Monday, September 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው አስተሳሰቦችና አሠራሮች ይወገዱ!

  መንግሥት ብዙ ጊዜ ከሚተችባቸው ወይም ከሚወቀስባቸው ጉዳዮች መካከል ለዘመናዊ አስተሳሰቦችና አሠራሮች ባዕድ መሆኑ ነው፡፡ በቢሮክራሲው ውስጥ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ በፖለቲካው ውስጥም እያንዳንዱ ዘመን የራሱ ትውልድ የሌለው ይመስል፣ የዛሬው ትውልድ በትናትናዎቹ እንዲቆዝም ይገደዳል፡፡ በግራና በቀኝ በተሠለፉት ፖለቲከኞች ዘንድ የሁሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻ ‹ያ ትውልድ› ይመስል የሚሰበከው ስለትናንቱ ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ የትናንቱን ፍፁም ዘንግቶ በዛሬው ላይ ብቻ መንጠልጠል ያስፈልጋል የሚለው ሐሳብ ተቀባይነት ባይኖረውም፣ ባረጁና ባፈጁ ወይም የመጠቀሚያ ጊዜ ባለፈባቸው አስተሳሰቦችና አሠራሮች ትውልዱን ለማጠር መሞከር ተገቢ አይደለም፡፡ ይህ ዘመን የሰው ልጅ አስተሳሰብ የመጠቀበት፣ ቴክኖሎጂ ከሚታሰበው በላይ የተመነደገበትና ለውጥ የየዕለቱ ክስተት የሆነበት ነው፡፡ በዚህ ዘመን በድሮ በሬ ለማረስ መሞከር በፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ አንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮችን እናነሳለን፡፡

  ዘመናዊው መንግሥታዊ ሥርዓት ከሚገለጽባቸው ዋነኛ ማሳያዎች መካከል ዴሞክራሲ አንደኛው ነው፡፡ ዴሞክራሲ ሥርዓት ሆኖ በተግባር የሚታየው በዘመናዊ ኅብረተሰብ ውስጥ ነው፡፡ ሜዳው እኩል የተመቻቸላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች አጀንዳቸውን በግልጽ አቅርበው የሥልጣን ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ዳኝነት በፍትሐዊ መንገድ ያገኛሉ፡፡ ይህም ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ትክክለኛ ሲሆን ማለት ነው፡፡ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች አንዳቸው ካንዳቸው በበለጠ ልዩ ድጋፍና እንክብካቤ ሳያገኙ፣ እኩል ሮጠው የሚወዳደሩበት ሜዳ እንዲኖር የሕግ የበላይነት ሊኖር ይገባል፡፡ መራጩ ሕዝብ በፈቃዱ የሚመራውን በድምፁ መሾም አለበት፡፡ ዴሞክራሲ ሰፈነ የሚባለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ጦር ሠራዊት፣ ፖሊስ፣ የፀጥታና የደኅንነት ኃይሉ በገለልተኝነት ሕጉን ብቻ ሲያከብሩና የፍትሕ አካላት በነፃነት ሥራቸውን ሲያከናውኑ ዴሞክራሲ ይገነባል፡፡ ከዚህ ውጪ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የአምባገነንነት መገለጫ ናቸው፡፡ ከዘመኑ ጋር አብረው አይሄዱም፡፡ ገለል መደረግ አለባቸው፡፡

  ዴሞክራሲ ሥርዓት ሆኖ እንዲቀጥል የመንግሥት ወይም የገዥው ፓርቲ ኃላፊነት ብቻ አይደለም፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎችን እገዛ ይፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ እንደ ሱቅ በደረቴ መሥርቶ አለሁ በማለት የተበታተነ ትግል ከመምራት ይልቅ፣ በርዕዮተ ዓለምና በዓላማ እንግባባለን የሚሉ ተሰባስበው ጠንካራ ድርጅት መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ በብሔራዊም ይሁን በኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀት ውስጥ ሆነው በምርጫ ጊዜ ብቻ ከያሉበት እየተጠራሩ ጠባቡን ምኅዳር የበለጠ ከሚያጣብቡ ይልቅ፣ ቢጤ ለቢጤ ተዋህደው ወይም ግንባር ፈጥረው የጠነከሩ ውስን የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩ ለፖለቲካው ዕድገት ይበጃል፡፡ ከገዥው ፓርቲ ጋር ለመደራደርም ሆነ ለመፎካከር የሚቻለው ከብዛት ይልቅ ጥራት ሲኖር ነው፡፡ በግለሰቦች ተክለ ሰውነት ሥር የተከለሉ፣ አባላቶቻቸውም ሆኑ ደጋፊዎቻቸው የማይታወቁ መናኛ ፓርቲዎች ለአገር ምንም አይፈይዱም፡፡ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር አይሄዱም፡፡ በዚህ ዓይነት ተደራጅተው የተለመደ አሰልቺ ሁኔታ ውስጥ መዘፈቅ ሊበቃ ይገባል፡፡ ከዘመኑ ጋር አይጣጣምም፡፡

  ከፖለቲካው መንደር ውስጥ ሲወጣ በአስተዳደራዊ ሥራዎች ላይ በየዕለቱ ሕዝቡን የሚያጋጥሙ በርካታ አሰልቺ ነገሮች አሉ፡፡ በብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ሥራን በጥራት ከማከናወንና ውጤት ከማስመዝገብ ይልቅ፣ ያለምንም አሳማኝ ምክንያት ማጓተት በጣም የተለመደ ነው፡፡ ‹‹እሺ›› ማለት ነውር ሆኖ ‹‹አይሆንም›› ማለት ይቀላል፡፡ አንድ ግብር ከፋይ ዜጋ አጣዳፊ ጉዳይ አጋጥሞት ወደ መንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሲሄድ፣ በሲስተም ስለማይመሩና ቁጥጥር ስለሌለባቸው ለእንግልት ይዳረጋል፡፡ በዘመኑ አጠራር ‹‹ጉዳይ ገዳይ›› በሚባሉ ደላሎች አግባቢነት ጉቦ ካልከፈለ ከቀናት አልፎ ለሳምንታት ብሎም ለወራት መፍትሔ አያገኝም፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሚባለው መርህ በመጣሱ ምክንያት ሕዝብ ምሬቱና ብሶቱ ገንፍሎ በመውጣቱ የደረሰውን የቅርብ ጊዜ ጉዳት ከቶ መዘንጋት አይቻልም፡፡ ሥራን በዘመናዊ ሲስተም አለመምራትና የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓት አለመዘርጋት የኋላ ቀርነት መገለጫ ነው፡፡ ዓለም በብርሃን ፍጥነት ሲለወጥ ለውጥን መቃወም ወይም ማደናቀፍ ለአገርም ሆነ ለሕዝብ ህልውና አይጠቅምም፡፡

   ከዘመናዊ አስተሳሰቦችና አሠራሮች ጋር በሚገባ መተዋወቅ የሚቻለው ለትምህርት በሚሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ነው፡፡ ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ ለጥራት ትልቅ ዋጋ መሰጠት ይኖርበታል፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመብዛታቸውን ያህል በጊዜ ለጥራት ትኩረት ካልተሰጠ ልፋቱ ሁሉ ኪሳራ ይሆናል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመምህራን፣ በድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች፣ በትምህርት መርጃ መሣሪያዎች፣ በቴክኖሎጂዎችና በመሳሰሉት ተደራጅተው ከዘመኑ ጋር እኩል ሊራመዱ ይገባል፡፡ ከሚያስተምሯቸው ተማሪዎቻቸው ባልተናነሰ በአካባቢያቸው ላሉ ማኅበረሰቦች ሁለገብ የሆነ ድጋፍ ማድረግ የሚችሉት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ አቻ ተቋማትና የመሳሰሉት ልምድ ለመቅሰም ሲተጉ ብቻ ነው፡፡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለዕውቀትና ለስርፀት ቅርብ ከመሆናቸው አንፃር ብዙ የሚቀሯቸው ነገሮች አሉ፡፡ በተለይ አንዳንዶቹ ለስም ያህል የትምህርት ተቋም ይባሉ እንጂ ለዚያ ደረጃ አይመጥኑም፡፡ ለዘመኑ ጥያቄ ምላሽ መስጠት የማይችል ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ይዞ መኩራራት ያሳፍራል፡፡ ይህ ዘመን እንዲህ ዓይነቶችን ለማስተናገድ ትዕግሥት የለውም፡፡

  ዘመናዊነትን ከኅብረተሰብ ዕድገትና ከዓለም ግስጋሴ አንፃር ማየት ተገቢ ነው፡፡ ዘመናዊነት ከዝቅተኛ ወደ ተሻለ ደረጃ ሽግግር የሚደረግበት ሒደት ሲሆን፣ ልማዳዊና አሳሪ የሆኑ አሠራሮች የሚወገዱበት ነው፡፡ አምባገነንነት የኋላቀርነት መገለጫ የመሆኑን ያህል ዴሞክራትነት ዘመናዊነት ነው፡፡ ሥራን በሚፈለገው ፍጥነትና የጊዜ ቀመር ውስጥ በጥራት ማከናወን የዘመናዊነት መገለጫ ሲሆን፣ ማጓተትና ማደናቀፍ ደግሞ ከሥልጣኔ ጋር መራራቅን ማሳያ ነው፡፡ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በዚህ ዘመን የማይፈለጉት ለሕዝብ የኑሮ ዕድገት ስለማይጠቅሙ ነው፡፡ ሙስና የዘቀጠ ሰብዕና መገለጫ የሚሆነው ድርጊቱ በማይረቡ ሰዎች ስለሚፈጸም ነው፡፡ ሥርዓት ግልጽነትና ተጠያቂነት ሲጠፋበት የአምባገነኖችና የሌቦች ዋሻ ይሆናል፡፡ አንድ አገር በሥልጣኔ እየገሰገሰ ነው ሲባል የሕዝብ ተሳትፎና ሚና ተለክቶ ነው፡፡ ጥቂቶች እየጠገቡ ብዙኃን የሚጎሳቆሉበት ዕድገት ባለቤት የለውም፡፡ ዴሞክራሲን የናቀ ዕድገት ለአገር አይበጅም፡፡ ይህ ዘመን ደግሞ የራሱ ትውልድ ስላለው ከዘመኑ ጋር የሚመጣጠን ተግባር ይቅደም፡፡ ከዘመኑ ጋር የማይመጣጠኑ አሠራሮች በአስቸኳይ ይወገዱ፡፡

  ዘመናዊነት ለማኅበራዊ ዕድገት ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ የለውጥ አንቀሳቃሽ በመሆኑም በሕዝቡ ባህል፣ ልማድ፣ አኗኗር፣ አስተሳሰብ፣ መስተጋብርና በመሳሰሉት ዕመርታ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ የረቀቁ ቴክኖሎጂዎችን ለማወቅና ለመላመድ ያግዛል፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን ሽግግር ያፋጥናል፡፡ ከግብርና ኢኮኖሚ በማላቀቅ የኢንዱስትሪ ሽግግርን ያቀላጥፋል፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ለግጭት የሚዳርጉ አላስፈላጊ ሽኩቻዎችን በውይይትና በድርድር ያለዝባል፡፡ ጭፍን ጥላቻዎችና በመረጃ ያልተደገፉ ጥርጣሬዎችን ከማስወገዱም በላይ፣ በግልጽ የሚታዩ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን በማቅረብ ሥልጡን ግንኙነቶችን ያዳብራል፡፡ ሀብታም፣ በምርት ዕድገታቸውም ሆነ በጥራታቸው አንቱ የተባሉ፣ የረቀቁ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀሙ፣ የተንደላቀቀ ኑሮ ለዜጎቻቸው ያመቻቹ፣ በሕዝባቸው ውስጥ ተመጣጣኝ ዕድገት የፈጠሩና ተሰሚነት ያተረፉ በሥልጣኔ ወደፊት የገፉ አገሮች ብቻ ናቸው፡፡ የኋላቀርነት ትርፉ ድህነትና በሽታ ብቻ ነው፡፡ ከዘመኑ ጋር መራመድ የግድ ነው፡፡ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው አስተሳሰቦችና አሠራሮች መወገድ ያለባቸው ለዚህ ነው!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ለትግራይ የተገዛው ነዳጅ ከጅቡቲ መግባት ጀመረ

  ድርድርን በሚመለከት የአሜሪካ መንግስት አቋም እንደማይዝ ተገለጸ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች...

  አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

  ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ ለቡ፣ ፉሪና...

  መንግስት 8 የስኳር ፋብሪካዎችን ለጨረታ አቀረበ

  መንግስት ስኳር ኢንተርፕራይዞችን ወደግል ለማዛወር በወጣው ጨረታ ባለሐብቶች እንዲሳተፉ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...

  በ15 ቢሊዮን ብር የተመዘገበ ካፒታል የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቱን ያሻገረው ስንቄ ባንክ ሥራ ጀመረ

  ከማክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ወደ ባንክ አገልግሎት ከተሸጋገሩ አምስት የማክሮ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

  በኢትዮጵያ ምድር ጦርነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ፊትን ወደ ልማት ለማዞር ያለው ፍላጎት አሁንም ፈተና እየገጠመው ነው፡፡ ኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት ሲብት በሙሉ...

  የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሁን!

  በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣...

  የኢኮኖሚው ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሆን!

  ጦርነት ውስጥ ያለች አገር ኢኮኖሚ ጤንነት እንደማይሰማው ለማንም ግልጽ ቢሆንም፣ ከጦርነቱ በተጨማሪ በየዕለቱ ገበያው ውስጥ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ግን አስደንጋጭ እየሆነ ነው፡፡ የብር የመግዛት...