Saturday, June 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርጥ ቡናዎች ጉባዔ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ እንዲያንሰራራ ተስፋ ተጥሎበታል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአንድ ዓመት ያህል በአገሪቱ የተካሄደው ሕዝባዊ ተቃውሞ የአገሪቱ የቡና ወጪ ንግድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ መቆየቱ ይታመናል፡፡ ምንም እንኳ ቡና እየተላከም ቢሆን የቀድሞውን ያህል እየወጣ እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ ወደ ውጭ የሚላከውን ቡና ይበልጥ ለማሻሻል እንደሚረዳ ተስፋ የተደረገበት ‹‹አፍሪካን ፋይን ኮፊስ ኮንፈረንስ ኤንድ ኤግዚቢሽን›› የተባለው ጉባዔ፣ ከወዲሁ አንድ ሺሕ ያህል የውጭ ታዳሚዎች እንደሚሳተፉበት ይጠበቃል፡፡

በአፍሪካ የምርጥ ቡናዎች ማኅበር (አፍሪካን ፋይን ኮፊስ አሶሲዬሽን አፍሪካ) አማካይነት በየዓመቱ በአባል አገሮች እየተዟዟረ የሚካሄደው ጉባዔ ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በተለያዩ ዝግጅቶች ታጅቦ ተሰናድቷል፡፡ በይፋ የሚከፈተው ዛሬ፣ የካቲት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ቢሆንም ካለፈው እሑድ ጀምሮ ግን የተለያዩ ዝግጅቶች ሲካሄዱበት ቆይቷል፡፡

ጉባዔው ለኢትዮጵያ የቡና ወጪ ንግድ ተስፋ የተጣለበት፣ በኢትዮጵያ በተፈጠረው ፖለቲካዊ ትኩሳት ምክንያት የውጭ ገዢዎች ከአገሪቱ የሚፈለገውን ያህል ቡና ማግኘት እንደማይቻል ያደረባቸውን ሥጋት ለመቅረፍ እንደሚረዳ ስለታመነበት መሆኑን፣ የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢና የኤስኤ ባገርሽ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብደላ ባገርሽ ጠቅሰዋል፡፡ አብዛኞቹ የውጭ ገዥዎች በአገሪቱ ታድመው ሁኔታውን ተመልክተው ቡና ለመግዛት ሥጋት እንዳይገባቸው ለማድረግ እንደሚረዳ ለሪፖርተር በሰጡት መግለጫ ጠቅሰዋል፡፡

ጉባዔው ይካሄዳል በተባለበት ጊዜ ሳይዛነፍ ከየካቲት 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ አቶ አብደላ ገልጸዋል፡፡ ከወራት በፊት ጉባዔው በኢትዮጵያ እንደሚካሄድ ይፋ ቢደረግም በአገሪቱ የተከሰተው ሕዝባዊ ተቃውሞና አለመረጋጋት፣ የውጭ ተዳሚዎች እንዳይገኙ እንቅፋት ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት ፈጥሯል፡፡ ማኅበሩ ግን በኢትዮጵያ ጉባዔው ያለችግር መካሄድ እንደሚችል ማረጋገጫ በመስጠት የውጭ ተሳታፊዎች እንዲገኙ ጥሪ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከውጭ ከሚመጡት ባሻገር በአገር ውስጥ በቡና መስክ የተሰማሩ አካላትም በብዛት እንዲታደሙበት ጥሪ ቀርቧል፡፡

የአገሪቱ ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቦ ከሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ባሻገር በአገር ውስጥ ያለው የገበያ ድርሻም ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህም በላይ በቡና እርሻና በንግድ ሥራ የተሰማሩ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎችም የህልውናቸው መሠረት በመሆኑ ፋይዳው በእጅጉ የሚታወቅ ቢሆንም፣ በተከታታይ ዓመታት በተለይ ለውጭ ከሚቀርበው የቡና ምርት እየተገኘ ያለው የውጭ ምንዛሪ ገቢ እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡  

የቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣን በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ በግማሽ ዓመቱ 98,561 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ይቀርባል ተብሎ ሲጠበቅ ማቅረብ የተቻለው ግን 85,425 ቶን ሆኗል፡፡ ከገቢ አንፃርም ቡና ያስገኛል ተብሎ የሚጠበቀው መጠን 385 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ የተገኘው ግን 315.7 ሚሊዮን ዶላር በመሆኑ ገቢው ከዕቅዱ በ19 በመቶ ያህል ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በአንፃሩ በ2008 ግማሽ ዓመት ለውጭ ገበያ የቀረበው ቡና መጠን 87,785 ቶን ሲሆን፣  በ2009 በጀት ዓመት ግማሽ ዓመት ወደ ውጭ ከተላከው ጋር ሲነፃፀር በ2,332 ቶን ወይም በ2.7 በመቶ የቀነሰ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡  ከገቢ አንፃር የተገኘው የውጭ ምንዛሪ በዘንድሮ ግማሽ ዓመት የ2.8 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ባለፉት ጥቂት ወራት የዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ መጠነኛ መሻሻል በማሳየቱ እንደሆነ ባለሥልጣኑ ጠቅሷል፡፡

የባለሥልጣኑ መረጃ ይህን ጨምሮ ከዚህ ቀደም ዕርምጃ በወሰደባቸው ላኪዎች አማካይት የውጭ ገበያው በተፈለገው መጠን ሊሳካ እንዳልቻለ ይጠቁማል፡፡ ባለፉት ዓመታት በሕገወጥ መንገድ የኤክስፖርት ቡና ምርት ከገበያ ገዝተው መላክ ባልቻሉ ላኪዎች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ ከመወሰዱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የባለሥልጣኑ የስድስት ወራት ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በምርት ገበያው ያላቸውን ወንበር በመጠቀም ምርት የገዙላቸው አንዳንድ የምርት ገበያው አገናኝ አባላት በሆኑ ላኪዎች ላይ የተወሰደው የዕግድ ዕርምጃ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡

የዓለም የቡና ገበያ ዋጋ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው የተሻለ እንደሆነ የሚጠቁመው የባለሥልጣኑ ሪፖርት፣ ቡና ላኪዎች በበጀት ዓመቱ ሦስት ወራት  (ከሐምሌ እስከ መስከረም) ቀደም ብሎ የዓለም ቡና ዋጋ ዝቅተኛ በነበረበት ወቅት ላይ ኮንትራት በመፈጸማቸው ከአገር ውስጥ ዋጋ ጋር መናበብና በግዥ መሟላት አለመቻሉ ለአፈጻጸሙ መቀነስ ምክንያት ሆኖ ቀርቧል፡፡

ባለፈው ዓመት በተከሰተው የአየር ጠባይ ለውጥና ድርቅ ምክንያት በቡና ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፈጠሩ፣ ጥቂት ላኪዎች የገቡትን ውል ለማክበር ተገቢውን ጥረት አለማድረግ፣ ቡና ገዥ ኩባንያዎችም አዲሱን ምርት የመጠበቅ አዝማሚያ ማሳየታቸው ለቡና ደካማ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ምክንያት ሆነው ቀርቧል፡፡ ላኪዎች በበኩላቸው ግን በአገሪቱ የተከሰተው ግርግርም አስተዋጽኦ ማበርከቱን እየተናገሩ ነው፡፡

                                                    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች