Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኦሮሚያ ክልል ለሥራ አጦች ለማከፋፈል የኢንቨስተሮችን የማዕድናት ማውጫዎች ነጠቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ለኢንቨስተሮች ሰጥቶ የነበረውን የተለያዩ ማዕድናት ማውጫዎች፣ ከሐሙስ የካቲት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ መንጠቅ ጀመረ፡፡ የክልሉ መንግሥት የሚነጥቃቸውን የማዕድን ማውጫዎች ለተደራጁ ሥራ አጥ ወጣቶች ለመስጠት አዲስ ዕቅድ አውጥቷል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ ከመልካም አስተዳደር ችግሮች ጋር በስፋት ሲነሳ የቆየውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ፣ በርካታ አዳዲስ የሥራ መስኮች በመፍጠር ላይ መሆኑን ይናገራል፡፡

ከእነዚህ የሥራ መስኮች ውስጥ ከዚህ ቀደም ለባለሀብቶች የተሰጡ የተፈጥሮ ማዕድናት ማውጫዎችን መልሶ በመውሰድ፣ ለተደራጁ ሥራ አጥ ወጣቶች ማከፋፈልና ወደ ሥራ ማስገባት አንደኛው ነው፡፡

በዚህ መሠረት በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ቀይ አሸዋ፣ አሸዋ፣ ድንጋይ (ካባ) ፑሚስና ታንታለም ማውጫ ሥፍራዎችን የሥራ አጥነት መቅረፊያ ለማድረግ ታስቧል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንትና የከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓብይ አህመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሥራ አጥነት ባለባቸው ቦታዎች ሁሉ ይህ አሠራር ተግባራዊ ይሆናል፡፡

‹‹አሁን የጀመርነው በምሥራቅ ሸዋ ዞን ነው፡፡ በዚህ ሥፍራ የሚገኙ የማዕድን ማውጫዎችን በመውሰድ ለ300 ሺሕ ወጣቶች ሥራ ለመፍጠር አቅደናል፤›› በማለት የገለጹት አቶ ዓብይ፣ ‹‹በአካባቢው ሲሠሩ ከነበሩ ኢንቨስተሮች ጋር በጋራ ለማካሄድ እየመከርን ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ወጣቶቹ ያመረቷቸውን ማዕድናት ኢንቨስተሮቹ ይገዛሉ ተብሎ ታቅዷል፡፡

አቶ ዓብይ ጨምረው እንደገለጹት በክልሉ የመሬትና የሰው ሀብት ካፒታል አለ፡፡ የሚጎድለው ማሽንና ትራንስፖርት ነው፡፡ ይህንን ጉድለት ከባለሀብቶች ጋር በመነጋገር ለመፍታትና ለወጣቶቹም ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ ነው፡፡

በኦሮሚያ ክልል ከዚህ በፊት ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ስም የተፈጥሮ ማዕድናትን እሴት ሳይጨምሩ እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ ክልሉ በአሁኑ ወቅት ይህን አሠራር በማስቀረት ባለሀብቶች እሴት ወደሚጨምሩባቸው ዘርፎች እንዲሄዱ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ቀይ አፈር፣ አሸዋ፣ ድንጋይ፣ ፑሚስና ታንታለም ለማምረት ብዙ ካፒታል አያስፈልግም፡፡ ካፒታል ቢያስፈልግ እንኳ ምርትን በመሸጥ፣ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን መግዛትም ሆነ መከራየት እንደሚቻል ክልሉ ያካሄደው ጥናት ያመለክታል፡፡

በዚህ መሠረት የኦሮሚያ ክልል እነዚህን የማዕድን ልማት ዘርፎች በክልሉ የተንሰራፋውን ሥራ አጥነት መቅረፊያ መንገድ አድርጎ ፓኬጅ ቀርጿል፡፡

እነዚህ ኩባንያዎች የማዕድን ማውጣት ሥራቸው በመስተጓጎል ላይ እንደሚገኝ እየገለጹ ነው፡፡ የደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ ከሐሙስ ጀምሮ ማምረት እንዳቆሙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹250 መኪኖች በአካባቢው ያለሥራ ቆመዋል፤›› ያሉት አቶ ኃይሌ፣ ‹‹በእጃችን የሚገኘው አንድ ሳምንት ማምረት የሚያስችል ፑሚስ ብቻ ነው፡፡ ላለፉት ስድስት ቀናት ማምረት ባለመቻላችን የምርት መስተጓጎል እንዳያጋጥመን ሠግተናል፤›› በማለት አክለዋል፡፡

አቶ ኃይሌ እንደሚያስረዱት፣ ደርባ ሚድሮክ የሥራ ፈጠራው መፍትሔ አካል መሆን ይፈልጋል፡፡ ኦሮሚያ ክልል ይህንን አሠራር ተግባራዊ ማድረጉ የሚደገፍ ሆኖ፣ ነገር ግን ይህ ስትራቴጂ ሌሎች የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ባሉባቸው ክልሎች ተግባራዊ የማይደረግ ከሆነ የገበያ ውድድር መዛባት ይፈጥራል፡፡ ‹‹ስትራቴጂው በፌዴራል ደረጃ ሊተገበር የሚገባው ነው፡፡ ካልሆነ ግን የገበያ ዋጋንና ውድድሩንም ፍትሐዊ አያደርገውም፡፡ ጥራት ያለው ማቴሪያል ከማምረት አንፃርም ሊመዘን ይገባዋል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በተለይ በዚህ አካባቢ ለሲሚንቶ ማምረቻ ዋነኛ ጥሬ ዕቃ የሆነውን ፑሚስ የሚያመርቱት ግዙፎቹ ኩባንያዎች ደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ፣ ዳንጎቴ ሲሚንቶና ሙገር ሲሚንቶ ይገኙበታል፡፡

ሥራውን ከኢንቨስተሮች ጋር በጋራ የመሥራት ዕቅድ እንዳለና የሽግግር ጊዜው ችግር የማይፈጠርበት እንዲሆን ይደረጋል ሲሉ አቶ ዓብይ አስረድተዋል፡፡ ጥራት ያለው ምርት ከማምረት አንፃርም ወጣቶቹ ከኢንቨስተሮቹ ጋር በጋራ የሚሠሩበትና ሥልጠና የሚያገኙበት ዕድልም ስለሚኖር፣ ችግሩ ይፈታል ሲሉ አቶ ዓብይ ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የተንሰራፋውን ሥራ አጥነት ለመቅረፍ በዚህ በጀት ዓመት የ6.6 ቢሊዮን ብር በጀት በመመደብ፣ 1.2 ሚሊዮን ሥራ አጥ ወጣቶችን ሥራ ለማስያዝ ዕቅድ አውጥቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች