– ሦስት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ተረክቧል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ለአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ የሚውል ቦታ በመነሻ የሊዝ ዋጋ እንዲሰጠው በመወሰነው መሠረት ንግድ ምክር ቤቱ ቦታውን መረከቡ ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ንግድ ምክር ቤቱ የራሱን ሕንፃ ለመገንባት ባቀረበው የቦታ ጥያቄ መሠረት መገናኛ አካባቢ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ጽሕፈት ቤት አጠገብ በአነስተኛ የሊዝ ዋጋ እንዲሰጠው የተወሰነለት ቦታ ሦስት ሺሕ ካሬ ሜትር ስፋት አለው፡፡
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፣ አስተዳደሩ ለንግድ ምክር ቤቱ የሕንፃ ግንባታ የፈቀደለት ቦታ እንዲሰጠው የተወሰነው በካሬ ሜትር 4,140 ብር የሊዝ ዋጋ መሠረት ነው፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ በተረከበው ቦታ አካባቢ ካለው የሊዝ ዋጋ እጅግ ዝቅ ባለ ዋጋ እንዲተመንለት አስተዳደሩ ከፍተኛ እገዛ አድርጎለታል ተብሏል፡፡
ለ60 ዓመታት በሚቆይ ሊዝ የተሰጠው ይህ ቦታ ጠቅላላ የሊዝ ዋጋው 12.4 ሚሊዮን ብር መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ በ30 ዓመት ተከፍሎ እንደሚያልቅ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ መሠረት ከጠቅላላው የሊዝ ዋጋ ውስጥ የቅድሚያ ክፍያውን 20 በመቶ ገንዘብ ማለትም የ2.1 ሚሊዮን ብር ሒሳብ ንግድ ምክር ቤቱ መክፈሉን አስታውቋል፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ የራሱን የሕንፃ ዲዛይን ካሠራ ከአራት ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ የሚታወቅ ሲሆን፣ ለግንባታ የሚሆነውን ቦታ ለማግኘት ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ሲጠባበቅ ቆይቷል፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ በማግኘቱ ወደ ግንባታ ለመግባት መዘጋጀቱን አቶ ጌታቸው ገልጸው፣ አርክቴክቶችን በማወዳደር ከዚህ ቀደም መርጦት በነበረው የሕንፃ ዲዛይን ላይ መጠነኛ ማስተካከያዎች ከተደረጉ በኋላ ወደ ግንባታ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡
በዲዛይኑ ላይ ይደረጋሉ ተብለው ከሚጠበቁ ለውጦች መካከል ቀደም ብሎ G+10 የነበረውን የሕንፃ ወለል ብዛት አሁን G+11 ማድረግ አንዱ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ግንባታው በሚካሄድበት አካባቢ መገንባት የሚፈቀደው የሕንፃ ወለል ብዛት ከG+10 በላይ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ዲዛይኑን ለማስተካከል የዲዛይን ክለሳ ሥራ መጀመሩን አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል፡፡
ዲዛይን የማስተካከል ሥራውንና የግንባታ ፈቃድ ሒደቱን በሦስት ወራት ውስጥ አጠናቆ ለግንባታ ተቋራጮች ጨረታ እንደሚወጣ ከዋና ጸሐፊው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የግንባታ ሥራውም በመጪው ዓመት ለማስጀመር መታቀዱን፣ ለሕንፃው ግንባታ የሚውለውን ወጪም ንግድ ምክር ቤቱ ከሚያዘጋጃቸው የገቢ ማሰባሰቢያዎችና ከተለያዩ ምንጮች ለመሸፈን ማቀዱን አቶ ጌታቸው ጠቅሰዋል፡፡
ለንግድ ምክር ቤቱ ዋና መሥሪያ ቤትነት የሚውለው ሕንፃ፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ክፍሎች እንደሚኖሩት ታውቋል፡፡ አነስተኛ የንግድ ዓውደ ርዕይ ማካሄጃ አዳራሽን ጨምሮ፣ የባንክና የኢንሹራንስ ድርጅቶች የሚጠቀሙባቸው ክፍሎችም ይኖሩታል፡፡ ከንግድና ኢንቨስትመንት ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች የሚሰጡበት አዲሱ ሕንፃ፣ ለንግድ ኅብረተሰቡ መሰብሰቢያነት የሚያገለግሉ፣ አዳራሾችም ይኖሩታል ተብሏል፡፡
የዚህ ሕንፃ ግንባታ ዕውን መሆን ንግድ ምክር ቤቱ ከ70 ዓመታት ቆይታው በኋላ የራሱ ሕንፃ ባለቤት እንዲሆን ያስችለዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለሕንፃው ግንባታ ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግ ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት፣ ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሕንፃ የተወሰኑ ክፍሎች በመጋራት እየተገለገለ ይገኛል፡፡ ለአንዳንድ የሥራ ክፍሎቹ የሚጠቀሙባቸውን ቢሮዎች ከሌሎች ሕንፃዎች ተከራይቶ ሲገለገል ቆይቷል፡፡ ‹‹ይህም ሆኖ በቢሮ እጥረትና ምክንያት መሥራት የምንችለውን ያህል ልንሠራ አላስቻልንም፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ለቢሮዎች ኪራይ በዓመት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ምክር ቤቱ እንደሚያወጣ ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በከተማና በክልል ደረጃ ከተዋቀሩት ንግድ ምክር ቤቶች ውስጥ የራሳቸው ሕንፃ ባለቤት እንደሆኑ የሚጠቀሱት የአዳማ፣ የድሬዳዋና የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ናቸው፡፡