Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከኢሕአዴግ ጋር የሚደረገው ድርድር በሰጥቶ መቀበል መርህ እንዲሆን 11 የፖለቲካ...

ከኢሕአዴግ ጋር የሚደረገው ድርድር በሰጥቶ መቀበል መርህ እንዲሆን 11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ

ቀን:

– የድርድሩ ስምምነት ውጤት ሕጋዊ ሆኖ እንዲፀድቅ ገዢው ፓርቲ ቃል ገብቷል

አሥራ አንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢሕአዴግ ጋር ሊደረግ የታሰበው ድርድር በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ጠየቁ፡፡

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባለፈው ዓመት በተቀሰቀሰው ሁከት ሳቢያ መንግሥትን የሚመራው ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ፣ የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት በመወሰን ከሕጋዊ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ቀነ ቀጠሮ ይዟል፡፡ በዚህም መሠረት ጥር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. በተደረገው የቅድመ ድርድር ውይይት በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የጋራ ስምምነት ላይ የተደረሰ በመሆኑ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በሁለት ረድፍ በመሆን ለድርድሩ በመዘጋጀት ላይ ናቸው፡፡

በውይይቱና በድርድሩ ላይ 21 የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚሳተፉ ማወቅ የተቻለ ሲሆን፣ ከመካከላቸው ስድስቱ ባለፈው ሳምንት ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

ሐሙስ የካቲት 2 ቀን 2009 ዓ.ም አሥራ አንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ደግሞ ሊደረግ የታሰበው ድርድር በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በመጠየቅ፣ ሕዝቡ ጉዳዩን ለፖለቲካ አመራሮች ብቻ ትቶ እንዳይቀመጥ አሳስበዋል፡፡

በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ለረዥም ጊዜ የሚታወቅ የመበታተን ባህልን የሚያስቀር ይሆናል የሚል ተስፋ የያዘው የአሥራ አንድ ፓርቲዎች ቡድን፣ ድርድሩ በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ሆደ ሰፊነት እንዲካሄድና ገዥው ፓርቲ ከዚህ ቀደም ሲያደርግ ከነበረው ለፖለቲካ ፍጆታ ከመጠቀም ወጣ እንዲል አሳስቧል፡፡

ከፓርቲዎቹ መካከል በመግለጫው ወቅት የተገኙት የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ አየለ ጫሚሶ፣ ኢሕአዴግ እዚህ የድርድር ውሳኔ ላይ መድረሱ ለፖለቲካ ችግሮች መፍትሔ ያስገኛል ብለዋል፡፡ ሒደቱ በቅንነትና በግልጽነት እንዲሆን በማሳሰብ፡፡ አቶ አየለ የስብስቡ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ ድርድሩ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን አፅንኦት ሰጥተው ንግግር ያደረጉ ደግሞ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፕሬዚዳንት አቶ ትዕግሥቱ አወሉ ናቸው፡፡

በስብስቡ ውስጥ የተካተቱት ሌሎች ፓርቲዎች አዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (ኢዴአን)፣ የኢትዮጵያ ፍትሕና ዴሞክራሲ ኃይሎች ግንባር (ኢፍዴኃግ)፣ የወለኔ ሕዝብ አንድነት ፓርቲ፣ የወለኔ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የመላው ኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ይገኙባቸዋል፡፡

ቀደም ሲል በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ መግለጫ የሰጡት ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድሩ ጠንከር ያለና ሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት እስከማሻሻል አልያም እስከመቀየር እንዲሆን የገለጹ ሲሆን፣ የአሥራ አንዱ ፓርቲዎች አቋም በአንፃሩ ለዘብ ያለ መስሏል፡፡

 በሌላ በኩል የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፣ ኢሕአዴግ በሚቀጥለው ረቡዕ የካቲት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሚካሄደው ውይይት ፕሮፖዛሉን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡

እንደ አቶ ሽፈራው ገለጻ ኢሕአዴግ መደራደር በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ ለመደራደር፣ መከራከር በሚያስፈልግባቸው የፖሊሲ ጉዳዮችም ላይ ለመከራከር ወስኗል፡፡ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በአራት ጉዳዮች ማለትም የስብሰባው አመራር ሥርዓት ምን ይምሰል? ስብሰባውን ማን ይምራው? ድርድሩን ማን ይታዘበው? ከውይይቶችና ከድርድሮች በኋላ ማን መግለጫ ይስጥና የመሰብሰቢያው ቦታ የት ይሁን የሚለው ቅድመ ድርድር ሐሳብ ተሰንዝሯል፡፡ ይህም በቀጣዩ ስብሰባ ይወሰናል ብለዋል፡፡ ኢሕአዴግ የመነሻ ፕሮፖዛሉን በማስገባቱ፣ ተቃዋሚዎችም ባስገቡት ፕሮፖዛል መሠረት ውይይት ተደርጎ ውሳኔ ይገኛል ሲሉ አቶ ሽፈራው ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ከዚህ በኋላ በሚኖሩት የውይይትና የድርድር ሒደቶች አጠቃላይ ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ሕግ ይሆናሉ ብለዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...