Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርሥልጣን ለማግኘት ስንል የፈጠርናቸውን ቅራኔዎች ሥልጣን ካገኘን በኋላ ለማስወገድ ይከብዳል

ሥልጣን ለማግኘት ስንል የፈጠርናቸውን ቅራኔዎች ሥልጣን ካገኘን በኋላ ለማስወገድ ይከብዳል

ቀን:

በሳሙኤል ረጋሳ

የአገራችን ሰላም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አስተማማኝ መሠረት ላይ የቆመ አይደለም፡፡ ሕዝቡም በመጪው ጊዜ ምንም የተረጋገጠ ተስፋ ሳይኖረው ወደፊት የሚፈጠረውን ሁኔታ በፅሞና እየተከታተለ ነው፡፡ የደርግን አሥራ ሰባት ዓመታት የእልቂትና የመከራ ዘመን አልፈን ለጊዜውም ቢሆን አንፃራዊ ሰላም እናገኛለን ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፡፡ ነገር ግን አሁንም ለእልቂት የሚጋብዝ ሌላ የጭካኔና የመከራ ዘመን ሊያስከትል የሚችል አዝማሚያ መኖሩን መገመት ይቻላል፡፡

በዚህ ሥጋት መነሻ ይመስላል ሰሞኑን የአገራችን የሃይማኖት አባቶች ጉዳዩ አሳስቦናል በሚል ስሜት ሰላምን ለማውረድ እርቅ እንፈጽማለን በማለት ደፋ ቀና እያሉ ያሉት፡፡ በሐሳብ ደረጃ ይኼ የተቀደሰ ተግባር ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸው ማኅበራዊና መንፈሳዊ ደረጃም ይኼንን እንዲፈጽሙ ያስገድዳቸዋል፡፡ ነገሩን በሚዲያ እንደተከታተልነው ግን ድፍንፍን ባለና ግልጽነት በሌለው መንገድ ነው የተላለፈው፡፡ ሰላምን የሚያወርዱት ማንንና ማንን አስታርቀው ነው? ሊያስማሙዋቸው ያሰቡት ወገኖችስ በጉዳዩ ላይ ምን ዓይነት አቋም አላቸው? የተጣላ ሰው የለምና የምታስታርቁት ሰው የለም ቢባሉስ? ይኼንን ለመዘርዘር ያልፈለጉት ተስማሚዎቹ ወገኖች በግልጽም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ አለ ብለው በማሰባቸው መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ ለነገሩማ በየጊዜው የተከሰቱትን ቅራኔዎች አንድ ጊዜ እንኳን ለመፍታት ያለመሞከራችን ሁኔታዎችን ያወሳሰበ ስለሆነ ለእርቅ ያስቸግራሉ ብሎ መፍራት ተገቢ ነው፡፡

- Advertisement -

በአሁኑ ጊዜ መንግሥት፣ ተቃዋሚዎችና ሕዝቡ አንዱ ሌላውን እየወቀሱ ነው፡፡ ለወቀሳ ያደረሳቸውም ቅራኔ ሰፊ ነው፡፡ ለጊዜው የሕዝቡ ብሶት ብዙ ብዙ የተባለለት ስለሆነ እሱን ወደ ጎን ትተነው፣ በመንግሥትና በተቃዋሚዎች መሀል ያለውን ብቻ እንመልከት፡፡

ሁልጊዜ በመንግሥትና በተቃዋሚዎች መካከል ተፈጥሮአዊ፣ ሊቀርና ሊወገድ የማይችል እርቅም የማያስፈልገው የሐሳብ ልዩነት ይኖራል፡፡ ይኼ የርዕዮተ ዓለማዊና የአመለካከት ልዩነት ጉዳይ ሁልጊዜ የማይታገድና ተገቢ በመሆኑ ሊኖር የሚገባ ነው፡፡ ነገር ግን ይኼ ልዩነት ገደቡን አልፎ ወደ ባላንጣነት ወይም ወደ ግጭትና ብጥብጥ አምርቶ የአገሪቱን ህልውና የሚፈታተን ከሆነ ሀይ ባይና አስታራቂ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የአገራችንም ሁኔታ ገደቡን ስላለፈ ነው የሃይማኖት አባቶች በነገሩ ለመግባት የፈለጉት፡፡ እስቲ ከአንድ ጥያቄ እንነሳ፡፡

በመጀመሪያ መንግሥትና ተቃዋሚዎችን አደራድሮ ችግሮቹን መፍታት ይቻላል?  ምንም እንኳን ለዚህ ጥያቄ ቁርጥ ያለ መልስ ማስቀመጥ ከባድና ውስብስብ ቢሆንም መልሱ አዎን ይቻላል ነው፡፡ ይኼ ከባድ ጥያቄ ከተመለሰ በተለያየ ጊዜ ከአንገት ይሁን ከአንጀት ባይታወቅም ከተለያዩ አካላት ሲነሳ የነበረው የብሔራዊ እርቅ ጉዳይ አንዱ ዋና ምዕራፍ ይጠቃለላል፡፡ እውነተኛ እርቅ ከልብ በተፈለገበት ቦታ ሁሉ አለ፡፡ ነገር ግን ከሌላው ጋር እርቅ የሚፈልግ ሁሉ በመጀመሪያ ከራሱ ጋር መታረቅ አለበት፡፡ ዋናውና ከባዱ የእርቅ ደረጃም ከራስ ጋር መታረቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ሌላ ገላጋይ ሽማግሌ የሌለበት ከህሊና ጋር የሚደረግ ሙግት በመሆኑ ነው፡፡ ከራስ ጋር ለመታረቅ የራስን ጥፋትም ሆነ ስህተት ማወቅና መቀበል የመጀመሪያው ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው ጉዳይ የሌሎችን ስህተትም ሆነ ጥፋት የማናይበት መንገድ የእኛ ትክክል ነው ብለን በምናስበው መንገድ ብቻ መሆን እንደሌለበት ነው፡፡ እኛ ትክክል ነው ብለን የምናምንባቸው ብዙ ጉዳዮች ስህተት ሆነው ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በብዙኃን ዘንድ ተቀባይነት ያገኘን እውነት ወይም እውነት መሳይ ነገሮችን ወደ ጎን ገፍተን የእኔ ካልሆነ ብሎ ግትር አቋም መያዝ አደገኛ የሆነ የሕይወት ፍልስፍና ነው፡፡

አንዳንድ ጊዜ በሁሉም የሕይወት ዘርፍ ውስጥ በሁለቱም በኩል አስታራቂ ሐሳብ ማግኘት የማይቻልበት ጊዜ ሊኖር ይችላል፡፡ የዚህ ዓይነት መንታ ሐሳቦች ሲገጥሙን ጉዳዩን በይደር አቆይተን በቂና አሳማኝ መረጃዎች ማሰባሰብ ያስፈልጋል፡፡ እኛ ለጊዜው ሳናውቀው ቀርተን ነው እንጂ መፍትሔ የሌለው ችግርና መድኃኒት የሌለው በሽታ በዚህ ዓለም ላይ የለም፡፡ የጊዜ ጉዳይና የምርምር ማነስ እንጂ ሁለቱም ውሎ አድሮ ይገኛል፡፡ እየተገኘም ነው፡፡ በዚህ እሳቤ ከራሳችን ጋር ከታረቅን ሌሎችን መታረቅም ሆነ ማስታረቅ የቀለለ ይሆናል፡፡ ቀጥሎ በተዘረዘሩት ቀደምት ኢትዮጵያውያን አባቶች ላይ ያለንን ሐሳብ እስቲ እንመርምር፡፡

ኢትዮጵያ በመንግሥትነት መተዳደር ከጀመረች ጊዜ ጀምሮ እስከ አፄ ኃይለ ሥላሴ ድረስ እጅግ በርካታ ነገሥታት ተቀያይረው አገሪቱን ገዝተዋል፡፡ ነገር ግን መቁጠር የሚችል ወደኋላ እስከ ንግሥተ ሳባ ቢቆጥር በጦር ሜዳ ከሞቱት ውጪ የሁሉም አሟሟት በግልጽ አልተነገረም፡፡ አንዳቸውንም እንደ አንድ ተራ ደሃ እንኳን  ሕዝቡ ወጥቶ አልቀበራቸውም፡፡ ራስ አሉላ፣ ራስ ጎበና፣ ራስ አባተ፣ ደጃዝማች ባልቻ፣ ሊጋባ በየነ፣ አብዲሳ አጋ፣ . . . ወዘተ በተለያዩ የጦር ሜዳዎች ከጣሊያኖች ከደረሱትና ከሌሎች በውጭና በውስጥ የጀብዱ ሥራን በከፍተኛ ተጋድሎ ፈጽመው የመጨረሻውን የሕይወት ዘመናቸውን ከሚገባቸው ክብር ወደ ተራ ሰውነት ወርደው ነው የኖሩት፡፡ ራስ ሥዩምና ራስ ሙሉጌታ በሰሜኑ የኢጣልያን ጦርነት የኢትዮጵያ ዋና የጦር አዛዦች ነበሩ፡፡ ግን ሁለቱም በወገናቸው ጥይት ነው የተገደሉት፡፡ ራስ መስፍን ስለሺ፣ ራስ አበበ አረጋይ፣ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ፣ በጅሮንድ ታከለ ወልደ ኃዋርያት፣ ሻለቃ አብዲሳ አጋ፣ ሜጀር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ ኮሎኔል ቢሹ ገብረ ተክሌ፣ ሜጄር ጄኔራል ኃየሎም አርዓያ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልካቸው መኮንን፣ . . . ወዘተ በሚቻላቸው ሁሉ ወቅቱና የጊዜው ሁኔታ በሚጠይቀው መሠረት በከፍተኛ የአርበኝነትና የዲፕሎማሲ ሥራዎችን በቆራጥነት ከፈጸሙ በኋላ፣ ሁሉም ያለጥፋትና ያለፍርድ የተገደሉት በወገኖቻቸው ጥይት ነው፡፡

ከላይ ስለተጠቀሱት ባለሥልጣናት ሁላችንም ያለን አረዳድ አንድ ዓይነት ነው? የምንደግፋቸውና የምንቃወማቸው ቢኖሩ አይገርምም፡፡ ነገር ግን እነሱ በነበሩበት ዘመን ወቅቱንና የነበሩበትን የፖለቲካ ሁኔታ ተጨባጩን ነገር ይዘው ኢትዮጵያን ለመታደግ ተገቢውን መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ሁሉም የየራሳቸው ጉድለት ይኖራቸዋል እንኳን ብንል፣ ኢትዮጵያን ከእነ ድህነትዋም ቢሆን በክብር አቆይተውልናል፡፡ ያለፉት አገራዊ ጉዳዮች ሁሉ የሚለኩት በወቅቱ በነበረው ተጨባጭ ሁኔታ እንጂ ዛሬ ላይ ቆመን በምንሰጠው ፖለቲካዊ ትንታኔ አይደለም፡፡ የእነዚህ ሰዎች ሥራ ከፊልም ቢሆን የማይጥመን ካለን ምክንያታችንን እናስቀመጥ፡፡ እነዚህን ሰዎች የምንደግፋቸው ወይም የምንቃወማቸው በብሔር ማንነታቸው፣ በመደብ ጀርባቸው፣ በሃይማኖታቸው ወይም በእኔ ብሔር ላይ በደል ፈጽመዋል ወይም ጠቁመዋል ከሚል መነሻ ከሆነ ዋናውን ግንድ ጉዳይ ትተን ቅርንጫፉ ላይ እየተንጠላጠልን ስለሆነ፣ መቼም ቢሆን ሐሳባችንን የምናስታርቅበት መነሻ ሐሳብ አይኖረንም፡፡

በጎ በጎውን ስናስብ እነዚህ ሰዎች ሁሉም ክብርና ሞገስ የሚገባቸው እንጂ፣ ሞተው ቀባሪ ማጣት ወይም በወገኖቻቸው ጥይት ተደብድበው መሞት የሚገባቸው አልነበሩም፡፡ በእነዚህ ሰዎች ጉዳይ ለመስማማት ብንሞክር ወደፊት ለምናደርጋቸው የእርቅ ድርድር ጠቃሚ ጉዳዮችን እንማርበታለን፡፡ አገራችን ለክፉ ቀን ልጆችዋና ለአንጋፋ ባለታሪኮቿ ውለታ መክፈል የማትችል ውለታ ቢስ አድርጓታል፡፡

ከላይ የገለጽናቸው ቀደምት ኢትዮጵያውያን ከእኛ ጊዜ ያላነሰ የእርስ በርስ ቅራኔዎች ነበሩባቸው፡፡ ለአብነት ያህል ሊጋባ በየነ በፖለቲካ ቁርሾ ምክንያት ብቻ በአደባባይ እንደ ሌባ አርባ ጅራፍ ተገርፈዋል፡፡ ያም ሆኖ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር ለሁለተኛ ጊዜ ሲመጣ ይኼን በደል ከልባቸው አውጥተው ወደ ጦር ግንባር ዘምተው ድንቅ ጅብዱ ከፈጸሙ በኋላ እዚያው በጦርነቱ ላይ ተሰውተዋል፡፡ አገሪቷ የቆየችው በእንዲህ ያለ መስዋዕትነት ነው፡፡ ከእኚህ ሰው ምን እንማር ይሆን? ሊጋባው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት በመጀመሪያ ከራሳቸው ጋር ታርቀው በመቀጠልም በዳዮቻቸውን ይቅር ብለው ነው፡፡ መንግሥትን መቀየም፣ መጥላት፣ መታሰር፣ ከሥልጣን መገፋት፣ . . . ሁሉ እያለ ነው ለአገር ጉዳይ አንድ የሚሆኑት፡፡ የፈለገውን ያህል መቃወም ቢኖርም በአገር ጉዳይ እኩል ይዋጋሉ፡፡ እኩል ይሞታሉ፡፡ እኩል ይሰደዳሉ፡፡ ልንከተለው የሚገባን የአባቶቻችን ፈለግ ይኼ ነው፡፡ እነዚህ ጥቂት ማሳያዎች እንጂ ብዙ ሺዎች አሉ፡፡

እንግዲህ ለሥልጣን ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ለሰላማችንና ለነፃነታችን ስንል ብሔራዊ እርቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ለብሔራዊ እርቅ ለመዘጋጀት መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚ ድርጅቶች መጀመሪያ ከራሳቸው ጋር መታረቅ አለባቸው፡፡ ከራስ ጋር ለመታረቅ ደግሞ በቅድሚያ ከሌሎች የሚለዩንን ነጥቦች አውቀን፣ ለምን እንደሚለዩንም እንወቅ፡፡ የሚያስማሙ ነገሮች እንዲበዙ እናድርግ፡፡ ጥቂት የሚለዩን ቅርንጫፎች ወይም ዋና የምንላቸውም ቢኖሩ በተስማማንባቸው ግንድ ጉዳዮች ዙሪያ ተሰባስበን ቀሪዎቹን በሒደት እንፈታለን፡፡ የማይጎዱንና አገሪቱን ለችግር የማያጋልጡ ከሆነም በልዩነት ይዘናቸው ልንዘልቅ እንችላለን፡፡ ያን ጊዜ የሸፈነንን ጉም ጥሰን መውጣት ስንጀምር በምናየው የብርሃን ጭላንጭል እየተመራን ሁሉንም ችግሮች እንቀርፋለን፣ የሚፈቃቀርና የሚከባበር ዜጋ እንፈጥራለን፡፡ ለማንኛውም ከብሔራዊ እርቅ በፊት መታረቅ ከራስ ጋር ነው፡፡

ሁልጊዜ ስለልዩነታችን ብቻ የምናስብና የምናወራ ከሆነ ስለአንድነታችን ያለን ስሜት በየጊዜው እየተሸረሸረና እየተነነ ከአዕምሮአችን ይጠፋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያለውም ችግር ይኼ ነው፡፡ አሁን አሁን እንደምናየው ጥላቻዎች ከምናስበው በላይ ስለከረሩ ገሚሱ አገሪቱን በባላ ደግፎ የያዘ ሲመስለው፣ ገሚሱ ደግሞ የሚቃወመውን ክፍል ብቻ ሳይሆን አገሪቱም አብራ እንድትንኮታኮት ይመኛል፡፡ እነዚህ ሁለቱም ጽንፎች እኩል አደገኛ ናቸው፡፡

ስለእርቅ ስናስብ ሁልጊዜ ከተደራዳሪዎቹ መካከል ክፉ የሚያስብና በጎ የሚያስብ ወገን ይኖራል ብለን መገመት አለብን፡፡ ነገር ግን ከማንኛውም ክፉ ሰው ልቦና ጥቂት በጎ ነገር አይጠፋም፡፡ ይቺኑ ጥቂቷን በጎ ነገር ይዘን እንዋሀደውና ክፉ ነገሮችን ከልቡ እናውጣለት፡፡ የሕዝባችን የጋራ የሆነ አገራዊ ፍቅርና መተማመን ከወትሮው በእጅጉ ተጎድቷል፡፡ በአንድ ባለሥልጣን የአንድ ጊዜ የበዓል ዲስኩር ወደ ነበረበት ሊመለስ አይችልም፡፡ የካድሬዎች የፖለቲካ ትምህርትም አልፈየደም፡፡ ሕዝቡ ልቦናውና መንፈሱ መዋሀድ አለበት፡፡ ይኼ ደግሞ የረዥም ጊዜ ሥራ ነው፡፡ ሥራው የሚሠራው በመተማመን ላይ በተመሠረተ ተከታታይ ውይይት ነው፡፡ አንዱ የሌላውን ሐሳብ የማይጫንበት በመርህ ላይ የተመሠረተ የመከባበር ውይይት መኖር አለበት፡፡

ከቀድሞ ጀምሮ በአገራችን ሥልጣን ለመያዝ የሚጥሩ ሰዎች መነሻቸው የሕዝብን ልዩነት ማስፋትና ልዩነቱን ተጠቅሞ ለሥልጣን መብቃት ነው፡፡ ሥልጣን  ከያዙ በኋላ ደግሞ ግዛታቸው እንዳይጠብ ልዩነቱን ቀንሶ አንድነቱን ለመመለስ ይባዝናሉ፡፡ ክፉ አሳቢዎችም በጎ መስለው ይቀርባሉ፡፡ እነዚህ ስናሸንፍና ስንሸነፍ የሚኖሩን ተፃራሪ አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ በጉልበት ሥልጣን ለመያዝ የሚያጣላ ቅራኔ መፍጠር ግድ ነው፡፡ ሥልጣን ለማግኘት ስንል የፈጠርናቸውን ቅራኔዎች ሥልጣን ካገኘን በኃላ ለማስወገድ ከባድ ነው፡፡   

የጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትና የሸዋው ምንሊክ በግዛት ጉዳይ ተጣልተው እምባቦ ላይ ጦርነት ገጥመው ነበር፡፡ በጦርነቱ ብዙ ሰው ካለቀ በኋላ ምንሊክ አሸንፈው ተክለ ሃይማኖትን ማርከው በክብር ወደ ቤተ መንግሥታቸው አምጥተው አኖሩአቸው፡፡ አብረው ከመቆየት የተነሳ የጦርነቱ ጉዳይ እየተረሳ ወዳጅነታቸው በርትቶ ነበር፡፡ አንድ ቀን በጨዋታ በጨዋታ የጦርነቱ ነገር ተነሳና አፄ ምንሊክ ለተክለ ሃይማኖት፣ ‹‹እኔ ማርኬዎ ክብር ሳይጓደል በንጉሥ ደረጃ አኖሬዎታለሁ፡፡ ለመሆኑ እርስዎ ቢሆኑ እንደኔ ያደርጉ ኖሯል?›› ብለው ጠየቁዋቸው፡፡ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትም፣ ‹‹አላደርገውም፣ እኔ ብሆን ሥጋህን ቆራርጬ ለአውሬ ሰጥቼ ነበር የምመለሰው፤›› አሉ፡፡ ምንሊክም፣ ‹‹ታዲያ የእኔ ነው የእርስዎ የሚሻል?›› ብለው ጠየቁዋቸው፡፡ ተክለ ሃይማኖትም፣ ‹‹ሲያሸንፉ የእርስዎ፣ ሲሸንፉ የእኔ ይሻላል፤›› አሉዋቸው ይባላል፡፡ በጭካኔና በጥፋት አሸንፎ ከድል በኋላ ገራገር የመምሰል ጉዳይ አሁንም ቢሆን በዓለም ላይ የፖለቲካ መርህ የሆነ ይመስላል፡፡ ሥልጣን ለመያዝ የፈጠርነውን ቅራኔ ሥልጣን ለማቆየት ማስወገድ የግድ ነው፡፡

የሃይማኖት አባቶቹ እርቅ ፈጽመው ሰላም ለማውረድ ሲያስቡ በመጀመሪያ መንግሥትና ተቃዋሚዎች ከራሳቸው ጋር ለመታረቅ ፈቃደኛ ሆነው መገኘት አለባቸው፡፡ መንግሥት ከራሱ ጋር መታረቁን የምናውቀው የሚቃወሙትን ሁሉ በክፉ ልቦና ተነሳስተው ሥልጣኔን በጉልበት ሊነጥቁኝ ነው ብሎ ማሰብን ማቆም ሲችል ነው፡፡ የአገሪቱን ሀብትና ንብረት ጥቂት የመንግሥት ሰዎች ሲቀራመቱትና ሕንፃ በሕንፃ ሲሆኑ፣ ቤተሰቦቻቸውን አሜሪካና አውሮፓ ወስደው ሲያምነሸንሹና ሲያሳክሙ መንግሥት የሚወስደው ዕርምጃ ሲታይና ሲታወቅ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደርን ችግር በሕዝብ ላይ አሳድሮት ያለው ከፍተኛ ቀውስና መንግሥት እንደ ሕዝቡ በአፍ ከማውገዝ አልፎ ከቋቱ ጠብ የሚል ነገር ሲኖር ነው፡፡ አንዳንድ ለፖለቲካ ፍጆታ የሚውሉ ጥቃቅን ሥራዎች ቢሠሩም ያዝ ለቀቅ እንጂ አስተማማኝነት የላቸውም፡፡ የቀረው ቀርቶ ለመንግሥት ሠራተኞች ትራንስፖርት አቅርቤያለሁ ባለበት ሁኔታ እንኳን ሠራተኞቹ የሥራ ሰዓታቸውን አክብረው በሰዓት መግባትና ተገቢውን ሥራ ሠርቶ በሰዓት የሚወጡ ሁሉም አይደሉም፡፡ መንግሥት በአብዛኛው ሥራውን በሕግ አግባብና ለሕዝብ በሚጠቅም መንገድ መከወን አልቻለም፡፡ ብሔራዊ እርቁን ለማምጣት በመጀመሪያ ከራሱ ጋር ታርቆ ጉዳዩቹን መስመር መያዝ አለበት፡፡ እነዚህንና ሌሎች መሰል ችግሮችን ለመፈጸም ጊዜ የሚወስድና በቂ የሰው ኃይል ባይኖረው እንኳን፣ የችግሮቹን መኖር አምኖ የመፍትሔያቸውን ጉዳይ ለድርድር ማቅረብ አለበት፡፡  

ተቃዋሚ ድርጅቶችም መንግሥት ለሥልጣን ያለውን ጉጉት አይተው ሥልጣን ለመጋራት ወይም ለመንጠቅ የሚፈልጉት በኃይልና በብጥብጥ ጭምር ነው፡፡ አልፎ አልፎም የአገርን አጠቃላይ ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል በሚችል መልኩ በውጭ ካሉ የአገሪቱ ታሪካዊና ወቅታዊ ጠላቶች ጭምር በማበር ነው፡፡ እነሱ የሚከፍቱት ቀዳዳና የሚከተሉት የፖለቲካ ሥልት መንግሥትን መጣል እንኳ ቢችል፣ እነሱ ለሚጓጉለትና ለሚታገሉለት ሥልጣን እንደማያበቃቸው ማወቅ አለባቸው፡፡ ይኼ ሥልት እንዲያውም የአገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥልና እንኳን የሚገዙት የሚኖሩበትን አገር እንደሚያሳጣቸው ማመን አለባቸው፡፡ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ትዃን ረብቶ ያስቸገረው ባተሌ፣ ለዘለቄታው ከትዃኑ ለመገላገል ሲል ቤቱን እሳት ለኩሶ ያቃጠለው ሞኝ ዓይነት ጨዋታ ነው፡፡   

መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚዎች አብሮአቸው ተወልደው ያደጉትን እነዚህን ባህሪያት በቀላሉ አስወግደው ሰላምን ያመጣሉ ማለት ላይታሰብ ይችላል፡፡ ነገር ግን የምናወራው ከራስ ጋር ስለመታረቅ እስከሆነ ድረስ ጉዳዩን በይቻላል መንፈስ መቀበል አለብን፡፡ እነዚህ ነገሮች መርምረው ገምግመው ቢያንስ በራስ ፍጆታ ወደ ውስጥ አስገብተው ማየት አለባቸው፡፡ ነጥቦቹን ከልብ ከተቀበልናቸው፣ እርቁ ቢዘገይም አሳሳቢ ጉዳይ አይደለም፡፡ እርቅ ማለት የለበጣ መሳሳም ወይም መጨባበጥ አይደለም፡፡ ስለተቃዋሚዎቻችንና ስለአገራችን ያሉንን አሉታዊ ስሜቶች ሁሉ ከልብ አውጥቶ ዘላቂ ሰላምን ብቻ ማሰብ ማለት ነው፡፡ በመጀመሪያ ከራሳችን ጋር ከታረቅን ለብሔራዊ እርቅ የሚያስፈልገን የበሰለ ውይይት ብቻ ነው፡፡ ይኼ ሲሆን አሁን ወደ መስመር መግባት የማይችሉ ሥልጣንንና ገንዘብ ብቻ ግብ አድርገው የሚንቀሳቀሰ ሁሉ በሒደት ጊዜያቸውንና ዕድሜያቸውን ጨርሰው ይወገዳሉ፡፡ ለመሆኑ አስታራቂዎቹ ከተቃዋሚዎቹና ከመንግሥት ይኼን መካከል መንገድ ላይ የመገናኘት መፍትሔ ይቀበሉት እንደሆነ  ባደረጉት ጥናት ያገኙት ፍንጭ አለ? የአስታራቂነትና የአማላጅነት ሚና ስለሚለያይ እንዳይቀላቀሉ፡፡

ለማጠቃለል ያህል ስለአማላጅነት አንድ ትዝብት እነሆ፡፡ ደርግ ከሚታወቅባቸው መለያ ባህሪያቱ ዋናዎቹ ጭካኔውና ነፍሰ ገዳይነቱ ነው፡፡ በደርግ ጊዜ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ አዋቂዎች፣ ወጣቶችና ለጋ ሕፃናት ከየቤታቸው እየተጎተቱ ተወስደው ያለፍርድና ያለበቂ ምክንያት ተረሽነዋል፡፡ ይኼም ብቻ ሳይሆን ሬሳቸው በየአደባባዩና በየጥሻው ተጥሎ ወላጆች ልጆቻቸው የተገደሉበትን የጥይት ዋጋ እየከፈሉ እስከሬናቸውን ከየቦታው ለቅመዋል፡፡ መንግሥት የሚባሉ ሰዎች ይኼን ሲፈጽሙ ለማስታረቅ ወይም ለማውገዝ የቃጣው አንድም የሃይማኖት መሪ አልነበረም፡፡ አቡነ ጴጥሮስ በአደባባይ የጣሊያንን መንግሥት አውግዘው በአደባባይ የሞቱት የዚህ ዓይነት ተመሳሳይ እልቂት ምናልባት ከዚህ ባነሰ የተፈጸመውን አይተው ነው፡፡

ደርግ ይኼን ሁሉ ግድያ እየደጋገመ ሲፈጽም እንኳን ማስታረቅ ወይም ማውገዝ ቀርቶ፣ በየሰንበቴው ቤት ያማው የሃይማኖት መሪ አልነበረም፡፡ በወቅቱ ዳግማዊ አቡነ ጴጥሮስ ያስፈልጉን ነበር፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ በአራት ኪሎ ሥላሴ ወይ በአራዳ ጊዮርጊስ ንግሥ ላይ ደርግን አውግዘውና ገዝተው እዚያው አራዳ ጊዮርጊስ በአቡነ ጴጥሮስ ሥፍራ መስዋዕትነት ይከፍሉ ነበር፡፡ ያን ቢፈሩ እንኳን እርቅ ለማውረድ ይሞክሩ ነበር፡፡ ታዲያ ይኼን ስናስብ አቡነ ጴጥሮስ ከሃይማኖት ግዴታቸው ይልቅ የአርበኝነት ባህሪያቸው በዝቶ ነው ያን የጀግንነት ውሳኔ የወሰኑትና የተሰውት ያሰኛል፡፡ የሚገርመው ነገር እነዚህ ወንጀለኞች በሕዝብ ላይ ያን ሁሉ ጭካኔ ሲሠሩ ለማስታረቅና ወንጀሉን ለማስቆም ሳይሞከር፣ ወንጀለኞቹ በሕግ የተወሰነባቸውን ቅጣት እንዳይቀበሉ አማላጅ ሁነው ቤተ መንግሥት መግባታቸው ነው፡፡ በእርቅ ጉዳዮችን ከጥፋት ለማዳን መሞከር አንድ ጉዳይ ሆኖ ወንጀለኛ አይቀጣ ብሎ ማማለድ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

     ኸኼሐኼ

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...