Sunday, June 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በ250 ሚሊዮን ብር የሲኖትራክ መገጣጠሚያ የገነባው ባለሀብት

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሥራውን ከአሥር ዓመታት በፊት ሲጀምር በአባቱ የብረታ ብረት ዎርክሾፕ ውስጥ ነበር፡፡ የተለያዩ የብረታ ብረት ውጤቶችን በተለይም ከመሬት በታች የሚቀበሩና የነዳጅ ማመላለሻ ቦቴዎች የሚሸከሟቸውን የነዳጅ ታንከሮች በማምረት ይታወቃል፡፡

በአሁኑ ወቅት ይህ ሥራው ተስፋፍቶ በአገሪቱ ከሚገኙ የከባድ ብረታ ብረት ውጤቶች አምራች  ኩባንያዎች አንዱ የሆነውን ድርጅት ለመመሥረት በቅቷል፡፡ ወጣት ነብዩ አሰፋ ይባላል፡፡ የራሱንና የአባቱን ስም የመጀመርያ የእንግሊዝኛ ፊደላት በመውሰድ ኤንኤ ሜታል ኢንዱስትሪ ኤንድ ኢንጂነሪንግ የተሰኘውን ኩባንያ በባለቤትና በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት ይመራል፡፡

ይህ ኩባንያ በአሁኑ ወቅት ከሚሠራቸው ሥራዎች ውስጥ የነዳጅ ታንከሮችንና ካርጎዎችን ከማምረት ባሻገር የከባድ መኪኖችን ተሳቢዎች (ትሬለርስ) በማምረት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚሁ ሁሉ በላይ ደግሞ የሲኖትራክ ከባድ መኪኖችን እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ መገጣጠም ጀምሯል፡፡ የሚገጣጥማቸው መኪኖች ሙሉ በሙሉ በብትን (Comeplete Knockdown) እንዲመጡ ከተደረጉ በኋላ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች እንደሚገጣጠሙ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የኢኮኖሚ ዕቅድ ውጤታማነትና ክትትል ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ታደሰ ኃይሌ ለተመራውና ፋብሪካዎቹን ለጎበኘው የመንግሥት ኃላፊዎች አካል ገለጻ ተደርጓል፡፡

ቅዳሜ፣ ኅዳር 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደ ሥነ ሥርዓትም በ250 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት የተገነቡ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካዎቹና የተሽከርካሪ ተሳቢዎች ማምረቻ ፋብሪካዎች ይፋ ተደርገዋል፡፡ በዕለቱ ምርት መጀመራቸው ይፋ የተደረጉት ፋብሪካዎች ተጎታች፣ ሰሚትሬለርስ እንዲሁም የሲኖትራክ መኪኖች መገጣጠሚያ ብሎም የነዳጅ ታንከሮች ምርቶች የተዋወቁ ሲሆን፣ እነዚህ ምርቶች ከአገር ውስጥ ገበያ ባሻገር ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርባቸው ወጣት ነቢዩ ተናግሯል፡፡

በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለቡ፣ ኃይሌ ጋርመት በሚባለው አካባቢ የተገነቡት ፋብሪካዎች አማካይነትም 22 ቶን የመጫን አቅም ያላቸው 1,000 ተጎታቾችና ከ45 እስከ 60 ቶን የሚጭኑ 300 ተጎታቾች (ሰሚትሬለርስ) እንዲሁም 1,000 ሲኖትራኮችን ለመገጣጠም መነሳቱን ኩባንያው አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት እነዚህን ሥራዎች አስፋፍቶ ለመሥራት ተጨማሪ መሬት እንዲሰጠው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥያቄ አቅርቦ ይሁንታ ማግኘቱን የገለጸው የነቢዩ ድርጅት፣ በተጨማሪ ማስፋፊያ ግንባታው ምክንያት በአሁኑ ወቅት ከ400 በላይ ለሆኑ ሰዎች ያስገኘው የሥራ ዕድልም እንደ ፕሮጀክቱ ማስፋፊያ ሒደት እንደሚጨምር አስታውቋል፡፡ ‹‹ምንም እንኳ በተሰጠን ቦታ ላይ የማምረቻና የመገጣጠሚያ ፋብሪካዎችን ብንገነባም ዛሬም ቢሆን ግን ሙሉ በሙሉ ከኪራይ ተላቀናል ማለት አይደለም፤›› ያለው ነብዩ፣ ‹‹ባለን ምርት የማስፋፋት ስትራቴጂ፣ በብዛት የማምረት አቅም (ኢኮኖሚስ ኦፍ ስኬል) ተጠቃሚ ለመሆን እንዲሁም በሰፊው ኢንቨስት በማድረግ ምርቶቻችንን ወደ ውጭ መላክ አለብን ብለን ከንግድ ሸሪኮቻችን ጋር ስምምነታችንን ጨርሰናል፤›› በማለት ኩባንያው ለማስፋፊያ ግንባታ እያደረገ የሚገኘውን ዝግጅት ጠቅሷል፡፡

ለምዕራፍ ሁለት ግንባታ ሥራዎች የሚረዱ የግንባታ ዕውን ለማድረግ የሚረዱ የዲዛይን ሥራዎች እንደተጠናቀቁ በመጥቀስ፣ ለማስፋፊያ ግንባታው ሰፊ ቦታ እንደሚያስፈልግና የአዲስ አበባ አስተዳደርም ቦታውን ሊሰጣቸው ጫፍ የደረሰበት ሒደት ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡ ከዚህ ቀደም ለሰጠው ቀና ምላሽም ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

ኩባንያው የገነባቸውን ፋብሪካዎች ወደ ሥራ ማስገባቱን ባስታወቀበት ሥነ ሥርዓት ወቅት የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ከአሥር ዓመት በፊት ማለትም በ2000 ዓ.ም. በአነስተኛ የብረታ ብረት ዎርክሾፕ መጀመሩን ገልጸው፣  ዛሬ ላይ በሚሊኖች የሚቆጠር ካፒታል የሚያንቀሳቅስ ግዙፍ ፋብሪካ ለመገንባት የበቃውን ወጣት ነብዩን ሚኒስቴራቸው በሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ከጎኑ እንደሚቆም ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጀማል ረዲም፣ የከተማው አስተዳደር መሬትን ጨምሮ ሌሎችም አስፈላጊ ድጋፎችን ለኤንኤ ሜታል እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

ነብዩ እንዳብራራው ከሆነ፣ ኩባንያው ቀድሞ ሲሠራቸው ከነበሩት የነዳጅ፣ የቅባትና ሌሎችም ፈሳሽ ምርቶችን ለማጓጓዝና ለማከማቸት ከሚውሉት ታንከሮች ምርት ባሻገር፣ ለተለያዩ ድርጅቶች ልዩ ልዩ ምርቶችን በትዕዛዝ እያመረተ እንደሚገኝ በምሳሌነት ያቀረበው ለብርታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የተመረተውና ለኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ የተገጠመው የዲፊውዘር ማሽን ተጠቃሽ ነው፡፡

እንዲህ ያሉትን ሥራዎች ጨምሮ የሲኖትራክ መገጣጠሚያውንና የተጎታች መኪኖቹን ምርት ለማስፋፋት የመሬት ርክክብ እስኪደረግ እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ነብዩ ገልጿል፡፡ ያቀረበው የመሬት ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ጫፍ እንደደረሰና በቅርቡም በሊዝ ተረክቦ ወደ ግንባታ ለመግባት መንግሥትን እየተጠባባቀ እንደሚገኝ በገለጸበት ሥነ ሥርዓት ወቅት፣ የመንግሥት ኃላፊዎች አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጡ የተናገሩት የተገነቡትን ፋብሪካዎች ዋቢ በማድረግ ነበር፡፡ ነብዩ እንደጠቀሰውም ከኩባንያው ሸሪኮች ጋር በመነጋገር የመገጣጠሚያ ፋብሪካውን አቅም እስከ ሦስት እጥፍ ለማሳደግ የሚያስችል ኢንቨስትመንት እንደሚካሄድ ለሪፖርተር አስታውቋል፡፡

የሲኖትራክ ኩባንያ የአፍሪካ ቅርንጫፍ ፕሬዚዳንት ዣንግ ዜንግ በበኩላቸው፣ ከኤንኤ ሜታል ኩባንያ ጋር አብሮ ለመሥራት የኩባንያው አቅምና የገበያ ድርሻ ከሌሎችም መመዘኛዎች አኳያ ተመራጭ እንዳደረጉት ገልጸዋል፡፡ ሲኖትራክ ከቀላል እስከ ከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎችን እንደሚያመርት የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ወታደራዊ መኪኖችን ጨምሮ ለሲቪል አገልግሎት የሚውሉ እንደ አውቶብስ  ያሉ የትራንስፖርት መኪኖችን በማምረት ከመቶ በላይ አገሮች  ውስጥ የገበያ ድርሻ እንዳለው፣ በምሥራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረገ የገበያ አቅጣጫ ለመከተል ማቀዱን አስታውቀዋል፡፡

በሲኖትራክና በኤንኤ ሜታል መካከል የተጀመረው የንግድ ግንኙነት እያደገ ለመዱ እርግጠኛ መሆናቸውን የተናገሩት ዜንግ፣ ላለፉት 60 ዓመታት እያደገ የመጣው ሲኖትራክ ኩባንያ የኢትዮጵያ አጋሩ የሆነውን ይህንኑ ኩባንያ ሙሉ በሙሉ በምርትና አገልግሎት አሰጣጡም እንደሚያግዘው አስታውቀዋል፡፡ በአውቶሞቲቭ ኢንዱትሪ መስክ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ለሚኖራት የጠበቀ የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት የሁለቱ ኩባንያዎች ሚና ወሳኝ እንደሚሆንም ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

      እንደ ነብዩ ከሆነ፣ በአገር ውስጥ ለሚገጣጠሙት መኪኖች የድረ ሽያጭ አገልግሎትና የመለዋወጫ አቅርቦት በሰፊው ለመስጠት ሥራዎች የተጀመሩ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የነበረውን አገልግሎት በማሻሻል ጭምር ከሲኖትራክ ኩባንያ ጋር እየተነጋገረ ይገኛል፡፡ እንዲህ ያሉትን ሥራዎች ለመጀመር ማነቆ የሆነበት የቦታ ጥበት እንደሆነ አበክሮ የገለጸው ነዩ፣ በአሁኑ ወቅት በአራት አከባቢዎች በኪራይ ለመገልገል መገደዱን፣ ይህም የኩባንያውን የሥራ እንቅስቃሴ እያወከው እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

     

     

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች