Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ከዚህ በፊት የታዩ ጉድለቶች በአሥረኛው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እንዳይደገሙ ይደረጋል››

አቶ ማቴዎስ አስፋው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ፕላን ኮሚሽነር

የ130 ዓመታት ዕድሜ ባለፀጋ የሆነችው አዲስ አበባ፣ አሥረኛውን ማስተር ፕላን በይፋ ተግባራዊ ለማድረግ የመጨረሻ ውሳኔ በመጠበቅ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ማስተር ፕላን በ2006 ዓ.ም. የመጠቀሚያ ጊዜው ያበቃውን ዘጠነኛውን ማስተር ፕላን የሚተካ ሲሆን፣ በውስጡ እጅግ አጓጊ ዕቅዶችን ይዞ ቀርቧል፡፡ ማስተር ፕላኑ በተለይ የመካከለኛውን የከተማው ክፍል ዞን አንድ ብሎ በመሰየም ረዣዥምና ከፍተኛ ጥግግት ያላቸው አገልግሎት መስጫ ግንባታዎች የትራንስፖርት አውታር መነሻ፣ የአረንጓዴ ልማት እምብርትና ለእግረኞች እንቅስቃሴም ሁነኛ ሥፍራ ሆኖ ተዘጋጅቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ይህንን አማላይ ዕቅድ በትክልል ተግባራዊ ለማድረግ አራት ተጨማሪ ተቋማት እንዲቋቋሙ ምክንያት ከመሆኑ ባሻገር፣ ፕላኑ በቅጡ ተግባራዊ እንዲደረግ ግዙፍ የመዋቅር ለውጥ ፕሮግራሞችን አስከትሎ ቀርቧል፡፡ በተለይ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በከተማው ታሪክ ትልልቅ ለውጦች እንዲመጡ ምክንያት የሆነውን ዘጠነኛው ማስተር ፕላን፣ እንዲሁም በዘጠነኛው ማስተር ፕላን የታዩ ክፍተቶችን ሞልቶ የራሱን ወርቃማ መለያዎች ይዞ የተዘጋጀው አሥረኛው ማስተር ፕላን በማዘጋጀት በኩል ዋነኛ ተዋናይ የሆኑትን አቶ ማቴዎስ አስፋውን ውድነህ ዘነበ አነጋግሯቸዋል፡፡ አቶ ማቴዎስ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ለተቋቋመው የአዲስ አበባ ከተማ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር አድርጎ ሾሟቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ ከተቆረቆረች 130 ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ በተለይ ከጣሊያን ወረራ በፊት ፍል ውኃ፣ አራት ኪሎና አራዳ ጊዮርጊስ፣ ከድል በኋላም የተወሰኑ ዘመናዊ አካባቢዎችን ማልማት ተችሏል፡፡ ከተማው በዚያን ጊዜ ከአሥርና ከሃያ ኪሎ ሜትር የበለጠ ስፋት አልነበረውም፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ከተማው ያለውን መሬት በሙሉ ተጠቅሟል ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ሁኔታ ፕላንን የተከተለ ነው ማለት ይቻላል? ምክንያቱም ከተማዋ ከተቆረቆረች ጊዜ ጀምሮ ዘጠኝ ማስተር ፕላን ብታስተናግድም ማስተር ፕላን የጎበኛቸው የማይመስሉ ግንባታዎች በስፋት ስላሉ ነው ይህንን የምጠይቅዎ?

አቶ ማቴዎስ፡- አዎን! ዕድገቱ ያመጣው ነው፡፡ ግን ግንባታው የተካሄደው በፕላን ብቻም አይደለም ልንል እንችላለን፡፡ ከፕላን ውጭ የተሠሩ ሥራዎችም ስላሉ ማለት ነው፡፡ የከተማይቱን የጎንዮሽ መስፋፋት እንዳየኸው ከአራዳ ተነስቶ በሁሉም አቅጣጫ በተለይ በምሥራቅ፣ በምዕራብና በደቡብ አቅጣጫዎች ተስፋፍቷል፡፡ በሰሜን እንኳ በብዙ ነገሮች  የተገታ ስለሆነ ያን ያህል አልሄደም፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት የተደረገው መስፋፋት ወደ ምሥራቅና ወደ ደቡብ ነው፡፡ እንዳልከው ከመሀል ተነስቶ በተለያየ አቅጣጫ እያደገ የመጣው በፕላኖቹ መሠረት ነው፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባ አሁን ያለችበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክልል የምንለው የተደረሰበት በደርግ ዘመን በ1967 ዓ.ም. ተጀምሮ፣ በ1976 ዓ.ም. የተጠናቀቀው የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ወቅት ነው፡፡ ከተማው የደረሰበት የጎንዮሽ መስፋፋት ማለት ነው፡፡ የዛሬ 32 ዓመት ይህ ማስተር ፕላን ለአዲስ አበባ መቶኛ ዓመት ቀርቦ  ተግባራዊ ሆኖ ነበር፡፡ ነገር ግን ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ከተማ እስከገባ ድረስ ይህ ማስተር ፕላን ሲሠራበት ቆይቷል፡፡ ከሞላ ጎደል ሳይፀድቅ ቆይቶ ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ማስተር ፕላኑን እንዳለ ወስዶ አፅድቆ ሲገለገል ቆይቷል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ በዘጠነኛውና በአሥረኛው ማስተር ፕላኖች ዝግጅት ላይ ዋነኛ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ከዚያ በፊት የነበሩት ስምንት ማስተር ፕላኖችን የመገምገም ዕድሉ ይኖሮዎታልና እንዴት ነበር አተገባበራቸው? በአብዛኛው ተግባራዊ ሆነዋል ማለት ይቻላል? በከተማው ላይ ያሳደሩት ተፅዕኖስ ምን ይመስላል?

አቶ ማቴዎስ፡- ስምንቱ ማስተር ፕላኖች የተወሰነ ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡ በተለይ ዋና ዋና የመሠረተ ልማት አውታሮችን ከማሟላት አኳያና የከተማዋን የዕድገት አቅጣጫ ከመወሰን አኳያ ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡ የመጀመርያው ማስተር ፕላን የምንለው በወረቀት ያልሰፈረው የእቴጌ ጣይቱ የአሰፋፈር ዕቅድ ጀምሮ፣ በየጊዜው የተዘጋጁት ማስተር ፕላኖች የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል፡፡ አንዳንዶቹ ማስተር ፕላኖች ለምሳሌ የቸርችል ጎዳናን ብንመለከት ማስተር ፕላኑን ተከትሎ የተሠራ ነው፡፡ ከተማይቱን እስከ አቃቂ ቃሊቲ የመውሰድ ዕቅድ ፕሮፌሰር ፓሎኒ ያዘጋጁት የማስተር ፕላን አካል ነው፡፡ የከተማይቱን ዕድገትና ዋና ዋና ማስተር ፕላኖች ከመወሰን አኳያ ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡ ግን ወደ ዝርዝሩ ከሄድን የመኖሪያ ቤቶች አካባቢ የሚሠሩትን የቤት ዓይነቶች፣ የሥራ ቦታ አካባቢ የሚሠሩ ሕንፃዎችን፣ የሥራ ቦታዎችና የመኖሪያ አካባቢዎች፣ እንዲሁም የመዝናኛ አካባቢዎች የሚገኙባቸው የትራንስፖርት አውታሮችና እንዲሁም በከተማው ሊኖሩ የሚገባቸውን አገልግሎቶች በተዋረድ የማስቀመጥ ሒደት ላይ፣ በማስተር ፕላኑ የተቀመጡትን የመሬት አጠቃቀሞች በአግባቡ ከመተግበር አኳያ በርካታ ከማስተር ፕላኑ ያፈነገጡ ሥራዎች ነበሩበት፡፡ ይህ የሆነበትን በርካታ ምክንያቶች ማየት እንችላለን፡፡ ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ አንደኛ ፕላኖቹ የተዘጋጁት በአመዛኙ ከተማውን በማያውቁ ሰዎች ነው፡፡ ወይም ባለሙያዎች ለተወሰነ ጊዜ ከተማውን ዓይቶ ማስተር ፕላኑን አዘጋጅተው ይሄዳሉ፡፡ አንዳንዶቹ ማስተር ፕላኖች ደግሞ በፍፁም አገሪቱንም ከተማይቱንም አይተው በማያውቁ ለምሳሌ በጣሊያን ወረራ ጊዜ አንደኛው ማስተር ፕላን ሮም ከተማ ውስጥ ነው የተዘጋጀው፡፡ ከተማይቱን በማያውቅ ሰው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ትልቁ ጉድለት የሚነሳው ከዚህ ነው፡፡ ማስተር ፕላኖቹ የተዘጋጁት የከተማውን ባህሪ፣ የሕዝቡን ሥነ ልቦና፣ ባህልና ታሪክ በማያውቁ ሰዎችና የከተማውንና የሕዝብን ፍላጎት በአግባቡ በማይረዱ ሰዎች ነበር፡፡ የማስተር ፕላን ዝግጅቱ በተመለደው የአውሮፓ ከተሞች ዕድገት ላይ ልምድ የነበራቸው ባለሙያዎች የሚያዘጋጁት ስለነበር ያንን አምጥቶ እዚህ ላይ የመጫን ሐሳብ ነበር፡፡

ሁለተኛው ለአንድ ከተማ ማስተር ፕላን ተዘጋጀ ማለት፣ ማስተር ፕላኑ ራሱ ወደ ተግባር የሚገባ አይደለም፡፡ ተግባር አካል ይፈልጋል፡፡ የአንድ ከተማ ማስተር ፕላን ማለት የአንድ ከተማ ሕገ መንግሥት ማለት ነው፡፡ በማስተር ፕላኑ ላይ የተቀመጠውን ራዕይ፣ በማስተር ፕላኑ ላይ የተቀመጡ ግቦችንና ዝርዝር ተግባራቸውን ለመተግበር የሚያስችሉ ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡  በሌላ በኩል ተግባሪ ተቋማት ብቻ ሳይሆን፣  ተቋማት ማስተር ፕላኑን ተከትለው መሥራት አለመሥራታቸውን የሚከታተልና የሚቆጣጠር የፕላኑ ባለቤት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም አልፎ ማስተር ፕላኑ የፈለገውን ወርቃማ ሐሳብ ቢኖረውም፣ ለነዋሪውም ለአገሪቱም የሚጠቅም የተዋበ ሐሳብ ቢኖውም፣ የሚተገበረው በሕዝብ ላይ ነው፡፡ ከሞላ ጎደል ማስተር ፕላኑን ጠንቅቆ የሚያውቅ የከተማ ነዋሪ ያስፈልጋል፡፡ እንግዲህ እነኝህን ነገሮች ስናይ በተለይ እስከ ሰባተኛው ማስተር ፕላን ድረስ ስናይ ሕዝብ  ያውቀዋል? የሚቆጣጠር አካልስ አለ ወይ? ተግባሪ ተቋማት ያውቁታል ወይ? ተግባሪ ተቋማትን የሚከታተልና የሚቆጣጠር አካል አለ ወይ? ስንል እነዚህ ሁሉ የሉም፡፡ የነበሩን ማስተር ፕላኖች በወረቀት ላይ የተቀመጡ ነበሩ፡፡ ያንን ፕላን ተከትሎ የተጻፉ ማብራሪያ ጽሑፎች ነበሩ፡፡ ስለዚህ ያንን ማስተር ፕላን በአግባቡ ለመተግበር ተቋማት ባልነበሩበትና ስለማስተር ፕላኑ የሚያውቁ ባለሙያዎች ባልነበሩበት፣ ባለሙያዎች ስንል አገር በቀል ባለሙያችዎች ማለታችን ነው፡፡ በሕዝብም ዘንድ ስለማስተር ፕላን ምንም ግንዛቤ ባልነበረበት ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡

በተለይ በአመዛኙ በከተማው ውስጥ የሚካሄዱትን የልማት እንቅስቃሴዎች ፈር ከማስያዝ አኳያ በንጉሡ ዘመን የመሬት ባላባቶች ነበሩ ትልቅ ሚና የነበራቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ነገሮች የየራሳቸው ሚና ነበራቸው፡፡ ምናልባት የተወሰነም ቢሆን ስለከተማ ፕላን ምንነት፣ የከተማ ፕላን እንዴት ይሠራል? የሚለው ነገር የመጣው በስምንተኛው ኢትዮ-ጣሊያን ማስተር ፕላን ጊዜ ነው፡፡ ይህ ስምንተኛው ማስተር ፕላን በፌዴራል የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ሥር በተቋቋመ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አብዛኛዎቹ ባለሙያዎች የጣሊያን፣ የተለያዩ የአውሮፓና የኛም ባለሙያዎች በተወሰነ ደረጃ ገብተውበት ማስተር ፕላኑ ተዘጋጅቷል፡፡ ያኔ ነው በተወሰነ ደረጃ ባለሙያዎቻችን ስለማስተር ፕላን ዝግጅት ሐሳብና ዕውቀት ለማግኘት የቻሉት፡፡ ስለዚህ ስምንተኛው ማስተር ፕላን ለብዙ ነገሮች ፋና ወጊ ነበር፡፡ ምንም እንኳ የጣሊያን ባለሙያዎች የነበሩበት ቢሆንም፣ የእኛም ባለሙያዎች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ የፕላን ዝግጀቱ ላይ ከጣሊያን አንድ ሥራ አስኪያጅ፣ ከኢትዮጵያ አንድ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ነበር ፕላኑን የመሩት፡፡ በእኛ ወገን ፕሮፌሰር ተከስተ ነበሩ፡፡ ፕሮፌሰር ተከስተ ዕውቅ ባለሙያ ነበሩ፡፡ በዚያን ጊዜ ለከተማችንና ለአገሪቱ በቀጣይ ማስተር ፕላን ሊያዘጋጁ የሚችሉ ባለሙያዎች እንዲሰባሰቡ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱና ፕሮፌሰር ተከስተ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ ከዚያ በተገኘ ልምድ ነው በአገር አቀፍ ደረጃ የከተማ ፕላን ኢንስቲትዩት ተብሎ የተቋቋመው፡፡ ለአገራችን ይህ የመጀመርያ ተቋም ነው፡፡ የኢንስቲትዩቱ ዓላማ ይህን የማስተር ፕላን ዝግጅት በተከታታይ የውጭ ባለሙያዎች እየመጡ የሚያዘጋጁት መሆን የለበትም፡፡ አገራዊ ባለሙያዎች በኢንስቲትዩቱ ሠልጥነው የአዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን፣ የክልሎችንም ማስተር ፕላን እንዲያዘጋጁ ጥረት ሲደረግ ነበር፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ነው ወደ ዘጠነኛው ማስተር ፕላን የተገባው፡፡  

ሪፖርተር፡- ሰባቱ ወይም ስምንቱ ማስተር ፕላኖች በውጭ ባለሙያዎች የተዘጋጁ ናቸው፡፡ እነዚህ ማስተር ፕላኖች የተዘጋጁት ከተማውን በሚያውቁ ሰዎች አልነበረምና አተገባበሩም መልካም አይደለም፡፡ በዘጠነኛውና አሁን በይፋ ይፀድቃል ተብሎ የሚጠቀበውን አሥረኛው ማስተር ፕላን በትክክል ተግባራዊ ለማድረግ፣ ከተማውን በሚገባ የሚያውቁ  ባለሙያዎችና አመራሮች ያስፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በተለይ በአመራር ቦታ ላይ የሚገኙ ከተማውን በቅጡ ይረዳሉ ብለው እንደማያምኑ በርካታ የከተማው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የእርስዎ መሥሪያ ቤት ከተማው፣ ከተማውን በሚያውቁ ሰዎች እንዲመራ ለመንግሥት ያቀረበው ሐሳብ ይኖር ይሆን? የአዲስ አበባ ቻርተርም አዲስ አበባ በአዲስ አበባውያን ትመራለች ይላል፡፡

አቶ ማቴዎስ፡- የከተማ ፕላንና የከተማ ሥራ አመራር ተነጣጥለው የሚታዩ አይደሉም፡፡ እንዲሁም የከተማ ፕላን ስንል፣ የከተማ ፕላን ምንነት ሲገለጽ፣ ማስተር ፕላንን በሚገባ ተግባራዊ ለማድረግ የከተማ ሥራ አመራር አንደኛው መሣሪያ ነው የምንለው፡፡ ከተማን መምራት የሚያስፈልጉ በርካታ ሌሎች መሣርያዎች አሉ፡፡ ነገር ግን አንደኛው ማስተር ፕላን ነው፡፡ ስለዚህ ተነጣጥለው የሚታዩ አይደሉም፡፡ ከተማ እመራለሁ ስትል እጅህ ላይ ማስተር ፕላን አለ ማለት ነው፡፡ ማስተር ፕላን ሳይጨበጥ ከተማ እመራለሁ ማለት ባትሪ ሳይኖር የጨለማ ጉዞ እንደ መጓዝ ነው፡፡ ማስተር ፕላኑን ጨበጥን ማለት ማስተር ፕላኑ ላይ የተቀመጡ ጉዳዮችን፣ ማስተር ፕላኑ ከምን ተነስቶ እንደተጠና የተቀመጡ ግቦችን፣ ማስተር ፕላንና የከተማ ሥራ አመራርን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ግቦቹ የማይመጥኑ፣ ከከተማው ታሪክ፣ ሥነ ልቦና ከተማው በአገሪቱ ዕድገት ላይ የሚጫወተው ሚና፣ ከእነዚህ ሁሉ ተነስቶ ማኅበራዊ ጥናቶች፣ የኢኮኖሚ ጥናቶች፣ የአካባቢ ጥበቃ ጥናቶች፣ የሥነ ሕዝብ ጥናቶችን ጨምሮ በርካታ የተወሳሰቡ ጥናቶች ይካሄዳሉ፡፡ እነኚህ ሁሉ ታክለው ነው ማስተር ፕላኑ ራዕይና ግቡ የሚቀመጥለት፡፡ ስለዚህ ከተማ ማስተዳደር ማለት ትልቁ ጉዳይ፣ ይህ ሁሉ ሐሳብ ያለበትን ማስተር ፕላን ተረድቶ በዚህ መሠረት ከተማውን መምራት ነው፡፡ ስለዚህ አንተም እንደጠቀስከው በተለያዩ መድረኮች ላይ እንደምንለው አመራሩ ማስተር ፕላኑን በአግባቡን መረዳት አለበት፡፡ እንደ ትልቅ የከተማ መሣርያ አድርጎ ማየት አለበት፡፡ ስለዚህ የአመራሩን ብቃት የምናየው ከማስተር ፕላኑ ጋር አያይዘን ነው ማለት ነው፡፡ ከተማውንም በአግባቡ መረዳት አለበት ስንል ይህን ማለታችን ነው፡፡ ማስተር ፕላኑ የሚዘጋጀው በመጀመርያ ከተማውን በአግባቡ ከመረዳት ነው፡፡ በአመዛኙ ደግሞ መነሻ የሚያደርገው ለአብነት አሥረኛው ማስተር ፕላን ዘጠነኛውን ማስተር ፕላን ይዞ ይነሳል፡፡ በዘጠነኛው ማስተር ፕላን የስምንተኛው ማስተር ፕላን ተፅዕኖ አለ እንደማለት ነው፡፡ አሥረኛው የዘጠነኛውን ማስተር ፕላን ጉድለትና ሐሳቦች አገናዝቧል፡፡ ምርምርና ትንተና አድርጎ ይነሳል ስንል በፊት የነበሩ ሐሳቦች ተካተውበታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከመሠረቱ ከተማይቱ እንዴት ነበረች? እንዴት መጣች? ከማስተር ፕላኑ አንፃር ደግሞ በቀጣይ መያዝ የሚገባቸው ምንድናቸው? በቀጣይነት ከተማይቱ የራሷን መለያ እየገነባች ነው ወይ? እነዚህ ነገሮች ሁሉ መታወቅ አለባቸው፡፡ ስለዚህ ነው አመራሩ ከተማይቱንና ማስተር ፕላኑን በወጉ መረዳት ይኖርበታል የምንለው፡፡

ሪፖርተር፡- በ1996 ዓ.ም. ተግባራዊ መደረግ ጀምሮ በ2006 ዓ.ም. የመጠቀሚያ ጊዜው ያበቃው ዘጠነኛው ማስተር ፕላን በኤግዚቢሽን ማዕከልና በተለያዩ ቦታዎች ሰፊ ውይይት ተደርጎበት ነበር፡፡ በዚህ ማስተር ፕላን የተካተቱት ዕቅዶች የከተማውን ነዋሪዎች ያማለሉ ነበሩ፡፡ ለአብነት 16 አዳዲስ ፓርኮችና በርካታ የገበያ ማዕከላት ግንባታ ታቅዶ ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህና ሌሎችም ዕቅዶች ሳይተገበሩ ቀርተዋል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ለምሳሌ ጀሞ አካባቢ የኢንዱስትሪ ዞን ተብሎ ታቅዶ፣ በኋላ የቤቶች ልማት ተካሂዶበታል፡፡ ከእነዚህ ቁም ነገሮች አንፃር ዘጠነኛው ማስተር ፕላን በትክክል ተተግብሯል ማለት ይቻላል? ከዚህ በተጨማሪም ማስተር ፕላኑ ወደ ተግባር በመጣበት ወቅት ትልቅ የመዋቅር ለውጥ ተደርጎ አብዛኞቹ የከተማው አስተዳደር ሠራተኞች ከደረጃቸው ዝቅና ከፍ ተደርገዋል፡፡ አሥረኛው ይህን ዓይነት ክስተት ያስተናግዳል ወይ? ማስተር ፕላን ሲመጣ የመዋቅር ለውጥ ለምን ያስከትላል?

አቶ ማቴዎስ፡- እንዳልከው ዘጠነኛው ማስተር ፕላን ይዞ የተነሳቸውና ያስቀመጣቸው ጉልህ ጉልህ ሐሳቦች ምን ያህሉ ተተግብረዋል? ስንል አንተ የጠቀስከው በኤግዚቢሽን ማዕከል ለ15 ቀናት ሕዝባዊ ኤግዚቢሽን አድርገን ነበር፡፡ በማዘጋጃ ቤትም እንዲሁ ከአዳራሽ ውጪ ድንኳን ተክለን ከ150 በላይ ዓውደ ጥናቶች አካሂደናል፡፡ ያኔ ባካሄድናቸው ሒደቶች ማስተር ፕላኑ ላይ አመጣን ከምንለው ለውጥ አንዱ እሱ ነው፡፡ ማስተር ፕላኑ የሕዝብ ነውና ምንም እንኳ ባለሙያው በማስተር ፕላን ዝግጅት ትልቅ ድርሻ አለው ብንልም፣ አመራሩም ትልቅ ሚና አለው ብንልም፣ ሕዝብ በተለይ ደግሞ ነዋሪው የማስተር ፕላኑ ባለቤት ነው፡፡ በወቅቱ ማስተር ፕላኑ በወረቀት ብቻ ሳይሆን በሞዴል ደረጃም ተዘጋጅቶ የነበረ በመሆኑ ሕዝቡ ማስተር ፕላኑ ምን ይመስላል? የሚለውን ጭምር የተረዳበት ነበር፡፡ የመጀመርያው ለሕዝብ የቀረበ ማስተር ፕላን ልንለው እንችላለን፡፡ ታዲያ ወደ ተግባር ስንሄድ ምን ሆነ ሲባል ሁለቱንም ወገን እናያለን፡፡ ተተግብሯል ወይ? አዎ! አልተተገበረም ወይ? አዎ! ይህን ለይተን ማየት ያስፈልገናል፡፡ ይህን ለይተን ስናይ፣ ማስተር ፕላኑ በራዕይ ያስቀመጣቸው በርካታ ሐሳቦች ወደ ተግባር ተተግብረዋል፡፡ ለአብነት የመንገድና የመንገድ ትራንስፖርትን በተመለከተ ባለፉት 15 ዓመታት በከተማው የተከናወኑት በርካታ የመንገድ አውታር ግንባታዎች ማስተር ፕላኑን ተከትለው የመጡ ናቸው፡፡ መቶ በመቶ የሚባል ግን የለም፡፡ ከሞላ ጎደል ማስተር ፕላኑን የተከተሉ ናቸው፡፡ ከተማው ውስጥ ተካሄዱ የተባሉ የልማት እንቅስቃሴዎች አብዛኛዎቹ ማስተር ፕላኑ ባስቀመጣቸው ዕቅዶች፣ ዘጠነኛው ማስተር ፕላንን ተከትሎ የመጣው የአዲስ አበባ ከተማ የመዋቅር ለውጥና እርሱን ተከትሎ የመጡ የልማት እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡ ስለዚህ ማስተር ፕላኑ ከነጉድለቱ በፊት ከነበሩት ስምንት ማስተር ፕላኖች እጅግ በገዘፈ ገጽታው ተተግብሯል፡፡ ምናልባት ማስተር ፕላኑ ካስቀመጣቸው ቁም ነገሮች ውስጥ 50 በመቶ ወይም 40 በመቶ  ሊሆን ይችላል የተተገበረው፡፡ በአብዛኛው አልተተገበረ ይሆናል፡፡

ነገር ግን ከነበረን የከተማ ሥራ አመራር፣ እንዲሁም ማስተር ፕላንን ከመተግበር አኳያ ዘጠነኛው ማስተር ፕላን በአገራችን ታሪክ፣ ማስተር ፕላን ተተግብሯል ብለን ልንናገር በምንችልበት ደረጃ አጽንኦት ሰጥተን ተተግብሯል ብለን ልንናገር እንችላለን፡፡ በተጨማሪም የአዲስ አበባ አስተዳደር መዋቅራዊ ለውጥ ሊያደርግ ይገባል፣ የከተማው ቻርተር ሊሻሻል ይገባል የሚሉት ሐሳቦች፣ የአመራርና አጠቃላይ መዋቅራዊ ለውጥ ሊደረግ ይገባል የሚሉት ሐሳቦች ከማስተር ፕላኑ የመነጩ ናቸው፡፡ ከዚያ በኋላ የፌዴራል መንግሥትም ሐሳቡን ወስዶና በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር መሪነት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደገና የማደራጀትና የመለወጥ ሥራ ተካሄደ፡፡ እሱን ግብ አድርጎ ማስተር ፕላኑ በነበረው የቀድሞ የከተማው አመራርና አወቃቀር ይኼን ማስተር ፕላን መተግበር የሚያስችል ሁኔታ የለም፡፡ ስለዚህ ይህን ማስተር ፕላን ለመተግበርና ከተማውን መለወጥ ካስፈለገ አመራሩንና መዋቅሩን መለወጥ አለበት የሚል እሳቤ ስለነበር፣ ቅድም እንደጠቀስከው ለውጡ ተደርጓል፡፡ ሌላው ትልቁ ለውጥ ማስተር ፕላኑ ተተግብሯል የምንለው፣ ከዘጠነኛው ማስተር ፕላን በፊት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአንድ ማዕከላዊ መዘጋጃ ቤት ብቻ ነበር የሚተዳደረው፡፡ ሁሉም አገልግሎቶች አራዳ ጊዮርጊስ ባለው መዘጋጃ ቤት ብቻ የሚሰጡ ነበሩ፡፡ የመሬት ጉዳይ፣ የግንባታ ፈቃድና የልደት ሰርተፍኬት ሁሉም ጉዳዮች የሚፈጸሙት እዚያው ነው፡፡ ዘጠነኛው ማስተር ፕላን ይህን ለውጦታል፡፡ ከተማው እያደገ ነው፡፡ የሕዝብ ቁጥሩ እያደገ ነው፡፡ (በወቅቱ ሁለት ሚሊዮን) የሕዝብ ፍላጎት እየጨመረ ነው፡፡

ስለዚህ በአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት ስለማይቻል ያልተማከለ የአስተዳደር ሥርዓት በሚለው የመንግሥት ፖሊሲ በመመራት፣ አዲስ አበባ በአሥር ክፍላተ ከተሞች እንደትከፋፈል ተደርጓል፡፡ አሥሩ ክፍላተ ከተሞች ማለት አሥር ማዘጋጃ ቤቶች ማለት ነው፡፡ በክፍለ ከተማ የሚሰጡ አገልግሎቶች እንዲወርዱ፣ ከዚያም አልፎ 305 ቀበሌዎችን በማሰባሰብና ወደ ወረዳ በማሳደግ በ116 ወረዳዎች ተቋቁመዋል፡፡ ወረዳዎቹ አቅም ኖሯቸው የተለመደው ዓይነት አስተዳደር ብቻ ሳይሆን የአገልግሎት ማዕከላት እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ይኼንን እንግዲህ ባለፉት 15 ዓመታት የተካሄዱትን የልማት እንቅስቃሴዎችን ስንመለከት ይህን አደረጃጀት ሳናመጣ ሊካሄዱ የሚችሉ አልነበሩም፡፡ ታንቀው የሚቀሩ ነበሩ፡፡ ሌሎችንም ጉዳዮች ስንመለከት፣ ለአብነት የመኖሪያ ቤቶችን ስንመለከት ከዘጠነኛው ማስተር ፕላን በፊት የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እንዲሟላ የሚታሰበው ለሁሉም አንድ ግቢ፣ ቦታ ሸንሽኖ የመስጠት ሐሳብ ነበር፡፡ ኮንዶሚኒየም ቤት የተፀነሰው የዚያን ጊዜ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዘጠነኛው ማስተር ፕላን መተግበር ሲጀምር ከተማው ቢያንስ 30 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ የነበረው ግንባታ ተስፋፍቶ ያለውን መሬት በሙሉ (54 ሺሕ ሔክታር) ተጠቅሟል፡፡ ምናልባት የቤቶቹ ልማት የታሰበው በመሀል ከተማ ቢሆንም፣ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ጋር ተያይዞ በተነሳው አለመረጋጋት የተሰየመው የባላደራው አስተዳደር ነዋሪዎችን አንስቶ ግንባታ ለማካሄድ አቅም ስላልነበረው፣ በአርሶ አደሮች የተያዘውን የከተማው ዳርቻ ቦታዎች ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡ ባላደራው አስተዳደር ከመሀል ከተማ ነዋሪዎች ይልቅ አርሶ አደሮችን ማንሳት ቀሎት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ከተማው ያለውን የመሬት ሀብት ተጠቅሞ ጨርሷል፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ጎን መስፋት አይቻልም፡፡ ግን ደግሞ የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች በአግባቡ አልተካሱም፡፡ ይህ የዘጠነኛው ማስተር ፕላን ውጤት አይደለም? የተጣበበ ከተማስ እየተፈጠረ አይደለም? ሌሎች አነስተኛ ከተሞችን መፍጠር አስፈላጊ አልነበረም?

አቶ ማቴዎስ፡- እንዳልከው ከዘጠነኛው ማስተር ፕላን በኋላ ኢንቨስትመንቱ በሰፊው  ተቀላቀለ፡፡ በብዛት ልማቱ ላይ የማተኮርና በአተገባበሩ ላይ የተፈጠሩ መዛነፎች በርካታ ናቸው፡፡ ነገር ግን በመርህ ደረጃ ስናስቀምጥ ልማት ሕዝብ ተኮር ነው፡፡ ልማት የሕዝብ ነው፡፡ የአገሪቱ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በሙሉ የሚሉት ይህንኑ ነው፡፡ ልማት የሚካሄደው የነዋሪውን ሕዝብ የኑሮ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ነው፡፡ ይኼን ብለን ወደ አፈጻጸም ስንሄድ የሚንጠባጠቡ ችግሮች ይከሰታሉ፡፡ እነኝህ ከምን ይመጣሉ? መነሻቸው ከማስተር ፕላኑ ነው? ወይስ ማስተር ፕላኑን ከሚመራው አካል ነው? የሚሉት ጉዳዮችን ስናስቀመጥ ጉዳዮቹ ብዙ ናቸው፡፡ አንደኛ ፕላኑ ያስቀመጣቸውን ሐሳቦች በትክልል ካለመረዳት የሚመጣ ነው፡፡ ሁለተኛ የአፈጻጸም ተቋማዊ ብቃት አነስተኛ ነው፡፡ በአፈጻጸም በኩል ያለው የሰው ኃይላችን እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ የተቋሞቻችንን በየጊዜው መቀያየር፣ ተቋማት ዛሬ ተተክለው ዛሬ የሚያድጉ አይደሉም፡፡ ተቋማት እንደ ሰው ልጅ ዕድገት ነው የሚያድጉት፡፡ እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል፡፡ አንድ ተቋም አልሠራ ሲል እሱን አፍርሶ ሌላ ማቋቋም አለ፡፡ እንዲህ ዓይነት አሠራሮች ላይ ስናተኩር ነበር፡፡ እነዚህ ችግሮች ለምንድነው የሚመጡት? በአጠቃላይ በከተማ ልማት ዕድገት ላይ በአገር ደረጃ ስንመለከት በአመራሩም በባለሙያም ያለን ልምድ አነስተኛ ነው፡፡ ይህ ነው ጉድለቱ፡፡ በከተማ ልማት ላይ ያለን ጉድለት ከፍተኛ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ገጠሬዎች ነን፡፡ በአመዛኙ እሱ ነው የሚገልጸን፡፡ ሁላችንም ገጠሬዎች ነን ብንል እኛን ይገልጸናል፡፡ ስለዚህ ወደ ከተሜነት በምናደርገው ሽግግር ባለሙያውንም፣ ነዋሪውንም፣ አመራሩንም በአብዛኛው የሥነ ልቦና ዝግጅታችን የሚገልጸው ገጠሬነትን ነው፡፡ አሁን ነው በቅርብ የከተሜ ነዋሪ 20 በመቶ፣ የገጠር ነዋሪ ደግሞ 80 በመቶ ማለት የጀመርነው፡፡

ስለዚህ በእነዚህ ሁሉ ነገሮች ውስጥ ነው ዘጠነኛው ማስተር ፕላን የተተገበረው፡፡ ከማኅበረሰብ፣ ከባለሙያው፣ ከአስተዳደሩና ከገነባቸው ተቋማት ሁሉ ስናይ ችግር አለ፡፡ ተቋሞቻችን ሁሉ ገና እንጭጮች ናቸው፡፡ ከተሞቻችንም አዳዲስ ናቸው፡፡ አዲስ አበባ የ130 ዓመት ወጣት ናት፡፡ ስለዚህ ይኼንን ስንመለከት አዲስ አበባ የምትማርባቸው ሌሎች ከተሞች የሉም፡፡ ለመማር ስንፈልግ አውሮፓ፣ አሜሪካ ወይ የሩቅ ምሥራቅ ከተሞችን ነው የምንመለከተው፡፡ ወደ ተግባር ሲመጣ የአገር ውስጥ ባለሙያ የለም፡፡ አመራሩ በከተማ አመራር ልምድ ያለው አይደለም፡፡ ቅድም የጠቃቀስኳቸው ጉድለቶች ከዚህ አንፃር ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ እንግዲህ ፕላን ሲተገበር ፕላኑን ለመፈጸም ምን ምን ያስከፍላል? ይኼን ለመፈጸም በምናደርገው እንቅስቃሴ ምን ላይ እንደርሳለን? የሚለው መታወቅ አለበት፡፡ ስለዚህ ያገኘነው ግብ ላይ ለመድረስ ይህን ሁሉ ዋጋ መክፈል ነበረብን ወይ? ስንል ከአቅማችን የመጣ እንጂ ፈልገን ያገኘነው ዋጋ አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህን በሒደት ማስተካከል አለብን፡፡ ከቦታቸው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች አያያዝ ላይ ይኼ ከቀረፅናቸው ዝርዝር ስትራቴጂና ፕላኑን ለማስፈጸም ካዘጋጀናቸው ዝርዝር ፕላኖች፣ ፕላኑን ለማስፈጸም ካቋቋምናቸው ተቋማት ብቃት፣ አመራሮችና ባለሙያዎች ብቃት ላይ ነው የሚወድቀው፡፡ አጠቃላይ የማስተር ፕላኑ ግብና መርህ ላይ ችግር ወይም ግጭት አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ከስትራቴጂው አኳያ ትኩረት የሚያደርገው ሕዝብ ላይ ነው፡፡ በማስተር ፕላኑ ምክንያት የሚነካ የከተማው ነዋሪ ቢኖር እንኳ ወደ ተሻለ ኑሮ ይሄዳል፡፡ በእርግጥ የማይነካ የከተማው ነዋሪ የለም፡፡ ሁሉም ይነካል፡፡ በሚነካበት ወቅት ግን የሚመጣው ልማት ተጠቃሚ ያደርገዋል የሚለውን ነው የሚያስቀምጠው፡፡ እዚያ ውስጥ ግን ውጣ ውረዶች ይኖራሉ፡፡ ምክንያቱም የከተማ ልማት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን ከተሞች ኮምፓክት (ከፍተኛ ጥግግት) በሆነ ቦታ ላይ ማደግ ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ከትራንስፖርትና  የበለጠ እሴት ከመፍጠር አኳያ ከተሞችን በከፍተኛ ጥግግት ማሳደግ አስፈላጊ ነው፡፡ አሁን ባለው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ አንፃርም ቢሆን ከፍተኛ ጥግግት (ኮምፓክት ሲቲ) ፕላን አስፈላጊ ነው፡፡ ቦታም ቢኖር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባን አሁን ባላት የቆዳ ስፋት ላይ መልሶ መጠቀም መቻል አስፈላጊ ነው፡፡ በእርግጥ የመሀል ከተማውን መልሶ ማልማት ብቃት ላይ አልነበርንም፡፡ አሁን ግን አቅም ተፈጥሯል፡፡ ተቋማትም እየፈጠሩ ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ጎን ሰፊ ቦታ ቢኖር እንኳ ወደዚያ መሄድ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ይህን በማድረጋችን ነው አረንጓዴ ቦታዎችን ያጣነው፡፡ ባለፉት 15 ዓታት የመሬት አጠቃቀማችን የተዛነፈው ለመኖሪያ የተባለውን ለኢንዱስትሪ፣ ለአረንጓዴ የተባለውን ለመኖሪያ የመጠቀም ችግሮች በዘጠነኛው ማስተር ፕላን ላይ ተፈጥረዋል፡፡ የማስተር ፕላኑ በጎ ውጤቶች እንዳሉ ሆኖ በርካታ ጉድለቶችም ተከስተው ነበር፡፡ ከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴ በምናደርግበት ጊዜ ማድረግ የነበረብንን ጥንቃቄ ባለማድረጋችን ከፍተኛ ጉድለቶች ተፈጽመዋል፡፡ ከዚህ በፊት የታዩ ጉድለቶች በአሥረኛው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እንዳይደገሙ ይደረጋል፡፡  

ሪፖርተር፡- አሥረኛው ማስተር ፕላን በሚታሰብበት ወቅት ሌሎችም አጎራባች ከተሞች አብረው እንዲያድጉ ታስቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ውጥኑ ረዥም ርቀት ከሄደ በኋላ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በተነሳው ተቃውሞ እንዲቆም ተደርጓል፡፡ ውጥኑ መልካም ቢሆንም ሳይሆን ቀርቷል የሚሉ አሉ፡፡ እዚህ ላይ ሕዝቡ ምን ዓይነት መንገድ መያዝ ይኖርበታል ይላሉ?

አቶ ማቴዎስ፡- በአገር አቀፍ ደረጃ የምናቅደውም ሆነ በአዲስ አበባ ደረጃ የምናቅዳቸው  የተዛመዱ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ እንግዲህ እንዳልከው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ማስተር ፕላኖች ሲያዘጋጁ፣ የአንዱ ከተማ ከሌላው ከተማ ጋር እንዳይጣረስ ለማድረግ ነው፡፡ ያንን ፕላን አስማምቶ የመሄድ ጉዳይ ነው፡፡ ይኼ እንግዲህ ትክክለኛውን መልክዕት ለሕዝቡ በአግባቡና በወቅቱ ባለመውረዱ፣ መንግሥትም እንዳስቀመጠው በኦሮሚያ ከተሞች ሲሠራ የነበረው እንዲቆም ተደረገ፡፡ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ለብቻው እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- አሥረኛው ማስተር ፕላን በቅርቡ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ ማስተር ፕላን እንደ ዘጠነኛው ማስተር ፕላን ከፍተኛ መዋቅራዊ ለውጥ ይዞ መጥቷል፡፡ ማስተር ፕላን ሲመጣ ግዙፍ የመዋቅር ለውጥ አስከትሎ መምጣቱ የግድ ነው?

አቶ ማቴዎስ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመዋቅር ጥናት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አቋቁሟል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ መዋቅራዊ ለውጥ ማካሄድ የሚያስችል ጥናት እየሠራ ነው፡፡ ለውይይቱም እያቀረበ ይገኛል፡፡ ከዚህ የሚጠበቀው እስካሁን ድረስ በከተማችን በተለይ በማስተር ፕላኑ አፈጻጸም ላይ ከ1997 ዓ.ም. በኋላ ከመምጣቱ በፊት፣ የነበረው አደረጃጀት ማስተር ፕላኑን ለመተግበር ተአምር ሊሠራ የሚችል መዋቅር ነበር (በዶ/ር አርከበ ዕቁባይ የሚመሩት ካቢኔ)፡፡ ከ1977 ዓ.ም. በኋላ መፋለሶች በመከሰታቸው አዲስ አበባ ላይ መንገራገጭ ተፈጥሯል፡፡ ስለዚህ እነዚያን ክፍተቶችና ጉድለቶች፣ በፕላን ዝግጅትና በአፈጻጸሙ ላይ የታዩት የአደረጃጀትና የአሠራር ሥርዓቶች ምንድናቸው? የሚለውን ጉዳይ የመረዳትና ክፍተቶቹን መሙላት ያስፈልጋል፡፡ በአዲስ መልክ እየተደራጀ ያለውና የከተማው ምክር ቤት ያፀደቀው ፕላን ኮሚሽን እንደ ዓላማ በአደረጃጀትና በመዋቅር የነበረበትን ክፍተት ይሞላል፡፡ በዘጠነኛው ማስተር ፕላን ተግባሪ ተቋማት፣ ማስተር ፕላኑን በሚተገብሩበት ወቅት በትክክል ስለመተግበራቸው የሚከታተልና የሚቆጣጠር ተቋም አልነበረም፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ፕላን ኮሚሽን ተቋቁሟል፡፡

ሁለተኛው በፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የተጠኑት ከፕላን ኮሚሽን ሌላ ሦስት ተቋማት እንዲቋቋሙ ይደረጋል፡፡ አንደኛው የማዕከላትና የኮሪደሮች ልማት ኮርፖሬሽን ነው፡፡ ሁለተኛው የልማት ቅንጅትና የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው፡፡ ሦስተኛው የተፋሰስና አረንጓዴ ቦታዎች ኤጀንሲ ነው፡፡ በድምሩ እነዚህ አራት ተቋማት ከዘጠነኛው ማስተር ፕላን በተማርነው መሠረት አሥረኛውን ማስተር ፕላን በትክክል ዕውን ለማድረግ ቁልፍ ሚና አላቸው ተብለው የተለዩ ናቸው፡፡ ፕላኑ ባለቤት እንዲኖረው ፕላኑን የሚጠብቅና የሚቆጣጠር ተቋም ተፈጥሯል፡፡ ይህን አሳክተናል፡፡ ሌላው የማዕከላትና የኮሪደሮች ልማት ነው፡፡ ዘጠነኛውን ማስተር ፕላን በምንገመግምበት ወቅት ያየነው አንዱ ትልቁ ጉድለት ማዕከላትና ኮሪደሮች፣ በተለይም ማዕከላት አካባቢ በተመቀጠው ፕላን መሠረት ማስተር ፕላኑን ተከትለው እየተፈጸሙ አይደለም፡፡ ማዕከላት ስንል እንግዲህ የከተማው ዋና እምብርት በመሆናቸው በልዩ ሁኔታ ተጠንቶ መተግበር ያለበት ነው፡፡ እንደ ሌላው የከተማው አካባቢ የሚለማ አይደለም፡፡ በየደረጃው ወደ ክፍለ ከተማም ስንሄድ የክፍለ ከተማ ማዕከላትም የወረዳ ማዕከላትም በልዩ ሁኔታ ነው መልማት ያለባቸው፡፡ በዘፈቀደና በተበጣጠሰ ሁኔታ መልማት የለባቸውም፡፡ ማዕከላት የምንለው የከተማው ሕይወት የሚንቀሳቀስባቸው ዋና ቦታዎች ናቸው፡፡ የአገልግሎት ቦታዎች፣ የአስተዳደር ቦታዎች፣ የመዝናኛ ማዕከላት ናቸው፡፡ እነዚህ ቦታዎች በልዩ ሁኔታ መልማት አለባቸው፡፡ ግን በዘጠነኛው ማስተር ፕላን አልተፈጸመም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ቦታዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ መንግሥታዊ የሆነ ተቋም ማቋቋም አስፈልጓል፡፡ የማዕከላትና የኮሪደሮች ልማት ኮርፖሬሽን እንዲቋቋም ሐሳብ አቅርበን ለማፀደቅ በሒደት ላይ እንገኛለን፡፡ ሌላው ከተማችን ውስጥ ደግመን የምናነሳው ከታችኛው ተራ ዜጋ አንስቶ ከፍተኛ አመራር ድረስ ደጋግመን የምናነሳው የመሠረተ ልማትና የልማት ቅንጅት አለመኖር ነው፡፡ በዘጠነኛው ማስተር ፕላን በዶ/ር አርከበ ዕቁባይ የሚመራው የከተማው ካቢኔ በተቋቋመበት ወቅት ይህን ችግር ለመፍታት ጥረት ተደርጎ ነበር፡፡ የመሠረተ ልማትና ግንባታ ሥራዎች ባለሥልጣን ተቋቁሞ ነበር፡፡ ባለሥልጣኑ ልማቶቹን እያቀናጀ ይመራ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ የ1997 ዓ.ም. ውጥንቅጥ ከመጣ በኋላ ያ ተቋም መልኩን ቀይሮ ይህን አገልግሎት ሳይሰጥ ቀረ፡፡ ስለዚህ ትልልቅ ልማቶችን የተቋሞቹን ዕቅድ አንግበው እንዲሠሩ የሚያደርግ፣ የከተማውን የግንባታ ሒደት የሚቆጣጠርና ፈቃድ የሚሰጥ የመጠቀሚያ ፈቃድ የሚሰጥ የልማት ቅንጅት የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን እንዲቋቋም እየተደረገ ነው፡፡

 ሌላው ከተማው ውስጥ ሁሉም ነዋሪ እሮሮ የሚያሰማበት የአረንጓዴ ቦታዎች ጉዳይ ነው፡፡ አረንጓዴ ቦታዎችን ቅርጥፍ አድርገን በልተን በሐሩር እየነደድን ነው፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት ከተማ ውስጥ በተደረገ ልማት ያጠፋናቸው አረንጓዴ ቦታዎች አሁን ዋጋ እያስከፈሉን ነው ያሉት፡፡ በ30 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የአዲስ አበባ አማካይ የሙቀት መጠን በአንድ ዲግሪ ሴልሺየስ ጨምሯል፡፡ ስለዚህ ይኼ በዚሁ ከቀጠለ ከተማችን ወደ በረሃማነት እየተለወጠ ይሄዳል፡፡ እዚህ ላይ ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል በማለት የተፋሰስና የአረንጓዴ ልማት ኤጀንሲ እንዲቋቋም እያደረግን ነው፡፡ እንግዲህ እነዚህ አዳዲስና የመዋቅር ጥናት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ በርካታ ተቋማት ማስተር ፕላኑን በትክልል ማስፈጸም እንዲችሉ፣ እርስ በርሳቸው መገናኘት ባለባቸው ደረጃ በተለይ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትና የመንግሥት ሥራዎች በሚባሉት መካከል የመቀላቀልና የመዘበራረቅ ሁኔታ ስለሚታይ ለይቶ ያስቀምጣል፡፡ የልማት እንቅስቃሴ ያላቸውን ወደ ማዘጋጃ ቤት ሥር በመካለል በባለሙያ እንዲመሩ የማድረግ፣ የፖለቲካ አመራሩ ደግሞ ይበልጥ ስትራቴጂክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር የሚያደርጉ ሥራዎችን እየሠራ ነው ያለው፡፡ ይህ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች