Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉትውልድን የመታደግ አደራና የገባንበት አጣብቂኝ

ትውልድን የመታደግ አደራና የገባንበት አጣብቂኝ

ቀን:

በሒሩት ደበበ

ለዛሬ አሁን ያለውን ትውልድ ስኬት በማንሳት ላሰለቻችሁ አልሻም፡፡ ይልቁንም እንደ አገር በማኅበረሰቡ በተለይም በወጣቱ ትውልድ ላይ የተደቀኑ ፈተናዎችን መንቀሴን መርጫለሁ፡፡ ከዚያም አልፎ የወደፊቷ ኢትዮጵያ እንደ መርግ ሊጫናት ያረበበውን አስከፊ ሁኔታ ሁሉ በማንሳት የመነጋገሪያ አጀንዳ ለመሰንዘር እሞክራለሁ፡፡ ለዚህም ስል ‹‹እውነትን ሰቀሏት›› በሚለው የግጥም መድብሉ የሚታወቀውን ሰለሞን ሞገሥ (2001) አንድ ግጥም የጽሑፌ መግቢያ አድርጌዋለሁ፡፡

አክሱም አቃጥሉት

በሥውር – በሥውር ሳትወጡ ይፋ፣

አክሱምን አቃጥሉት ላሊበላም ይጥፋ!

ሁሉም ቢተባበር የሚያቅት አይደለም፣

ጢያና ጀጎልን ባንድ ላይ ለማውደም፤

መስጅድ ቅርሳ ቅርሱ፣ ፍልፍል ቤተ መቅደስ፣

በዘዴ በዘዴ በየተራ ይፍረስ፤

የጥበብ መጻሕፍት ጥንታዊ ብራና፣

በእሳት ይቃጠል ጋዝ ይርከፍከፍና!

የአያቶቹ ጥበብ ደብዛው የጠፋበት፣

ለምን ይኼ ትውልድ ወቀሳ ይብዛበት?

አክሱም ፋሲል ግምብን ማቃጠል ነው ጥሩ፣

በዘመናችን ላይ እንዳይመሰክሩ!!

      በእርግጥ እነዚህ ስንኞች ‹‹ሁሉ ድሮ ቀረ›› የሚሉ ሊመስሉ ይችላሉ፡፡ የቀደመው ትውልድ የአክሱም ሐውልቶችን፣ የጎንደር ግንብን፣ የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ኪነ ሕንፃዎች የጀጎል ግንብ ወዘተ ሲያንፅ የአሁኑስ ምን ሠራ? በደምሳሳው የሚልም ይመስላል፡፡ ይሁንና ከግንብና ከግድብ በላይ በአስተሳሰብ አገራዊ ፍቅር፣ ሞራላዊና ሥነ ምግባር ያለው ትውልድ እየተገነባ ነው ወይ? የሚለው ነው አንገብጋቢው ጥያቄ፡፡ በዚህ ጸሐፊ ዕይታ ግን ትውልዳዊ ክፍተት የተፈጠረባቸው ተጨባጭ ምልክቶች እየተንፀባረቁ ነው፡፡

ብዙዎች እንደሚስማሙት በአሁኒቷ ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት፣ ቋንቋ፣ ታሪክና ማንነት. . . ብዙ የተባለላቸውን ያህል ስለ አገራዊ ክብር፣ የጋራ እሴትና አንድነት የተባለው ከበቂ በታች ነው፡፡ ለዚህም፣ ነው ብሔር ተኮሩ ፌዴራሊዝም ዴሞክራሲያዊ አንድነትን አልገነባም እየተባለ ያለው፡፡ አንዳንዶችም በሕዝቦች አንድነት ላይ ብሔራዊ መግባባት ባለመፈጠሩ፣ አንዱ ማኅበረሰብ ወደ ሌላው አካባቢ በነፃነት ተንቀሳቅሶ መኖርና መሥራት የሚቸገርበት ድክመት መፈጠሩን በፀፀት እየገለጹ የሚገኙት፡፡

የሥርዓቱ ነፀብራቅ የሆነው አዲሱ ትውልድ ‹‹ከኢትዮጵያ አገሬ፣ ወደ መርካቶ ሰፋሬ ወርዷል፤›› ሲል የመንደርተኝነቱን መባባስ ክፉኛ የተቸው መንግሥታዊው ዘመን መጽሔት በኅዳር 2009 ዕትሙ ነው፡፡ ትውልዱ የጋራ አገር፣ የወል ባንዲራ፣ መግባቢያ የጋራ ቋንቋ፣ የአብሮነት፣ የጋራ እሴት፣. . . የሌለው ይመስል በየቀበሌ አድባር ሥር እንደተወሸቀ ነው፡፡ ‹‹ትልቁ›› ምሁራን የፖለቲካ ልሂቃን የሚባለው እንኳን የብሔር ባርኔጣ የሚጎትተው ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ለአገራች ሉዓላዊነት ቀናዒነት የነበራቸው፣ በሃይማት መቻቻልና አብሮነት የሚጠቀሱ፣ የመረዳዳትና እንግዳ የመቀበል. . . እሴት የነበራቸው ድንቅ ሕዝቦች ናቸው፡፡ አሁንስ እነኝህ እሴቶች አሉ ወይ? ነው ጥያቄው፡፡

ኢትዮጵያውያን በጭቆና ውስጥ እንኳ ሆነው የአገዛዞቹን ጥሪ የሚሰሙ፣ አገራዊ የእኔነት ስሜት ያላቸው፣ ከልዩነቱም ቢሆን የጋራ ታሪክ (በተለይ የነፃነት) ለመገንባት የሚጥሩም ነበሩ፡፡ ለዚህም ነው የሰሜኑ ከደቡብ፣ የምሥራቁ ከምዕራቡ ሕዝብ ታሪክ ጋር እየተጋመደ የሦስት ሺሕ ዓመታት ባለታሪክ ሲያስብለን የኖረው፡፡ አሁንስ ይኼ እውነታ አድጓል ወይስ ቀጭጯል? ነው ጥያቄው፡፡

አሁን አሁን ያለው የታሪክ መጎተት፣ ‹‹የእኛና የእነሱ›› ሙግት በአንድ አገር ውስጥ የምንኖር ሕዝቦች አላስመስል ብሎናል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር የአገሪቱ ሕዝብ በስደት ላይ ነው፡፡ አሁንም የያዘ ይዞት እንጂ ከአገር በመውጣት በየበረሃው የሚወድቀውና ውቅያኖስ የሚበላው ቁጥሩ ትንሽ አይደለም፡፡ በአገሩ ጥሮ ግሮ የሚቀየር የለም ባይባልም፣ ሒደቱ ብዙኃንን እያሳተፈ ለመሆኑ ያጠራጥራል፡፡ ምክንያቱም አሁንም ከ22 በመቶ የማያንስ ሕዝብ ከድህነት ወለል በታችና 17 በመቶ ሥራ አጥ መኖሩ አባባሉን የሚያሳይ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር አዲሱ ትውልድ ከማኅበራዊ ድረ ገጽ የክፋት ወሬዎች፣ ከአልባሌ ሱሰኝነትና የጎጠኝነት ንትርክ ወጥቶ በድህነት ላይ ለመዝመትም ሆነ ዴሞክራሲያዊት አገር ለመገንባት በአንድነት ሊቆም ይገባዋል፡፡ የተፈጠሩ ዕድሎችን ሁሉ አሟጦ በመጠቀም ፍትሐዊነትና አሳታፊነትን በትግሉ ዕውን ማድረግም ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲሆን ነው ከስሜት ወጥቶ በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተ ጥያቄ፣ ታቀውሞና ድጋፍ ሊያራምድ የሚችለው፡፡ አሁን በተጀመረው መንገድ እየተጓዘ ትውልዳዊ ኃላፊነትን መወጣት ግን በእጅጉ ከባድ ነው፡፡

በእርግጥ ትውልድን መውቀስ ቀላል ይመስላል፡፡ ምንም ተባለ ምን አሁን ያለው የእኛ ትውልድ ከቀደሙት ኢትዮጵያዊ ትውልዶች የሚያንስባቸው ጉዳዮች የሚበዙ ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ፣ የተጠራቀመው ችግራችንና ሥርዓቱና አገራዊ ልማዱ የየራሳቸው አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖራቸው ጥርጥር የለውም፡፡ ቀጪና ተቆጪ የጠፋበት፣ መተፋፈርና ፈሪኃ እግዚአብሔር የተዳከመበት የጉድ ጊዜ እየመጣ እንዳይሆን ያሳስባል፡፡

ይህ አባባል ልቦለድ ሳይሆን እውነት መሆኑን የሚያረጋግጠው በእምነት ተቋማት ሳይቀር ውሸት፣ ማጭበርበር፣ የሥልጣን ሽኩቻና ምድራዊ ፉክክር አይሎ መታየቱ ነው፡፡ ከታችኛው የትምህርት ደረጃ አንስቶ መኮረጅ፣ ኮፒ አድርጎ ፈተና ማለፍ በርክቷል፡፡ በሐሰተኛ የትምህርት መረጃ ሥራ መያዝና ገንዘብ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን፣ አገር መምራትም ‹‹ኖርማል›› ሆኗል፡፡  ይህን ጽሑፍ በምጽፍበት አንድ ምሽት በብሔራዊው የአገራችን ቴሌቪዥን ጣቢያ ከጋምቤላ ክልል ካቢኔ አባላት ዘጠኝ ያህሉ በፎርጅድ (ሐሰተኛ) የትምህርት መረጃ ወንጀል ተጠርጥረው መባረራቸውን ሰማሁ፡፡

እውነት ለመናገር ምርመራው ተጠናክሮ ከቀጠለ ግን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በአንዳንድ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶችም የባሰ ውጤት ሊገኝ ይችላል፡፡ በተለይ በርቀት ትምህርትና በውጭ ሥልጠና ስም ተወዳድሮ ማሸነፍ የማይችለው ግብስብስ ሁሉ፣ የፓርቲና የመንግሥት ሥልጣን ካባ እየደረበ አገር እየበደለ ይገኛል፡፡ በንፋስ አመጣሽ መንገድ የደለበ አንዳንዱ ‹‹ባለሀብትም›› አዋቂ ለመባል ያህል የትምህርት ማዕረግ ሲያግበሰብስ ማየት፣ ሥልጣንና ገንዘብ ከዕውቀትም በላይ ናቸው የሚለው ድምዳሜ እንደ ጉም አገሩን እንዲጋርደው እያደረገ ነው፡፡

በዕውቀት፣ በብቃትና በተወዳዳሪነት ላይ ያልተመሠረተ የአገር ግንባታ ሥር እንዳይሰድም ሊደረግ ይገባል፡፡ ገና ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ ወደ ፓርቲ አባልነት ወይም ከምክንያታዊ አስተሳሰብ ይልቅ ወደ አድርባይነት የሚጣበቅ ትውልድ እየታየ ነው፡፡ በእንዲህ ያለ መርህ አልባ ጉዞ የሚነጉድ ኃይል ደግሞ ሄዶ ሄዶ ለመልካም አስተዳደር ብልሽት፣ ለኢፍትሕዊነትና ለሙስና የተጋለጠ መሆኑ የሚገርም አይሆንም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ እንዳለውና መንግሥትም እንዳረጋገጠው፣ በአገሪቱ  በአቋራጭ መበልፀግና ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም ጎልቶ ታይቷል፡፡ ትናንት ባዶ እጅ የነበሩ አንዳንድ አባላት በአገርና የሕዝብ ሀብት ላይ እያዘዙ መበልፀጋቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በተለይ የከተማ መሬት፣ የቀረጥና ግብር ጉዳይ፣ ኮንትሮባንድ፣ የመንግሥት ግዥና ሽያጭ፣ እንዲሁም የኮንትራት ግዥ ላይ የሚታየው ጥፋት ከወዲሁ ወገቡን ካልተመታ አገር የሚያፈርስ ነው፡፡ ይህ የሥርዓት ብልሽት ደግሞ ያለ ጥርጥር ትውልዱን ሌብነት እንዲጫጫነው አድርጎታል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

እንግዲህ አሁን ያለውን ትውልድ ከኩረጃና ከሌብነት አውጥቶ ለተሻለ ውጤት ለማድረስና አገር ገንቢ እንዲሆን ለማስቻል ብዙ ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ ከሃይማኖት ተቋማት ጀምሮ፣ ትምህርት ቤቶች፣ መንግሥትና የሲቪክ ማኅበራትም ኃላፊነታቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ የራሱ የትውልዱ ሚና ግን ተኪ ሊኖረው አይችልም፡፡

ይኼ አገር የታሪክ ችግር ያለበት አይደለም፡፡ የውጭ ወራሪን በሌለ አቅምና በኋላ ቀር መሣሪያ ቀጥቅጦና ደጋግሞ ካሳፈረው ቀደምቱ ትውልድ አንስቶ ‹‹ፋኖ ተሰማራ እንደ ቼጉ ቬራ. . .›› እያለ በረሃ ወርዶና ተፋልሞ አምባገነን ሥርዓቶችን እስካሽቀነጠረው የቅርቡ ትውልድ ድረስ ብዙ መስዋዕትነት፣ ገድልና ትርክት ሞልቶናል፡፡ እውነት ለመናገር ድሮም ሆነ ዛሬ በግል ጥረታቸውና በላባቸው ሠርተው የተቀየሩ (ነጋዴዎች፣ ሯጮች፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ ምሁራንና የፈጠራ ሙያተኞች. . .) ቁጥራቸው አይበርክት እንጂ ታሪክ ሠሪነታቸው ሊናቅና ሊንኳሰስ አይገባም፡፡

አሁን አሁን እየመጣ ያለው አዲስ ትውልድ ግን ይህን እውነት ምን ያህል ይገነዘባል? የራሱንስ የታሪክ አሻራ ለማሳረፍ ምን ያህል ይተጋል? ነው የጥርጣሬ ጥያቄው፡፡ በአንድ በኩል ትውልዱ በአወዛጋቢ እውነታዎችና በግል ፍላጎት በተጠመዘዙ መረጃዎች እየተደናገረ ይመስላል፡፡ በሌላ በኩል ‹‹ታሪክን አድንቆ ታሪክ ለመሥራት እንዳይተጋ›› ብዙ እንቅፋቶች እየተደነቀሩበት ያለ ባለአደራ መስሏል፡፡ መገናኛ ብዙኃኖቻችን፣ የፊልም፣ የቴአትርና የሥነ ጽሑፍ ለዛችን ሁሉ ‹‹እንትንሽ እንትንህ›› ውስጥ ገብቶ መስመጥ ዓላማው ይኼው መስሏል፡፡

እዚህ ላይ መንግሥታዊ ሥርዓቱም ቢሆን ከ25 ዓመታት ወዲህ ላለው ስኬት እንጂ፣ ከዚያ በፊት ለነበሩ ጭላንጭል በጎ ሥራዎች ዕድል አለመስጠቱ የራሱን ተፅዕኖ አላሳደረም ማለት ያዳግታል፡፡ ከቀደሙት ሥርዓቶችም ሆነ ሕዝብ ጥፋትና ጉድለት የመኖሩን ያህል በጎነት፣ ጀግንነት፣ አንድነትና ሃይማኖተኝነት የሌለ ይመስል ሲድፈነፈን መታየቱ ትውልዱ ለአዲስ ታሪክ እንዳይነሳም እያደረገው ነው ባይ ነኝ፡፡

ከዚያ ይልቅ የእኛ ትውልድ እንቅልፍ እያጣበት ያለው ጉዳይ ስደት፣ የሌላውን ዓለም ‹‹ሞዴል›› ማድነቅና ለራሱ ትውፊት ትኩረት ያለመስጠት ሆኗል፡፡ ጠዋት ማታ አገሩን ከሚያደነቁሩት ሬዲዮኖች ጀምሮ የአውሮፓን እግር ኳስ ከነቅንጥብጣቢው ማመንዥክ ተለምዷል፡፡ ለሽብርም ሆነ ለጥፋት ወሬ ቀልብን ሰጥቶ መመሰጥም አለ፡፡ ይህ የማይጠቅም አካሄድ ደግሞ ትውልድን ከታሪክ ሠሪነት ያናጥባል፡፡ የአገሩን ታሪክ አውቆ፣ በጋራ እሴት ላይ እንዲቆም የሚረዳውን ተመራማሪነት እንዳያጠናክርም ያውከዋል፡፡

የማይካደው እውነት በመንግሥታዊ ሥርዓት ደረጃ እየተሠራ ያለ ታሪክ መኖሩ ነው፡፡ እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት፣ የማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ግንባታዎች . . . ያሉ አመርቂ የልማት ፍሬዎችን እያሳየ ነው፡፡ ይህ የፍጥነትና የጥራት ጥያቄ ብቻ ሊሳበት የሚችል የልማት መስክ፣ ‹‹ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ለሚሠራ ትውልድ ራሱን የቻለ ታሪክ›› እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ ግን የብዙኃኑን አዲስ ትውልድ ቀልብ ሰቅዞ የሚይዝ አገራዊ ራዕይና ‹‹እኔነትን›› የሚፈጥር አስኳል መሆን አለበት፡፡

በአጠቃላይ አሁን ያለው ትውልድ ያለውን ዕድልና መልካም አጋጣሚ ያህል የገባበት ልክ ያልሆነ አካሄድም አለ፡፡ በተለይ ከታሪክ አዋቂነት፣ ከብሔራዊ መግባባት፣ ከዴሞክራሲያዊ አንድነትና ከታሪክ ሠሪነት ውጪ ሆኖ ረዥም ርቀት መሄድ አይቻልምና ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...