Sunday, June 4, 2023

ሶማሊያን እንደገና አገር የማድረግ ፈተና

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹በሃያ ሰባት ዓመታት የስደት ሕይወቴ የተማርኩት አገር አልባና ባይተዋር ሆኖ መኖር የቁም ሞት መሆኑን ነው፤›› የሚሉት አብዱላሂ ሐሰን ጌዶ አዲስ አበባ ቦሌ በተለምዶ 24 ቀበሌ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ውስጥ የሚኖሩ የ67 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ የሶማሊያ ስደተኛ ናቸው፡፡ በዚያድ ባሬ ዘመነ መንግሥት በመምህርነት፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተርነትና በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ደግሞ በሱፐርቫይዘርነት አገልግለዋል፡፡ በኬንያና በኢትዮጵያ በስደተኝነት ከ26 ዓመታት በላይ ማሳለፋቸውን የሚናገሩት ጌዶ፣ ‹‹አሁን ገና ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል እያየን ይመስለኛል፤›› ሲሉ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በሶማሊያ የተካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አስመልክተው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

‹‹አገራችን በጦርነት ፈራርሳ በሚሊዮኖች የምንቆጠር ሶማሊያዊያን ሞተን፣ ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት ተዳርገን፣ በአስከፊው ስደት ከገሃነም ያልተሻለ ስቃይ ተቀብለን ብዙ ነገሮችን አሳልፈናል፡፡ በስደት የተወለዱ ልጆቻችን በመከራ አድገው እነሱም በስደት ሌላ ትውልድ ፈጥረዋል፡፡ አገራችን ግን አሁንም ገሃነም ውስጥ ናት፡፡ ከዚህ ስቃይና መከራ ወጥተን አገራችንን እንደ አገር የምናዋቅርበት ጊዜ ላይ መሆን ይገባናል፡፡ ምርጫው እንዴትም ይካሄድ፣ ምንም ይሁን ብቻ አገሪቱን እንደገና ከማዋቀር የተሻለ ምንም አማራጭ የለንም፤›› ያሉት ጌዶ፣ ይህንን ተስፋ ሰጪ ጅምር መቀልበስ የሚሞክሩ ካሉ መወገዝ አለባቸው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች ከፍተኛ ጫና አድርገው ባለፈው ሳምንት አጋማሽ የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በምንም መመዘኛ የምርጫ ደረጃን ባያሟላም፣ ብዙዎች የተስማሙት ሶማሊያ እንደ አገር ለመቀጠል መንደርደሪያዋ እንደሚሆን ነው፡፡ ዋናው ጥያቄ ግን አዲሱ መንግሥት በሁለት እግሩ ቆሞ አገሪቱን ከገባችበት ቀውስ ውስጥ ያወጣታል የሚለው ነው፡፡ ያለፉት ሃያ ስድስት የባከኑ ዓመታትን ለታሪክ ትቶ እንደገና ከባዶ የመጀመር ጉዳይ አሳሳቢነቱ ግልጽ ነው፡፡ አልሸባብን የመሰለ ጽንፈኛ ቡድንና በጎሳዎች መካከል ያለውን ፉክክር አለዝቦ መረጋጋት ለማምጣት የሶማሊያዊያን አንድ ላይ መቆም የግድ የሚልበት ጊዜ መሆኑ በብዙዎች እየተነገረ ነው፡፡

ሶማሊያ በጣም ውስብስብ ከሆነው የጎሳ መረብ በተወከሉ 275 የሕግ አውጪና 54 የሴኔት አባላት ድምፅ የሰጡበት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ ከፍተኛ ጥበቃ በተደረገለት የቀድሞ የአየር ኃይል ጦር ሠፈር ውስጥ ያካሄደችው ረቡዕ የካቲት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው፡፡ የቀድሞው አምባገነን መሪ መሐመድ ዚያድ ባሬ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ በጦር አበጋዞች በሚመሩ የጎሳ ታጣቂዎች፣ የተለያዩ ፍላጎት ባላቸው ቡድኖችና ከዓመታት ወዲህ ደግሞ አልሻባብ በሚባለው ጽንፈኛ ቡድን ስትናጥ 26 ዓመታት አስቆጥራለች፡፡ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ (ፎርማጆ) የተመረጡበት የቀድሞ የአውሮፕላን ሃንጋር አካባቢ ከአንድ ቀን በፊት ሁለት ዙር የሞርታር ጥቃት ተሰንዝሮበት የነበረ ቢሆንም፣ ምርጫው ግን በሰላም ተጠናቋል፡፡

ከዚህ ቀደም ሶማሊያን ለማረጋጋትና ወደ ሰላም ለመመለስ በተደረጉ ጥረቶች እ.ኤ.አ. በ2004 በጂቡቲ፣ በ2007 በኬንያ፣ በ2012 ደግሞ ሞቃዲሾ በሚገኘው ፖሊስ አካዳሚ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች መካሄዳቸው ይታወሳል፡፡ የአሁኑ ምርጫ ከፖሊስ አካዳሚ ወደ ቀድሞው የአየር ኃይል የጦር ሠፈር የተዘዋወረው በፀጥታ ሥጋት ምክንያት መሆኑን ከሶማሊያ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በኤርፖርት ሃንጋር ውስጥ የተገኙት የፓርላማና የሴኔት አባላት ድምፅ ለሰጡበት የአሁኑ ምርጫ 20 ተወዳዳሪዎች ቢቀርቡም፣ በሁለተኛው ዙር የተወዳደሩት ግን ሁለት ዕጩዎች ናቸው፡፡ ከሃያዎቹ ተወዳዳሪዎች መካከል 16 ያህሉ የተለያየ ዜግነት ሲኖራቸው፣ ዘጠኙ የአሜሪካ ፓስፖርት የያዙ ናቸው ተብሏል፡፡ አራት የእንግሊዝ፣ ሦስት ደግሞ የካናዳ ፓስፖርት የያዙም አሉበት፡፡ የሶማሊያ የእርስ በርስ ጦርነት ለሚሊዮኖች መሰደድ መንስዔ በመሆኑ፣ ብዙዎቹ ስደተኞች የተለያዩ አገሮች ፓስፖርቶች አሉዋቸው፡፡ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ካናዳ፣ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በብዛት ይኖራሉ፡፡

የአሜሪካ ፓስፖርት ያላቸው ‘ፎርማጆ’ (ቺዝ የሚጠራበት የጣሊያን ስያሜ ሲሆን፣ ሰውየው የእንስሳት ተዋጽኦ ውጤቶችን ስለሚወዱ የተሰጣቸው ስያሜ ነው) ዕድሜያቸው 55 ሲሆን፣ ከኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ (ቡፋሎ) በታሪክና በፖለቲካ ሳይንስ ሁለት ዲግሪዎች ማግኘታቸውን የምርጫ ቅስቀሳ ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ ታዮ በመባል የሚታወቀው የፖለቲካ ፓርቲ መሥራችና የዳሮድ ጎሳ ተወላጅ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1985 ጀምሮ ነዋሪነታቸው አሜሪካ ሲሆን፣ በወቅቱ የ18 ዓመት ጎረምሳ ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቢሾሙም፣ ስምንት ወራት ብቻ ሠርተው ከሥልጣናቸው ተነስተዋል፡፡ እሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ነበር አልሸባብ ከሞቃዲሾ ተጠራርጎ የወጣው፡፡ አልሸባብን በማስወጣቱ ሒደት ደግሞ የኢትዮጵያ ጦር ትልቅ ድርሻ ነበረው፡፡ በወቅቱ ደመወዝ ተከፍሎት ለማያውቀው የአገሪቱ ጦር ክፍያ እንዲጀመር ማድረጋቸው ዝና አጎናፅፏቸዋል፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት ከዚህ ቀደም በአሜሪካ የሶማሊያ አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል፡፡ ለአሜሪካ መንግሥትም በተለያዩ ድርጅቶች ተቀጥረው ሠርተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1991 ጀምሮ በዚያድ ባሬና በጦር አበጋዞቹ፣ ከዚያም በአልሸባብ የፈራረሰችው ሶማሊያ 12 ሚሊዮን ሕዝቧ ለመከራ ከመዳረጉም በላይ፣ በየጊዜው የሚጎበኛት ረሃብ ደግሞ ሌላው ሰቆቃዋ ነበር፡፡ የአሁኑ ምርጫ ምን ይዞላት እንደሚመጣ ካሁኑ መተንበይ ባይቻልም፣ በሶማሊያ ውስጥ የተስፋ ስሜት መታየቱን ከመገናኛ ብዙኃን ዘገባ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሶማሊያን ይታደጋሉ በማለት ተስፋ ያደረጉ ሶማሊያውያን ድምፃቸው ተሰምቷል፡፡

እንደ ሮይተርስ ዘገባ በመኖሪያ ቤቶችና በካፌዎች ውስጥ የሞቃዲሾ ነዋሪዎች የምርጫውን ሒደት በጉጉት ተከታትለዋል፡፡ የሃያ ስድስት ዓመቱ አህመድ ሐሰን፣ ‹‹ወደፊት ሊያራምደን የሚችል ታማኝ መሪ እንፈልጋለን፤›› ብሏል፡፡ በቢቢሲ ዘገባ መሠረት በሺዎች የሚቆጠሩ አደባባይ በመውጣት የተመራጩን ፕሬዚዳንት ድል አክብረዋል፡፡ አሶሼትድ ፕሬስ በበኩሉ በደስታ የተዋጡ የሶማሊያ ወታደሮች ወደ ሰማይ በመተኮስ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል ብሏል፡፡ መሐመድ አብዱላሂ የአሜሪካ ፓስፖርት ቢይዙም፣ በብዙዎች ዘንድ እንደ ሶማሊያ መድህን ነው የተቆጠሩት፡፡ ለዚህም ይመስላል 184 ድምፅ በማግኘት 97 ድምፅ ያገኙትን ተሰናባቹን ፕሬዚዳንት ያሸነፉት በማለት ውጤቱን በንፅፅር ማሳየት የሚፈልጉ አሉ፡፡ ‹‹ታሪክ ተሠራ›› ያሉት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ፣ ‹‹ወደ ዴሞክራሲ የሚያመራንን መንገድ ይዘናል፡፡ በመሆኑም መሐመድ አብዱላሂ ፎርማጆን እንኳን ደስ ያለህ ማለት እፈልጋለሁ፤›› በማለት ሽንፈታቸውን በፀጋ መቀበላቸው ተዘግቧል፡፡ ተመራጩ ፕሬዚዳንት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለስምንት ወራት ያህል በሠሩበት ወቅት ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር የነበራቸው ግንኙነት መልካም እንደነበር የሚያወሱ አሉ፡፡ ነገር ግን ሥራቸውን በነፃነት ማከናወንና የማንንም ተፅዕኖ ማስተናገድ ስለማይፈልጉ፣ በተለይ ከኢትዮጵያና ከኬንያ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ጠንከር ሊሉ ይችላሉ የሚሉ ወሬዎች ተሰምተዋል፡፡ ከተሰናባቹ ፕሬዚዳንት የሚለዩትም በዚህ እንደሆነ ከወደ ሶማሊያ እየተሰማ ነው፡፡

ሶማሊያ እ.ኤ.አ. በ1991 ማዕከላዊ መንግሥቷ ፈርሶ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ከአገር ከኮበለሉ በኋላ፣ በቀጥታ የገባችው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ነበር፡፡ በጦር አበጋዞች የጎሳ ግጭት ስትናጥ የነበረችው አገር አንዴ በእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት፣ ከዚያም በአልሸባብ መከራዋን አይታለች፡፡ ማዕከላዊ መንግሥት ለመመሥረት በጎረቤት አገሮችና በሌሎች የውጭ ኃይሎች ጥረት ቢደረግም፣ አቅመ ቢስና በሌሎች ላይ ጥገኛ የሆኑ መንግሥታት በየጊዜው ለመፍጠር ተሞክሯል፡፡ ነገር ግን ውስብስቡ የጎሳዎች መስተጋብርና ሽብርተኝነት የተጠናወተው አልሸባብ ግን ጠንካራ መንግሥት እንዳይፈጠር አድርገዋል፡፡ ለይስሙላ መንግሥት አለ ቢባልም አገሪቱ አሁንም የምትጠበቀው 22 ሺሕ በሚሆኑ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ድባብ ውስጥ ነው አዲሱ ፕሬዚዳንት ሥልጣን ይዘው መንግሥት የሚመሠርቱት፡፡ ሰውየው በብዙዎች ታማኝና ንፁህ ሆነው ቢታዩም፣ የፓርላማ አባላት ድምፅ የሰጡበት ሁኔታ ግን በሙስና የተበከለ መሆኑን በበርካታ ዘገባዎች ተገልጿል፡፡ የፓርላማ አባላቱ የተመረጡት በ14 ሺሕ መራጮች ብቻ መሆኑንና እነሱም ድምፃቸውን በገንዘብ ሸጠዋል ተብሎ በተለያዩ ዘገባዎች ተጠቅሷል፡፡ ይህም ምርጫ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮች የተከሰከሱበት በጣም ውድ ምርጫ ተብሏል፡፡ በእርግጥ ወጪው ከተለያዩ አገሮች በልገሳ የተገኘ ነው፡፡ ይህ ሆኖም ግን አዲሱ ፕሬዚዳንት ከሙስና የፀዱ ስለሆኑ እስቲ ዕድሉ ይሰጣቸው የሚሉ በርክተዋል፡፡

ተመራጩ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ የሚጠብቁዋቸው ፈተናዎች ብዙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ለ26 ዓመታት የዘለቀውን የጎሳዎች ግጭት ማስቆም፣ ጠንካራና ውጤታማ መንግሥት መመሥረት፣ ጽንፈኛውን አልሸባብ አዳክሞ ማጥፋት፣ ለረሃብ የተጋለጡ 2.9 ሚሊዮን ሶማሊያዊያንን መታደግ፣ ሁሉንም ወገኖች አሳታፊ የሚያደርግ የፖለቲካ ዓውድ ማመቻቸት፣ የተንኮታኮተውን ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ማድረግ፣ ወዘተ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ የሶማሊያ ቀውስ በጣም ጥልቅ ከመሆኑ የተነሳ አገሪቱን በሁለት እግሮቿ ለማቆም ሁሉም ሶማሊያዊያን ከነልዩነቶቻቸው አብረዋቸው ካልቆሙ፣ ሁሉም ነገር ወደነበረበት መመለሱ እንደማይቀር ብዙዎችን ያስማማል፡፡ ለዚህ ሁሉ መሠረቱ ግን የሰላምና የፀጥታ ጉዳይ ነው፡፡ የሶማሊያ ጦር ኃይል አለ ቢባልምና በተለያዩ ዘመቻዎች ተሳትፎው ቢነገርም፣ ከወረቀት የዘለለ እዚህ ግባ የሚባል ሚና እንደሌለው ነው የሚታወቀው፡፡ ከጦሩ ይልቅ የጎሳ ሚሊሻዎች አልሸባብን በመዋጋት ይታወቃሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የምዕራብ ዲፕሎማት፣ ‹‹ለሶማሊያ ሠራዊት ግንባታ ከበቂ በላይ ገንዘብ ቢመደብም የተገኘው ውጤት ግን እዚህ ግባ የማይባል ነው፤›› ነበር ያሉት፡፡

ሌላው ቀርቶ ዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ የፀጥታዋ ሁኔታ አስተማማኝ አይደለም፡፡ ሆቴሎች፣ ገበያዎች፣ ተሽከርካሪዎች፣ የአፍሪካ ኅብረት ቤዝ፣ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ፓርላማ፣ ወዘተ በተለያዩ ጊዜያት የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት በአልሸባብ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ባለፈው ወር ብቻ በአንድ ሆቴል ላይ በተፈጸመ ጥቃት 21 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ብዙዎቹ የውጭ ዜጎች በታጠቁ ጠባቂዎች አጀብ ነው ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱት፡፡ ይህ የደኅንነት ክፍተት አገሪቱ አሁንም ከፍተኛ የፀጥታ ችግር እንዳለባት ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ ሠራዊትና በአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል አከርካሪው ተመቶ የነበረው አልሸባብ፣ አሁንም በርካታ ሥፍራዎች በቁጥጥሩ ሥር ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማንሰራራት የፈጸማቸው ጥቃቶች ለአዲሱ መንግሥት ራስ ምታት መሆናቸው አይቀሬ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ምርጫው ራሱ በከፍተኛ ጥበቃ ሥር መጠናቀቁ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ እጃቸውን ማስገባት የሚፈልጉ የአካባቢው አገሮች፣ ምዕራባውያንና የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች የተለያዩ ፍላጎቶች ለሰላምና መረጋጋት ጠንቅ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

በሶማሊያ የፍትሕ ሥርዓቱም ሆነ የታክስ ሥርዓቱ እንደሌሉ ነው የሚቆጠሩት፡፡ ይህ ክፍተት ደግሞ ለሕገወጥ ድርጊቶች አገሪቱን አጋልጧታል፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር መተዳደር ምን ማለት እንደሆነ የማያውቅ አንድ ትውልድ መፈጠሩ ሌላው ችግር ነው፡፡ የግል ሴክተሩ በአነስተኛ ደረጃ የተስፋፋ ቢሆንም ለመንግሥት ካዝና ጠብ የሚል ነገር የለውም፡፡ ይልቁንም የመንግሥት ዕዳ ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር ማሻቀቡ ሲነገር፣ መንግሥት ባለፈው ዓመት ያገኘው ያውም ከኤርፖርት ክፍያዎች 230 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ በአገሪቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በሚመለከት ምንም ዓይነት የሕግ ማዕቀፍ የለም፡፡ ሁሉም ነገር በዘፈቀደ የሚከናወን በመሆኑና ሥርዓት አልበኝነት በመንገሡ፣ በመንግሥታዊ መዋቅር ውስጥም ሆነ በሕዝቡ ውስጥ ሙስና መንሰራፋቱ ነው የሚነገረው፡፡ ትራንስፓርንሲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ሶማሊያ ሙስና ውስጥ በጣም ከተዘፈቁ አገሮች ተርታ ግንባር ቀደሟ ናት፡፡ ላለፉት አሥር ዓመታት በዚህ አስከፊ ጎዳና ላይ መሆኗን ነው ሪፖርቱ ያረጋገጠው፡፡ የአዲሱ የሶማሊያ መንግሥት አንዱ ፈተና ደግሞ ይኼ ነው፡፡

ሶማሊያዊያን ለአዲሱ ፕሬዚዳንት ድጋፋቸውን ለመግለጽ በብዛት በሞቃዲሾ ጎዳናዎች ላይ መታየታቸውና ወታደሮችም ደስታውን በተኩስ ማጀባቸው ለመገናኛ ብዙኃን አስገራሚ ክስተት ነበር፡፡ ከፍተኛ የሆነ የፀጥታ ሥጋት ባለባት ሞቃዲሾ ደስታ የፈነቀላቸው ዜጎች በድፍረት አደባባይ መውጣት አዲስ ተስፋ የመሻት እንደሆነና ይህም ተስፋ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ የጨነገፈች አገርን እንደ አገር የማቆም ፍላጎት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይህንን ፍላጎት ደግሞ የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደተጋሩት በመግለጫዎቻቸው አስታውቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ፎርማጆ አገሪቱን ከተዘፈቀችበት ቀውስ ውስጥ የማውጣት ትልቅ ኃላፊነት ተቀብለው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡ ኢድሪስ ሸሪፍ የተባለ የሞቃዲሾ ነዋሪ አደባባይ በደስታ ወጥቶ፣ ‹‹ይህ ሰው መልካም አስተዳደር ብቻ አይደለም የሚያመጣልን፡፡ እኛ ሶማሊያዊያንን እንደገና አንድ ያደርገናል፡፡ እሱ የዚህ ሕዝብ ፕሬዚዳንት ሲሆን፣ እኛ ደግሞ ድጋፋችንን እንሰጠዋለን፤›› በማለት ተስፋውን በተመራጩ ፕሬዚዳንት ላይ መጣሉን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

የአዲስ አበባው አብዱላሂ ሐሰን ጌዶ ደግሞ፣ ‹‹ይህ ሰው ለአጭር ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ሲሠራ መንግሥት እንዴት መመራት እንዳለበት ምልክት አሳይቶ ነበር፡፡ አሁን ግን ሙሉ ሥልጣን ጨብጦ ሶማሊያዊያን በሙሉ ከጎኑ ከቆምን ሶማሊያ እንደገና አገር ትሆናለች የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ የእኛም ሆነ የልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን ስደት ያበቃል፡፡ ፈጣሪ ይኼንን ካሳካልን በችግራችን ጊዜ የደረሱልንን በሙሉ እያመሰገንን ሶማሊያን ሰላማዊትና ዴሞክራሲያዊት አገር ለማድረግ ወጣቶቻችን እንዲነሱ እንመክራቸዋለን፡፡ ያለው አማራጭ ይኼ ብቻ ነው፡፡ አሁን የአንድነታችንና የሰላማችን ጅምር ተስፋ ላይ ያለን ይመስለኛል፤›› በማለት ተስፋቸውን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ሥጋታቸውን የገለጹም አሉ፡፡ የእነዚህኞቹ ጥቅል ሐሳብ ከመጠን ያለፈ ስሜታዊነትና ጉጉት ውስጥ ሆኖ መጪውን ጊዜ መተንበይ አስቸጋሪ ነው የሚል ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ በሰከነ መንፈስ ሁኔታዎችን መመልከት ያሻል ብለው፣ ለውጥ መጥቶ አገሪቱ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ እንድትወጣ በትዕግሥት ነገሮችን መከታተል ያስፈልጋል ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡ ጽንፈኝነትና ጎሰኝነት ለነገሠባት ሶማሊያ መልካሙን መመኘት ጥሩ ቢሆንም፣ ፈተናዎችን እንዴት ማለፍ እንደሚቻል በጥንቃቄ ማሰብ ይገባል ባይ ናቸው፡፡ ይሁንና የአራት ልጆች አባል የሆኑትና ከዳሮድ ጎሳ የተገኙት መሐመድ አብዱላሂ ፎርማጆ፣ በሐውዬ ጎሳ በተከታታይ ይያዝ የነበረውን የሶማሊያ ፕሬዚዳንትነት ሥልጣን መያዛቸው ብዙዎችን ሶማሊያውያን ሊያግባባ ይችላል ተብሏል፡፡ የጎሳ ክፍፍሉ የአገሪቱን ፖለቲካ በተቆጣጠረበት ሶማሊያ የአብዛኛውን ሕዝብ ድጋፍ ማግኘት ከምንም ነገር በላይ ሰላም ለማስፈንና ሙስናን ለማስታገስ ጠቃሚነቱ እየተወሳ ነው፡፡ ‹‹ይህ ለሶማሊያ የአንድነት ጅማሬ ነው፡፡ እንዲሁም በአልሸባብና በሙስና ላይ ዘመቻ የምንጀምርበት ነው፤›› ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ለሶማሊያዊያን ቃል ገብተው ሥራቸውን ጀምረዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -