Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሔኒከንና ካንጋሮ ፕላስት ሲወዛገቡበት የነበረው የንግድ ምልክት እንዳይሰረዝ ውሳኔ ተሰጠ

ሔኒከንና ካንጋሮ ፕላስት ሲወዛገቡበት የነበረው የንግድ ምልክት እንዳይሰረዝ ውሳኔ ተሰጠ

ቀን:

ካንጋሮ ፕላስት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከስድስት ዓመታት በፊት በአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት አስመዝግቦት የነበረውን ‹‹አይቤክስ›› የንግድ ምልክት፣ በሔኒከን ብሪዌሪስ አክሲዮን ማኅበር አመልካችነት ጽሕፈት ቤቱ ሰርዞት የነበረ ቢሆንም በቅርቡ ፍርድ ቤት እንዳይሰረዝ ውሳኔ ሰጠ፡፡

የአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ካንጋሮ ፕላስት አስመዝግቦት የነበረውን የንግድ ምልክት የሰረዘው ሔኒከን ብሪዌሪስ አክሲዮን ማኅበር ሙሉ ውክልና የሰጣቸው ወይዘሪት ማህሌት ሀብተወልድ፣ የንግድ ምልክቱ ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በገበያ ውስጥ ለሚገኘው ዋልያ ቢራ በንግድ ምልክትነት እንዲመዘገብላቸው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ነው፡፡

ሔኒከን በተወካይዋ በኩል ጥያቄውን ያቀረበው ካንጋሮ ፕላስት የንግድ ምልክቱን አስመዝግቦ ሳይጠቀምበት ሦስት ዓመታት በማለፋቸው፣ በንግድ ምልክት ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 501 መሠረት አንድ የተመዘገበ የንግድ ምልክት ሦስት ዓመት በአገልግሎት ላይ ሳይውል ከቀረ እንደሚሰረዝ የተደነገገውን መሠረት አድርጎ መሆኑን የውሳኔ መዝገቡ ያሳያል፡፡

ቀደም ብሎ በ2003 ዓ.ም. በምዝገባ ቁጥር 5283 የተመዘገበውን ‹‹አይቤክስ›› የንግድ ምልክት እያለ ሔኒከን ‹‹ዋልያ›› የሚል ንግድ ምልክት እንዲመዘገብለት ሲጠይቅ፣ የአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት በወቅቱ ተመሳሳይ ምልክት መመዝገቡን ጠቅሶ መልሶት እንደነበር ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡ ነገር ግን ተስፋ ያልቆረጠው ሔኒከን ለሁለተኛ ጊዜ በመጠየቁ ጽሕፈት ቤቱ ኮሚቴ በማቋቋም እንዲጣራ አድርጓል፡፡ በመሆኑም ካንጋሮ ፕላስት ለምን የንግድ ምልክቱን ሳይጠቀም እንደቀረም ተጠይቆ ሲያስረዳ፣ በቃላትና በምሥል ያስመዘገበውን “IBEX” (አይቤክስ) የንግድ ምልክት አገልግሎት ላይ ሳያውል የቀረው እናት ማኅበሩ (Holding Company) ካንጋሮ ፕላስት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ላይ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ምክንያት መሆኑን አስረድቷል፡፡ እናት ማኅበሩ በሥሩ በርካታ ድርጅቶችን ማቋቋሙንና አንዱም ሞጆ ከተማ ውስጥ ተገንብቶ የሚገኘው የቢራ ፋብሪካ መሆኑን በማስረዳት፣ የፋይናንስ ምንጩ የሆነው ድርጅት በመቃጠሉ የንግድ ምልክቱን ሳይጠቀም መቆየቱን አስረድቷል፡፡

ሔኒከን ብሪዌሪስ በበኩሉ ባነሳው የተቃውሞ መከራከሪያ፣ የተቃጠለው ድርጅትና የንግድ ምልክት ያወጣበት ድርጅት ራሳቸውን ችለው የሚተዳደሩ ሕጋዊ ድርጅቶች መሆናቸውን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ድርጅቶቹ የተለያዩ በመሆናቸው በንግድ ምልክቱ ላይ ያነሳው ጥያቄ ተገቢ እንደሆነም አስረድቷል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ ያቋቋመው ኮሚቴም የሁለቱን ወገኖች ክርክር ከሰማ በኋላ፣ ካንጋሮ ፕላስት የንግድ ምልክቱን ያልተጠቀመበትን ምክንያት በአግባቡ አለማስረዳቱን በመግለጽ፣ የንግድ ምልክቱ እንዲሰረዝ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ የኮሚቴውን ውሳኔ በወቅቱ የነበሩት የጽሕፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አዴሎ በማፅደቃቸው ምልክቱ መሰረዙም ይታወሳል፡፡ የጽሕፈት ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ካንጋሮ ፕላስት ጉዳዩን በይግባኝ ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በመውሰዱ፣ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከተገቢው አዋጅና ሕግ ጋር አገናዝቦ በመመርመር የንግድ ምልክቱ እንዳይሰረዝና በካንጋሮ ፕላስት ተመዝግቦ እንዲቆይ ውሳኔ መስጠቱ አይዘነጋም፡፡

ሔኒከንን በመወከል በጠበቃቸው በአቶ መሀሪ ረዳኢ አማካይነት የይግባኝ አቤቱታ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወይዘሮ ማኅሌት ሀብተወልድ ይግባኝ አቅርበዋል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ችሎትም ግንቦት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ፍርድ ሰጥቷል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ችሎት በሰጠው ፍርድ፣ ካንጋሮ ፕላስት የንግድ ምልክቱን ሳይጠቀም የቆየው ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ምክንያት መሆን አለመሆኑን የአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤትን ጣልቃ በማስገባት አከራክሮ የመሰለውን ውሳኔ እንዲያሳልፍ መዝገቡን ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት መልሶታል፡፡ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ካንጋሮ ፕላስትን በይግባኝ ባይነት፣ ወይዘሮ ማህሌት ሀብተወልድንና የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤትን በመልስ ሰጪነት አስቀርቦ አከራክሯል፡፡ የሦስቱንም ወገኖች መከራከሪያ ነጥቦች ከሰማ በኋላ በሰጠው ፍርድ እንደገለጸው፣ ካንጋሮ ፕላስት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሲቋቋም በውስጡ ሌሎች በተለያዩ የሥራ ዘርፍ የሚሰማሩ ድርጅቶች እንዲኖሩት ተደርጎ የተቋቋመ ማኅበር መሆኑን ማረጋገጡን ገልጿል፡፡

በንግድ ሕግም እናት ማኅበር (Holding Company) ተብሎ እንደሚጠራም ገልጿል፡፡ በእናት ማኅበሩ ሥር የሚቋቋሙ ድርጅቶች የፋይናንስ ድጋፍና የአስተዳደር ቁጥጥር እየተደረገላቸው የሚሠሩ (Subsidiary Company) ተብለው እንደሚታወቁም በፍርዱ ተጠቅሷል፡፡ በመሆኑም በተከራካሪ ወገኖች በኩል ድርጅቶቹ ራሳቸውን የቻሉ ናቸው በማለት የቀረበው የመከራከሪያ ነጥብ ትክክል አለመሆኑን ፍርድ ቤቱ በፍርዱ ገልጿል፡፡ በእናት ማኅበሩ ላይ የደረሰው ጉዳት በድርጅቱ ላይ ጉዳት መፍጠሩን ፍርድ ቤቱ አረጋግጦ፣ ተከራካሪዎችም ድርጅቱ ሌላ ገቢ አለው ብለው አለመከራከራቸውንም አስረድቷል፡፡ በመሆኑም በካንጋሮ ፕላስት ላይ የደረሰው ቃጠሎ፣ ለገነባው የቢራ ፋብሪካ ባላጠናቀቀው የማሽነሪ ግዢ ላይ የፋይናንስ እጥረት በመፍጠሩ የንግድ ምልክቱን እንዳይጠቀምበት መሰናክል መፍጠሩን፣ በአዋጅ 501/98 አንቀጽ 35(3) መሠረት ካንጋሮ ፕላስት ምልክቱን ያልተጠቀመው በቂ በሚባል ምክንያት መሆኑን ገልጿል፡፡ በአንቀጽ 35(4) እና በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1792 መሠረትም ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት መሆኑ በመረጋገጡ፣ የንግድ ምልክቱ መሰረዙ ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ ፍርድ ቤቱ/ፍርድ ሰጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ጽሕፈት ቤት ጣልቃ ገብቶ እንዲከራከር የተደረገ ቢሆንም ምንም ያለው ነገር እንደሌለ በፍርዱ ተገልጿል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...