Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአንበሳ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት 11 አውቶቡሶች በእሳት ቃጠሎ ወደሙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ከ46 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ደርሶበታል

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት መካኒሳ ዲፖ ቅዳሜ የካቲት 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት ላይ በደረሰ ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ፣ 11 አውቶቡሶች ሙሉ በሙሉ ወደሙ፡፡

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ውስጥ የሚገኘው የከተማ አውቶቡስ ዲፖ ውስጥ ከነበሩ 556 አውቶቡሶች ውስጥ 11 ተቃጥለው 545 መትረፋቸውን፣ የዲፖው ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ገብረ ሚካኤል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የእሳቱ መነሻ ምክንያት በፖሊስ እየተጣራ መሆኑን የገለጹት አቶ ሳሙኤል፣ ተረኛ ሠራተኞች ተረባርበው በነዳጅ ዲፖው አካባቢ ቆመው የነበሩ አውቶቡሶችን ባያሸሹና የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጠርና መካላከል ባለሥልጣን ፈጥኖ ባይደርስ፣ ከፍተኛ ጉዳት ይደርስ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

በደረሰው የእሳት ቃጠሎ 18 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 11 አውቶቡሶች፣ የ25 ሚሊዮን ብር መለዋወጫዎች ከነመጋዘኑና ሦስት ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ቤቶች በድምሩ የ46 ሚሊዮን ብር ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡

አደጋውን መቆጣጠር ባይቻል ኖሮ በዲፖው ውስጥ የነበረ 50 ሺሕ ሊትር ነዳጅ፣ 95 የሸገር አውቶቡሶችና 461 የከተማ አውቶቡሶች ሊወድሙ ይችሉ እንደነበርም አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል፡፡ ምናልባትም የእሳት ቃጠሎው በአካባቢው ለሚኖሩ ሁሉ ሊተርፍ ይችል እንደነበር አክለዋል፡፡

በ1994 ዓ.ም. በ75 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ የተገነባው የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ መካኒሳ ዲፖ ውስጥ ጥገና የሚደረግላቸውና በተለያየ አቅጣጫ የሚሰማሩ አውቶቡሶች የሚስተናገዱበት፣ ከሦስቱ የድርጅቱ ዲፖዎች አንዱ መሆኑን አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል፡፡

የእሳት ቃጠሎው በተከሰተ በ15 ደቂቃ ልዩነት ከሌሊቱ 9፡15 ሰዓት ላይ የደረሰው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን፣ እሳቱን ከሁለት ሰዓት በላይ በፈጀ ጊዜ ውስጥ ሊቆጣጠር መቻሉን አስታውቋል፡፡

የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ እንደገለጹት፣ ስምንት የአደጋ መቆጣጠሪያ ተሽከርካሪዎችንና 60 ባለሙያዎችን በማሰማራት ይደርስ የነበረውን ከፍተኛ የቃጠሎ አደጋ መከላከል መቻሉን ገልጸዋል፡፡ 545 አውቶቡሶችንም ለማዳን መቻሉን አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል ሰኞ የካቲት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በጣለው ዝናብ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንትና በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት ገርጂ ቴሌ ጀርባ፣ እንዲሁም ወረዳ ዘጠኝ ጐላጉል ጀርባ የጐርፍ አደጋ ተከስቷል፡፡ በተጨማሪም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አሥር ዳማ ሆቴል አካባቢና በወረዳ 11 ፓስታና ማኮረኒ አካባቢ የጐርፍ ጉዳት መድረሱን አቶ ንጋቱ ገልጸዋል፡፡

ዝናቡን ተከትሎ በተነሳው አውሎ ንፋስም ዓባይ ትራንስፎርመር ማምረቻ ፋብሪካ ላይ ጉዳት በመድረሱ፣ አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙንም አክለዋል፡፡ ለጐርፍ አደጋ በሚያጋልጡ ቦታዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡      

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች