጅቶችን ለማለት ነው) ሠራዊቱ በመንግሥት ላይ ክንዱን እንዲያነሳ እስከመጋበዝ ይደርሳሉ፡፡ በተገናኘን ቁጥር ሕገ መንግሥቱ ሠራዊቱን በውስጣዊ ፖለቲካ እንዳይገባ የከለከለ መሆኑን እያስታወስን ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ብንጠይቅም ልቦናቸው አልከፈት እንዳለ ነበር፡፡ አንዳንዴ በቀላሉ ይገባቸው እንደሆን ብለን ሠራዊቱ በአንድ ወቅት የኢሕአዴግ መንትያ ፍጥረት እንደነበርና ክፉ ነገር ከመጣ አሰላለፉ ከማን ወገን እንደሚሆን የሚገነዘብ መሆኑን ብንነግራቸውም ከልባቸው አልጻፍ ብሏል፤” ይላሉ፡፡

ከዚህ የምንረዳው አንዱ መልዕክት የኢሕአዴግን ህልውና የሚነቀንቅ ክፉ ነገር ቢከሰት ሠራዊቱ ከፓርቲው መንትያ ፍጥረትነት ገና አለመላቀቁንና አሰላለፉም ግልጽ እንደሆነ ነው፡፡ ለዚህ ነው ከላይ ሚዛናዊ ስብጥሩ ብቻውን በቂ አይደለም ያልነው፡፡ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ነፃ መሆኑም ጭምር እንጂ፡፡ የነጄነራል ጃገማ ኬሎ ኦሮሞነት ዋቆ ጉቱን ሲማርኩ፣ የነጉበና ዳጨም አፄ ምኒልክ ብዙ የኦሮሚያ አካባቢን ሲይዙ አጋፋሪ እንጂ ተከላካይ አልነበሩም፡፡ በወቅቱ የነበረውን ሥርዓት በመደገፋቸው በብሔራቸውም ላይ ሳይቀር ዘምተዋል፡፡ ስለዚህ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝባዊ ስብጥር ብቻውን ግብ አይደለም፡፡ ከሌሎች ጋር ተደጋጋፊ እንጂ!

ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱ እስከፀደቀበት እስከ 1987 ዓ.ም. ድረስ በሕወሓት፣ በብአዴን (ኢሕዴን) እና በወታደሩ መካከል ልዩነት አልነበረም፡፡ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ሁሉም የሕወሓት፣ ኢሕዴንና ሌሎችም ድርጅቶች አባላት ወታደርም ጭምር ሆነው ያገለግሉ ነበር፡፡ ሲቪልና ወታደር የሚባል ልዩነት አልነበረም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ ግን አባላቱ ከሁለት አንዱን መርጠዋል፡፡ በመሆኑም ነባር የሕወሓት ወይም የኢሕዴን አባላት አሁን ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች በመሆን በሠራዊቱ ውስጥ አሉ፡፡ እነዚህ ነባር አባላት ኢሕአዴግን አይወግኑም ማለት ዘበት ነው፡፡ የሰው ባህርይም አይደለም፡፡ በረሃ ለበረሃ ብጣሽ ጨርቅ ለብሰው ኮዳ ተንተርስው ተዋግተው የተከሉትን ሥርዓት አትወግኑ ማለት የሚቻል አይመስልም፡፡ መከላከያ ሠራዊቱ ከእንደዚህ ዓይነቱ ወገንተኝነት ነፃ ለመሆን ትውልድ ማለፍ አለበት፡፡

መከላከያ ሠራዊቱ ከፖለቲካዊም ሆነ ከማናቸውም ቡድን ጋር ወገንተኛ ሳይሆን የአገር መሆን እንዳለበት ነው ሕገ መንግሥቱ የደነገገው፡፡ ከላይ ካየናቸው ነጥቦች በተጨማሪ የመከላከያ ሠራዊቱን ወገንተኛ እንዲሆን የሚያደርገው ከአወቃቀር (Structure) የሚመነጭ ሳንካ አለበት፡፡ ይኸውም፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥነቱን የሚሰጠው ለርዕሰ ብሔሩ ወይም ፕሬዚዳንቱ (Head of State) ሳይሆን ለርዕሰ መስተዳድሩ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ (Head of Government) መሆኑ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ የአገሪቱ ወኪል ፕሬዚዳንቱ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር የመንግሥት ወኪል ወይም የአስፈጻሚውን አካል የመጨረሻው አለቃ ነው፡፡ ርዕሰ ብሔሩና ርዕሰ መስተዳደሩ በተለያዩ ባለሥልጣናት እጅ በሚሆንባቸው ፓርላሜንታዊ ሥርዓትን የሚከተሉ አገሮች የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥነትን በጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅ እንዲሆን ማድረግ የተለመደ አይደለም፡፡ ብሪታኒያ፣ አውስትራሊያ፣ ስዊድን፣ ካናዳን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሮቹ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ አይደሉም፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም የተሻለው አማራጭ አይደለም፡፡

መከላከያ ሠራዊቱን ከአገር ወይም ከሕዝብ ይልቅ ወደ መንግሥት ሠራዊትነት እንዲወርድ ያደርገዋል፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ፓርቲም ለራሱ የአገዛዝ ዘመን ለማስቀጠል ሠራዊቱን ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱ፣ ፖለቲካዊ ወገንተኛ እንዳይሆን አድርጎ የማዋቀርንና ክትትል የማድረግን ኃላፊነት የሚጥለው መከላከያ ሚኒስትሩ ላይ ነው፡፡ ይህ ኃላፊነት የሚመስለው ሠራዊቱ ከአሸናፊው ፓርቲ ውጭ ለሆነ ፓርቲ እንዳይወግን ማረጋገጥን እንጂ የመከላከያ ሚኒስትሩ አባል የሆኑበትን ፓርቲ እንዳይወግኑ አይመስልም፡፡ ይህ ዓይነቱ የመከላከያ ሠራዊት አመራር ታማኝነቱ የመንግሥት እንጂ የአገሪቱ እንዲሆን አያስችልም፡፡ እንዲህ ሲሆን በበርካታ አገሮች ዘንድ ወታደራዊ ቃለ መሀላውን “ሂትለራዊ መሀላ” ይሉታል፡፡ አንድምታው ሠራዊቱ ለፓርቲው ወይም ለፕሬዚዳንቱ ወይም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተገዥ መሆንን እንጂ ለሕገ መንግሥቱ አለመሆንን ለማሳየት ነው፡፡ በፕሬዚዳንት ኦባማ የአስተዳደር ዘመንም ሠራዊቱ ታማኝነቱ ለሕገ መንግሥቱ ነው የሆነው ወይስ ለኦባማ የሚለው የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡ ሠራዊት የአገር አገልጋይ እንጂ የፓርቲ ሎሌ መሆንም የለበትም፡፡ በፖለቲካዊ አስተሳሰብ ከገዥ ፓርቲም ይሁን ሌላ ቡድን የተለየ አቋም ያለውን ማጥቃት የመከላከያ ሠራዊት ባህርይ አይደለም፡፡ በመሆኑም ሌላው የሠራዊቱ ስኬት ሕገ መንግሥታዊ መለኪያ ይህ ነው፡፡

ሠራዊቱ በውስጥ ጉዳይ

መከላከያ ሠራዊቱ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማስጠበቅ፣ አገርን ከውጭ ወራሪና ጠላት መጠበቅ ይገባዋል፡፡ ነገር ግን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካልሆነ በስተቀር ለዚያውም በፖሊስ አመራር ሥር ወይም አብሮ በመቀላቀል ከፖሊስና ከደኅንነት ሠራተኞች አቅም በላይ የሆነ ችግርና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰት ነው በውስጥ ጉዳይ መሳተፍ የሚችለው፡፡ በዴሞክራሲያዊና በፖለቲካዊ ስልት ሊፈቱ በሚችሉና በሚገባቸው ውስጣዊ ጉዳዮች ከመግባት መቆጠብ አለበት፡፡ ተአማኒነቱ ለአገሪቱ ለጅምላነቷ እንጂ ለአንድ ቡድን መሆን የለበትም፡፡

የመከላከያ ሠራዊት ዋና ተግባሩ የውጭ ወራሪን መመከት እንጂ የውስጥ ፓለቲካ ውስጥ መግባት የማይሆንበት ምክንያት የውስጥ ጉዳይ ላይ መግባት ክፍፍል ሊፈጥር መቻሉ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የብሔር ወይም የሃይማኖት ጦርነት ሊያስከትል ይችላል፡፡ እንኳን ጣልቃ ገብቶ ይቅርና ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር በሚደረግ ጥረት ደቡብ ሱዳን (በሳልቫኪር ማያርዲትና በሪክ ማቻር መካከል በተነሳው ብጥብጥ ምክንያት) ውስጥ ወታደሩ ጎራ በመለየት ስንት ንፁሃን ዜጎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ሐቅ ነው፡፡ በአንፃሩ በግብፅ የሆስኒ ሙባረክ አስተዳደር ከተወገደ ጊዜ ጀምሮ የመከላከያ ሠራዊቱ ያለምንም መከፋፈል የአገሪቱን አንድነት በመጠበቅ ያሳየው ብቃት የሚደነቅ ነው፡፡ በመሆኑም ምንም እንኳን ሕገ መንግሥቱ በአስቸኳይ ጊዜ ካልሆነ በስተቀር ሠራዊቱ በውስጥ ጉዳይ እንዲገባ የሚፈቅድበት ሁኔታ ባይኖርም፣ የፌደራል መንግሥቱ በክልሎች ጣልቃ እንዴት እንደሚገባ በሚደነግገው አዋጅ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ ሳይታወጅ ሊገባ የሚችልበት ሁኔታ መገለጹ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በአጠቃላይ የመከላከያ ሠራዊት ቀን ሲከበር  ራሱ ሠራዊቱም፣ መንግሥትም እንዲሁም ሕዝቡም ስኬቱን ለመለካት ቢያንስ ከላይ የተገለጹትን ሕገ መንግሥታዊ መርሆች ከግምት በማስገባት መሆን አለበት፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...