Saturday, May 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ የሚጠይቁ መንገዶች በአዲስ አበባ ሊገነቡ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከጥቂት ወራት በፊት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣንን እንዲመሩ በቀድሞው ሥራ አስኪያጅ እግር የተተኩት ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ፣ አዲሱን የኃላፊነት ቦታ ሲረከቡ ቀዳሚ ያደረጉት ተግባር በአራቱም የከተማዋ አቅጣጫዎች የሚገኙ የተበላሹ መንገዶችን መጠገን ነው፡፡

ባለሥልጣኑ ከዋና ተግባራቱ መካከል የሚያሰፍረው የአዲስ አበባ መንገዶች ጥገና ሥራ በእስካሁኑ ሒደት 80 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ መንገዶችን ለመጠገን አብቅቶታል፡፡ ይህ ተግባር ቀጥሏል፡፡ ለመንገድ ጥገና ተብሎ ከአስተዳደሩ የተመደበው 270 ሚሊዮን ብርም ለጥገና የተመደበ ከፍተኛው በጀት ሆኗል፡፡ ለከተማዋ የትራፊክ መጨናነቅ መንስዔ ናቸው የተባሉ አደባባዮችን በማፍረስና ለትራፊክ ፍሰቱ አመቺ እንዲሆኑ ለማድረግ በአዲሱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሚመራው ባለሥልጣን እስካሁን ሁለት አደባባዮችን በማፍረስ፣ በምትኩ ተሽከርካሪዎች በትራፊክ መብራት እንዲስተናገዱ አድርጓል፡፡ በተለይ በቀለበት መንገድ ውስጥ የሚገኙ አደባባዮችም ተራቸውን እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡ የዕድሳቱ ሥራ ለተጨናነቀው የከተማው የትራፊክ ፍሰት ማስተንፈሻ በመሆን፣ በተወሰነ ደረጃ ማቃለል እንዳስቻለ እየታየ ነው፡፡

እንዲህ ባሉ ተግባራት ከግማሽ ዓመት በላይ ለዘለቁት ኢንጂነር ሀብታሙ፣ የጥገና ሥራዎቹ መበራከት አዲስ የመንገድ ግንባታ ውሎች እንዳይፈርሙ ተፅዕኖ ሳያሳድርባቸው አልቀረም፡፡ በእርግጥ በአሁኑ ወቅት ባለሥልጣኑ ከ200 በላይ የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን እያስተዳደረ ቢሆንም፣ ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ በአንድ የበጀት ዓመት አዲስ ኮንትራት ሳይፈርም ከግማሽ ዓመት በላይ የቆየበት ጊዜ እስካሁን አልነበረም፡፡

ዓርብ የካቲት 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ባለሥልጣኑ በሰፊው ከተያያዘው የመንገድ ጥገናና የትራፊክ ፍሰትን የማቃለል ሥራ ላይ ካነጣጠረው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ከአገር በቀል ኮንትራክተሮች ጋር ውለታ ገብቷል፡፡ ኢንጂነር ሀብታሙም አዲሱን ኃላፊነታቸውን ከተረከቡ ወዲህ የመጀመሪያቸው በሆኑት  የመንገድ ግንባታ ስምምነቶች ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ስምንተኛው ወር ላይ ስምምነት የተፈረሙባቸውና በአዲስ አበባ ከተማ የሚገነቡት አምስቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች በጥቅሉ ከ887 ሚሊዮን ብር በላይ የሚጠይቁ ናቸው፡፡

ኢንጂነር ሀብታሙ እንደገለጹት፣ ከአምስት ተቋራጮች ጋር ውለታ የተፈጸመባቸው አምስት ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ ከ20 እስከ 30 ሜትር ስፋትና ከ11 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው መንገደች ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተመደበው በጀት የግንባታ ወጪያቸው የሚሸፈኑትን መንገዶች ለመገንባት በጨረታ ያሸነፉት ተቋራጮች፣ ድሪባ ደፈሻ፣ ተክለብርሃን አምባዬ፣ የማነ ግርማይ፣ ስናንና ኢትዮ ጠቅላላ የተባሉት ተቋራጮች ናቸው፡፡

መንገዶቹ ለከተማው ሕዝብ የተቀላጠፈ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲያገኝ ከማድረግ ባሻገር፣ የመንገድ ሽፋኑ እንዲሻሻል የሚያስችሉ ናቸው ተብሏል፡፡ የግንባታ ሒደታቸውም የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላንን ተከትለው ለነባር መንገዶች ደረጃውን የጠበቀ ዲዛይን ሠርቶ የማስፋት ሥራንና ለአዳዲስ ኮንዶሚኒየም ቤቶች አዲስ የመንገድ መሠረተ ልማት የማቅረብን ሥራ እንደሚያጠቃልሉ ኢንጂነር ሀብታሙ ገልጸዋል፡፡

በከተማው ማስተር ፕላን መሠረት ከሚገነቡ ነባር መንገዶች መካከል አራራት ሆቴል፣ ኮተቤ ኮሌጅ ካራ የመንገድ ሥራ ይጠቀሳሉ፡፡ የዲዛይን ሥራው በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ የተሠራው ይህ መንገድ ለሁለት ተቋራጮች ተከፍሎ ተሰጥቷል፡፡

በዕለቱ እንደተገለጸው ከሁለቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ የሆነውና በ5.94 ኪሎ ሜትር ርዝመትና በ30 ሜትር ስፋት የሚገነባው ከአራራት ሆቴል እስከ ኮተቤ ኮሌጅ ያለውን ፕሮጀክት ለመገንባት በጨረታ ያሸነፈው ዲሪባ ደፈርሻ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ነው፡፡ የጨረታ አሸናፊ በመሆን ሥራውን የተረከበበት ዋጋ 272.9 ሚሊዮን ብር መሆኑም ታውቋል፡፡ የግንባታ ሥራው በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡

ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ 2.84 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 30 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ ከኮተቤ ኮሌጅ እስከ ካራ ያለውን አካባቢ የሚሸፍን ነው፡፡ ይህንን መንገድ ለመገንባት በጨረታ ያሸነፈው ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ነው፡፡ ለመንገዱ ሥራ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ በ260.7 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡ ተክለብርሃን አምባዬ በአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ ግንባታ ሥራ ሲረከብ የመጀመሪያው ነው፡፡ ለዚህ መንገድም የተያዘለት የግንባታ ጊዜ ሁለት ዓመት ተኩል ነው፡፡

በተጨማሪም ከሲቪል ሰርቪስ መገንጠያ ጉርድ ሾላ መንገድ ሥራ ፕሮጀክት በ68.9 ሚሊዮን ብር አሸናፊ የሆነው የማነ ግርማይ ተቋራጭ ነው፡፡ 1.04 ኪሎ ሜትር ርዝመትና የ20 ሜትር ስፋት ያለው ይህንን መንገድ በ240 ቀናት ውስጥ ለማጠናቀቅ ውለታ ተገብቶለታል፡፡

ለአዳዲስ የኮንዶሚኒየም ቤቶች አዲስ የመንገድ መሠረተ ልማት ለማቅረብ ከሚከናወኑት ሁለት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው የተባለውን የቦሌ አራብሳ ኮንዶሚኒየም-አያት ኮንዶሚኒየም መንገድ ሥራ ፕሮጀክት ደግሞ ስናን የተባለው ኮንስትራክሽን ኩባንያ በ194 ሚሊዮን ብር ይገነባዋል፡፡ በ540 ቀናት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል፡፡ የኮሎ ፍቼ ሁለት ኮንዶሚኒየም የመንገድ ሥራ ፕሮጀክትን ደግሞ ኢትዮ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ በ79.6 ሚሊዮን ብር ገንብቶ ለማስረከብ ተዋውሏል፡፡ ለግንባታ የተሰጠውም ጊዜ 365 ቀናት ናቸው፡፡

በዕለቱ ግንባታቸው እንዲፈጸም ከሥራ ተቋራጮች ጋር ውለታ የተፈጸመባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ በከተማዋ የመንገድ መሠረተ ልማት አቅርቦት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚያመጡ የታመነባቸው መሆኑን ኢንጂነር ሀብታሙ ገልጸዋል፡፡ የመንገድ ግንባታዎቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንደውም ከዚያ በፊት መጠናቀቅ እንዳለባቸው ያስገነዘቡት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ጥራቱን በጠበቀ ደረጃ እንደገነቡ አሳስበዋል፡፡ ተቋራጮችም ሥራውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች