Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ባለፈው ሳምንት የአንዲት ጓደኛዬን አባት ለመጠየቅ ራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል ተገኝቼ ነበር። በሆስፒታሉ ሕንፃ ታሪካዊነትና የአርክቴቸር ውበት እየተደመምኩ ወደ ሆስፒታሉ ግቢና የውስጥ ክፍል ሳመራ ደግሞ በንፅህናው፣ በአበቦችና በአረንጓዴ ሳር በተዋበው መናፈሻው ልቤ በደስታና በአድናቆት ተሞላ። ይህን አስደሳችና ቀለል ያለ ስሜት በውስጤ እያስተናገድኩ የጓደኛዬ አባት ወደተኙበት የራስ ደስታ የአጥንት ሕክምና ክፍል አመራሁ።

በክፍሉ ውስጥ ለተኙት ታካሚዎችና ለጓደኛዬ አባት እንደ አገራችን ባህል ፈጣሪ አምላክ በቶሎ ምሕረትን እንዲያደርግላቸው ልባዊ ምኞቴን ከገለጽኩ በኋላ ሰላምታ ተለዋውጬ አረፍ አልኩ። አባቷን እያስታመመች ከምትገኘው ጓደኛዬና አብረዋት ካሉ ጠያቂዎች ጋር መጫዋወት ጀመርን። በድንገት ቁመቱ ዘለግ ያለ ጎልማሳ ሰው ታማሚዎች ወደተኙበት ክፍል እያዘገመ፣ “እስረኛው ማነው? ፖሊሶቹስ የታሉ?!” ሲል ታካሚዎችን በዓይኑ እየገረመመ ጠየቀ። ከውጭ ተቀምጠው የነበሩ ሁለት ፖሊሶች ፈጠን ብለው፣ “አቤት አለን!” እያሉ ወደ መኝታ ክፍሉ ገቡ። ወዲያውም አንዲት ነርስ በመኝታ ክፍሉ ውስጥ ያለን አስታማሚዎችና ሌሎቻችን ወደ ውጭ እንድንወጣ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈች።

ያ እስረኛው የታለ በማለት የጠየቀው ሰው ለካ የሕክምና ባለሙያ/ዶክተር ነው። በመሠረቱ ይህ ሰው የሕክምና ባለሙያ ስለመሆኑ የሚናገር የደንብ ልብስና የደረት ባጅ አላደረገም። ግን የሆስፒታሉ አስተዳደር በየግድግዳው ላይ በለጠፈው የሕክምና ሥነ ምግባር ደንብ/መመርያ በሆስፒታሉ ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች የደንብ ልብስና የደረት ባጅ እንዲያደርጉ ይመክራል። ይህ ሰው ግን የሕክምና ባለሙያ ስለመሆኑ የሚገልጽ አንዳንች ነገር የለውም። ከዚህ በላይ ደግሞ የሚያሳዝነውና የሚያስተዛዝበው ጉዳይ ባለሙያው/ሐኪሙ  በክፍሉ ተኝተው ለሚታከሙ ታማሚዎች ከፍቅር የመነጨ ፈገግታንና ሰላምታን በማስቀደም ሳይሆን የገባው ስሜትን በሚረብሽ አኳኋን፣ “እስረኛው ማነው?!” በሚል ድርቅ ያለ ጥያቄን በማስቀደም ነው።

ከአንድ የሕክምና ባለሙያ በማይጠበቅ፣ ለታካሚዎቹ ፍቅርና ክብር የሌለው በሚመስል የተሰላቸ ስሜት፣ ሙያዊ ሥነ ምግባርና ጨዋነት በጎደለው ሁኔታ “እስረኛው ማነው?!” በሚል ጥያቄ የሕክምና ዕርዳታ ለመስጠት ጥያቄውን ያቀረበው ሐኪም፣ ክፍሉን እንድንለቅ ካደረገ በኋላ የሕክምና ዕርዳታ ለመስጠት ሥራውን ጀመረ። ከመኝታ ክፍሉ ወደ ውጭ እንደወጣንም ከሰዎች ጋር በተፈጠረ ግጭት ተጎድተውና በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ለሕክምና በሆስፒታሉ የተገኙት አባት ልጅ የሆነችው ጓደኛዬ፣ ስሜቷ ተለዋውጦና ዓይኗ በእንባ ተጋርዶ አየኋት። ጓደኛዬ በቅጽበት ስሜቷ እንዲያ የተለዋወጠበትንና ሐዘን ውስጥ የከተታት ጉዳይ ምን እንደሆነ ወዲያውኑ ገባኝ። እሷም ዓይኗ እንባ እንዳቀረረ፣ “እንዴት በሥቃይ ውስጥ ሆኖ እያቃሰተ፣ የእሱን ዕርዳታ እየተጠባበቀ ያለውን አባቴን በዚህ ሁሉ ሰው መካከል እስረኛው ማነው ይለዋል?! አባቴ ወላጆቹ ያወጡለት ስም አለው … ሰው እንዴት እስረኛ ተብሎ ይጠራል … አንድ የሕክምና ባለሙያስ ለታካሚዎቹ ስሜትና ሞራል አይጠነቀቅም ማለት ነው?! በእውነት አሳዝኖኛል፣ አናዶኛልም፤” ስትል የተከፋ ስሜቷን አጋራችኝ።

በእርግጥም የሕክምና ባለሙያው በተናገረው ነገር እኔም ደንግጫለሁ፣ አዝኛለሁም። በምንም ሚዛን ትክክል አልነበረም። ሰው እንስሳ/ውሻ  አይደለም፣ አይታሰርም። ሰውን ያህል ክቡር ፍጥረትም “እስረኛ” ብሎ መጥራትም ነውር ነው። ከፍተኛ የሆነ ሥነ ምግባርና ጨዋነት የሚጠይቅ እጅግ የተከበረ የሙያ መስክ ውስጥ ያለ አንድ ሐኪም ታካሚውን “እስረኛ” ብሎ ሲጠራ መስማት ይቀፋል፣ በእጅጉ ያስደነግጣልም። እንደ አገራችን ሕግ/የፍትሕ ሥርዓት ማንኛውም በሕግ ቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው የፈጸመው ወንጀል እስኪጣራ ድረስ ተጠርጣሪ ተብሎ ነው የሚጠራው፡፡ በሕግ ቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው በሰነድ ማስረጃ፣ በሰዎች ምስክርነትና በሌሎች ቴክኒካዊ መረጃዎች ወንጀል መሥራቱ ተረጋግጦ በሕጉ አግባብ ፍርድ ሲሰጠው ደግሞ ታራሚ እንጂ በምንም መልኩ “እስረኛ” ተብሎ አይጠራም። የሕግ ዋነኛ ዓላማውም ሕግና ደንብን የተላለፈ ሰውን ማረምና ሌሎችም እንዲህ ዓይነት ወንጀል ውስጥ እንዳይገቡ ወይም እንዳይፈጽሙ ማስተማር ነው።

ይህ በአገራችን እንዲሁ በዘልማድ በሕግ ቁጥጥር ሥር የዋለን ሰው “እስረኛ” ብሎ መጥራት የተለመደና ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ እንደሆነ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ በአገራችን ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት እንዲህ ዓይነት ተገቢ ያልሆኑ፣ የሰው ክብርና ማንነት፣ ሰብዕናና ሞራል የሚነኩ አዋራጅና ክብረ ነክ ቃላት ተወግዘው እንዲወገዱ ተደርገዋል። ይኼም ብቻ ሳይሆን እነዚህን አዋራጅና ክብረ ነክ (Pejorative and Derogative) ቃላትን መጠቀምም በሕግ ጭምር የሚያስጠይቅ መሆኑም በግልጽ ይታወቃል። አንድ የተማረ ሰው ያውም ደግሞ የሕክምና ባለሙያ ይህን ሊያውቅ ይገባል፣ ደግሞም ግድም ነው።

በመጨረሻም የሕክምና ባለሙያ በሥቃይ፣ በሕመም ውስጥ ያሉ ታካሚዎችን በእንዲህ ዓይነት የሚያሸማቅቅ፣ ስሜትን የሚጎዳና ሞራልን የሚነካ ቃላትን በመጠቀም ለሥነ ልቦናዊ ቀውስ ሊዳርጓቸው አይገባም። ይህ በሕግም ያስጠይቃል። የሕክምና ባለሙያዎች ከሙያቸው ባሻገር ለታካሚዎቻቸው ፍቅርንና ርኅራኄን በማሳየት በመልካም ቃላትና አንደበት ጭምር ሊያክሙ እንደሚገባቸው ግልጽ ነው። በመሠረቱ የሕክምና ሙያ ተማሪዎች በትምህርታቸው ከፍተኛ ነጥብ ብቻ ስላመጡ የሚገቡበት ሊሆን አይገባውም። ከምንም በላይ ፍቅርን፣ ርኅራኄና ትሕትናን የተላበሰ ባህርይ ሊኖራቸው ይገባል። ይህ መልካም ባህርይና ሥነ ምግባር ወደ ሕክምና ሙያ ለሚገቡ ተማሪዎች ከትምህርት ውጤታቸው ባልተናነሰ እንደ መመዘኛ ሊቀመጥ ይገባዋል።

(ፍቅር፣ ከአዲስ አበባ) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...