Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉለተጠናወቱን ችግሮች ዓይንና ልቦናን መክፈት ይበጃል

ለተጠናወቱን ችግሮች ዓይንና ልቦናን መክፈት ይበጃል

ቀን:

በደጊቱ ቱፋ

ኢትዮጵያ በብዙኃንነት ብቻ ሳይሆን በሕዝብ ቁጥርም ትልቅና ሰፊ የምትባል አገር ነች፡፡ ከ80 የማያንሱ የራሳቸው ባህል፣ ቋንቋና ማንነት ያላቸው ብሔር ብሔረሰቦችና በጥቂት ዓመታት ውስጥ 100 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ያላት አገር መሆኗን ያስታውሷል፡፡ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ የዓለም ጭራ ደሃ አገር፣ በጦርነትና በኋላ ቀርነት የኖረች ምሥራቅ አፍሪካዊት ቀደምት ምድር የሚል ስያሜ ተሰጥቷት ቢቆይም፣ አሁን አሁን በሌላ ገጽታ ስሟ እየተነሳ ይገኛል፡፡

አሁን ኢትዮጵያ የፈጣን ልማትና የተከታታይ ዕድገት ተምሳሌት (በተለይ ከምዕተ ዓመቱ ግብ አኳያ)፣ የሰላም አስከባሪ ሠራዊት ዋነኛ አሳታፊ፣ በአገር ውስጥም አንፃራዊ ሰላምና የተረጋጋ ሁኔታ ያለባት ተደርጋ እየተወሰደች ነው፡፡ በአትሌቲክሱ መስክ ስሟ ተደጋግሞ መጠራቱ፣ ቡናና አበባን የመሳሰሉ ልዩ የኤክስፖርት ምርቶች መጠናከርና የታሪክና የብዙኃንነት ገጽታዋ የቱሪስት መስህብ የመሆናቸው ዕድልም፣ ገጽታዋን በመቀየር ረገድ ዓይነተኛ ሚና በመጫወት ላይ ናቸው፡፡

ለእነዚህና ሌሎች ተስፋ ሰጪ ስኬቶች የዓለም ነባራዊ ሁኔታና የአጋር አካላት መብዛት ወይም ሉላዊነት (Globalization) የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ብቻ አመስግኖ ማለፍ አይቻልም፡፡ ይልቁንም ባለፉት 25 ዓመታት አገሪቷን የመራው ኢሕአዴግና በእርሱ የሚመራው መንግሥት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም አሠራር፣ አደረጃጀትና አመራር ከፍተኛውን ሚና እንደተጫወቱ መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡ ሕዝቡ ራሱም የተፈጠረለትን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እጁን አጣጥፎ ከመቀመጥና ተስፋ ከመቁረጥ በመውጣት ያደረገው ርብርብ በቀላሉ አይታይም፡፡

ይህ ሁሉ ሆኖ ሲያበቃ ግን የኢሕአዴግና የመንግሥቱ ዋነኛ ፈተናዎች እንደሆኑ የቀጠሉት የተሟላ ዴሞክራሲንና የጠነከረ መልካም አስተዳደርን የማስፈን ጉዳዮች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጋር የተያያዙት የግልጽነትና ተጠያቂነት መጥፋት፣ የሙስና ማቆጥቆጥ፣ የቡድንተኝነት ፈተናዎች፣ የትምክህትም ሆነ የጠባብነት ልክፍቶች ሥርዓቱን ወደ ብልሸት ይመሩታል የሚል ሥጋት አለ፡፡

ብዙ ጊዜ እንደሚባለው የኢሕአዴግ አብዛኛው ነባር አመራርና አባል ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የታገለና ከብሔር ጭቆና ነፃ ለመውጣት የተፋለመ ብቻ ሳይሆን፣ የገዥዎችን የተዛባ አገዛዝ ለማስወገድ ዋጋ የከፈለ ነው፡፡ ስለሆነም ለታገለባቸው ጉዳዮች መስተካከልና ለዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ በዋናነት ዘብ መቆም ያለበት ይኼው አካል ነው፡፡ በእርግጥም ብዙዎቹ የከፍተኛ አመራሩ አካላት ይኼንን አስተሳሰብ ሊይዙ እንደሚችሉ መገመት ጤናማነት ነው፡፡ ግን ‹‹ምን ዓይነት ዴሞክራሲ?!›› የሚለው ጥያቄ በግልጽና በማያሻማ መንገድ ካልተመለሰ ሲያወዛግብ መቆየቱ አይቀርም፡፡

ገዥው ፓርቲ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ልማታዊ ዴሞክራሲ በኋላም የህዳሴው መስመር የሚለው ከኒዮ ሊብራሊዝም የተለየ ግራ ዘመም ፖለቲካን አዋጭ ነው ብሎ ከያዘ ሰነባብቷል፡፡ ይህንኑ የፖለቲካ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ ‹አስመሳይ ዴሞክራሲ፣ ሶሻሊስታዊ ባህሪ የሚበዛበት፣ የተሞላ ዴሞክራሲን ለማስፈን የሚያስቸግር›› እንደሆነ የሚገልጹ አሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በራሱ በኢሕአዴግ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የታገሉና አሁን የተነጠሉ ወገኖች ‹‹ኢሕአዴግ ዴሞክራት አልነበረም፣ አይደለም…›› ሲሉ፣ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት፣ የአንዳንዶች ፈላጭ ቆራጭነትን፣ እስካሁን ኅብረ ብሔራዊ ጠንካራ ድርጅት ሆኖ አለመውጣቱን…›› የጠላት ወዳጅ ፖለቲካዊ ጉዞውን በመምዘዝ ሲተቹ ይታያሉ፡፡ ገዥ መደብ ያፈረሰ ፓርቲ በየአካባቢው ሌሎች ‹‹ገዥ መደቦች››ን እየቀፈቀፈ መጥቷል የሚሉ መከራከሪያዎች ይደመጣሉ፡፡

በዚህ ጽሑፍ ላይ ማተኮር የተፈለገው ግን የኢሕአዴግን ዴሞክራሲያዊ ጥረትና የመልካም አስተዳደር መስፈን ትግል እያንሻፈፈው ያለውን የበታች መንግሥታዊ ድርጅታዊ አካል ችግሮች ማሳየት ነው፡፡ ከዚህ ተነስቶም ራሱ ግንባሩ አሊያም ሌሎች አገር ወዳድ አካላት ሕዝቡን ያሳተፈ መፍትሔ እንዲያቀጣጥሉ የውይይት መነሻን ማንፀባረቅም ነው፡፡ አንባቢያን የመሰላቸውን አቋም የመያዝ መብታቸውን ግን ለመጋፋት አልሻም፡፡

ተደጋጋሚ ወሬና ንግግር ተግባርን ያዘገያል

ቭላድሚር ኢሊች ሌኒን ከሚጠቀሱለት ንግግሮች አንዱ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹እስካሁን ብዙ ንግግር፣ ውይይት፣ ቧልትና ወሬ አድርገናል፡፡ ከዚህ በኋላ ፈጥነን ወደ ተግባር እንግባ!›› ጠንካራው ኮሚኒስታዊ መሪ ይህን ያለው ወዶ አይደለም፡፡ ይልቁንም ልክ አሁን እንደ አገር እንደተደቀነብን ያለ ሁሉም የአጠቃላዩን ስኬት ብቻ እያደመቀ ማውራት፣ መለፍለፍ፣ የመድረክ አንደኛና ሀቀኛ መሆን ሲበዛና በተግባር መቆራረጥ ሞዴል መሆን የሚችል ሲጠፋበት ነው፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ሁኔታ በተለይ በከተሞች መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ ለምን አልተቻለም?›› ብሎ በድፍረት መጠይቅ ያስፈልጋል፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ በሚመራው ሲቪል ሰርቪስ አንስቶ እስከ ቀበሌ ባሉ የቅሬታ ሰሚና መልካም አስተዳደር ተቋማት ዕውን የአገልጋይነት ቁርጠኛ መንፈስ አለን? ሌላው ቀርቶ ሕዝብ መረጃም ሆነ አገልግሎት የመጠየቅ መብትና ሥልጣን እንዳለው ተረድቶ የሚተገብረው ስንቱ ነው?

ቀደም ባሉት ዓመታት በቢፒአር፣ በቢኤስሲ ወይም በሲቪል ሰርቪስና በፍትሕ ማሻሻያ ሥራዎች በከፍተኛ በጀትና ድካም ግንዛቤ እንዲያዝባቸው ተደርጓል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ መሻሻል የታየባቸው ተግባራትም ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በመረጃ አያያዝ፣ በሲቪል ሰርቪሱ ተደራሽነትና ማብቃት የመጡ መሻሻሎች አሉ፡፡ በብዙዎቹ መሥሪያ ቤቶች የሰው ኃይል፣ የግብዓትና የአሠራር ሥርዓትን ለማሳደግ የተደረገው ጥረትም ፍሬ አላፈራም ሊባል አይችልም፡፡

የተጻፉ መፈክሮች፣ የተደረጉ ስብሰባዎችና ንግግሮችን ያህል ውጤቱ የሚያኩራራ አይደለም፡፡ የፈሰሰውን በጀትም ሆነ የመንግሥት ትኩረትና ድካም የሚመጥን የሕዝብ እርካታም አልተገኘም፡፡ ይኼ ሲባል ከመሬት በመነሳትና በመላምት አይደለም፡፡ ተጨባጩ እውነት ስለሚናገር ነው፡፡

በዘርፉ የተለያዩ  ጥናትን በማድረግ የሚታወቁ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህር እንደሚሉት፣ ‹‹የእኛ አገር የመልካም አስተዳደር ዋነኛ ችግር የአብዛኛው ሲቪል ሰርቫንትም ሆነ አመራር አባል ቁርጠኝነት ዝቅተኛ መሆን ነው፡፡ ከሁሉ በላይ በቅንነትና በታማኝነት ሕዝብ ማገልገል የሚሰጠውን ክብርና ሞራላዊ ልዕልና ለማጣጣም የሚመኘው ሰው ቁጥር ዝቅተኛ ነው፡፡››

ምሁሩ ለዚህ ደግሞ ዋነኛ መንስዔ ነው የሚሉት በማኅበረሰቡ ውስጥ ለዘመናት የበላይነት ይዞ የኖረው አመለካከት ‹‹ሲሾም ያልበላ…›› በመሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም በታማኝነት ሠርቶና በቅንነት አገልግሎ ሕይወቱን ከሚቀይረው ይልቅ ተብለጥልጦና በአቋራጭ (በእጅ መንሻ) እየሠራ የሚበለፅግና የሚሾም በመብዛቱ ነው፡፡ በራሱ በድርጅቱም ውስጥ ቢሆን እያደር የአድርባይነት፣ የመሸካከምና እከክልኝ ልከክልህ እየበረታ እንደመጣ በየግምገማ መድረኩ ተደምጧል፡፡ ግን አመርቂ የእርምት ዕርምጃ ሊወሰድ አልቻለም፡፡

ተሿሚዎችም ሆኑ ተቀጣሪዎች የፖለቲካ እምነትና የጠራ አመለካከት መያዛቸው ተገቢ ቢሆንም፣ ዕውቀትና ክህሎት ሊኖራቸው ግድ መሆን አለበት፡፡ ዓለምም ሆነ አገሪቱ በፈጣን የለውጥ ምኅዳር ውስጥ መግባታቸው እየታወቀ፣ በትናንት በሬ ለማረስ መመኘት የሚሆን አይደለም፡፡ ስለዚህ ሌኒን እንዳለው እስካሁን በተሳካውም ባልተሳካውም ጉዳይ ብዙ ተወርቷል፣ ስንት ነገር ተነግሯል፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ወደ ቁርጠኛ ተግባር መግባት ግድ ይላል፡፡

የታችኛው የኢሕአዴግ አመራር ዴሞክራሲያዊነትን አልዘነጋውም?

የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከአንድም በላይ በሆነ ትውልድ ቅብብሎሽ ሊገነባ እንደሚችል ብዙ ነጋሪ አያሻውም፡፡ ይኼ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌላውም ዓለም ቢሆን ያለና የሚኖር ነው፡፡ ይኼን ተጨባጭ ሀቅ በሚታሰበው ጊዜ ዕውን ለማድረግ ግን ከወዲሁ ሥራ መሥራት ግድ ይላል፡፡

በእኛ አገር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አመቺ የሆነ ሕገ መንግሥት መውጣቱ አንድ ዕርምጃ ነው፡፡ አፈጻጸሙ ላይ ግን ከላይና ከታች የመንግሥት መዋቅር አንፃር ሲመዘን፣ የሁለት መንግሥታት ሕገ መንግሥት መምሰሉ በይፋ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡

ለዚህ እንደ አብነት የሚጠቀሰው በአገሪቱ የመደራጀትና ያመኑበትን የፖለቲካ እምነት የማራመድ መብት ጉዳይ ነው፡፡ በላይኛው የመንግሥት ኃላፊዎች ዘንድ የፖለቲካ ተፎካካሪነት ሰላማዊና ሕጋዊ መንገድን ይከተል እንጂ ኃጢያት አይደለም፡፡ በአንፃሩም ቢሆን ከኢሕአዴግ ኃላፊዎች ጋር የመነጋገር ዕድልም አለው፡፡ ወደ ታችኛው እርከን እየተወረደ ሲሄድ ግን ሁኔታው ይቀየራል፡፡ ‹‹በሌላ የፖለቲካ ፓርቲ (ተቃዋሚ) ሥር ተደራጅቶ ዴሞክራሲያዊ መብትን ለመተግበር መሞከር በጠላትነት ያስፈርጃል፤›› ይላሉ አንድ ታዛቢ፡፡ ገዥው ፓርቲ አገር እየመራ ያለ አካል በመሆኑ በንግድ፣ በግብርና በታክስ፣ በገጠር የማዳበሪያና የግብዓት አቅርቦት ጫናን በመሸሽ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን ለመደገፍም ሆነ ለማረምና ለመተቸት ራሱን የሚያሳምን ሰው ቁጥር እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡

‹‹እንደ አገር የሕግ የበላይነት እያደገ መሄድ ሲገባው አሁንም የአስፈጻሚው ጫና የሕግ ተርጓሚው ላይ በመኖሩ የመደራጀትና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ጥቅምን በማስከበር ረገድ ተከራክሮ መርታት እየከበደ ነው፤›› ያሉኝ ደግሞ በመኢአድ ውስጥ በረጅም ጊዜ በአባልነትና በአመራርነት የቆዩ ፖለቲከኛ ናቸው፡፡ ይኼም በመሆኑ በሕጋዊ መንገድ የተቋቋሙ ፓርቲዎች በየክልሉ ጽሕፈት ቤት መክፈትም ሆነ መደራጀት አልቻሉም፡፡ ለመንቀሳቀስ ቢፈቀድላቸውም ለምርጫ ሰሞን ብቻ እየሆነ ነው፡፡

ሌላው የአገሪቱን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሸራፋ እንዲሆን እያደረገው ያለ እውነት በክልሎች በተለይ በወረዳዎች ያለው የፖለቲካ አመራር፣ ‹‹ኢሕአዴግ ወይም ሞት›› አስተሳሰብ ነው፡፡ ባለፈው ምርጫ ወቅት በአንዳንድ ቦታዎች እንደታየው ሕዝቡ ፈቀደም አልፈቀደም በወረዳችን ማሸነፍ ያለበት ኢሕአዴግ ብቻ ነው ብለው የተንቀሳቀሱ የሥራ ኃላፊዎች መታየታቸው ይወሳል፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ያጎናፀፈውን መብት ማንም መንጠቅ እንደማይችል ነው፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ችግር የሚፈጥሩ ሲያጋጥሙ የማረቅ ኃላፊነት የማን ነው? ይኼ በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ዴሞክራሲያዊነት ሲደበዝዝ ግልጽነትና ተጠያቂነት ይንበረከካል

ሰላማችን ያኮራናል፡፡ ልማታችን ያለጥርጥር እየተጠናከረ ነው፡፡ በዴሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ጉዳይ ላይ ግን ሥራ ይቀረናል፡፡ መንግሥትና የላይኛው አመራር ‹‹ሮም በአንድ ጀንበር አልተገነባችም ዴሞክራሲም እንደዚያው ስለሆነ በሒደት እንጃ በአንድ ጊዜ አይመጣም፤›› ሲሉ ይደመጣል፡፡ ይኼ ማለት ግን በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ሊጣሱ እንደማይገባ በማሳሰብ፡፡

ይሁንና ከላይ እስከ ታችኛው የመንግሥት መዋቅርም ሆነ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ባለው መንግሥታዊ እርከንና ማኅበረሰብ ውስጥ ጉድለቶችን መፈተሽ ይገባል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የዜጎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝ፣ በፀጥታ ኃይሎች መደብደብና አለፍ ሲልም በምርመራ ወቅት ጫና መደረግ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ይኼ ችግር በአንዳንድ ማረሚያ ቤቶች መፈጸሙንም ፍርድ ቤት በችሎት ላይ ተጠርጣሪዎች አቤቱታ ሲያሰሙ አዳምጠናል፡፡

በዳኝነት አካሉ፣ በፖሊስና በትራፊክ ፖሊስ የምርመራና ውሳኔ ሒደቶች ላይ ሙስና፣ መድልኦና የተዛባ ፍርድ ላለመሰጠቱ እንዴት እየተረጋገጠ ነው ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው፡፡ መንግሥት የፍትሕ ሴክተሩን ተደራሽነት ለማስፋት እሠራለሁ የሚለውን ያህል በሥነ ምግባርና ሞራል የተነሳ፣ ለሕግ የበላይነት ቁርጠኝነት እየተጋ ያለ ‹‹የፍትሕና የፀጥታ ሠራዊት›› (በኢሕአዴግ ቋንቋ) ገንብቷልን?

ይኼን ጥያቄ እንድናነሳ የሚያስገድደው የአንዳንድ ወገኖቻችን ደመወዝ እንደማናውቀው ሁሉ ባለሕንፃ፣ የሚከራዩ ሁለት ሦስት አራት ተሽከርካሪዎች ባለቤቶች፣ የቪላና የሆቴል ቤቶች ባለንብረቶች ያደረጋቸው ምንድነው ስንል ነው፡፡ በመንግሥት ሹመትና ‹‹ጥቅም›› የሚያስገኝ ሙያ ላይ ከአሥር ዓመታት ያነሰ አገልግሎት ያላቸው ባለሕንፃዎች፣ ባለግዙፍ ቪላ ባለቤቶች፣ የተሽከርካሪዎችና ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ባለቤቶች አልተፈጠሩምን? ሌላው ቀርቶ በዝምድና፣ በአገር ልጅነትና በቅርበት ስም ስንቶች ሕገወጥ ደላሎችና ‹‹ጉዳይ ገዳይ›› ሆነዋል? ይኼ ከሕዝቡ ያልተሰወረ ሀቅ ቢሆንም የግልጽነትና የተጠያቂነት ሥርዓቱ መዳከም ‹‹ተከድኖ ይብሰል›› የሚል እንዲበዛ አድርጎታል፡፡

በአንድ ወቅት የመንግሥት ልሳን የሆነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የፀረ ሙስና ኮሚሽንን ሀብት የማሳወቅና ይፋ የማድረግ ሕገ ደንብ ለምን አይተገበርም ሲል በአጽንኦት ጠይቋል፡፡ የጠቀሳቸው የመረጃ ምንጮች (ምሁራንና የሕግ አዋቂዎች) ብቻ ሳይሆኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ጉዳዩ ከንክኖት በቀናት ውስጥ መወያያ አጀንዳም አድርጎታል፡፡ ነገር ግን ኮሚሽኑ ወደኋላ የተመለሰ መስሎ ‹‹የተሿሚዎችን ሀብት መዝግበን ሲፈለግ ወይም የጠየቀ ሕጋዊ አካል ሲቀርብ መረጃ መስጠት እንጂ ለሕዝብ ይፋ የማድረግ ግዴታ የለብንም፤›› ሲል የግልጽነት መርሁን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል፡፡

እንግዲህ የዴሞክራሲ ሥርዓት መደብዘዝን እንደ ጉዳት መቁጠር የሚያስፈልገው የመልካም አስተዳደር ግንባታውንም ስለሚሰነክለው ነው፡፡ በሠለጠነ ማኀበረሰብ ግንባታም ሆነ በዴሞክራሲ አስተሳሰብ ማነፅና የቀደመውን ኋላቀር አስተሳሰብ የመናድ ተግባር ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚያክሉ ጠንካራ መልሶች የሉም፡፡ ለእነዚህ ቁልፍ ጉዳዮች ዘብ የማይቆም መንግሥት ደግሞ ሄዶ ሄዶ የወደቁትን ዓይነት ቀን ነው የሚጠብቀው፡፡ ስለሆነም ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታና ለዜጎች ነፃነት ደጋግመን ማሰብ ያስፈልጋል መባል አለበት፡፡

በአገራችን በቅርቡ ተከስቶ የነበረው ሕዝባዊ አመፅ ይኼ ሁሉ ብሶት የወለደው እንደነበር መርሳት ተላላነት ነው፡፡ ያ ሁሉ ሕዝብ ሞቶ፣ ቆስሎና የአገሪቱ አንጡራ ሀብት ወድሞ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜያዊ እፎይታ ቢገኝም፣ እያመረቀዙ ያሉ ችግሮች ዘለቄታዊ መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› እንዲሉ፣ በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ያየናቸው ችግሮች አዙሪት ሆነው ሊቀጥሉ ይችላሉ፡፡ በተቻለ መጠን ዓይንንና ልቦናን መክፈት ተገቢ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...