Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች እጃቸው ከምን?

ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች እጃቸው ከምን?

ቀን:

በቶላ ሊካሳ

በተጠቃለለችውና ጥቂት የኢንዱስትሪና የፋይናንስ ኮርፖሬሽኖች በተንሰራፉባት የዛሬዋ ዓለም ውስጥ የሚያንገላቱን የልማት፣ የነፃነትና የሰላም መሰናክሎችና መፍትሔዎቻቸው እንኳን በብሔረሰብ ደረጃ፣ በአገር ደረጃም የማይገባደዱ (አገር አለፍ ትብብርና የጋራ እንቅስቃሴ የሚሹ) ሆነዋል፡፡ ይህ በጊዜያት ውስጥ የተጠራቀመ የእውነታ መቀየር “ሉዓላዊ አገር ነኝ፤” “ሉዓላዊ መብቴ ተጣሰ”፣ . . . የሚሉ ጩኸቶችን የቂል ጩኸት አድርጓቸዋል፡፡ “የራስን ዕድል በራስ መወሰን” የሚባልን ነገር አሮጌ ህልም አድርጎታል፡፡

ከዚህ ዓለማዊ ጉዞ ኢትዮጵያ የማታመልጥ ቢሆንም ሕዝቦቿ ግን አንድ አገራዊ ልብና ክንድ ሆነው በዴሞክራሲ ዙሪያ ማበርና መንቀሳቀስ ገና ፈተናቸው እንደሆነ ነው፡፡ ልማትን በክፍለ አኅጉራዊ አካባቢ ደረጃ ማቀድና ማስኬድ አስፈላጊ በሆነበት ዘመን ውስጥ፣ የአዲስ አበባንና የወሰንተኞቿን ጅምር ከተሞች ልማት እንኳ አንድ ላይ ማቀናበር ችግር ሆኗል፡፡ ለዚህ ድክመት ኢሕአዴግ ያመጣው ሸንካፋ ለውጥ ብዙ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የኢሕአዴግ ‹‹የአዲስ አገር ግንባታ፤›› በኢትዮጵያ የተማከለ ገዥነት ታሪክ ውስጥ፣ እንደ ሥርዓት የዘለቀውን ሰሜን ገብ (የአማራ፣ ትግሬ) የበላይ ገዥነትን እንኳ አጠናቆ መበጠስ ያልቻለ ነበር፡፡ የተለወጠው ነገር ደርግ በአያሌው አሮጌዎቹን መሳፍንትና መኳንንት መንቅሮ የወታደራዊ ቢሮክራሲ መኳንንቶች የደረተበትን አገዛዝ፣ ኢሕአዴግ እስከ አውታራቱ ጠልቆ አፈራረሰና “ኢትዮጵያዊነት በውዴታ/በመፈቃቀድ”፣ “የብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል”፣ “የብሔረሰቦች የራስን ዕድል በራስ መወሰን” … በሚሉ ሐረጎች ያሸበረቀና በዚህ ሽብርቅና በኅብረ ብሔራዊ ገላ ውስጥ የተሰወረ ብሔረሰባዊ የቡድን ትርታ ያለው ፌዴራላዊ አገዛዝ አቋቋመ፡፡ በዚህ አገዛዝ ውስጥ የተሰወረውን የበላይ ገዥነት ምርጫ አያናጋውም፣ ካቢኔ ላይ የሚደረግ ለውጥ አይረብሸውም፡፡

በማይረብሸው ፌዴራላዊ የበላይ ገዥነት ጉያ ውስጥ ደግሞ በብሔረሰባዊ ማንነቶችና የማንነት ምድሮች ላይ የተጣበቡ፣ ዜጎችን “ባለቤት” እና “መጤ” ብሎ መለያየትንና ማዳላትን እውቀትና መብት ያደረጉ ገዥነቶችን አረባ፡፡ ቡድናዊው የበላይ ገዢነትና የግለሰቦች እብሪት ያላግባብና ያለበደሉ በትግራዊ ብሔር ላይ የጠለሸ ስሜት እንዳስከተለ ሁሉ አካባቢያዊ ገዥነቶችም የንቁሪያ፣ የአሸማቃቂና የተሸማቃቂ፣ የፈንቃይና የተፈንቃይ ግንኙነቶች መፈልፈያ ሆኑ፡፡ መሬት ቀረኝ እያሉ ለ‹‹ማንነት›› ምድር መንገብገብና የደም መስዋዕትነት መክፈልም ለሉዓላዊ አገር ከመዋደቅ ጋር የማይተናነስ ሆኖ ህሊናን ሊያሰክር ቻለ፡፡ እሳት የሚወልዱ እነዚህ ድፍርስርስ ግንኙነቶች መቀጠላቸው ለገዢው ኢሕአዴግም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ህልውና ወዮልን የሚያሰኝ ነው፡፡ ይህ “ወዮልን” ጨለምተኛ አዕምሮ የወለደው ወይም “ምፅአት ደረሰ” የሚል አስፈራሪ ስብከት አይደለም፡፡ የኮረብታውን ንዝረትና የግለት ጭሰት ከርቀት እያስተዋሉ ወደፊት ሊከሰት የሚችለውን የገሞራ ፍንዳታ የመተንበይን ያህል ለእውነት ቅርብ የሆነ ሥጋት ነው፡፡ እስከ 2009 ዓ.ም. መባቻ ድረስ የተሻገረው የአንድ ዓመት ቅዋሜና የመንግሥት አያያዝም ለዚህ ሥጋት ዕውናዊነት በቂ ምስክር ነው፡፡

የጥያቄዎችና የቅዋሜዎች መንግሥታዊ አያያዝ ምን ይመስላል?

ስለአገሪቱ እውነታ ኢሕአዴግ ለሕዝብ ሊያስጨብጥ የሚፈልገው ሥዕልና ብዙ ሰው የጨበጠው ሥዕል ለየቅል ነው፡፡ ኢሕአዴግ በልማታዊ መንገድ ሕዝብን እየመራሁ ከድህነትና ከኢፍትሐዊነት እያወጣሁ ነው ሲል፣ “ድንቄም! እንዲህ እያላችሁ ጊዜ እስኪያልፍ ጋጡ!” እያለ የሚተክን አያሌ ነው፡፡ ኢሕአዴግ “የመልካም አስተዳደርን” ዕጦት በሕዝብ አገልግሎትና አስተዳደር ውስጥ ያሉና በእሱ አገዛዝ ውስጥ ሊወገዱ የሚችሉ ችግሮች መሆናቸውን ለማሳመን ሲጥር፣ በብዙ ሰዎች ዘንድ ደግሞ “የመልካም አስተዳደር ችግር መድረሻ አሳጣን!” ባይነት በአገልግሎት አሰጣጥ ውስጥ ያሉ በደሎችን ብቻ ሳይሆን፣ በአገዛዙና በገዢዎች ላይ ያለ ቅዋሜንም አድበስብሶ መግለጫ ነው፡፡

ከሕዝብ የፈለቁት የቅማንት፣ የኮንሶ፣ የወልቃይት፣ የወለኔ፣ . . .  ወዘተ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ኢሕአዴግ     ማንነትን ከተረጎመበትና አዕምሮን ካሰሰበት የፖለቲካ “ፍልስፍና” እና ከአዋቀረው አገዛዝ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ኢሕአዴግ እስከ ዛሬ አልተረዳም፡፡ በ2009 ዓ.ም. መስከረም ማለቂያ ላይ በጌዴኦ ምድር ተገኝተው ሀብት ላፈሩ መጤዎች እንደምን የመሬት ክርክር ይፈረድላቸዋል (እንደምን ሕጉ ለጌዴኦ ሳያደላ ቀረ?) በሚል አስተሳሳብ ተቀጣጥሎ ደም ያፋሰሰውና ብዙ ንብረት ያወደመው (የአካባቢ ፖሊስ ኃይል እንኳ ሀይ ያላለው) ጥቃትም፣ የሥርዓቱን ውስጣዊ ችግር የሚያሳይ ሌላ ፈርጅ ነው፡፡ አረሳስተው ሲቀብሩት አልረሳ ብሎ ኖሮ ኖሮ ቱግ ያለው የወልቃይት ጉዳይም ሕዝብ አብላልቶ ሳይመክርበትና ሳይፈቅደው የተዘረጋ የአስተዳደር መዋቅር የፈጠረውና ያለአዲስ ዕይታ የማይመክን፣ አሁን ባለው ሁኔታ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ በማድረግ የማይገላገሉት፣ የኢሕአዴግ የሥልጣን ዕድሜ አሁን ባለ ዘይቤው ቢረዝምም የማይጠፋ አደገኛ ፈንጂ ነው፡፡ ዙሪያ ከተሞችን ያቀፈ የአዲስ አበባ የልማት ዕቅድን በመቃረን በ2006 ዓ.ም. ተነስቶ የነበረው የኦሮሞ ቅዋሜ አሸልቦ ቆይቶ በ2008 ዓ.ም. ኅዳር እንደገና ያገረሸውና ብዙ ሥፍራዎችን እያዳረሰ ለወራት የቀጠለው፣ ጥር መግቢያ ላይ ኦሕዴድ ስለኦሮሞ የሉዓላዊነት ውሳኔ እያወራ ፕሮጀክቱ መታጠፉን ቢለፈፍም ቅዋሜው በመብረድ ፋንታ ብሶበት ያረፈው፣ የመነሻው ቅዋሜ የሌላ ትልቅ ቅዋሜ (የፀረ ኦሕዴድ ኢሕአዴግ ቅዋሜ) ልጥ ስለነበረ ነበር፡፡ ሌሎች አካባቢ ነክ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች አነሰም በዛ እርስ በርስ እየተያያዙ በአጠቃላዩ አገዛዝ ላይ ማፍጠጥ ችለው የነበረው በሁሉም ውስጥ አፈናና እብሪት በቃን የሚል ይዘት ስለነበር ነበር፡፡

ይኼን መሳዩን የሥርዓቱን ችግር በትክክል አስተውሎ ከሕዝብና ከዴሞክራሲ ወገኖች ጋር መፍትሔ በመፈለግ ፋንታ፣ ብቅ ያለ ቅዋሜን ሁሉ ከፀረ ሰላምነትና ከፅንፈኛነት ጋር እያያያዙና በድቆሳ ለማሸነፍ አገዛዙ እንደለመደው ያካሄደው ግትር መንገታገት የቅዋሜ መስፋፊያና ለራሱም መዋረጃ ሆኖ አርፏል፡፡

በቅዋሜ ምክንያት የፈተና ዝግጅት ካላሟሉ አካባቢዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት የሚያስገባው (የ12ኛ ክፍል) የፈተና ጊዜ ይራዘም የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ ለዚህ ጥያቄም ሆነ “ፈተናው ተሰርቋል” ለሚል ወሬ ጆሮ ያልሰጠው መንግሥት፣ ባቀደው ቀን (ግንቦት 22 ቀን 2008 ዓ.ም.) እሽግ አስከፍቶ የፈተና ሒደት ሲያስጀምር ፈተናዎቹ በዋዜማው በስልክ አማካይነት ከተሠራጩት ጋር አንድ መሆናቸው ይታያል፡፡ እናም በፊት መንግሥት ፈተና የማራዘም ጥያቄን ተቀብሎ ቢሆን ኖሮ በቅን አሳቢነት ሊተረጎምለት ይችል የነበረው ጉዳይ ወደ ቅሌትነት ተቀይሮ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ይኼ ልምድ የተተነፈሰች አታመልጠውም የሚል ዝና አበጅቶ ለኖረው የአገዛዙ የመረጃ መረብ የማይረሳ ምት ነበር፡፡ በዚሁ ምክንያትም ሁለተኛው የፈተና ጊዜ ደርሶ እስኪካሄድ ድረስ በሕዝብም ሆነ በተፈታኞች ዘንድ ፈተናው ከስርቆት ስለመጠበቁ ከፍተኛ ጥርጣሬ ነበር፡፡

በ2008 ዓ.ም. የክረምት ጊዜ የቅዋሜ ማዕበል ከአገዛዙ አያያዝ ነዳጅ እያገኘ የተጋጋለበት፣ የመንግሥትም የመቆጣጠር አቅም ያጠራጠረበት ወቅት ነበር፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ የኮንሶ ቤቶች ቃጠሎ፣ የቂሊንጦ እስር ቤት ቃጠሎ፣ የጎንደር ቅዳሜ ገበያ ቃጠሎ፣ . . . በዚሁ ጊዜ የታዩ ማፈሪያ ቅርሶች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ሁሉ በበለጠ ግን መንግሥትን በማራድም ሆነ አስተዋይነት የጎደለው ዕርምጃ ምን ያህል መዘዘኛ ሊሆን እንደሚችል በማሳየት ረገድ፣ የመስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. የኢሬቻ በዓልን አሳዛኝ ክስተት የሚስተካከለው አልነበረም፡፡

በበዓሉ ሰሞን ኢሬቻን ዩኔስኮ በቅርስነት እንዲመዘግበው እየተደረገ ስለነበረው ጥረት መራገቡና ዕለተ ዋዜማው በሩጫ ውድድር መድመቁ በኢሕአዴግ ኦሕዴድ ገዢነት ላይ ያሻቀበውን የዓይንህ ላፈር ቅዋሜ የማርገብ ሙከራዎች ነበሩ፡፡ ልዩ ልዩ የሕዝብ በዓላትን ለመንግሥታዊ ድጋፍ መነገጃነት መጠቀም አዲስ ባይሆንም፣ በ2009 ዓ.ም. መስከረም እየገረረ የመጣው ተቃውሞ ግን ይኼን እንዳላየ ለማሳለፍ የፈቀደ አልነበረም፡፡ የመንግሥትን የፖለቲካ ንግድ በማክሸፍ ብቻ ሳይወሰን የኢሬቻ ዋዜማ ምሽትን እስከ ዕለተ ቀኑ ድረስ በቅዋሜ መድረክነት ተቆጣጥሮት ነበር፡፡ ባህላዊውና እምነታዊው የኢሬቻ ክብረ በዓል ከየትኛውም የፖለቲካ ጫና ነፃ ሆኖ እንዳይካሄድ ያደረገው የመንግሥትና የተቃዋሚ እኔ አተርፍ እኔ አተርፍ ትንቅንቅ መሆኑ ባያጠያይቅም፣ ወጣቶችና አገር የሚመራ መንግሥት የሚኖራቸው የኃላፊነትና የተጠያቂነት ድርሻ ሰማይና መሬት ነው፡፡ የሰላማዊ ሠልፍ መብት በተኮላሸበት ሁኔታ ላይ ቆሞ፣ ተቃዋሚዎች የበዓሉን አጋጣሚ ለምን ተጠቀሙበት ብሎ መፍረድ ህሊናን ይተናነቃል፡፡

እንደዚያም ሆኖ ክብረ በዓሉ ወደ ሚካሄድበት የሆራ ሥፍራ ሰው እየተፈተሸ ማለፉ፣ በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት የነበሩት ፖሊሶች መሣሪያ አለመያዛቸውና በታጋሽነት መሞላታቸው የትንኮሳ ሰበብ ላለመሆን በፀጥታ ኃይሉ በኩል ዝግጁነት እንደነበር ያሳየ ነው፡፡ የቅዋሜ ሁካታውን በሀይ ሀይታ አስቁሞ ሥነ ሥርዓቱን ማጠናቀቅ እንደማይቻል ለማንም ግልጽ ከሆነ በኋላም፣ የሐይቁን ዳርቻ ጠባብነትና የሰውን ብዛት ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ፣ በአስለቃሽ ጋዝ ተቃውሞን መበተንና እንደገና በዓሉን ማስቀጠልም የሚቻል እንደማይሆን አጢኖ ማቋረጥና ሕዝብ ከሥፍራው እስኪለቅ መጠበቅ ኃላፊነት የሚሰማው ተግባር ነበር፡፡ ይህ ተደርጎ ቢሆን ኖሮም ከተቃዋሚዎቹ ይበልጥ የፖለቲካ ትርፍ ለመንግሥት ባስገኘለት ነበር፡፡ ይኼን አዙሮ ማየት ከብዶ ወይም ለተቃውሞ አልሸነፍ ባይ እልህ ያንን ሁሉ ትዕግሥት ገደል ሰዶ አስለቃሽ ጋዝ ይተኮሳል፡፡ ተኩሱ የፈጠረው ድንጋጤና የሽሽት መጋፋትም ዘግናኝ አደጋ ይወልዳል፡፡ ከዚያ በኋላ እየጮሁ ለማረጋጋትና ሰው ለማትረፍ ቢራወጡት፣ ብዙ ሕዝብ ባለበት ገደላማ የሐይቅ ዳርቻ ሥፍራ የከፋ አደጋና እየዬ መድረሱ የት ሊቀር!

በገልለተኛ የመረጃ ምንጭ ችግር የጉዳቱን መጠን በቁጥር መግለጽ ባይቻልም፣ ሰቅጣጭ ጉዳት ለመድረሱ ግን አንድና ሁለት የለውም፡፡ በዕለቱ ማታ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሰጡት መግለጫ የታየባቸው ክውታ፣ ተቃውሞን ለጉዳቱ ሁሉ ተጠያቂ አድርገው ከፀጥታ ኃይሉ በኩል አስለቃሽ ጢስ መተኮሱን መደበቃቸው፣ የደረሰው ጉዳትና እልቂት ፀረ ኢሕአዴግ ዝልዘላና ማዕበል ለማስነሳት እንደሚውል በመፍራት እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ መረጃ ደብቆ ኃጢያቱን በተቃውሞ ላይ የመደፍደፉ ጥፋት የተፈራውን ከመሆን አላስቀረውም፡፡ በታወቁ የምዕራብ የዜና ማሠራጫዎች ከአስለቃሽ ጭስ ባለፈ የጎማ ጥይት ስለመተኮሱ ተዘግቦ ሳለ፣ አስለቃሽ ጭሱና የተከተለው የሽሽት ትዕይንት በምሥል ተቀርፆ የተላለፈ ሆኖ ሳለ፣ በሪፖርተር ጋዜጣና በአሜሪካ ድምፅ ሬድዮም በኩል አስለቃሽ ጢስ ስለፈጠረው ድንጋጤ የዓይን ምስክር ዘገባ የተሰጠና ይኸውም በወሬ ቅብብል ብዙ ሰዎች ዘንድ መድረሱ አይቀሬ ሆኖ ሳለ፣ የኢሕአዴግ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተቃውሞን ብቸኛ ተጠያቂ አድርጎ መድረቁ፣ ጭራሽ ተቃዋሚዎቹ ድንጋይ ውርወራ ጀምረው ሕዝብ ከድንጋይ ለመሸሽ ሲሞክር አደጋ ደረሰ የሚል ሽምጠጣ ውስጥ መዘፈቁ፣ በዚህም ቅሌቱ ጭራሽ ንዴት እያባዛ የተፈራውን የተቃውሞ ማዕበል ማባባሱን አለማስተዋሉ፣ ገደልና ሜዳንም ማየት እስኪሳነው ድረስ ዞሮበት እንደነበር ያሳየ ነበር፡፡

ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ (እስከ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድረስ) ከፍተኛ ቁጣና እልህ ገንፍሎ በመንግሥታዊና በግል የልማት ሥራዎች ላይ ዘረፋንና ቃጠሎን ያካተተ ልዩ ልዩ ጉዳት ሊደርስ ቻለ፡፡ ለአዲስ አበባ ቅርብ በሆነ አካባቢ ውስጥ እንኳ የረባ የተቋማት ጥበቃ ማድረግ ተስኖ በሰበታ ከተማ ውስጥ 1.2 ቢሊዮን ብር የሚገመት የንብረት ውድመት (መንግሥት ጥቅምት 19 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጠው መረጃ መሠረት) ደረሰ፡፡

ውድመቱ የተፈጸመው በተገተረ ንረብት ላይ ብቻ አልነበረም፡፡ ከአፍሪካ አልፎ የአውሮፓና የአሜሪካ መንግሥታትን ሲያስገርም የቆየው የውስጥ ፀጥታ ተቦተራርፎ አገሪቱ በሚያስፈራ ብሶትና ምሬት መሞላቷ ለዓለም ተጋልጧል፡፡  ኢትዮጵያን ውድ የምሥራቅ አፍሪካ “ሸሪክ” አድርገው ለሚቆጥሯት አውሮፓና አሜሪካም ይኼ ያልተጠበቀ ጉድ በኢሕአዴግ ገዥነት ላይ ብቻ መተማመን እንደማይችሉ ቁርጡን አሳይቷቸዋል፡፡ የጀርመኗ አንገላ መርክልን እያሮጠ አዲስ አበባ ድረስ ያስመጣቸው የአገሪቱ ሰላምነትና አጋርነት ዕድሜ የማግኘቱ ጉዳይ ማሳሰቡ ነበር፡፡ አንገላ መርክል ለኢትዮጵያው ፓርላማ ንግግር ለማድረግ አለመፍቀዳቸውም ያገዛዙን ዴሞክራሲ አልባነት ያሳጣ ውሳኔ እንደሆነ ሁሉ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይል አሠልጥኑልን ባይነት የፀጥታ ኃይሉን ድቆሳ ከአቅም ማነስ የመጣ አስመስሎ አላሳሳተም፡፡ እንዲያውም ’እኔ እንደሆን መሶብ አልከፈትኩም’ ከሚል ዓይነት የልጅ ብልጠት የተሻለ ዋጋ አልነበረውም፡፡

ፋብሪካዎችንና የልማት ተቋማትን ከቃጠሎና ከውድመት ማዳን ቀርቶ፣ የፖሊስ ጣቢያዎችን፣ ጠመንጃዎችና የአስተዳደር ተቋማቱን ከዝርፊያ ለማትረፍ እስኪያቅት ድረስ የአገዛዙ መደንዘዝ፣ መለምለም ጀምሮ በነበረው የቱሪዝም ንግድና የውጭ ኢንቨስትመንት ላይ ድንጋጤና መሸማቀቅ አስከትሏል፡፡ በተወሰኑ አካባቢዎች ውስጥም  የውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት ዕድልን የሚጎዳ ጠባሳ ትቶ አልፏል፡፡ ኢትዮጵያ በአካባቢዋና በአፍሪካ ውስጥ ያላትን የአስታራቂነትና ሰላማዊ መፍትሔ የማፈላለግ ተስሚነትም አዋርዷል፡፡ በቅርቡ መውተርተር ለጀመረች አገር ይኼ ሁሉ ኪሳራ ትልቅ ጉዳት ነው፡፡ ለዚህም አገዛዙም ተቃውሞውም የየራሳቸውን ድርሻ አዋጥተዋል፡፡

  • እሳት ጠፍቷል? በቀድሞው የዶለዶመ ዘይቤስ መግዛት ይቻላል?

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጊዜያዊ ዕረጭታ አስገኝቷል፡፡ ሰላምና መረጋጋት ግን በፍፁም የሉም፡፡ ምክንያቱም በገፍ እያሠሩ ከመስበክና ፀጥ ከማስኘት በቀር ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የምሬት ምክንያቶች ላይ የተደረገ ለውጥ ገና የለምና፡፡ የዕረጭታው ቀፎ ሳይበረቀስ እስከ መቼ እንደሚቆይ እንኳ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ “ሰላምና መረጋጋት ተገኝቷል፣ የሁከትና የብጥብጥ ኃይሎች ከሽብርና ከጠላት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ሕዝብ ለመገንዘብ ችሏል” የሚለው የመንግሥት ፕሮፓጋንዳ ሁሉ ፍርኃት መከለያ ነው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ “ኢሳት” እና “ኦኤም ኤን” የሚባሉ የተቃውሞ ሥርጭቶችን ማድመጥን  እስከ መከልከል መድፈሩ፣ በዚሁም መሠረት በተለይ ከአዲስ አበባ ውጪ አከንባሎ አንቴናንና ሲግናል መሰብሰቢያን እስከ ማስነቀል ድረስ የተጓዘ ዕርምጃ ውስጥ መገባቱ፣ የኢሕአዴግ መንግሥት የውጭ ተቃዋሚዎቹን በፖለቲካ ማሸነፍ እንዳቀተው ብቻ ሳይሆን ክፉኛ እንደፈራቸው፣ የራሱንም ዓለም አቋራጭ ፕሮፓጋንዳ መካንነት ያመነበት ክንዋኔ ነበር፡፡

የማድመጥ መብትን መከልከል ወይም የኢንተርኔት ግንኙነትንና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን መዝጋትና የውጭ ተቃዋሚዎችን ከሕዝብ ለመለያየት አያስችልም፡፡ እንዲያውም የድምፅና  የምሥል መልዕክቶችና ቅስቀሳዎችን መንግሥት ተከታትሎ በማያስቀራቸው ብዙ ቀዳዳዎች እንዲሹለከለኩ የሚገፋና የሚመራ ነው፡፡ ብዙም አስታዋሽ ያልነበራቸውን ጥቂት መጻሕፍት (በቅዋሜ ዓመቱ ውስጥ) ከገበያ ለማውጣት በሻጮች ላይ የተፈጸመ የማሠር ዕርምጃ ጭራሽ መጻሕፍቱ ብዙ ፈላጊ እንዲኖራቸውና በውድ ዋጋ እንዲቸበቸቡ ያደረገ ውጤት አስከትሎ ማየታችን፣ የማድመጥ ክልከላውን የከፋ ውጤት አይቀሬነት የሚደግፍ ነው፡፡

የአሮጌው ኦነግ ሙጣጭ ፖለቲከኞች ግብፆችን ለመጣባት ሲሞክሩ የሚያሳይ ምሥልን፣ ወይንም የኦሮሞ ብሔረተኞች እርስ በርስ ለመቀራረብ ለንደን ላይ ባደረጉት ስብሰባ ውስጥ ከአንድ ወገን የተነገረን “የኦሮሞን ነፃነት የምናገኘው ኢትዮጵያን በመበታተን ነው” ያለ ጃጂያቲያም አስተሳሰብን ለሕዝብ ማቅረብና ይኼንኑ እያናፈሱ የውጭ ተቃዋሚዎችን በሞላ  በበታማኝነት ማጠልሸትም ለኢሕአዴግ ትርፍ አያስገኝለትም፡፡ አዙሮ ማየት የሚችል ከሆነ የዚህ ዓይነቱ ተግባር ለፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አገር ግንባታ የቆሙ ኃይሎች ከፅንፈኞች ተለይተው እንዳይሰባሰቡና የአገሪቱ የፖለቲካ ሰላምና የልማት አቅም እንዳይደራጅ የማወላከፍ፣ ሊታፈርበትና ሀይ ባይ ሊያገኝ የሚገባው ጥፋት ነው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ፕሮፓጋንዳ በዋሾነት ዝና እንደማትረፉ (የቢሾፍቱውን የኢሬቻ አደጋ መንስዔ በመሸምጠጥም የቅርብ ጊዜ ሐውልት እንደማቆሙ) በማጠልሸት የተቃዋሚዎቹን ተሰሚነት አያቆስልም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሰፈነ ማግሥት “አርበኞች ግንቦት ሰባት” እና “የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር” (ሌሎችም) የተሰባሰቡበትና ፌዴራላዊ ዴሞክራሲዊ የጋራ ቤት የመገንባት ዓላማ ያለው “የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ” የሚል ቅንብር መፈጠሩ፣ የውጭ ተቃዋሚዎችን በጅምላ አሸባሪና ፀረ ኢትዮጵያ አድርጎ ለሚሥለው የኢሕአዴግ ፖለቲካ ሌላ መርዶ ነበር፡፡ ልዩነቶች እየጠበቡና ረድፎች እየጠሩ ገና ብዙ ቡድኖች ወደዚህ ንቅናቄ እንደሚሳቡ የኢሕአዴግም መንግሥት ካለፈው የበለጠ ፈተና ወደፊት እንደሚጠብቀው አያጠራጥርም፡፡ ኢሕአዴግም ከሱዳንና ከደቡብ ሱዳን ጋር አጥር የማጠባበቅ ሥራን ሲያኪያሂድ የታየውም ይኼንኑ በመረዳት ነበር፡፡

ወዲህም ተባለ ወዲያ ግን የኢሕአዴግና የተቃዋሚዎቹ ትንንቅ ከሰላማዊና ከሕጋዊ መድረክ ውጪ እስከሆነ ድረስ ለአገሪቱ የፖለቲካ ሰላም ፈተና መሆኑ አይቀርም፡፡ በድርድርና በእርቅ ተቀራርበው በፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ለሕዝቦች አዲስ ሕይወት ሊያበጁ የሚችሉ ወገኖች መቀናደብ ለቡድኖቹም ለአገሪቱም ሕዝቦች በምንም ዓይነት ጥቅማቸው ሊሆን አይችልም፡፡ መቀራረብ የሚቻልበትን መንገድ የመፈለግ ተግባር የሽብርተኛነትና የትርምስ ማጥ ባልደረቀበት አካባቢ ለምትገኝና ከማዶዋ የነ የመንንና የነ ሶሪያን አወዳደቅ እየተመለከተች ላለች አገር ቸል የማይባልበት ነው፡፡

ከዚህ ሌላ ትምክኅትና ጠባብነት ሕዝቦችን አፃርሮ የማቆየት ጉልበታቸው ወላልቋል፡፡ ብሔረሰባዊ ልዩነቶችን ባጠበቁ ማንነቶች ልቦናንና ኑሮን ከታትፎ ከአናት ያለተጋፊ የመግዛት ሥሌትም ለገዢም ሆነ ለሕዝቦች ሰላም የማይበጅ ሆኖ ከሽፏል፡፡ የውስጥ ተቃዋሚን ማዳከም ለኢሕአዴግ ጥንካሬ እንዳልሆነው፣ ከውስጥ ያስቸገሩ ተቃዋሚዎችንና አደባባይ ተናጋሪዎች አስደንብሮ ወደ ውጭ እንዲፈረጥጡ ማድረግም መገላገል እንዳልሆነ፣ ከውጭ ሆኖ መቆሚያ መቀመጫ መንሳት እንደሚቻል ይኸው የቅርብ ልምዳችን ወለል አድርጎ አሳይቷል፡፡ የፖለቲካ ሰላም ላይ ያልተመሠረተና በስነጋ የተገኘ የሕዝብ ፀጥታ ያፈተለከ ቀን ምን ያህል መዝረክረክና ጥፋት ሊያመጣ እንደሚችል፣ የቁጣ መፈንጃ መዘዝ እየሆኑ ያሉት ሕዝብን ያስመረሩ የአገዛዙ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባራት እንደሆኑ መማር ለሚሻ የ2008 እና የ2009 ዓ.ም. የፖለቲካ ቀውስ ልምድ ከበቂ በላይ ነው፡፡

በኮንፈረንስና በሥልጠና ስም ብዙ የሕዝብ ገንዘብ ሲያነክት የቆየውና የኢሕአዴግን ሥልጣን ለኢትዮጵያ ልማትና ሰላም ብቸኛ ቁልፍ ያደረገና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ የብሔሮች እኩልነት ተረጋግጧል/ብሔረሰባዊ የበላይነት ተሰርዟል የሚል ፕሮፓጋንዳ፣ የከሳን ሰው ቦርጭ መቀነስ ይጠቅምሃል ብሎ የማስተማር ያህል ከንቱ ጩኸት ከመሆን አልፎ ቁጣ ሊጭር የሚችል ሆኗልና ሊቆም አለዚያም ሊያስጠይቅ ይገባል፡፡ የቅርቡን የቁጣ ማዕበል ንብረት አውዳሚነት እያነሱ መንቀፍ እንኳ ለኢሕአዴግ መንግሥት የተቆርቋሪነት ብልጫን የሚያቀዳጀው ሳይሆን፣ ከቅዋሜ ፍንዳታ በፊትም ሆነ ከዚያ ወዲያ በነበረ ረዥም ጊዜ ውስጥ ከውድመት የሚያርቅ መፍትሔ ያለመስጠት ጥፋተኝነቱንና በዚህም ለደረሰው ውድመት ተጠያቂነት እንዳለበት የሚያስታውስ ነው፡፡

መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. የተካሄደው ከኢሕአዴግ ግቢ ያልራቀ የካቢኔ ሹምሽርና ሽግሽግም ቢሆን መሠረታዊ የዴሞክራሲ ለውጦች ተከትለውት እስካልመጡ ድረስ፣ እርባናው ገርሮ የነበረ ቅዋሜን ከመደለልና ከካቢኔ ጀርባ ያለ አምባገነናዊ ማጅራትን ከመከለል አያልፍም፡፡ የፓርላማ አወካከልን ሥርዓት ማስፋት ለዴሞክራሲ ግንባታችን የሚበጅና አስፈላጊ ቢሆንም ብቻውን ትንሽ ነገር ነው፡፡ በዋናነት ለከተማና ለገጠር ወጣቶች ሥራ የመፍጠር ተግባር ከተቃናልኝ ወጣቱን ከቅዋሜ ውጪ አደርጋለሁ፣ ለተቃዋሚዎች የፓርላማ ወንበሮች አቃምሼ በተለመደው የምርጫ ጨዋታዬ ሥልጣኔን አረዝማለሁ የሚል ንድፍ ተይዞ ከሆነም ንድፉ የእሳት መንገድን የመረጠ ጅልነት ነው፡፡ የኢሕአዴግ በውድም በግድም በሥልጣን ላይ መቆየት ለመደቤ/ ለአካባቢዬ ጥቅም ይበጃል፣ ኢትዮጵያም የልማት ገነት ትሆናለች ብለው የሚያስቡ ካሉም ዓይናቸውን ከፍተው ያለፈውን የቁጣ መዓት ውስብስብ ፈትል ቢመረምሩ ይሻላቸዋል፡፡ ካሁን በኋላ ለአገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች ጠንቃቃና የተሟላ መፍቻ ከመስጠት መቦዘንና በድብስብስ ለመግዛት መሞከር ድንገት ፈንድቶ ገዢውንም፣ አገሪቱንና ሕዝቦቿን ሊበላ ለሚችል ገሞራ ማጋለጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ምን ያህል የቆየ አደጋ ውስጥ እንደሆኑ በትክክል ለመረዳት የሚሹ የሚያስፈልጋቸው በምድሯ ውስጥ ከላይ እስከ ታችና ከአዲስ አበባ እስከ ዳርቻ ድረስ በየዕለቱ ስንት የሚያበግኑ ጥፋቶችና ሸሮች እንደሚፈጽሙ፣ እነዚህ ብቻቸውንም ሆነ ከውጭ ጠላት ሴራና ከሽብርተኝነት ትንኮሳ ጋር ተገናኝተው ምን ያክል አቅጣጫው አስቀድሞ የማይታወቅ ድንገተኛ የቁጣ እሳት ሊያቀጣጥሉ እንደሚችሉ ማስተዋል ብቻ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ህልውናና ዕጣ ካንድ ቡድን የሥልጣን ጥቅም በላይ ነው፡፡ ኢሕአዴግም የሕዝብን ጥቅም የሚያበልጥ ከሆነና ከሽንገላ ያለፈ “ዴሞክራሲን የማጥለቅና የማስፋፋት” ዓላማ ካለው፣ እስከ 2012 ዓ.ም. ምርጫ ድረስ ምን ምን ለመሥራት እንዳቀደ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ዴሞክራሲ የሚጠልቀውና የሚስፋፋውም በካድሬዊ ስብከት አዕምሮን ለመቀየር በመሞከር አይደለም፡፡ ኢዴሞክራሲያዊነትና ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ከሰዎች መራገፍ የሚችለው ሕይወት ራሷ የካድሬነቱን ቦታ ከወሰደችና ዴሞክራሲና ተሃድሶን ለመስበክ ከቻለች ነው፡፡ ማለትም የዴሞክራሲ ነፃነቶች በተግባር ተከብረው በማኅበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ ሲሠሩ በነፃነት መወያየት/መከራከር፣ መደራጀትና መንቀሳቀስ ዕውን ሲሆኑ፤ የአጥፊዎች ተጋላጭነትና ተጠያቂነት ከታች እስከ መንግሥት አናት ድረስ የሚሠራ ሆኖ ሽፍንፍን ሽፍጦችና ስርቆቶች ከወዲሁ መሽማቀቅ ሲደርስባችው፣ በሥራ ማደግና መኩራት ወለል ተደርጎ በር ሲከፈትላቸው ነው፡፡ መልካም አስተዳደር የሚበቅለው ከዚህ ዓይነቱ ለውጥ ነው፡፡ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ከወረት የዘለለ ዕድሜ ሊኖራቸው የሚችለው ደግሞ ህልውናቸው ከሥራ አስፈጻሚው በጎ ፈቃድ ውጪ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም  የሥልጣነ መንግሥቱ ወታደራዊና ሲቪል አምዶች ከቡድናዊ ሙሽትና መረባዊ ውጦሽ ሲፀዱና ሲጠበቁ፣ እንዲሁም የሕግ ተርጓሚው፣ የሕግ አውጪውና የአስፈጻሚው የሥልጣን ዘርፎች፣ የመማገጥ ዝንባሌዎችን ለመቆጣጠር በሚያስችል ተገናዛቢነት ሲደራጁ ነው፡፡

እነዚህ ተግባሮች በኢትዮጵያ ውስጥ ዕውን የመሆናቸው ጉዳይ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታዎችን በጥንቃቄና በብልኃት እየተጠቀሙ የአገሪቱን ጣጣዎች ለማቃለል ከመቻል ጋር በቀጥታ የተቀራኘ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ቢፈጠርም የሐሳብ ሥርጭቱ፣ ቅስቀሳና ክርክሩ ሁሉ የመመራረዝና የመጠማመድ ክንዋኔ ከሆነ፣ ከዚሁ ጋር የተፋተሉ የሠልፍና የንቁሪያ ጋጋታዎች ምኅዳሩን ካመሱ፣ የምርጫ ውድድሩም ሸፍጥ፣ የገንዘብ ጉርሻ፣ ማስፈራራትና የኃይል ተግባራት ሁሉ የተሠማሩበት ግብግብ ሆኖ ካረፈ ልፋቱ ሁሉ ዞሮ ዞሮ እዚያው የፍጅት እሳት ውስጥ መግባት፣ ከዚያም ካነሰ ደም አፋሳሽ በሆነ ወታደራዊ ግልበጣ መደፍጠጥ ይሆናል፡፡

መመራረዝን ከፓርቲዎችና ከሕዝብ ውስጥ የማስወገድ ሒደት፣ በሥልጡንነት እየተወያዩና እየተከራከሩ ለችግሮች ቅን መፍትሔ የመፈለግ ብቃት፣ እንዲሁም ለቡድን አዘንብለው የቆዩ የመንግሥት ተቋማትን እንዳያገረሽባቸው አድርጎ ወደ ገልለተኝነት የማምጣት ሥራ፣ ጊዜ የሚወስዱና የሁሉንም ወገን መተባበር የሚጠይቁ ናቸውና ከሁሉ በፊት ይኼን ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎቹ አጢነውና የጋራ ስምምነት ፈጥረው ለተልዕኮው አንድ ላይ መሠለፍ ግድ ይላቸዋል፡፡ ፓርቲዎች እዚህ ወሳኝ ተግባር ላይ ከተገናኙና  አቅማቸውን  ማስተባበር ከቻሉ ለአገሪቱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት፣ ለሕዝቦቿ ሕይወት መቃናት፣ ለኢሕአዴግና ለተቃዋሚዎቹ ፍሬያማ አስተዋጽኦ እጅግ አስፈላጊ የማዕዘን ድንጋይ ተቀመጠ ማለት ነው፡፡

ይኼ ከተሟላ ፓርቲዎች በእርስ በርስ የመሰራረግ ተንኮል ሳይጠቃቁ፣ በመከባበርና በቅንነት እየተወያዩና እየተራረሙ ለችግሮች መፍትሔ ለመፈለግና ለመቀባበል ይችላሉ፡፡ በውጭም ሆነ በጫካ ውስጥ ያሉ በፌዴራላዊ ዴሞክራሰያዊ ሥርዓት ውስጥ መሳተፍ የሚሹ ኃይሎችን ማሰባሰብ ቀላል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ከመንግሥት የቃል መግለጫ ይበልጥ ራሱ የሕጋዊ መድረኩ ሆደ ሰፊነት በጠመንጃ ጎዳና ውስጥ ያሉትን ወደ ሰላም የመጥራት ጉልበት ስለሚኖረው ነው፡፡ “የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና መስፋፋት ማዕከል” ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት የሚቻለውም ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ውስጥ ከሚኒስትርነት የወረዱ ሹሞችን አዝሎ ሲፈጠር ሳይሆን፣ የፓርቲዎችን የጋራ ተልዕኮ ተቆናጦ ሁሉንም ፓርቲዎችና የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎችን አካትቶ እስከ ታች ድረስ ከሕዝብ ጋር የሚሠሩ ቅርንጫፎች ሲኖሩት ነው፡፡

እየተጠቃለለ በመጣው ዓለም ውስጥ መልካም ኑሮን በልማት ለመጨበጥ ከሚካሄድ አገር ዘለል የመሰባሰብ ጉዞ ጋር የሚያጣጥመንና ፍሬያማ ለመሆን የሚያበቃን ምን ዓይነት አገራዊ አደረጃጀትና አዕምሮ ነው? ብሔረሰባዊ ልዩ ልዩ ማንነቶችንና ኅብረ ብሔራዊ የጋራ ማንነትን እንዴት ማጣጣም ይቻላል? በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ የፖለቲካ መጣመምና መበረዝ ሳይደርስበት እንደምን ይደራጅ? ማኅበረሰቦች ባለቤትና መጤ ተባብለው የማይላተሙበት፣ አንዱ ወገን አሽቆጥቋጭ ሌላው ተሽቆጥቁጦ አዳሪ የማይሆኑበት እኩል የዜግነት ግንኙነት እንዴት ይበጅ? ማኅበረሰቦችን ከማኅበረሰቦች የሚያዛንቀውን የዕድገትና የመጠቃለል ጉዞ ተቃርነን ዜጎችን በየብሔረሰባዊ ምድራቸው እንዘርዝርና ጥንቅራቸው እንዳይቀየጥ እንጠብቅ ወይስ ከዕድገትና ከመጠቃለል ጋር የማያላትም ሌላ መፍትሔ አለን? የፌዴራል አባላቱ የአስተዳደር ይዞታዎች ምድር መቃረጪያና መናጪያ ከመሆንስ እንዴት መላቀቅ ይችላሉ? ለአንድ ብሔረሰብ እታገላለሁ የሚል ብሔረተኛ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን በሚወክል ሥልጣን ላይ መቀመጥ ይገባዋል? እንዲቀመጥ ተፈቅዶለት ለብሔረሰቡ ሲያደላ ቢገኝ ጥፋተኛው እሱ ሊሆን ነው? የፖለቲካ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ወደ ብረት ትግል እንዳይሻገሩና አገሪቱ ዳግም የጠመንጃ ሜዳ እንዳትሆን የሚጠብቃት ምንድነው? አገርና ሕገ መንግሥት በመጠበቅ ሽፋን ከሚካሄድ ጭፍጨፋ ሕዝቦች መጥጠበቅ የሚችሉት እንደምን ነው? “የኃይለ ሥላሴ ሕገ መንግሥት”፣ “የደርግ ሕገ መንግሥት” እና “የኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት” የሚባሉ ታሪኮችን ተዘግተው፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ቀጥተኛ የእኛ ባይነት የታተመበት የሕገ መንግሥትና የሰንደቅ ዓላማ ምዕራፍ ውስጥ እንዴት ይገባ? … እነዚህን የመሳሰሉትን የአገሪቱን ብዙ ጉዳዮች ያለስሜታዊ መታወርና ያለጥድፊያ የመመርመርና የማብላላት ሥራ ከላይ የተገለጸውን ዓይነት ከፀብ የወጣ ሽግግራዊ ሒደት ይፈልጋል፡፡

በአጠቃላይ ለአገሪቱ የፖለቲካ ሰላምና ግስጋሴ የፓርቲዎች ተከባብሮ መኖር አስፈላጊነቱ ተጢኖ መጠማመድ  ከተወገደ፣ በሕዝብ ምርጫ ውጤት መሠረት ከሥልጣን መውረድ የሞት አፍንጫን ማሽተት ተደርጎ አያስፈራም፡፡ ወደ ሥልጣን የሚወጣውም ወራጁን በመበቀል ፍላጎት አይጠመድም፡፡ ኢትዮጵያን ማተራመስ የሚሹ የውጭ ኃይሎችም የተቃዋሚ ታኮ ማግኘት ይቸግራቸዋል፡፡

ኢሕአዴግና የዛሬ ተቃዋሚዎቹ የኢትዮጵያን ሕዝቦች እዚህ ምዕራፍ ላይ ለማድረስ ተጋግዘው መሥራት ከቻሉ፣ በአዲሲቱ ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ማንም የማያነቃንቀው የስም ሐውልት ያቆማሉ፡፡ ልብ እንበል! ኢትዮጵያን ለመበታተንና ከእሳት ጋር ለማገናኘት በጎረቤት “ጠላቶች” ጉርሻ መገዛትን ወይም የአሮጌዎቹ ኦነግና ሻዕቢያ ደቀ መዝሙር መሆንን አይጠይቅም፡፡ በታኞችንና የትርምስ ኃይሎችን እንታገላለን እያሉ ከሕዝብ እውነተኛ የድምፅ ፈቃድ ውጪ የአንድ ቡድን በሥልጣን ላይ መሟዘዝም እዚያ ውጤት ላይ ያደርሳል፡፡ በኢሕአዴግም ሆነ በተቃዋሚዎቹ ውስጥ ያሉ የሕዝብ ተቆርቋሪዎች ይኼ እንዲሆን ከፈቀዱ ታሪካቸውን የሚጽፍላቸው ፍምና ነበልባል ይሆናል፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...