Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልማኅበራዊ መስተጋብር በአፋር

ማኅበራዊ መስተጋብር በአፋር

ቀን:

ከሰሞኑ በአፋር ክልል በነበረን ቆይታ ከአስደናቂ መልክዓ ምድር ጀምሮ በርካታ መስህቦች አስተውለናል፡፡ በተዘዋወርንባቸው አካባቢዎች ከገጠመን መካከል የመረጃ ልውውጥ ሥርዓቱ ይጠቀሳል፡፡ በክልሉ ከቆየንባቸው ቀናት አንዱን ያሳለፍነው በአህመድ ኤላ (የአህመድ ጉድጓድ እንደ ማለት) ቀበሌ ነበር፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች የሚኖሩት በእጅጉ ተጠጋግተው ነውና፣ ወደ አንድ ሰው መኖሪያ ስንዘልቅ ጎረቤቶችንም እናገኛለን፡፡ እንግዶች ሞቅ ያለ አቀበባል ተደርጎላቸው ቤት ያፈራውንም ይጋበዛሉ፡፡ ሪፖርተር ጎራ ወዳለበት ቤት የጋበዘችን የ12 ዓመት ታዳጊ ስትሆን፣ በአቅራቢያው ያሉ ዘመዶቿንና ጓደኞቿንም ሰበሰበችና በሚኖሩበት አካባቢ፣ በክልሉ ዋና ከተማ ሰመራና በሌሎች ከተሞችም ስላሉ ጉዳዮች መነጋገር ተጀመረ፡፡

የአፋርኛ፣ ትግርኛና አማርኛ ዉህድ በነበረው ውይይት መካከል በተደጋጋሚ ዳጉ የሚለው ቃል ይደመጣል፡፡ ዳጉ የአፋር ሕዝብ መረጃ የሚለዋወጥበት ሥርዓት ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹልን፣ የአፋር ሕዝብ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው በሚጓጓዝበት ወቅት በመንገዱ ለሚያገኘው ሰው መረጃ ሳይሰጥ አያልፍም፡፡ አንዱ አልፎት በመጣው አካባቢ ስላለው ሁኔታ በአጠቃላይ ለሌላው ይነግራል፡፡ ዘመናትን ያስቆጠረው ይህ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት የአካባቢው ነዋሪዎች ለክንውኖች ቅርብ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት፣ የአፋር ሰው በበረሃማዋ አፋር ሲጓጓዝ መጠጥና ምግብ ከመጠያየቅ አስቀድሞ መረጃ ይለዋወጣል፡፡ የሚዋሽ አለ ተብሎ ስለማይገመትም መረጃው ትክክል እንደሆነ ይታመናል፡፡ የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ማስፋፋትና ፓርኮች ሥራ ሒደት ባለቤት አቶ አህመድ አብዱልቃድር ግዙፍነት ከሌላቸው የክልሉ  ቅርሶች (ኢንታንጀብል ካልቸራል ሔሪቴጅስ) መካከል ዳጉን ይጠቅሳሉ፡፡ ሥርዓቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕውቅና እያገኘ በመምጣቱ ከክልሉ ተወላጆች ባሻገር ብዙዎች ስለ ዳጉ መጠነኛም ቢሆን መረጃ አላቸው፡፡ ዳጉ መረጃ ከመለዋወጥ ጎን ለጎን ማኅበራዊ መስተጋብሩን ያጠነክራል፡፡ በነዋሪዎች መካከል ላለው ቅርርብ የራሱን አስተዋጽኦም ያበረክታል፡፡ በእርግጥ ስለ ማኅበረሰባዊ ትስስር ሲነሳ የአካባቢውን ነዋሪዎች ኅብረት የሚያፀኑ ሌሎችም ባህላዊ እሴቶች አሉ፡፡ አረፍ ባልንበት ቤትም ባህላዊ እሴቶችን የሚያንፀባርቁ ክንውኖች የነበሩ ሲሆን፣ ስለ ሥርዓቶቹ በጥቅል የሚያብራራ ጥናትም አግኝተናል፡፡

‹‹የአፋር ብሔረሰብ ባህላዊ እሴቶች›› በሚል ርዕስ በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተዘጋጀው ጥናት እንደሚያትተው፣ በክልሉ የማኅበራዊ ትስስር መገለጫ ከሆኑ በርካታ የባህል እሴቶች መካከል አፌሂና፣ ፊኢማ፣ ኦላ፣ አለጊና፣ ሙጋኢና፣ ኦንኦር፣ ፈረንገኢና፣ ኢብናይቲኖ፣ ሀራይ፣ እድቦንታ እና ኩራ የተባሉት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ባህላዊ እሴቶች የየራሳቸው ሥርዓት (ሪችዋል) ያላቸው ሲሆኑ፣ ማኅበረሰቡ እርስ በርስ እንዲቀራረብና እንዲደጋገፍ ያደርጋሉ፡፡

ወደ 141,1902 ሕዝብ በሚኖርበት ክልሉ አፌሂና በመባል የሚታወቀው ሥርዓት አንድ ጎሳ ከሌላ ጎሳ ጋር መልካም ግንኙነት የሚፈጥርበት ነው፡፡ በጎሳዎች መካከል አፌሂና ከተደረገ በኋላ በመካከላቸው ግጭት እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ ግጭት ቢከሰት እንኳን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የሚደረግበት ሥርዓት አለ፡፡ ባህላዊ ሥርዓቶች ለማኅበራዊ መስተጋብር መጠናከር ያላቸው አበርክቶም ይታይበታል፡፡

ሌላው ባህላዊ እሴት ፊኢማ ዕድሜና ጾታን መሠረት ያደረገ አደረጃጀት ሲሆን፣ የየአካባቢው ነዋሪዎች የየራሳቸው ፊኢማ አላቸው፡፡ በየአካባቢው የወጣቶች፣ የአዋቂዎችና የሴቶች ፊኢማዎች አሉ፡፡ የወጣቶች ፊኢማ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሚና ያለው ሲሆን፣ እያንዳንዱ ፊኢማ በአባላት የተመረጠ መሪ (ፊኢማ አባ) አለው፡፡ ፊኢማ አባዎች አባላትን የመምከር፣ ሲያጠፉ የመቅጣትና ማኅበረሰቡን  እርስ በርስ የማስተባበር ኃላፊነትን ይወጣሉ፡፡ በተመሳሳይ በሴቶች ፊኢማም፣ ፊኢማ አባዋ በአባሎች መካከል ትስስር እንዲኖር ታደርጋለች፡፡ በደስታና በሐዘን ወቅትም የማስተባበርና ግጭት ሲፈጠር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የማድረግ ሚናም አላት፡፡ የወጣቶች ፊኢማ አባላት በዕድሜ ሲገፉ ወደ አዋቂዎች ፊኢማ ይሸጋገራሉ፡፡

ማኅበራዊ ትስስር በግለሰቦች ግንኙነት ደረጃ የሚገለጽበት ሥርዓት አላ ሲሆን፣ በአጋጣሚ ተገናኝተው ወይም አንዳቸው ከሌላቸው ጋር ወዳጅነት መመሥረት ፈልገው በተመራረጡ ሰዎች መካከል የሚፈጠር ወዳጅነትን ያመለክታል፡፡ ሁለት ግለሰቦች ወዳጅነት ለመመሥረት ከወሰኑ በኋላ ወዳጅነታቸውን ይፋ ለማድረግ ምስክር የሚሆኑ ትልልቅ ሰዎች በባህላዊ ሥርዓቱ ይገኛሉ፡፡ ይህ ወዳጅነት ዘላቂ እንጂ ጊዜያዊ አይደለም፡፡ ወዳጅነቱ ጠንክሮ ከግለሰቦቹ ባለፈ የቤተሰቦቻቸውንም ትስስር ይፈጥራል፡፡

በተያያዥም አሊጊኑ የተሰኘው ሥርዓት ይጠቀሳል፡፡ በሠርግ ወቅት በሙሽሮችና በሚዜዎቻቸው መካከል ያለው ጠንካራ ትስስር፣ ጥንዶች በትዳር ተሳስረውም እንደሚቀጥል ያመለክታል፡፡ በጥንዶች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር በማድረግና ግጭት ሲኖርም በመፍታት ረገድ የሚዜዎቹ ሚና ቀላል አይደለም፡፡ ሙጋኢና ልጆች ሲወለዱ ያለው የስም አወጣጥ ሒደት ሲሆን፣ የአንድ ልጅ ስም በእናት ወይም በአባት ሲወጣ የአንድ ዘመድ ወይም ወዳጅን መጠሪያ ተከትሎ ይሆናል፡፡ የጥንዶች ልጅ በስሙ የተሰየመለት ሰው መረጃው የሚደርሰው በመግቢያችን በተጠቀሰው ዳጉ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት ነው፡፡ በስሙ ልጅ የተሰየመለት ሰው ለቤተሰቡ ያለው ክብርና ፍቅር ይጨምራል፡፡ የልጅ ስያሜ ከሁለት ቤተሰቦች ባለፈ በማኅበረሰቡም መካከል ወዳጅነትን ያጠናክራል፡፡

አንኦር ደግሞ በአፋር ብሔረሰብ ልጅ ሲወለድ ቤተሰቦቹ ልጁ እንዲሆንላቸው የሚፈልጉትን (ምኞት) የሚገልጹበት ሥርዓት ነው፡፡ ከልጁ እናት ዘመዶች አንዱ ተመርጦ ሕፃኑን ለመጀመርያ ጊዜ ውኃ፣ ቴምር፣ ወተት ወይም ሌላ እንዲያቀምስ ይደረጋል፡፡ ሥርዓቱ ልጁ ለወደፊት ቤተሰቦቹ የተመኙለትን እንዲሆን ያስችላል ከሚለው እምነት በተጨማሪ አንኦር ካደረገው ቤተሰብ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲፈጠር መንገድ ይከፍታል፡፡

ፍራንጋኢና አንድ ቤተሰብ ወንድ ልጁ ከተወለደ አራት ወር ሴት ልጅ ከተወለደች ሦስት ወር ሲሆናቸው ለልጆቹ ወዳጅ እንዲሆኑ ከሚፈልጋቸው ልጆች ቤተሰቦች ጋር ትስስር የሚፈጥርበት ሒደት ነው፡፡ ልጄ የልጅህ ወዳጅ ነው የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍ ልጅን በሚፈለገው ሰው ትከሻ ወይም እጅ ላይ የማስቀመጥ ሥርዓት ያለ ሲሆን፣ ልጆቻቸው ወዳጅ እንዲሆኑ የፈለጉ ቤተሰቦች መካከል መልካም ግንኙነት አለ፡፡

የማኅበራዊ ትስስር መገለጫ የሆኑ እነዚህ ባህላዊ እሴቶች ከግለሰቦች ጀምሮ በማኅበረሰቡ ያለው ቅርርብ መሠረት መሆናቸው ይገለጻል፡፡ ባህላዊ እሴቶቹ ማኅበረሰቡ በኅብረት የቆመባቸው ናቸው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ሥርዓቶች በተጨማሪ የሚጠቀሰው ኢብናይቲኖ ለእንግዳ የሚደረግ አቀባበል ሲሆን፣ አንድ ሰው ራቅ ወዳለ ቦታ ሲሄድ ቢርበው ባገኘው ሰው ቤት ጎራ ብሎ ስለሚመገብ ስንቅ እንደማያስፈልገው ይነገራል፡፡ ተጓዡና ዕረፍት ያደረገበት ቤተሰብ ትስስርም ከአንድ ቀን በላይ ዘላቂነት ይኖረዋል፡፡

ሀራይ በመባል የሚታወቀው ሥርዓት ሕዝቡ በደስታም ይሁን በሐዘን የሚያደርገውን መደጋገፍ ያመለክታል፡፡ በሥርዓቱ አቅም የሌለው ሰው ተዋጥቶለት ትዳር እንዲመሠርት ይደረጋል፡፡ ራሱን እንዲችልም ግመል፣ ፍየል ወይም በግ ይሰጠዋል፡፡ በተመሳሳይ የእድቦንታ ሥርዓት የተፈጥሮም ይሁን ሰው ሠራሽ አደጋ የደረሰበትን ሰው መልሶ የማቋቋም ሒደት ነው፡፡ ከሀራይና ከእድቦንታ በተጨማሪ የኩራ ሥርዓት ሰው የሞተባቸውን ግለሰቦች ለማጽናናት የሚደረግ ነው፡፡ የቤት እንስሳ ይዞ መሄድ የሥርዓቱ መገለጫ ሲሆን፣ አንዲት ሴት ስታገባ በአካባቢዋ ያሉ ሴቶች ወተት፣ ቅቤና የተለያዩ ምግቦች በመውሰድ እንዲሁም ቤቷን የምትሠራበት ሰሌን በማዋጣት ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ ሥርዓቱ እንደ ባህላዊና ማኅበራዊ ግዴታ ስለሚታይ ከመረዳዳት ወደ ኋላ ያለ ሰው ይነቀፋል፡፡

ወደ ቤተሰቦቿ መኖሪያ ቤት የጋበዘችን ታዳጊና ሌሎችም የአካባቢው ነዋሪዎች የባህላዊ ሥርዓቶቹ ህያው ምስክር ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ማኅበራዊ መስተጋብሩ የቆመባቸው ባህላዊ እሴቶችም ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገሩ ዛሬ ላይ ደርሰዋል፡፡ በአህመድ ኤላ የነበረንን ቆይታ ስናገባድድ ባህላዊ እሴቶቹን ለማስተዋወቅ ምን ያህል ተሠርቷል? የሚል ጥያቄ አንግበን ነበር፡፡

የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ ያዩ ‹‹የአፋር ብሔራዊ ባህላዊ እሴቶች›› ጥናት ላይ እንደገለጹት፣ ባህላዊ እሴቶቹ ረዥም ዕድሜን ያስቆጠሩ የማኅበራዊ ትስስር መገለጫዎች ናቸው፡፡ ስለነዚህ ግዙፍነት የሌላቸው የክልሉ ቅርሶች ጥናት በተደረገበት ወቅት ከጎሳ መሪዎች፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከአርብቶ አደሮች መረጃ መሰብሰቡን አትተዋል፡፡ ባህላዊ እሴቶቹ በመጽሐፍ ታትመው ስለክልሉ ባህላዊ እሴቶች መረጃ ማግኘት ለሚፈልጉ ግለሰቦች እንዲሁም ተመራማሪዎችም ቀርቧል፡፡ ኃላፊው ባህላዊ እሴቶቹን ከማስተዋወቅ ባለፈ በዓለም አቀፍ ቅርስነት በማስመዝገብ ረገድ፣ የአፋር ባህላዊ ሕግ (መድአ)ን በዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት)  ለማስመዝገብ የተጀመረውን ጥረት ይጠቅሳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...