ዶ/ር ደረጀ ንጉሤ፣ የኢትዮጵያ የፅንስና የማሕፀን ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዚዳንት
ዶ/ር ደረጀ ንጉሤ የማሕፀንና ጽንስ ሕክምና ስፔሻሊስትና የኅብረተሰብ ጤና ባለሙያ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ1992 ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በሕክምና የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ከ1997-2001 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማሕፀንና ጽንስ ሕክምና ስፔሻላይዝ አድርገዋል፡፡ በ2008 ዴንማርክ ከሚገኘው ኮፐንሀገን ዩኒቨርሲቲ በምርምር መስክ የድህረ ምረቃ ዲፕሎማ እንዲሁም በ2015 በኅብረተሰብ ጤና ከኩንዳን ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ጽንስና የማሕፀን ሀኪሞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡
የአፍሪካ የማሕፀንና ጽንስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባልና የዓለም የማሕፀንና ጽንስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ አባልም ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የጽንስና ማሕፀን ሐኪሞች ማኅበር (ኢሶግ) እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ዙሪያ ምሕረት አስቻለው አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡– የኢትዮጵያ የጽንስና ማሕፀን ሐኪሞች ማኅበር (ኢሶግ) ከ25 ዓመታት በፊት ሲመሠረት ዓላማው ምን ነበር?
ዶ/ር ደረጀ፡- እ.ኤ.አ በ1987 ናይሮቢ ኬንያ ላይ የሥነ ተዋልዶና የእናቶች ጤና ደኅንነትን በተመለከተ ጉባዔ ተካሄዶ ነበር፡፡ በ1989 ደግሞ አዲስ አባባ ላይ የዚሁ ጉባዔ ቀጣይ ስብሰባ ተደርጎ፣ በዋነኛነት በወቅቱ የነበረውን ከፍተኛ የእናቶች ሞት ለመቀነስ የባለሙያዎች ርብርብ አስፈላጊነት በምክረ ሀሳብነት የወጣበት ወቅት ነበር፡፡ ከዚህ ምክረ ሐሳብ በመነሳት ባለሙያዎችን አስተባብሮ የሚሠራና ስነ ተዋልዶ ላይ በቂ የሥራ ድርሻ ሊኖረው የሚገባ የሙያ ማኅበር ማቋቋም አስፈላጊነት ተሰምሮበት ነበር፡፡ ከዚህ በመነሳት የኢትዮጵያ የጽንስና የማሕፀን ሐኪሞች ማኅበር በ1992 ተቋቋመ፡፡ ሲቋቋም ራዕይ አድርጎ የተነሳው ማኅበረሰቡ የሥነ ተዋልዶ ጤናንና ይዘቶችን በሚገባ እንዲረዳ፣ የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን ሲጠቀም ማየት ሲሆን፣ ራዕዩን ለማሳካት ደግሞ ሙያዊ ትግበራ የሚኖርበት ተገቢ መድረክ ማግኘት ነው፡፡ በተልዕኮ ደረጃ መረጃን መሠረት ባደረገ መልኩ የኅብረተሰብ ጥምር ትግበራ፣ የማኅበረሰብ አባላትን እንዲሁም የአገር ውስጥና የውጭ አጋሮችን በንቃት በማሳተፍ የሥነተዋልዶ ጤናን በአገሪቱ ማስፋፋት ነው፡፡ እንደ ግብ የተቀመጠው የሥነ ተዋልዶ ጤናን ደረጃ ሥነምግባር በጠበቀ ሁኔታ መደገፍና ማሻሻል ነው፡፡ ከእነዚህ ራዕይ፣ ተልዕኮና ግብ አንጻር ዘርዘር ያሉ ዓላማዎችም ተካተዋል፡፡ ከእነዚህ ከእነዚህ የሴቶችና ሕፃናት ጤና አጠባበቅና አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲኖር ማስቻል ነው፡፡ በተያያዘም በሥነ ተዋልዶ ጤና መስክ ላይ የሚወጡ ፓሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ የዕቅድ ተፅዕኖ መፍጠር፣ በሥልጠናና ተገቢ እውቀትና የሥነ ተዋልዶ ጤና አሠራሮችን በማስፋፋት የሙያ ልቀትን ማሻሻል፣ የሥነምግባር ደረጃዎችን መደገፍ፣ በሥነ ተዋልዶ ጤና የሚያከናውኑ ማኅበራትና ድርጅቶች ማለትም በአገር ውስጥና በውጭ ካሉት ጋር በንቃት መሳተፍ፣ በተጨማሪም ለማኅበረሰቡ የሥነ ተዋልዶ ጥቅሞችን ማስገንዘብ በአጠቃላይም ለአገሪቱ ልማት የበኩላችንን አስተዋፅኦ ለማድረግ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሲቋቋም ያስቀመጣቸው ግቦች በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ መሠረት አድርገው ነው፡፡ ካለው እውነታ አንጻር ኢሶግ ምን ያህል ተፅዕኖ መፍጠር ችሏል?
ዶ/ር ደረጀ፡- ማኅበሩ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ለመጥቀስም ያህል ያልተቋረጡ ውጤታማ ዓመታዊ ጉባዔዎችን በ25 ዓመታት ውስጥ አከናውኗል፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ ሁለት፣ በአምስት ክልል ከተሞች ውስጥ ስድስት በአጠቃላይ ስምንት ቢሮዎችና ሠራተኞችን በመያዝ ተግባሩን እያከናወነ ነው፡፡ ሁለት የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዶችን በሥኬት ተግብሯል፡፡ ሦስተኛውን ስትራቴጂክ ፕላን ለመተግበር በዝግጅት ላይም ይገኛል፡፡ ሁሉም የማሕፀንና ጽንስ ሕክምና ባለሙያዎች የማኅበሩ አባል ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው ወደ 318 የሚደርሱ የሙሉ ጊዜ አባላትና 76 የሚሆኑ ተባባሪ አባላት አሉን፡፡ በአብዛኛውም የስፔሻሊቲ ትምህርት በመማር ላይ ያሉ ይገኙበታል፡፡
ሪፖርተር፡- በአገሪቱ የሚገኙ የማሕፀንና ጽንስ ሐኪሞች በሙሉ የማኅበሩ አባል ናቸው ማለት ይቻላል?
ዶ/ር ደረጀ፡- አዎ! ሙሉ ለሙሉ አባል ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ከተከናወኑ ተግባራት ጋር በተያያዘ ባለፉት 25 ዓመታት ቁጥራቸው 21 የሚደርሱ የተለያዩ ፕሮጀክቶችንና የምርምር ሥራዎችን ሥነ ተዋልዶ ጤና እንቅስቃሴ ላይ አከናውኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከአገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር አራት በትግበራ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ ሥነ ተዋልዶ እንቅስቃሴዎች ሁነኛ አጋር በመሆን ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ እውቅናን ማግኘት የቻለ ማኅበር ነው፡፡ በሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ በተለይ በሦስተኛ ደረጃ ምጥ ላይ ከሚከሰተው ደም መፍሰስና ወሲባዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ወገኖች የሕክምና እንክብካቤ ከማድረግ ጋር በተያያዘ የሥልጠና ማንዋል ተዘጋጅቷል፡፡ የቤተሰብ ዕቅድና ደረጃውን የጠበቀ የማስወረድ ሕክምና አሰጣጥ መግለጫ (ጋይድላይን)ም አዘጋጅቷል፡፡ ከዚህ በተረፈ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችንና አውደ ጥናቶችን አከናውኗል፡፡ በአፍሪካ ደረጃ የምሥራቅ፣ የመካከለኛውና የደቡብ አፍሪካ አገሮች የጽንስና የማሕፀን ሕክምና ፌዴሬሽን አባል ነን፡፡ በአህጉር ደረጃ የአፍሪካ የማሕፀን ጽንስ ሕክምና ፌዴሬሽን አባል ነን፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዓለም አቀፍ የጽንስና ማሕፀን ሕክምና አባል ነን፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት ሥራችንን ሥንሠራ ከአጋሮቻችን በዋናነት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የተለያዩ የሙያ ማኅበራት በተለይ ከአዋላጅ ነርሶች ማኅበር፣ ከኢትዮጵያ የሕክምና ማኅበር፣ ከኢትዮጵያ የሕፃናት ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበርና ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች ማኅበር ጋር አብረን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲዎችና የሕክምና ትምህርት ቤቶች አጋሮቻችን ናቸው፡፡ በብሔራዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ ከሚሠሩ ድርጅቶች ጋር በአጋርነት ሠርተናል፡፡ በተያያዘም ከተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች ጋር ሠርተናል፡፡
ሪፖርተር፡– በእነዚህ ዓመታት 21 ያህል ፕሮጀክቶች ተሠርተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ጥናቶችም አሉ፡፡ በትግበራ ላይ ያሉም አሉ፡፡ የጥናት ዋና ዓላማ በግኝቱ ላይ ተመስርቶ ለችግሮች የመፍትሔ ማመላከት ነው፡፡ ኢሶግ የሠራቸው ጥናቶችምን ያህል ለፖሊሲ ግብዓትነት ውለዋል?
ዶ/ር ደረጀ፡- ከቤተሰብ ዕቅድ ጋር በተያያዘ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የትግበራ ጋይድ ላይን እንዲወጣ ሚና ተጫውቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ለግልጋሎት የሚውል የድንገተኛ ጊዜ የወሊድ መከላከያ ላይ ጥናት አድርጎ ስርጭቱን በፓይለት ፕሮጀክት ሠርቷል፡፡ ከዚያም ወደ ትግበራ እንዲገባ አድርጓል፡፡ በከፍተኛ ደረጃ በእርግዝና ጊዜ በሚከሰተው የደም ግፊት ሳቢያ በመድኃኒት እጥረት ተገቢ ሕክምና መስጠት የማይቻልበት ሁኔታ ነበር፡፡ ለዚህም በፓይለት ፕሮጀክት መድኃኒት ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በማስመጣት፣ ሥልጠናም ተሰጥቶ ወደ ትግበራ ተገብቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተለይ ጾታዊና ወሲባዊ ጥቃት ለሚደርስባቸው ሴቶች ሕክምና ከማሰጠት አኳያ እንዲሁም የችግሩን ስፋት በዳሰሳ ጥናት ከተረጋገጠ በኋላ ስድስት ቦታዎች ላይ ሞዴል ክሊኒኮች እንዲከፈቱ አድርጓል፡፡ በአዲስ አበባና በዋና ዋና ክልል ከተሞች በተከፈቱት ክሊኒኮች ባለሙያዎችን በማሰልጠን የሚያስፈልገውን ቁሳቁስና የሕክምና መርጃ መሳሪያ በመስጠት፣ በኋላም ሥራውን በሚሠሩበት ወቅት ተገቢውን ሙያዊ ድጋፍና ክትትል በማካሄድ፣ የሥልጠና መመሪያ ዶክመንቶችንና ጋይድ ላይኖችን አውጥቷል፡፡
ሪፖርተር፡- አስቸጋሪ የምትሏቸው ነገሮች ምን ነበሩ?
ዶ/ር ደረጀ፡- ማኅበረሰቡ ሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ ያለውን ግንዛቤ ከማሳደግ አንጻር ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በቋሚነት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ‹‹ላንቺና ላንተ›› በሚል አምድ ግንዛቤ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ባለፈ ላለፉት ሰባት ዓመታት በሬዲዮ ፕሮግራም ላንተና ላንቺ በሚል ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል፡፡ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ሆስፒታል በማሕፀን መውጣት ችግር ይሰቃዩ ለነበሩ 204 ሴቶች አባላቶቻችንን በማስተባበር ሕክምና ሰጥተናል፡፡ በዚሁ ወቅት ለ546 ሴቶች ቅድመ የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ምርመራ አድርጓል፡፡ ወደ ችግሮቹ ሲገባ የሥልጠና ጥራት ችግር አንዱ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ካሉን አራት ፕሮግራሞች አንዱ ከአሜሪካ የማሕፀንና ጽንስ ሕክምና ማኅበር ጋር በተጓዳኝነት የምንሠራው ሥራ ስድስት ወር ሆኖታል፡፡ በዋነኝነት የስፔሻሊቲ ሥልጠና በተሻለ ጥራት እንዲሰጥ ለማድረግ የቴክኒክ ድጋፍ እያገኘን ሲሆን፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስትር ጋር በመሆንም እየሠራንበት ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ የቢሮ ችግር ዋናው ነው፡፡ ቢሮ በውድ ዋጋ ተከራይተን የምንሠራ በመሆኑ ከዘላቂነት አኳያ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአምስት ክልሎች ውስጥ ስድስት ቅርንጫፍ ቢሮዎች አሉን፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች መልካም ፈቃድ ቢሮ አግኝተን እየሠራን ነው፡፡ ፋይናንስን በተመለከተም የምናገኘው የገንዘብ ድጋፍ ከፕሮጀክት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ከአስተዳደር ጋር አያይዘን ገንዘብ ባለመጠየቃችን ጥሩ የገንዘብ አቅም ላይ አልደረስንም፡፡ በአመዘጋገባችንም ገንዘብ በሚያመጣ ተግባር ውስጥ በቀጥታ መሳተፍ ስለማንችል የገንዘብ አቅማችን የተገደበ ነው፡፡ ለአሁኑ ከአባላቶቻችን ባገኘነው የዓመት መዋጮና በዓመት አንዴ በሚኖረው ጠቅላላ ጉባዔ ከስፖንሰሮች በምናገኘው እንጠቀማለን፡፡
ሪፖርተር፡- የሕክምና ባለሙያዎች በየአምስት ዓመቱ ፈቃድ ለማደስ መውሰድ ያለባቸውን ሥልጠና ነው?
ዶ/ር ደረጀ፡- አዎ፡፡ መንግሥት በሕግ ደረጃ አስቀምጦታል፡፡ በየአምስት ዓመቱ የሙያ ፈቃድ ሲታደስ ባለሙያው በአምስት ዓመት 150 ወይም በዓመት 30 ተከታታይ የሥልጠና ክፍል መውሰድ አለበት፡፡ ይህንን በዓመታዊ ጉባዔ ወቅት በሚሰጡ ተከታታይ ትምህርቶች ብቻ ማሳካት አንችልም፡፡ ስለሆነም በየአካባቢው ባሉ ቢሮዎች ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ተከታታይ ትምህርቱን ለመስጠት እያሰብን ነው፡፡ ይሁንና ባሰብነው መጠን ማካሄድ አልቻልንም፡፡ በኢንተርኔት መቆራረጥ ምክንያት በዚህ ይሰጥ የነበረው ሥልጠና ላይ ችግር ገጥሞናል ማለት እችላለሁ፡፡ ሌላው የማኅበሩን አባላት ዳታ ቤዝ በተገቢው ሁኔታ አደራጅተን እስካሁን አልያዝንም፡፡ በመጪው ዓመታት ክፍተቶችን ለመሙላት ጥረት እናደርጋለን፡፡
ሪፖርተር፡- እንደ ችግር ከተነሱት አንደኛው የገንዘብ አቅም ነው፡፡ አንዱ ገቢያችሁም የአባላት መዋጮ ነው፡፡ በብዙ ሙያዊ ማኅበራት የቁርጠኝነት ችግር አለ፡፡ በሙያም በገንዘብም ለመርዳት ብዙም ጥረት ሲደረግ አይታይም፡፡ በአብዛኛው ያለው አመለካከት ከማኅበሩ ተጠቃሚነት ላይ ነው፡፡ የአባላት መዋጮ ላይ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
ዶ/ር ደረጀ፡- እስካሁን ማኅበራችን ከአባላት በዓመት የሚቀበለው 100 ብር አሁን ካለው ግልጋሎት አንጻር በቂ አይደለም፡፡ በመሆኑም ዓመታዊ ጉባዔ ላይ አቅርበነው ለማሻሻል ከስምምነት ተደርሷል፡፡ ያም ቢሆን ሥራዎችን ለማከናወን በቂ አይደለም፡፡ ከዚሁ ጋር በተጓዳኝ አባላት ጊዜ አግኝተው ለማኅበራቸው የማገልገል ችግር አለ፡፡ አብዛኛው አባላት በሆስፒታሎች፣ በጤና ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስለሚሠሩ ባሉበት ደረጃ በተገቢ ለማኅበሩ አስተዋፅኦ አድርገዋል ለማለት ይከብዳል፡፡ ለወደፊት አባላት በተገቢው ሁኔታ ይሳተፉ ዘንድ ከሳምንት በፊት ባደረግነው ጠቅላላ ጉባዔ ከስምምነት ተደርሷል፡፡ አባላት በየተሰማሩበት ቦታ ሆነው ማኅበሩን ለማጠናከር ቃል ገብተዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ኢሶግ ከሥነምግባር አንጻር የሚሠራቸው ተግባራት አሉ፡፡ በአገራችን በተለያዩ ጊዜያት የሕክምና የሥነምግባር ጉድለቶች እንሰማለን፡፡ ዳሰሳ ያደረጉ ሰዎች በተለይ በግሉ ዘርፍ ይበልጥ አትራፊ የመሆን ነገር እንዳለ ይናገራሉ፡፡ ይህ በሌላው ሕክምና ቢኖርም ወደ ማሕፀንና ጽንስ ሕክምና ሲመጣ ተጋንኖ ይታያል፡፡ ለምሳሌ ነፍሰጡሮች በምጥ መውለድ እየቻሉ በቀዶ ሕክምና እንዲወልዱ የመገፋፋት ነገር ይስተዋላል፡፡ ሌሎችም የሥነ ምግባር ጉድለቶች ይስተዋላሉ፡፡ ይህን እንደ ማኅበር መሪም ሆነ እንደ ባለሙያ እንዴት ያዩታል፡፡
ዶ/ር ደረጀ፡- የሥነ ምግባር ሁኔታን ከአባላት የሕክምና አተገባበር ጋር ስናይ፣ ማኅበሩ በግቦቹ ውስጥ ተገቢ ሥነ ምግባሩን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ በሚል አስቀምጦታል፡፡ እንደተባለው ያነሳሻቸው ችግሮች ይከሰታሉ፡፡ በትምህርት ቤት ውስጥ በቂ የሆነ የሕክምና ሥነ ምግባርን የተመለከተ ትምህርት አለመሰጠት እንደ አንድ ክፍተት አይተነዋል፡፡ ከዚህም በኃላ በተለያዩ የግል ሆስፒታሎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ባለሙያዎች ገንዘብ ከማግኘት አንጻር ብቻ በመገፋፋት ተገቢ ያልሆኑ ተግባራትን ሊያከናውኑ እንደሚችሉ ግንዛቤው አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆኑ ነገሮች ሊከሰቱ የሚችሉት ራስን ከጊዜው ጋር ካለማስኬድና ከግዴለሽነት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ አብዛኛው የማኅበሩ አባላት በተሰለፉበት ሙያ ተገቢውን አገልግሎት የሚሰጡ ቢሆንም ማኅበሩ አልፎ አልፎ ችግሩ እንዳለ ያምናል፡፡ ስለዚህ ይህንን ለመወጣት ሥነ ምግባርን በተመለከተ በሥራ አመራር ቦርድ የሚመራ ቋሚ ኮሚቴ አዋቅረናል፡፡ ኮሚቴው ከአሜሪካ የጽንስና የማሕፀን ሕክምና ማኅበር የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያገኝ ጠይቀን እያገዙን ነው፡፡ መሥራት የምንፈልገው በሥነ ተዋልዶ ጤና የሥነ ምግባር ደንብ እንዲኖረን፣ የማኅበሩ አባላት እንዲያውቁትና ተገዢ እንዲሆኑ ቅድመ ዝግጅት አድርገናል፡፡ ከዚህ ባለፈ ሥነ ምግባርን በተመለከተ በትምህርት አሰጣጥ ላይ ክፍተት አለ፡፡ ስለዚህ ለአባላት የተለያዩ ሥልጠናዎችን ከተከታታይ የሕክምና ትምህርት ጋር እንዲወስዱ፣ ባለሙያዎችን እየጋበዝን በሥነ ምግባር ላይ ያላቸው እውቀት የተሻለ እንዲሆን እየሠራን ነው፡፡ ሊሰመርበት የሚገባው ግን የእርጉዝ እናቶች ሕክምና እንደሌላው ሕክምና አለመሆኑ ነው፡፡ እርጉዝ ሴቶች በተፈጥሮ ደህና ይሁኑ እንጂ በያዙት ጽንስና ጽንሱ በሚያመጣው ስሜት የተነሳ ውስጣቸው ችግር አለ፡፡ ይህ እንደሌላው ሕመም በግልፅ ላይታይ ይችላል፡፡ ስለዚህ ጤናማ መስለው እየታዩ ውስጣቸው ግን ችግር ሊኖር ይችላል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጽንሱ ለብቻው አንድ ፍጡር ነው፡፡ ስለዚህ እናትየው ባላት የተለያየ ችግር ጽንስ ሊጎዳ ይችላል፡፡ በመሆኑም ሁለት ፍጡሮችን በአንድ ጊዜ ማከም ተጨማሪ ኃላፊነት ያስከትላል፡፡ ከዚህ በተረፈ ምጥ ላይ እንዲሁም ከምጥ በኋላ የሚከሰቱ ችግሮች ስላሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንኳን ብዙ ጊዜ ለየት ባለ መልኩ ተጋላጭነተ ያለበት የሕክምና ዘርፍ ነው፡፡ በአሜሪካ ብናይ ብዙዎች ወደ ማሕፀንና ጽንስ ሐኪምነት የማይሄዱት የኢንሹራንስ ክፍያቸው ስለሚበዛ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ልጅ ሲወለድ አተነፋፈሱ ትክክል ካልሆነ፣ ቤተሰብ ይከሳል፡፡ ኦክስጅን በሰውነቱ በትክክል ካልተዘዋወረ ሲያድግ አዕምሮው ሕመምተኛ ሊሆን ስለሚችል ሐኪሙ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በዓለም ደረጃም እንደሌላ የሕክምና ዘርፍ ቀላል አይደለም፡፡ ሁለተኛው ሁሉንም ዓይነት የእርጉዝ ሴቶች ችግር፣ በምጥ ወይም በእርግዝና ጊዜ የሚያጋጥማቸውን ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም እጅግ በሕክምናው መጥቀዋል በሚባሉት አገሮች ላይ ራሱ ማስቀረት አይቻልም፡፡ ይህ ማለት የእናቶች ሞት ዜሮ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ እኛ አገር ‘አንድም እናት አትሙት’ የሚባለውን ነገር አልስማማበትም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ የእናቶች ሞት በ1000 እናቶች በ412 ላይ ነው፡፡ እነ አሜሪካና ስዊድን የደረሱበት ደረጃም ከ1000 ሺሕ እናት ከ20-30 ነው፡፡ ስለዚህ አንድም እናት አትሙት ሳይሆን በቀላሉ ማወቅ፣ መከላከልና፣ ማከም በሚቻሉ ችግሮች አንድም እናት አትሙት እሚለው ያስማማናል፡፡ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በቅርቡ ያወጣው ጥናት ማሕፀንና ጽንስ አስመልክቶ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው ሁኔታ በቀላሉ መከላከልና ማከም የሚቻለው 82 በመቶ ብቻ ነው፡፡ 18 በመቶው አይቻልም፡፡ በአገራችን ያለው የባለሙያ እጥረት፣ የመድኃኒትና የሕክምና መስጫ አቅርቦት ሲታከልበት ደግሞ ችግሩ ገዘፍ ይላል፡፡ ለእርጉዝ እናቶች አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ እየተደረጉና የማኅበራችን አባላትም የሚችሉትን እየሠሩ ከሕክምናው ውስብስብነት አንጻር እናቶችም ሆኑ ጽንሱ ጉዳት ሊደርስባቸው ወይም ሊሞቱ ይችላሉ፡፡ ይህ ሲታይ ሁሉም ባለሙያ በግዴለሽነት አድርጎታል ወይም ሁሉም ባለሙያ በሁሉም ሁኔታ ላይ የሚገባውን ስላላደረገ የሕክምና ስህተት ተፈጽሟል ማለት አይደለም፡፡ የሚገባውን ያላደረገ ባለሙያ መጠየቅ አለበት፣ ያስጠይቃልም፡፡ ግን በአንጻሩ ልናያቸው የሚገቡ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ስለዚህ የሙያ ማኅበሩ ሥነ ምግባርን በተመለከተ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡ ከጤና ጥበቃና ከኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር በጋራ እየሠራን ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ማኅበሩ 25ኛ ዓመቱን ሲያከብር ጥናት የተደረገባቸውን ልዩ ልዩ ጉዳዮች አንስቷል፡፡ ከእናቶችና ጽንስ አንጻር ያለብን ችግር የትኛው ነው?
ዶ/ር ደረጀ፡- ከጥር 25-27 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ካፒታል ሆቴልና ስፓ የማኅበራችንን 25ኛ ዓመት ጉባዔና የአፍሪካ ፌዴሬሽን ሁለተኛ ጉባዔ አንድ ላይ አካሂደናል፡፡ በዚህ ዓመታዊ ጉባዔ 450 ኢትዮጵያውያንን ተሳትፈዋል፡፡ እንዲሁም ከኡጋንዳ፣ ከቤኒን፣ ከናይጄሪያ፣ ከማላዊ፣ ከሱዳንና ከሩዋንዳ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡ አቻ የሙያ ማኅበራችን ከአሜሪካ ኮሌጅ 12 ባለሙያ ልኮ ተከታታይ ትምህርት በመስጠት ተሳትፈዋል፡፡ በዓመታዊ ጉባዔያችን በዋነኛነት የጉባዔው መሪ ቃል በዘላቂ ልማት ግቦች የስነ ተዋልዶ ጤና ሁነኛ አማራጭና ተግዳሮቶቹ ለአፍሪካ ምንድን ናቸው የሚል ሲሆን፣ ከዓለም አቀፍ የማሕፀንና ጽንስ፣ ከአፍሪካ የማሕፀንና ጽንስ ሕክምና ፌዴሬሽን፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲሁም ከዓለም ጤና ድርጅት ፓናሊስቶች ነበሩ፡፡ በውይይቱ አማራጮችንና ፈተናዎችን አይተናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አራት የፓናል ውይይቶች ነበሩ፡፡ አንዱ በእርግዝና፣ ወሊድና ከወሊድ በኋላ በደም መፍሰስ ችግር ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽኖችና የየአገሩ ሕጎች ምን እንደሚመስሉ ተወያይተናል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ከእርግዝና በፊት የእናቶችን የሥነ ወሊድ ሁኔታን ማስተካከል፣ በእርግዝና ጊዜ የአመጋገብ ሁኔታ ከማስተካከል አኳያና እድሜያቸው ገፋ ብሎ የሚያረግዙ እናቶች የሚኖራቸው አመጋገብ ለጽንሱ ዕድገት ከሚኖረው ጠቀሜታ አንጻር ዓለምአቀፍ ተሞክሮዎች ምን እንደሚመስሉ ቀርቧል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የሕክምና ሥነ ምግባርን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ምንድን ናቸው? የኢትዮጵያ የጽንስና የማሕፀን ሐኪሞች ማኅበር ምን እየሠራ ነው? ምን ችግሮች አጋጠሙት የሚለውና የኢትዮጵያ የመድኃኒት የምግብና ጤና ክብካቤ ቁጥጥር ባለሥልጣን እንደተቆጣጣሪ ባለሥልጣን በአሰራሩ ላይ ምንድነው የሚጠብቀው? እስካሁንስ ያሉ ችግሮች ምንድን ናቸው? በሚል ውይይት ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቅድመ ኮንፍረንስና ከኮንፈረንስ በኋላ ተከታታይ ትምህርት አካሂደናል፡፡ እነዚህ በተለያዩ የማሕፀንና ጽንስ ችግሮች ላይ የተካሄዱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ አልትራሳውንድ፣ ሂስትሮስኮፒ (የውስጥ ማሕፀንን አጉልቶ የሚመለከት)፣ ሳይንሳዊ ጽሑፎች አቀራረብ፣ የማሕፀን ጫፍ ካንሰር፣ የማሕፀን ግድግዳ ካንሰርና ያለመውለድ ችግር በመሳሰሉ ላይ በበርካታ ዓለም አቀፍ ምሁራን ትምህርት ተሰጥቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 70 ያህል ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፣ ትንታኔ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ባሉ የሥነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች፣ በቤተሰብ ምጣኔ፣ በእርግዝና በወሊድና ከወሊድ በኋላ ባሉ ችግሮች፣ በውርጅና በተለያዩ የሴቶች የጤና ችግሮች ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡ 25ኛ ዓመታችንን ምክንያት በማድረግ ለማኅበሩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉ፣ ለማሕፀንና ጽንስ ሕክምና ትምህርት የሙያ ድርሻ ላበረከቱና በህክምናው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ላደረጉት ለሁለት አባላት ማለትም ለፕሮፌሰር ሉክማን ዮሱፍና ለዶ/ር ይርጉ ገብረ ሕይወት የሕይወት ዘመን ሽልማት ሰጥተናል፡፡ ሽልማቱ ባለፉት ሦስት አሥር ዓመታት በሙያቸው ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅና ለመስጠትና ወጣት የማኅበሩ አባላት ተገቢውን ሥነምግባር የጠበቀ ግልጋሎት ለማበርከት ተነሳሽነት እንዲኖራቸው ለማድረግ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በድንገተኛ ቀዶ ሕክምና የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በተመለከተ የማኅበሩ አስተዋኦ ምንድን ነው?
ዶ/ር ደረጀ፡- በቅርብ ጊዜ ያካሄድነው ጥናት አለ፡፡ በድንገተኛ ቀዶ ሕክምና የሰለጠኑ ባለሙያዎችና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተሰማርተው የማሕፀንና ጽንስ እንዲሁም የቀዶ ሕክምና ባለሙያ በሌለበት ተክተው እየሠሩ ነው፡፡ ቢሳካልንና ቢኖረን ሁሉም ጋር የማሕፀንና ጽንስ ሐኪም ቢኖር መልካም ነበር፡፡ ስላልቻልን ግን በማስተርስ ደረጃ ሰልጥነው እየሠሩ ነው፡፡ የእነዚህ ሥራ ምን ይመስላል በሚል በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ 97 ሆስፒታሎች ላይ የሥራ ትግበራ ዳሰሳ አድርገናል፡፡ በሽተኛ የመረመሩበትና ያከሙበት ሰንጠረዥ፣ ቀዶ ሕክምና ክፍል እንዴት እንደሚሠሩና ተያያዥ የሕክምና ሒደቶችን ዳሰናል፡፡
ሪፖርተር፡- ማሕፀንና ጽንስ ላይ ብቻ ነው? ወይስ አጠቃላይ ሕክምና ላይም?
ዶ/ር ደረጀ፡- በአብዛኛው የሰለጠኑት እርጉዝ እናቶችን እንዲረዱ ተብሎ ነው፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ ድንገተኛ ጉዳት ለደረሰባቸውና አስቸኳይ ቀዶ ሕክምና ይሠራሉ፡፡ በዋነኛነት ግን ማሕፀንና ጽንስ ላይ ነው፡፡ ሥልጠናው ላይ አብዛኛው አባላቶቻችን በአስተማሪነት ተሳትፈዋል፡፡ ስለሆነም አሠራሩ እስከምን ድረስ ተሳክቷል፣ ችግሮቹስ ምንድን ናቸው? በሚለው ዙሪያ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ጥናት ተደርጎ ውጤቱ ደርሶናል፡፡ ስለዚህ ጥሩ አሰራሮች እንዲቀጥሉ፣ ያጋጠሙ ችግሮች ደግሞ ባለሙያዎቹ የተሻለ ድጋፍ እየተደረገላቸው ባሉበት ቦታ እንዲሠሩ ማድረግ ነው፡፡ ይህ የተሻለ ሥራ ሰራን የምንለው ተግባር ነው፡፡ ሌላው ከእናት ወደ ጽንስ ኤችአይቪ እንዳይተላለፍ ላለፉት ሰባት ዓመታት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከሲዲሲ ኢትዮጵያ እንዲሁም ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በመሆን በ70 ጤና ተቋማት ላይ ደረጃውን የጠበቀ ሕክምና እንዲሰጥ እገዛ አድርገናል፡፡ ከ48 እስከ 50 የሚሆኑ አርቲክሎችም ታትመዋል፡፡