Wednesday, September 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የ‹‹አጐዋ›› ነፃ ንግድ ሥርዓት በአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እንዳይቋረጥ...

  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የ‹‹አጐዋ›› ነፃ ንግድ ሥርዓት በአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እንዳይቋረጥ ጠየቁ

  ቀን:

  አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ለአፍሪካ አገሮች ምርቶች የፈቀደችውን “AGOA” በሚባል መጠሪያ የሚታወቀው ከኮታና ከታሪፍ ነፃ የንግድ ሥርዓት ሊያቋርጡት እንደማይገባ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ገለጹ፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዎል ስትሪት ጆርናል ከተባለው ታዋቂ የአሜሪካ ጋዜጣ ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው ለአፍሪካ ምርቶች በተፈቀደው ነፃ የንግድ ሥርዓት ላይ፣ አዲሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምንም ዓይነት ተፃራሪ ውሳኔ ሊያሳልፉ እንደማይገባ የተናገሩት፡፡

  ፕሬዚዳንት ትራምፕ ቃለ መሃላ ፈጽመው የፕሬዚዳንትነቱን በትረ ሥልጣን በተረከቡ ማግሥት፣ አሜሪካ ከትራንስ ፓስፊክ አገሮች ጋር የፈጠረችው የንግድ ግንኙነት እንዲቋረጥ መወሰናቸው ይታወሳል፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በዋናነት በሁሉም መስኮች ቅድሚያ ለአሜሪካ እንደሚሰጡ ቃል በገቡት መሠረት ሥልጣናቸውን እንደተረከቡ ዕርምጃ መውሰድ መጀመራቸው፣ የበርካታ አገር መሪዎችን ትኩረት እያሳሰበ የሚገኝና በዓለም አቀፍ ደረጃም ዋነኛ መነጋገሪያ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡

  ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር ቃለ ምልልስ ያደረገው ዎል ስትሪት ጆርናል የተባለው ጋዜጣም በዚሁ ጉዳይ ላይ በመመሥረት፣ የኢትዮጵያና የአሜሪካ የቆየ ወዳጅነት በአዲሱ ፕሬዚዳንት ዘመን እንዴት ሊቀጥል እንደሚችል ጥያቄ አቅርቦላቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በሰጡት ምላሽም፣ የሁለቱ አገሮች ወዳጅነትና ትብብር በፕሬዚዳንት ትራምፕ ዘመንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

  በተለይ ሁለቱ አገሮች የሚታወቁበት የፀረ ሽብር ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸው መሆኑን፣ ለዚህም ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሜሪካ ለአፍሪካ አገሮች ምርቶች “African Growth Opportunity Act” በሚል ስያሜ የፈቀደችው ነፃ የታክስና የኮታ ዕድል መቋረጥ የለበትም ብለዋል፡፡

  ይህ ዕድል በፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ዘመን የአፍሪካ አገሮች የኢንዱስትሪ ሽግግርን ለማገዝ ለስምንት ዓመታት የተፈቀደ ነበር፡፡ ለአፍሪካ አገሮች የተፈቀደው ይህ የገበያ ዕድል ማብቂያው እ.ኤ.አ. በ2008 የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ እ.ኤ.አ. እስከ 2015 ተራዝሟል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን በማግባባት ለተጨማሪ አሥር ዓመታት እንደገና እንዲራዘም ማድረግ ችለዋል፡፡

  ይህ የገበያ ዕድል በተለይ ኢትዮጵያ አሁን በጀመረችው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ምክንያት ተጠቃሚ ሊያደርጋት ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጨርቃ ጨርቅና ልብስ ስፌት ለመሰማራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ የአሜሪካና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ኩባንያዎች የገቡትም፣ ይህንኑ የአሜሪካ ነፃ የገበያ ዕድል ላይ ተስፋ አድርገው መሆኑ ይነገራል፡፡ 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ‹‹ለሰላምና ለዕርቅ መሸነፍ የለብንም›› ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ

  የሰው ልጅ ጠብን በዕርቅ፣ በደልን በይቅርታ፣ ድህነትን በልማት፣ ክህደትን...

  መፍትሔ አልባ ጉዞ የትም አያደርስም!

  ኢትዮጵያ ችግሮቿን የሚቀርፉ አገር በቀል መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይኖርባታል፡፡...

  ጦርነቱና ውስጣዊ ችግሮች

  መስከረም 14 ቀን 2015 ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው...