Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለመልካም ምግባር እንጣር

ለአገራችን የግብይት ሥርዓትና የምንኮንነው ለግብይቱ ሥርዓቱ መዘበራረቅ በፊት አውራሪ ተጠያቂነት የምናሰልፋቸው ነጋዴዎችን ነው፡፡ የግብይት ሥርዓቱ የሚጠይቃቸውንና የሚጠብቅባቸውን ሥነ ምግባር ወደ ጎን በማለት እንዳሻቸው የሚንቀሳቀሱት አብዛኞቹ ነጋዴዎች ጨዋ የሚባሉትንም በክፉ ያስነሳሉ፡፡ ሥነ ምግባር የለሾቹ ሁሉም በጅምላ እንዲነቆጡ ሰበብ ይሆናሉ፡፡

አንዳንዱ የንግድ ዘርፍ በአሁኑ ወቅት ‹‹ጉልቤ ነጋዴዎች›› በሚወስኑት ዋጋ ይሽከረከራል ማለት ማጋነን አይሆንም፡፡ ጉልቤዎቹ በጠረጉት መንገድ የማይጓዝ ካለ በሚዘጋጅለት ወጥመድ ከጨዋታ ውጭ ይደረጋል፡፡ በመሆኑም ጥቂቶች ሰፊውን ገበያ የመረበሽ አቅም የሚጎናፀፉበት አጋጣሚ እየበዛ መጥቷል፡፡ እንደውም የጉልቤ ነጋዴዎች አቅም ከመንግሥት በላይ የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ ጉልቤዎቹ ነጋዴዎች እጀ ረዥም ስለመሆናቸው የሚያስረዱ በርካታ ምሳሌዎችን ማቅረብ ቢቻልም፣ ተስፋ የተጣለበትን፣ የተበላሸውን የንግድ ሥርዓት ለማቃናት መንግሥት የፈጠረው አለ በጅምላን በምሳሌነት ማቅረብ ይቻላል፡፡

አለ በጅምላ ጉልቤና ስብግብ ነጋዴዎችን ለመግታት ገበያውንም ለማረጋጋት፣ ኅብረተሰቡም በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምት ለማስቻል ታስቦ ቢቋቋም፣ ባሰበው ልክ መጓዝ ግን አልቻለም፡፡ አለ በጅምላ እንደ አጀማመሩ በፍጥነት መጓዝ ያልቻለበት ምክንያት ጉልቤዎቹን መቋቋም አለመቻሉ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ይታሰባል፡፡  ተልዕኮውን እንዳያሳካ የእነዚህ ነጋዴዎች ሸፍጥ አሰነካክሎታል ቢባል ያስኬዳል፡፡ ይዞት የተነሳው ዕቅድ ለገበያው መረጋጋት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ቢታመንም፣ ድርጅቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እዚያው ባለበት እየረገጠ አለ ለማለት ብቻ ያለ ሆኗል ቢባል የተጋነነ አይሆንም፡፡

በእርግጥ ከሚጠበቀው ደረጃ በታችም ሆኖም መኖሩ አንድ ነገር ሆኖ፣ ለገበያው መበረዝ ምክንያት የሆኑትን ነጋዴዎች እየተፈታተኑ ዕድገቱን አቀዝቅዘውታል፡፡ የጉልቤዎቹን ያህል ገበያውን ሊቃኝ አልቻለም፡፡ ለዚህ ነው ከመንግሥት አቅም በላይ የሚሆኑ ሰዎች አሉ የምንለው፡፡ እንዳነሳሱ አለ በጅምላ የት በደረሰ ነበር፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ጤናማ ስላልሆነ፣ በሕግና በሥርዓት ለመሥራት እንኳ የጥቂቶች ጉልበትና በእነሱ አምሳል የሚጓዙ ተባባሪዎች መብዛት ለመንግሥትም እንቅፋት እስከመሆን ደርሷል፡፡

በጥቅል ሲታይ ግን ይብዛም ይነስ በሁሉም የቢዝነስ ዘርፍ ከሥነ ምግባር ወጣ ያለ አካሄድ እንዳለ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ይካሄዳሉ የተባሉ ጨዋታዎች ባህሪይ በየጊዜው የሚቀያየሩ በመሆናቸው ተቆጣጥሮ ዕርምጃ ለመውሰድ ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ቢባልም ቅሉ ከልብ ከታሰበበትና ከተሠራበት ግን መፍትሔ  አይጠፋም፡፡ አለ በጅምላ መስዕዋት ከመሆን ይልቅ ቢጎለብትና ትኩረት ቢሰጠው ዛሬ በአለ እና በየለም መካከል ባልዋለለ ነበር፡፡ ተልዕኮው እንዲሳካ መንግሥት ተገቢውን ድጋፍና እግዛ ያለመስጠቱም ጭምር ለአለ መዳከም ድርሻ ነበረው፡፡

ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ አሠራር እንዴት ሊገታ ይችላል? የሚለውና በመንግሥት ሊወሰዱ የሚገቡ ዕርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ድርጊቱን ሙሉ ለሙሉ ማስቆም  ባይቻል እንኳ የበለጠ ጉዳት እንዳያስከትል ፍሬውን ከገለባ የመለየት ሥራ ግን የግድ ያስፈልጋል፡፡ መልካም ሥነ ምግባር ያለው የንግድ ኅብረተሰብ ለመፍጠር ሊወሰዱ ከሚገባቸው ዕርምጃዎች አንዱ ትምህርት ነው፡፡

የግብይት ሥርዓቱን ማተረማመስ ወንጀል መሆኑ ባይጠረጠርም እንዴት ወንጀል እንደሚሆን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ምን ያህል ተሠርቶበታል? ቢባል የለም ነው ምላሹ፡፡ የንግድ ሥነ ምግባር ደንብ አዘጋጅቶ ነጋዴው እንዲህ ነው መሥራት ያለበት ብሎ ከልቡ የሚሠራ ተቋም ያሻል፡፡ በእርግጥ የንግዱ ኅብረተሰብ የሚገዛበት ገዥ ሕግ ቢኖረውም፣ አሁን ካለው የአብዛኛው የንግድ ኅብረተሰብ ግንዛቤ አንፃር የሚመራበት ደንብ የለውም፡፡ መንግሥትም ቢሆን ሕጉን ለማስከበር ሙሉ አቅሙን አለመጠቀሙና ከአንድ ሰሞን ማስፈራራት የዘለለ ነገር የሌለው መሆኑ ሌላው ችግር ነው፡፡

ለዚህም ነው ዛሬም ከግብይት ሥርዓቱና ከንግድ አሠራር ሥነ ምግባር ጋር ተያይዘው የሚነሱ ብሶቶች ሲባባሱ እንጂ እፎይ የሚያስብሉ ድርጊቶች የማይታዩት፡፡ ሰሞኑን የሰማሁትን አንድ ጉዳይ ልጥቀስ፡፡ በሸማቾች ማኅበራት በኩል የሚከፋፈለው ዘይት በትክክል ለተጠቃሚው ስለማይደርስ መፍትሔ ተደርጎ ተወሰደ የተባለው ውሳኔ የግብይት ሥርዓቱ እንዴት እየተበላሸ እንደመጣ በመጠኑ ሊያሳይ የሚችል ነው፡፡ ዘይት ከሸማቾች ማኅበራት ገዝተው በተወሰነው ዋጋ መሠረት እንዲቸረችሩ የሚሰጣቸው መደብሮች ለኅብረተሰቡ እየሰጣችሁ ባለመሆኑ ለማን እንደሸጣችሁ ለማወቅ መሸጥ ያለባችሁ ለእከሌና ለእከሌ ነው የሚል አሠራር ተጀምሯል፡፡

ይህ ውሳኔ በሕዝቡ ቁጥር ልክ እንደሚመጣ የሚታወቀው ዘይት፣ ከሸማች ማኅበሩ መጋዘን ሲወጣ አየር ባየር እየተቸበቸበ ችግር በመፈጠሩ ነው፡፡ ለአካባቢው ሸማቾች አዳርስ የተባለውም ከተተመነለት ዋጋ በላይ ለአትርፎ ሻጮች የሚሸጥ በመሆኑ፣ ይህንን ለመከላከል የሸጥክለትን ሰው ማንነት አሳውቅ እስከመባል ተደርሷል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ውጤት የለውም፡፡ የዚህን ያህል ደረጃ የተደረሰው በብልሹ የግብይት ሥርዓታችን ምክንያት ነው፡፡ የንግዱ ኅብረተሰብ የሚመራበት የሥነ ምግባር ደንብ ያሻዋል፡፡ ንግድ ራሱን የቻለ ሥነ ምግባር ያለው መሆኑን ማስተማር ይገባል፡፡ የንግዱ ኅብረተሰብ በሥነ ምግባር እንዲመራ መልፋት ያሻል፡፡ ቢያንስ መጪው ትውልድ ምግባር ያለው የመጠቀ ነጋዴ እንዲኖረው ጥሩውን ጥሩ መጥፎውን መጥፎ የማለት ባህላችን ሊዳብር ይገባል፡፡ አልታረም ያለውን ነጋዴ ማንነቱን ለሕዝብ ይፋ ማውጣት  በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ጤናማ አሠራር በግድ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡

ግንዛቤ በማስጨበጡ ረገድ ኃላፊነት እንዳለባቸው ከሚታሰቡ ውስጥ የንግድ ምክር ቤቶች ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ምክር ቤቶች አባሎቻቸው ሥነ ምግባር እንዲላበሱ ሲተጉ አናይም፡፡ ድምፃቸው አይሰማም፡፡ ንግድ ምክር ቤቶች አባሎቻቸውን ሥርዓት ማስያዝ፣ ያጠፉትን መስመር እንዲይዙ፣ ሸማቹን በአግባቡ እንዲያገለግሉ ማበረታታት ቀዳሚ ሥራቸው በሆነ ነበር፡፡ ምክር ቤቶቹ በዚህ ሁሉ ውስጥ የሌሉበት በመሆናቸው ለግብይት ሥርዓቱ መዘበራረቅ ተጠያቂ አካላት ሆነው ይመደባሉ፡፡ ለነገሩ አብዛኞቹ ንግድ ምክር ቤቶች ራሳቸው መቼ ሥነ ምግባር ተላበሱና ያስብላሉ፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት