– በአዲስ አበባ የታቀዱት ማስፋፊያዎች ከማስተር ፕላኑ ጋር መጣጣም ይጠበቅባቸዋል
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፕሬሽን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ከያዛቸው ግዙፍ የባቡር መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች መካከል፣ የሞጆ-ሐዋሳ-ሞያሌና የአዲስ አበባ-ጅማ-በደሌ መስመሮችን በራሳቸው ፋይናንስ ገንብተው ማንቀሳቀስ ለሚችሉ የውጭ ኩባንያዎች ለመስጠት ታቅዷል፡፡ የባቡር መስመሮቹ ኢትዮጵያን ከኬንያና ከሱዳን ጋር የሚያገናኙ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
የባቡር መሠረተ ልማት ግንባታ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ በመሆኑ በሁለተኛው የአምስት ዓመት የታቀዱትም ሆነ ወደፊት የሚከናወኑ የባቡር መሠረተ ልማቶች፣ ከተጓዳኝ የልማት ፕሮጀክቶች ጋር በተጣመሩ የግል ባለሀብቶች ወይም በመንግሥትና ግል ኩባንያዎች ጥምረት እንዲከናወኑ መንግሥት በሰጠው አቅጣጫ ነው፣ ኮርፖሬሽኑ የተጠቀሱትን ሁለት መስመሮች ለግል ባለሀብቶች ተላልፈው እንዲገነቡ ለማድረግ ዝግጅቱን የጀመረው፡፡
ፕሮጀክቶቹን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ጌታቸው በትሩ፣ በተለይ ከሞጆ-ሐዋሳ-ሞያሌ የሚዘረጋው መስመር እጅግ አዋጭ ከመሆኑ የተነሳ በርካታ ኩባንያዎችን እንደሚስብ ጥርጥር እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ይህ ፕሮጀክት ከኬንያ ሞምባሳ ወደብ ጋር የሚገናኝና ለኢትዮጵያ ሁለተኛ የባህር በር የሚፈጥር በመሆኑ ነው፡፡
ይኼንን ፕሮጀክት ለማስጀመርም በአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ግንባታ ላይ የተሳተፈው የቻይናው ኩባንያ ሲሲኢሲሲ የአዋጭነት ጥናት ለማካሄድ፣ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ስምምነት ፈርሞ ሥራ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡
እ.ኤ.አ በኦገስት 2016 በኬንያ ተካሄዶ በነበረው ስድስተኛው የጃፓን-አፍሪካ የልማት ጉባዔ (Tokyo International Conference on African Development) ላይ፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሞጆ-ሐዋሳ-ሞያሌ የባቡር መሠረተ ልማት ዕቅዱን አስተዋውቆ ነበር፡፡
ላሙ ፖርትና ላሙ ደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያ ኮሪደር (LAPSSET) በሚባል መጠሪያ የሚታወቀው የኬንያ ግዙፍ ፕሮጀክት ባለሥልጣናት፣ የሞጆ-ሐዋሳ-ሞያሌ የባቡር መስመር የሚያልፉባቸው አካባቢዎችን በአካል ተገኝተው መጎብኘታቸውና በፕሮጀክቱም ደስተኛ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ከሞያሌ ድንበር እስከ ላሙ ወደብ ድረስ ያለውን የባቡር መስመር የኬንያ መንግሥት እንደሚገነባ ታውቋል፡፡
ከአዲስ አበባ-ጅማ-በደሌ የሚዘረጋው በኋላም ከሱዳን ጋር ለሚገናኘው የባቡር መስመር የተለያዩ አገር ኩባንያዎች የራሳቸውን ገንዘብ ይዘው ለመገንባት ፍላጎት ማሳየታቸውን ዶ/ር ጌታቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በተለይ የብራዚል ኩባንያዎች ገፍተው እየመጡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከበደሌ ወደ ሱዳን ድንበር የሚዘረጋውን የባቡር መስመር በተመለከተ የአፍሪካ ልማት ባንክ በገንዘብ ለመደገፍ ፍላጎት ከማሳየት ባለፈም፣ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ሥራ የጀመረውን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ወደተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎችና ወደ ኦሮሚያ ክልል ልዩ ዞን የማስፋፋት ፍላጎት እንዳለው ቢታወቅም፣ ይህ ፕሮጀክት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአሥር ዓመታት የሚያገለግል ማስተር ፕላን እያወጣ በመሆኑ በዕቅዱ የተያዙት ፕሮጀክቶች ከዚህ ማስተር ፕላን ጋር እንዲጣጣሙ የግድ ሆኗል፡፡ የኮርፖሬሽኑ የመጀመሪያ ዕቅድ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር መስመሮችን በአራቱም አቅጣጫ ማስፋፋት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከመገኛኛ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት አድርጎ ሳሪስ፣ እንዲሁም ከሜክሲኮ በአፍሪካ ኅብረት አድርጎ ለቡ ድረስ ማስፋፋት ናቸው፡፡
ሁለቱም ዕቅዶች ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር መጣጣም የሚጠበቅባቸው በመሆኑ፣ በተለይ ከአያት ወደ ለገጣፎ እንዲሁም ከጦር ኃይሎች ወደ ሰበታ የሚስፋፉት መስመሮች ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን ጋር መጣጣም ይኖርባቸዋል ተብሏል፡፡