በአዲስ አበባ ክብረ በዓላትን ጨምሮ የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ከሚዘወተርባቸው አካባቢዎች ጃንሜዳ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ቀደምቱ ነገሥታት፣ መሳፍንትና መኳንንቱ ሳይቀሩ ለልዩ ልዩ የስፖርት ክንውኖች እንደታደሙበት ሲነገርለት የቆየው ጃንሜዳ፣ ለኢትዮጵያ ስፖርትና አትሌቶች የላቀ ትርጉም እንዳለው ለመረዳት አያዳግትም፡፡ በዚያ ላይ መዛግብት እንደሚያስረዱት የፈረስ ጉግስ፣ ትግል፣ የገና ጨዋታ፣ የዒላማ ተኩስና የመሳሰሉትን በማስተናገድ ይታወቃል፡፡
ጃንሜዳ ባለፈው እሑድ የተከናወነው 34ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ የሩጫ ውድድርን ጨምሮ እግር ኳስና ሌሎችም ስፖርቶችን በማስተናገድ ቋሚ ድርሻ ይዟል፡፡ ከዚህ በመነሳት አንዳንዶች ጃንሜዳን ‹‹ተፈጥሯዊው ማዕከል›› ሲሉ የሚጠሩት አሉ፡፡ ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሜዳውን የወደፊት የስፖርት ማዕከልነት ሥጋት ውስጥ የሚጥሉ ክስተቶች በዙሪያው እየታዩ መምጣቱ የሚያሳስባቸው አሉ፡፡
በዙሪያው እየተስፋፉ የመጡ የቤትና የሕንፃ ግንባታዎች ጃንሜዳን ቀስ በቀስ እየሸነሸኑ የሜዳው ስፋትና ወርድ እየጠበበ መምጣት ጀምሯል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በዚሁ ከቀጠለ የወደፊት ዕጣ ፈንታውን አሳሳቢ እንደሚያደርገው ጭምር ሥጋት የገባቸው አሉ፡፡
እሑድ የካቲት 5 ቀን 2009 ዓ.ም. በተከናወነው 34ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከክለብና በግል 1,200 በላይ አትሌቶች ተሳትፈዋል፡፡ ውድድሩን ለመመልከት የተገኙ ታዳሚዎች፣ አትሌቶችና ባለሙያተኞች ከውድድሩ ይልቅ ህልውናው በግንባታ ሥጋት ውስጥ እየወደቀ የመጣው የጃንሜዳ ጉዳይ መነጋገሪያ እንደነበር ታውቋል፡፡ አዲስ አበባ ከቀደሙት ጀምሮ ‹‹አሉኝ›› ብላ ከምትመካባቸው ማዘውተሪያዎች አንዱና ግንባር ቀደሙ እንደሆነ የሚነገርለት ጃንሜዳ ከወዲሁ የሚመለከተው አካል የመፍትሔ አቅጣጫ ካላስቀመጠለት በኮንዶሚኒየምና መሰል ግንባታዎች ህልውናቸው እንዳከተመው ማዘውተሪያዎች ተመሳሳይ ዕጣ ፋንታ ‹‹ይገጥመዋል›› ያሉም አልታጡም፡፡
በሌላ በኩል ዘንድሮ ከ40 በላይ ታላላቅ ስም ያላቸው አትሌቶች በተሳተፉበት በዘንድሮ የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ስድስት ኪሎ ሜትር ወጣቶች ሴቶች መካከል በተደረገው ፉክክር ለተሰንበት ግደይ ከትራንስ ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆናለች፡፡ አትሌቷ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 21፡16.53 ጊዜ ወስዶባታል፡፡ ዘይነባ ይመር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 21፡36.38 እና ሐዊ ፈይሳ ከመከላከያ 21፡43.08 በመግባት የሜዳሊያ ባለቤት ሆነዋል፡፡ ውዴ ከፋለ ከደብረ ብርሃን 21፡44.25 ቀጣዩን ደረጃ በመያዝ አጠናቃለች፡፡ ከምድቡ በቡድን አሸናፊ የሆኑት ደግሞ ትራንስ ኢትዮጵያ፣ ኦሮሚያ ክልልና አማራ ክልል ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ አግኝተዋል፡፡
በስምንት ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶች ተፈራ ሞሲሳ ከኦሮሚያ 24፡50.26 በሆነ ጊዜ ርቀቱን አጠናቆ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ሰለሞን ባረጋ ከደቡብ 24፡52.24 እና ሰለሞን በሪሁን ከትራንስ ኢትዮጵያ 24፡54.28 በመግባት ተከታትለው በመግባት የሜዳሊያ ባለቤት ሆነዋል፡፡ በቡድን ደግሞ አማራ፣ ኦሮሚያና ሲዳማ ቡና አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡
በአሥር ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶች ዳራ ዲዳ ከኦሮሚያ 35፡27.74 አሸናፊ ስትሆን፣ በላይነሽ ኦልጅራ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 35፡36.09 እና ገበያነሽ አየለ ከመከላከያ 35፡43.47 በመግባት፣ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል፡፡ ዘርፌ ልመንህ ከመከላከያ 35፡51.06 ርቀቱን አጠናቃ አራተኛ ሆና አጠናቃለች፡፡ በቡድን መከላከያ፣ አማራ ክልልና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊ ሆነዋል፡፡
በአሥር ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች ጌታነህ ሞላ ከመከላከያ በ31 ደቂቃ በማጠናቀቅ አሸናፊ ሆኗል፡፡ አባዲ ሐዲሽ ከትራንስ ኢትዮጵያ 31፡00.07 እና ሞገስ ጥኡማይ ከመሰቦ 31፡11.12 አጠናቀው እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ጨርሰዋል፡፡ ቦንሳ ዲዳ ደግሞ ከኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት 31፡17.23 አጠናቆ አራተኛ ሆኗል፡፡ በቡድን ደግሞ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ መከላከያና ኦሮሚያ ክልል አሸናፊ ሆነዋል፡፡ በመጨረሻም በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ የመጀመርያ በሆነው፣ የወንድና ሴት ድብልቅ ሩጫ (ዱላ ቅብብል) የኦሮሚያ ክልል አንደኛ ሲሆን፣ ፌዴራል ማረሚያና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለተኛና ሦስተኛ በመውጣት የሜዳሊያ ባለቤት ሆነዋል፡፡