Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምአነጋጋሪው የአሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ የሥራ ስንብት

አነጋጋሪው የአሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ የሥራ ስንብት

ቀን:

በአሜሪካ በከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ ያሉ ባለሥልጣናት በወንበራቸው አንድ ወር ሳያገለግሉ ሥራ የለቀቁበት የቅርብ ጊዜ ታሪክ የለም፡፡ በተለይ ለፕሬዚዳንት አማካሪነት የሚሾሙ ባለሥልጣናት ለፕሬዚዳንቱም ሆነ ለሕዝቡ ዓይንና ጆሮ ከመሆናቸው ጎን ለጎን፣ ያለባቸው ኃላፊነት ከፕሬዚዳንቱ ያልተናነሰ በመሆኑ ለሾማቸው ፕሬዚዳንት በታማኝነት ያገለግላሉ፡፡

ቀድሞውንም ትችት ለበዛባቸው 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን ዕድል አልቀናቸውም፡፡ የአሜሪካን የፕሬዚዳንትነት መንበር ተቆናጠው ወር ሳይሞላቸው ለብሔራዊ ደኅንነት አማካሪነት የሾሟቸው የ56 ዓመቱ ጄኔራል ማይክል ቶማስ ፍለን፣ ሦስት ሳምንታት ከሦስት ቀናት ብቻ ሠርተው የሥራ መልቀቂያቸውን አስገብተዋል፡፡

ለደኅንነት አማካሪነት በፕሬዚዳንት ትራምፕ ከመሾማቸው አስቀድሞ፣ በትራምፕ ምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት ትራምፕን ሲያማክሩ የነበሩትና ትራምፕ ቢመረጡም የአገሪቱ የደኅንነት አማካሪ እንደሚሆኑ የተነገረላቸው ፍለን፣ ገና ከጠዋቱ ነበር በየሚዲያው ትችት የተሰነዘረባቸው፡፡

አዲሱን ሥልጣን ከመቆናጠጣቸው አስቀድሞም ዋሽንግተን ፖስትና አሶሼትድ ፕሬስ ፍለን ከአሜሪካ ባላንጣ ሩሲያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው ብለው ሲያብጠለጥሏቸው ከርመዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም ሒላሪ ክሊንተንን የሚያጥላላ ዜና ከማናፈስ አንስቶ ሸፍጥ ሠርተዋል ተብለውም ተኮንነዋል፡፡

ዎል ስትሪት ጆርናል ደግሞ ትራምፕ ሥልጣን በያዙ በሁለተኛ ቀናቸው፣ ፍለን ከሩሲያ ባለሥልጣናት ጋር ስላላቸው ግንኙነት ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ይዞ ወጥቷል፡፡ ፍለን ለአንድ ወር እንኳን ያላገለገሉበትን ከፍተኛ ሥልጣን የለቀቁት ደግሞ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነው፡፡

ማይክል ቶማስ ፍለን ከሥልጣናቸው ለምን ለቀቁ?

የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ውስብስብ ችግሮች አሉባቸው እያሉ የሚገልጿቸው ፍለን፣ ሥራ ለመልቀቃቸው ዋናው ምክንያት ከሩሲያ ጋር ሚስጥራዊ ግንኙነት አላቸው በሚል የሚሰነዘርባቸው ወቀሳ ነው፡፡ ባለፈው ወር ማብቂያ ላይም የፍትሕ ዲፓርትመንቱ ለትራምፕ አስተዳደር ያስገባው ፍለን በአሜሪካ ከሩሲያ አምባሳደር ጋር ያላቸውን ሚስጥራዊ ግንኙነት፣ እንዲሁም የአሜሪካን ሚስጥር ለሩሲያ አሳልፈው ለመስጠት ያላቸውን ተጋላጭነት ያካተተ ሪፖርት በየሚዲያው መናኘቱ ሌላው ምክንያት ነው፡፡

ፍለን በጻፉት የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ፣ ‹‹ባለማወቅ ከሩሲያው አምባሳደር ጋር ስለነበረኝ የስልክ ንግግር ያልተሟላ መረጃ ለምክትል ፕሬዚዳንቱ ማይክ ፔንስና ለሌሎችም ተናግሬያለሁ፡፡ ለፕሬዚዳንቱና ለምክትል ፕሬዚዳንቱ ይቅርታ ጠይቄ ተቀብለውኛል፤›› ብለው ማስፈራቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡

በአሜሪካ ጦር ኃይል ሌተና ጄኔራል፣ 18ኛው የመከላከያ ደኅንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተርና 25ኛው ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሆነው ያገለገሉት ፍለን፣ የአሜሪካን ሕዝብ በቁርጠኝነት ማገልገላቸውን በመጥቀስ፣ መልቀቂያቸውም ከኃላፊነት የመነጨ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ትራምፕ ሥልጣን በተረከቡ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ሳምንታት ውስጥ የአስተዳደሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ውስጥ ለውስጥ ለነበራቸው ውዝግብና የተቀናጁ ላለመሆናቸው ማሳያው የፍለን ከሥራ ድንገት መልቀቅ ሲሆን፣ እሳቸውም ለአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ፔንስ ከሩሲያ ጋር በነበራቸው የስልክ ግንኙነት ስለማዕቀቡም ሆነ ሌሎች ቁልፍ ጉዳዮች ያወራቸውን በሙሉ እውነቱን ተናግረዋል ወይስ? የሚለውና ፍለን የትራምፕን አስተዳደር ዋሽተዋል የሚሉት ጉዳዮች ካለመተማመን፣ ካለመቀናጀትና ኃላፊነትን በአግባቡ ካለመወጣት የመነጩ ናቸው ተብሏል፡፡

ሆኖም ዋይት ሀውስ የደረሰበት ድምዳሜ ፍለን ምክትል ፕሬዚዳንቱን ለመዋሸት አስበው ሳይሆን፣ ምናልባትም ከሩሲያ ጋር በነበረው ንግግር የተነሱ ጉዳዮችን በሙሉ ካለማስታወስ ሊሆን ይችላል የሚል ነው፡፡

ሆኖም ‹ከብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ መርሳት አይጠበቅም› የሚሉ የውስጥ አዋቂዎች፣ ትራምፕ በጉዳዩ ላይ ስላላቸው አቋም እንዲናገሩ ተጠይቀው፣ ‹‹ትራምፕ እንዲሁ እየተጓዘ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከ2016 ፕሬዚዳንታዊ ቅስቀሳ ጀምሮ ለትራምፕ የውጭ ፖሊሲና የደኅንነት ጉዳዮች አማካሪ የነበሩት ፍለን በግሰለብ ደረጃ አሜሪካን ወክለው ከአገሮች ጋር መምከር የሌለባቸው ቢሆንም፣ ይኼንን በመተላለፍ አሜሪካ በዓይነ ቁራኛ ከምትጠብቃት ሩሲያ ጋር በተለይ በሩሲያ ላይ በተጣሉ ማዕቀቦችና ወሳኝ ጉዳዮች በስልክ መነጋገራቸው፣ እያንዳንዷ ንግግር በአሜሪካ የኢንተለጀንስና የሕግ አስፈጻሚ ኤጀንሲ ክትትል የሚደረግበት ቢሆንም፣ የነበራቸውን ሚስጥራዊ ግንኙነት አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ መዋሸታቸው ከሥራ ለመልቀቅ እንዳበቃቸው የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

ቀጣዩ አሜሪካ የደኅንነት አማካሪ ማን ነው?

እ.ኤ.አ. ከ2016 ማብቂያ ጀምሮ ከሩሲያ ጋር ሚስጥራዊ ግንኙነት እንደነበራቸው፣ የአሜሪካ የደኅንነት አማካሪ ሆነው ሳይሾሙ የአሜሪካን ደኅንነት በሚጎዳ ሁኔታ በአሜሪካ ከሩሲያ አምባሳደር ጋር የግል የስልክ ውይይት አድርገዋል የተባሉትን ፍለን ተክተው፣ የአሜሪካ ተጠባባቂ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የሆኑት ኬት ኬሎግ ናቸው፡፡ ጡረተኛው ሌተና ጄኔራል ኬሎግ 72 ዓመታቸው ሲሆን፣ በአሜሪካ ጦር ኃይል ውስጥ ለ36 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በቬትናም ለነበረው የአሜሪካ ጦር የካምቦዲያ ልዩ ጦር ኦፊሰር፣ በኢራቅ በነበረው ጦርነት የ28ኛው አየር ወለድ ክፍል ኤታማዦር ሹም ሆነውም አገልግለዋል፡፡

ከጡረታ በኋላ ኦራክል፣ ኪዮቤክና ሲኤሲአይ ለተባሉ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሠሩት ክሎግ፣ የትራምፕን የምረጡኝ ዘመቻ በአማካሪነት የተቀላቀሉት እ.ኤ.አ. በመጋቢት 2016 ነው፡፡ ሆኖም ኬሎግ በዋይት ሀውስ ከእርሳቸው በፊት ከነበሩ አማካሪዎች ዝቅተኛ ፕሮፋይል ያላቸው መሆኑን ኒውዮርክ ታይምስ አስፍሯል፡፡

ትራምፕ ኬሎግን በተጠባባቂ አማካሪነት ቢሾሟቸውም፣ ከአስተዳደሩ የሚወጡ መረጃዎች ወደ ዋይት ሀውስ የሚያመሩ ሌላ ዕጩ መኖራቸውን ይጠቁማሉ፡፡ የቀድሞው የሲአይኤ ዳይሬክተርና ጡረተኛው ጄኔራል ዴቪድ ፔትሪየስ ቀጣዩ የአሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ተገምቷል፡፡       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...