Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

​አምስት ነፍስ በአንድ ዶቅዶቄ

ትኩስ ፅሁፎች

ከሐዋሳ ዲላ መስመር በምትገኘዋ አንፈራራ የገጠር ከተማ፣ ዶቅዶቄ (ሞተር ሳይክል) አሽከርካሪው አራት ሰዎችን አፈናጦ ሲጓዝ፡፡ በአሽከርካሪውና በኋላው ካለችው እናት መካከል ሦስት ዓመት ያልሞላት ሕፃን በእቅፍ ተይዛለች፡፡

(ፎቶ በታምራት ጌታቸው)

* * * * * * *

500 ኪሎ ግራም የምትመዝነው ግብጻዊት በህንድ ቀዶ ሕክምና ሊደረግላት ነው

የ37 ዓመቷ ኢማን አህመድ በክብደቷ ምክንያት መንቀሳቀስና ከቤት መውጣት ሳትችል 20 ዓመታት አስቆጥራለች፡፡ 500 ኪሎ ግራም የምትመዝነው ኢማን በዓለም አንደኛዋ ወፍራም ሴት ተብላለች፡፡ ልጅ ሳለች በዝሆኔ በሽታ ተይዛ ታክማ እንደነበር ቤተሰቦቿ ለገልፍ ሐውስ ገልጸዋል፡፡ ስኳር፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ ጭንቀትና የእንቅልፍ ማጣት በክብደቷ ምክንያት የተጠናወቷት በሽታዎች ናቸው፡፡ ለዚህ ሁሉ ነገሮች የዳረጋትን ውፍረቷን በቀዶ ሕክምና ለመቀነስ ባለፈው ቅዳሜ ወደ ህንድ ተጉዛለች፡፡

ወደ ህንድ የበረረችው በልዩ አውሮፕላን ነበር፡፡ ሕክምናውን የምትከታተለው ሙምባይ ውስጥ በሚገኘው ሳይፊ በተባለው ሆስፒታል ነው፡፡ ቀዶ ሕክምናው ከመጀመሩ በፊት 50 ኪሎ ግራም መቀነስ የሚያስችላትን ፈሳሽ ለ25 ቀናት ያህል እንደምትጠጣ ተነግሯል፡፡ ከዚያ በመቀጠል ተጨማሪ 150 ኪሎ ግራም መቀነስ የሚያስችላት ቀዶ ሕክምና እንደሚደረግላት፣ ከሆስፒታሉ ሳትወጣ በሐኪሞቿ የቅርብ ክትትል እየተደረገላት ለአምስት ወራት ያህል እንደምትቆይ፣ የመጀመሪያው የቀዶ ሕክምና ከተሳካ በሁለት ዓመታት ውስጥ ከ100 ኪሎ ግራም በታች ልትሆን የሚያስችላትን ሁለተኛውን የቀዶ ጥገና ሕክምና እንደሚያደርጉላት ሐኪሞቿ ተናግረዋል፡፡

* * * * * * *

‹‹አምስቱ ገጾች››

‹‹አምስቱ ገጾች›› በሚል ርዕስ በሰለሞን ሹምዬ የተዘጋጀውና የ25 ስኬታማ ኢንተርፕረነሮች፣ የሥራ መሪዎችና ምሁራን ታሪክ የያዘው መጽሐፍ የካቲት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በ11፡00 በአዲሱ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ይመረቃል፡፡

‹‹ከረባት›› እና ‹‹ገዥነት››

‹‹ከረባት›› የተሰኘው የፋሲካ ደነቀው የግጥም ሲዲ ገበያ ላይ የዋለው በቅርቡ ነው፡፡ በሲዲው 14 ግጥሞች የተካተቱ ሲሆን፣ በ30 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ በተያያዥም በአማረች ጎሹ የተጻፈው ‹‹ገዥነት›› የፍልስፍና፣ ሥነ ልቦናና ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስስ ሲሆን፣ በ40 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

* * * * * * *

አስከሬን የጫነ ሚኒባስ በመስረቅ የተጠረጠረው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ዋለ

በደቡብ ካሊፎርኒያ የሚገኝ የአንድ ቀብር አስፈጻሚ ድርጅት ይዞታ የሆነችውን ሚኒባስ የሰረቀው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡ አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው፣ ግለሰቡ መኪናውን ሰርቆ ከተሰወረ በኋላ ውስጡ አስከሬን መኖሩን እንደተመለከተ መኪናውን ከወሰደበት መልሶ፣ በምትኩ ሌላ ሰርቆ ለመሰወር ሙከራ ባደረገበት ወቅት ነው በቁጥጥር ሥር የዋለው፡፡

የሪቨርሳይድ ፖሊስ ኦፊሰሩ ርያን ሬይልስባክ እንዳለው፣ አንድ የድርጅቱ ሠራተኛ ባይሳካለትም ተጣርጣሪውን ለመያዝ ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ መያዝ የተቻለው ግን ሁለተኛውን ሚኒባስ ሰርቆ ሁለት ማይል ያህል ከነዳ በኋላ ነው፡፡ ጉዳዩን እየተመለከተ ያለው የሪቨርሳይድ ፖሊስ ክፍል ተጠርጣሪው የሚከሰሰው በመኪና ስርቆት እንጂ በአስከሬኑ አለመሆኑን ገልጿል፡፡  

* * *

ከረባት

ከረባት ሙሉ ልብሱን የለበሰ

ጫማውን በወግ ተጫምቶ

ወገቡን  በልክ ያሰረ

ባልናተበው ቀበቶ

ከረባቱን በውበቱ አስሮ ከፊቱ ሲመጣ

ማነው የማይገነዘብ ከጣቶቹ ቁጥር በላይ መስታወት አይቶ እንደወጣ

ደግሞ ከሥራው ሲመለስ በያው ልብሱ በዛው ጫማ

የአንገቱ ከረባት ብቻ ላልታ አልያም ተጣማ

 በውበት አልቦነት ሲጓዝ ድንገት ከዓይኑ የገባ

መገመት አይሳነውም አሰልቺ እንደነበረ ያረፈደበት ስብሰባ

 ድካም ነው ወይንስ ሐዘን የዚህ ሰው ውሎ ምን ነበር

ሐሳብ ነው አልያ ችግር በማለት ማሰቡም አይቀር

አመሻሽ ላይ ከበረንዳ ቆማ የምትጠብቀው ሚስቱ

 ይገባታል ከመጠጥ እንደተነሳ  ከረባቱ ወጉ በመታጣቱ

 እንደከረባት ምጣኔ ሰፊው ከፊት ከጀርባው ሰላላ

በውበት ከፊት የሚታየው ከሚሰወረው ከኋላ

ያመጣጠኑ ልኬት ቢጠብቅ አልያ ቢላላ

የቀለም ምርጫው ቢዛነፍ  ጥምረቱ ውበት ባያሟላ

ሕይወት አደባባይ ነው አንሰውረውም  ከሌላ

 የሁኔታችን ነፀብራቅ ለሚያውቀን ለሚያየን ላለ በውጭ

ደስታ ነው ወይ አጸያፊ ተስፋ ነው ወይ ተስፋ አስቆራጭ

 ሐሳብ ነው የመብሰልሰያ እራስን በሰው ውስጥ ማያ  

ከረባት ናት ሕይወት የልኬት ጥናት ጠያቂ

በመጠን የምንኖራት ሚዛን  በልክ አስጠያቂ

ፋሲካ ደነቀው ‹‹ከረባት›› (2009)

* * *

የፈስ ነገር

ፈስ፣ ታችኛ ትንፋሽ ግም የዓይነ ምድር ወላፈን፡፡ (ተረት) የጠበኛ ፈስ ዓይን ያፈስ፤ እንዲያውም በመላ ፈስ ዳለቻ ነው፡፡

ፈሰ ከንቱ (ቲ) የፈሱ ሽታ ራስ የሚበጠብጥ ሆድ የሚቆርጥ የሚያም ቁናሳም፡፡

ፈሳም፡፡

ፈረሱን ጠበሰ፣ ሮጠ ሸሸ ጋለበ (የአሮጊት ፈስ) ክረምት አፈራሽ ነገር፣ በበጋ እንደ ፈስ የሚበን የሚተን፣ ክብ እንክብል ዓይን የሚያኽል ፍጥረት፡፡ ልጆች በተሰበሰቡበት ፈስ ተፈስቶ የፈሳው ባይታወቅ፣ የፈስ አፈርሳታ ለማውጣት ‹‹ፈስ ፈሶ ፈስ አራራ፣ ቆርጦ ቆርጦ ደም ያሳራ፣ ደሙ ሲረጋ በለው ባለንጋ፡፡ . . . ያጤ መስቀል ሲንቀለቀል የፈሳውን ልቡን ይንቀል›› ይባላል፡፡

ደስታ ተክለወልድ

‹‹ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት›› (1962)

* * *

     ‹‹ያይብ ልጥልጥ››

በየካቲት መባቻ የተመረጡት አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ በቅጽል ስማቸው፣ ‹‹ፎርማጆ›› በመባል ይታወቃሉ፡፡ በ50ዎቹ አጋማሽ  የሚገኙት ፕሬዚዳንቱ በአማርኛ ‹‹ጅብና›› ማለትም፣ ያይብ ልጥልጥ ወይም ዱቄት የሚባለው ፎርማጆ (ቺዝ) ስለሚወዱ ስያሜውን እንዳገኙ ይነገራል፡፡

የሶማሊያና የአሜሪካ ጥምር ዜግነት ያላቸው ‹‹ያይብ ልጥልጡ›› አብዱላሂ መሐመድ ቡፋሉ ከሚገኘው፣ የኒው ዮርክ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በታሪክ የባችለር ዲግሪ፣ በፖለቲካ ሳይንስ የማስትሬት ዲግሪ አላቸው፡፡ በአሜሪካ በስደት መኖር ከጀመሩበት ከ1977 ዓ.ም. ወዲህ በተለያዩ ሙያዎች ዲፕሎማት፣ ፕሮፌሰርና ፖለቲከኛ ሆነው ብቻ አላሳለፉም፡፡ የእግር ኳስ ዳኛም ነበሩ፡፡ በቲውተር ገጽ ላይ የተገኘው ፎቶዋቸው በአሜሪካ ኦሃዮ ግዛት በኮሎምቦስ፣ የቤት ውስጥ ግጥሚያን የመሩበትን ያሳያል፡፡

(ሔኖክ መደብር)

 

 

 

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች