Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርከትራምፕም የከፋ አለ

ከትራምፕም የከፋ አለ

ቀን:

በቅርቡ 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሲጠቀሙበት የነበረውን የብትመርጡኝ አደርግላችኋለሁ ዘመቻ፣  ኋይት ሐውስ ከገቡ በኋላ በፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ እኚህን ሰው ከቀደሙት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ሁሉ የሚለያቸው አንድ ነገር ቢኖር የገቡትን ቃል ለመፈጸም የሚያተጉ ሆነው መታየታቸው ነው፡፡ የቀድሞዎቹ ፕሬዚዳንቶች በምረጡኝ የቅስቀሳ ዘመቻቸው ወቅት ለአሜሪካ ሕዝብና ለዓለም በርካታ አማላይ ተስፋዎችንና ዕቅዶችን በርቱዕ አንደበታቸው ቢያነበንቡም፣ ሕዝባቸውን አሳምነው የዓለም ንግሥና ሥልጣናቸው ከተቆናጠጡ በኋላ ግን ከገቧቸው ቃልኪዳኖች መካከል ግማሹን እንኳ ሳይፈጽሙ የአራት ወይም የስምንት ዓመት የሥልጣን ጊዜ ገደብ ይገላግላቸዋል፡፡

በቅርቡ የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸውን ያጠናቀቁትና ነጩን ቤተ መንግሥት በእምባ የተሰናበቱት ባራክ ኦባማ፣ ለአሜሪካ ሕዝብና ለተቀረው ዓለም ከገቧቸው ተስፋዎች መካከል ምን ያህሉን ተግባር ላይ እንዳዋሉ የታወቀ ነው፡፡ ይልቁን ፕሬዚዳንት ኦባማን የታዘብኳቸው ነገር ቢኖር ለአፍሪካ የተመኙትና ያቀዱት የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት እንዲሁም የትክክለኛና የሐቀኛ ምርጫ ጉዳይ ተከድኖ ይብሰል እንደሚሉት መሆኑ ነው፡፡ ከቤተ መንግሥት መውጫቸው ጊዜ ሲደርስ ፕሬዚዳንቱን የተናነቃቸው እምባ መልዕክቱ ምን ይሆን? እንድል አድርጎኛል፡፡

 ምናልባትም አፍሪካዊ ደማቸው መጥቶባቸው ሥልጣን ላለመልቀቅ ፈልገው ቢሆንስ? ቃል የገቧቸው ጉዳዮች የሥልጣን ዘመናቸው ጊዜ በማነሱ ሳይፈጽሟቸው በመቅረታቸው ተቆጭተው ማዘናቸው ይሆን? አላውቅም፡፡ ከአሁን በፊት የሥልጣን ዘመናቸውን የፈጸሙ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ለተተኪው ዙፋኑን ሲያስረክቡ የእፎይታ ሳቅና ደስታ ሲነበብባቸው ይታዩ ነበር፡፡ የኦባማ ግን ያጠያይቃል፡፡ እንደ አፍሪካዊ ዘመዶቻቸው የአሜሪካን ሕገ መንግሥት ላሻሽልና ሥልጣን ላይ ልቆይላችሁ አለማለታቸውም እሰየው ነው፡፡ የሆነው ሆነና ጊዜው ደርሶ ኋይት ሐውስን ለቀው በሄሊኮፕተር ተሳፍረው ወደ ጡረታ ቤታቸው ሄደዋል፡፡

ተረካቢው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የማይተገበር ተስፋ የሚሰጡ ሰው አልነበሩምና የአሜሪካ ድንበርን ከሜክሲኮ የሚለየውን ግምብ ለማስገንባት ወዲያውኑ ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ፣ ስደተኞችን ላለመቀበልና የተወነሱ አገሮች ዜጎችም ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ እንደሚያደርጉ ሲገልጹ የነበረውን በፊርማቸው አፅድቀው ወደ መንግሥት ሥራ ቀይረዋል፡፡ ይህንን ተክትሎ ግን የተወሰኑ አሜሪካውያን ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ለመመልከት ችለናል፡፡ የአፍሪካ ኅብረትም ከአዲስ አበባ ተቃውሞውን እንደገለጸ ከአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ሰምቻለሁ፡፡ የሥራ ጊዜያቸውን የጨረሱት የቀድሞዋ የኅብረቱ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ድላሚኒ ዙማ፣ የተወሰኑ የአፍሪካ አገሮች ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ዕግድ ባስተላለፉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ላይ ነቀፌታቸውን ሰንዝረዋል የሚል ዜና ከዚያው ከአሜሪካ ድምፅ የሰማሁ መሰለኝ፡፡

እኔ ግን ተሰናባቿን የአፍሪካ ኅብረት ዋና ጸሐፊ አንድ ጥያቄ መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡ ክብርት ሆይ ለመሆኑ ከዓመት በፊት የአገርዎ የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ዜጎች በስደተኛ ኢትዮጵያውያንና በሌሎች የአፍሪካ ዜጎች ላይ ያውም ኢሰብዓዊና አረመኔያዊ ተግባር እየፈጸሙ ከአገራቸው እንዲወጡላቸው በማስገደድ ያንን ሁሉ አስጸያፊ ተግባር ሲፈጽሙ፣ እሳቸው የት ነበሩ? ምነው የዚያን ጊዜ አንድም ቃል አልተነፈሱ? ያሳዝናል፡፡ ይህ በመሆኑም ድንቄም የአፍሪካዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እንድል ገፋፍቶኛል፡፡ በቅርቡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከዛምቢያ እስር ቤት መለቀቃቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቦናል፡፡ ለመሆኑ እነዚህ አፍሪካውያን ስደተኞች በአፍሪካውያን ወንድሞቻቸው የሚደርስባቸው ግፍና በደል ተወግዞ ያውቃል?

የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ከወራት በፊት ካርቱም እስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ በደልና ዘግናኝ ግፍ ስለሚፈጸምባቸው ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን አበሳ እዚያው ቦታው ተገኝቶ ያቀረበውን ዘገባ ያነበበ ሰው፣ ዶናልድ ትራምፕ አፍሪካውያን ስደተኞች ወደ አገሬ አሜሪካ እንዳትመጡ ቢሉ ምን ይደንቀዋል? በተፈጥሮ ሀብት የታደለችው አፍሪካ ሁልጊዜም አሜሪካን ከማለም ይልቅ በአገሯ የሚኮሩ ዜጎች እንዲኖሯት መሪዎቿ ለምን አይጥሩም? እንቆቅልሹ ይኼው ነው፡፡

ለመሆኑ እንደ ሳዑዲ ዓረቢያ ያሉ ሀብታም የዓረብ አገሮች መጸዳጃ ቤታቸውን የሚያፀዱላቸውን ኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያን ምስኪን ሠራተኞችን ባልፈለጓቸው ጊዜ  እንደ እንስሳ በገፍ እየጎተቱ፣ እየገደሉና እያሰሩ ወደየአገራቸው ሲመልሷቸው ለምንድን ነው በዘረኝነት የማይወገዙት? ለምንድን ነው በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠይቀው የማያውቁትና በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የማይቆሙት? ለዶናልድ ትራምፕ ሲሆን ጊዜ ግን ዘረኝነት ፈጽመዋል እየተባሉ ከየአቅጣጫው ውግዘቱና ፉከራው ይዥጎደጎዳል፡፡ እኔ ግን ለምን አሜሪካ ላይ ብቻ እላለሁ፡፡ በአውሮፓ በተለይም በእንግሊዝ የተደረጉ የተቃውሞና ትራምፕን የሚያወግዙ ሠልፎችን ስመለከት ግር ተሰኝቻለሁ፡፡ ለመሆኑ እንግሊዝ የየትኛውንም አገር ዜጋ ስደተኛ ለመቀበል ፈቃደኛነቷን አንስታ የለም እንዴ? ከአውሮፓ ኅብረት ሳይቀር ለመውጣት የወሰነች ራስ ወዳድ አገር ሆና ሳለ ደርሶ ትራምፕን በዘረኝነት ለማውገዝ አደባባይ መውጣት ምን የሚሉት ነው?

የትራምፕን ፖሊሲ ለመቃወም ከመጣደፍ በፊት በቅድሚያ በየራሳችን ጓዳ ያለውን የዘረኝነት አስተሳሰብ ማሻሻል ያስፈልጋል ባይ ነኝ፡፡ በአገሬ ኢትዮጵያ እንኳ አንዱ ኢትዮጵያዊ ጎረቤቱን ኢትዮጵያዊ ከኖረበት ክልል እያስወጣ፣ ይኼ ያንተ ክልል አይደለም፣ የእኔ ነው የሚባልበት ይህ ዘመን አመጣሹ ዘረኝነት ምን ዓይነት ስያሜ ይሆን የሚሰጠው? አሜሪካ የሌሎች አገሮችን ዜጎች ነው አትምጡብኝ ያለችው፡፡ እንደእኛ ከክልላችን ውጡ በማለት ዜጎችን ከዜጎች የሚያጋጩ ባለሥልጣናት አልመረጠችም፡፡

በኢትዮጵያ ከገዛ አገሩና ከቀዬው ሕዝብ ንብረቱን እየተቀማ ሲባረር ኧረ የሕግ ያለህ ተብሎ ይታወቃል? ከኦሮሚያና ከደቡብ ክልል የተባረሩ አማሮች፣ ከአማራ ክልል እንዲወጡ ዘመቻ የተካሄደባቸው የትግራይ ተወላጆችን እያየን አይደለም እንዴ? አባራሪዎቹ ምን ዓይነት ስያሜ ይሰጣቸው ይሆን? ሩቅ ያለውን የአሜሪካውን ዶናልድ ትራምፕን ዘረኛ፣ ራስ ወዳድ ከማለት በፊት እዚህ አጠገቤ እየተፈጸመ ያለውን ዘረኝነት በቅድሚያ ማውገዝ ይጠበቅብኛል፡፡

የአሜሪካና የካናዳን ሀብትና ዶላር ከመመኘት  ይልቅ ጠንክሮ ሠርቶ ሀብታም መሆን ይበጃል እላለሁ፡፡

(ተክልዬ ጀማነህ፣ ከምሥራቅ አዲስ አበባ)

* * * * * * *

ጫት ሁሌ ጥፋት

በዓለማችን ጫት እንደ አደንዛዥ ዕፅ ስለሚቆጠር፣ በርካታ አገሮች ጫትን የሚያዘዋውር ሰው ላይ እስር ሲበይኑ ይታያሉ፡፡ ጥቂት አገሮች በሞት እንደሚቀጡም ይታወቃል፡፡ በሐረሪ ክልል ግን በተለይ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሳይቀር ዕለታዊ ፍጆታ እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በሐረሪ ክልል የመንግሥት ተሽከርካሪዎች በየዕለቱ ለአለቆች ጫት ለመሸመት ወደ ገበያ ወይም ወደ እርሻ ማሳያዎች እየሄዱ የገዙትን ጫት ባለሥልጣኑ ቤት ድረስ የማመላለስ ዕለታዊ ተግባራቸው እየሆነ ነው፡፡

ግለሰቦችም ቢሆኑ እንደ እጅ መንሻ በየሹማምንቱ ቤት መውሰዳቸውም የተለመደ ነው፡፡ በሐረሪ ክልል ካቢኔ የሚባለው የሥልጣን ክፍል እንደሌለ ይቆጠራል፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም የአስተዳደር፣ የልማት፣ የሹመት ወዘተ. ጉዳይ የሚንቆረቆረው በበርጫ ወቅት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጫት መቃም እስከ ምሽቱ ስለሚዘልቅ የከተማና የእርሻ ቦታ ሽያጭ ድርድር መናኸሪያ በመሆን ከፍተኛ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር የሚከናወንበት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ሰዎች ቤታቸው ጓሮ ካናቢስ (ሐሺሽ) ተክለው ቢገኙ እንደሚከሰሱና እንደሚቀጡበት ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን አደገኛነቱ ከሐሺሽ የማይተናነሰው ጫት በግላጭ ያውም ባልተገባ መንገድ ጥቅም ላይ ሲውል ዝም ማለት ጥፋትን መጋበዝ ይሆናል፡፡ ጫት ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለአካባቢም አደጋ እንዳለው የሐሮማያ ሐይቅ ምሳሌ ነው፡፡ የጫት እርሻዎች መብዛትና በሐይቁ ውኃ መጠቀማቸው ሐይቁን ሊያደርቀው ችሏል፡፡ የጫት ተጠቃሚነት ወደ ሱስ ሲዛመት፣ የአዕምሮ መቃወስን ያስከትላል፡፡ በቤተሰብ ላይ የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ያደርሳል፡፡ ለስንፈተ ወሲብም ምክንያት ይሆናል፡፡ በመሆኑም በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ያውም በሥራ ሰዓት ጫትን መጠቀም በሕግ ክልከላ እንዲደረግበት ማድረጉ ለነገ የማይባል ነው፡፡

(ከድጃ ኡመር፣ ከሐረር)

* * * * * * *

ስታዲየም ዙሪያ መጠጥ መሸጥ ስለተከለከለ ሁከት አይወገድም

ዳጎስ ባሉ ገጾች ታጅቦ በየሳምንቱ የሚወጣውን ሪፖርተር ጋዜጣ በዘመኑ ቴክኖሎጂ አማካይነት በኢንተርኔት ሳነብ አንድ ርዕስ ትኩረቴን ሳበውና በደንብ አነበብኩት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሐሳቡን በማጠንጠንና በማፅደቅ በአዲስ አበባ ስታዲየም ዙሪያ ያሉ ምግብ ቤቶች በስታዲየሙ አካባቢ የአልኮል መጠጥ በመሸጥ ለሚነሱ ሁከትና ረብሻዎች ሁሉ እሳት ለኳሽ እንደሆኑ በመግለጽ፣ ዘወትር ከቀኑ 11 ሰዓት በኋላ የአልኮል መጠጥ ሽያጭ እንዳይፈጽሙ የሚከለክል ሕግ መረቀቁንና ለማፅደቅም በማኮብኮብ ላይ እንደሆነ ጋዜጣው አስነብቧል፡፡ ‹‹ጉድ ነሽ የአንኮበር ቅጠል›› አለ የመንዝ ገበሬ ይሏል አሁን ነው፡፡ ይህንን የአትጠጡ አጀንዳ ወደ ምክር ቤቱ ይዞ የቀረበው አካል አንድ ወሳኝ ጉዳይ አላየም፡፡ በምክር ቤቱ የሚመለከተው ክፍል ይህን አጀንዳ ቀርጾ ሲወያይ ነገሮችን ግራና ቀኝ  በማገናዘብ፣ ጠቃሚና ጎጂ ጎኑን፣ ሕዝብ የሚለውን፣ የመብት ጉዳይ ወዘተ. ያሉንት ነጥቦች ሁሉ ለምን ማየት እንደተሳናቸው አልገባኝም፡፡

ልብ በሉ ይህ በቀደመው ዘመን አንድ ለእናቱ የነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየም፣ ኢትዮጵያ የአሥረኛውን የአፍሪካ ጨዋታ ከማዘጋጀቷ በፊት የስታዲየሙ ዙሪያ በሙሉ  የከተማው ማዘጋጃ ቤትም በቅጡ በሚያውቀው አግባብ መፀዳጃ ቤት ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ በስታዲየሙ የሚካሄደውን ጨዋታ እያየን ሳለ ከጠራራው ፀሐይ ጋር ተዳምሮ የሚመጣው የከረፋ ሽታ ትልቅ የበሽታ ምንጭ ነበር፡፡ ነፍሳቸውን ይማርና ጋሽ ይድንቃቸው ተሰማ በሰጡት አመራር  የከረፋው መፀዳጃ ሥፍራ ግሩም በሆኑ የንግድ ቤቶች ተቀይሮ ላለፉት 35 እና 40 ዓመታት ለእግር ኳስ ፌዴሬሽን ቋሚ የገቢ ምንጭ ከመሆን ባሻገር ለስፖርት አፍቃሪውም የመዝናኛ ቦታ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ይህን መጣጥፍ ስሰድ በስማ በለው አይደለም፡፡ ‹‹ማን ያርዳ የቀበረ ማን ይናገር የነበረ፤›› እንደምንለው በዓይኔ ያስተዋልኩትን ነው የጻፍኩት፡፡ የኳስ ጥበብ በፍቅር በሚታይበት ዘመን መቻልና ጊዮርጊስ፣ ንብና ሕንፃ፣ መብራትና መድኅን የሚያደርጉትን ጉደኛ ጨዋታ ለመመልከት ወደ ስታዲየም ስናቀና በስታዲየም ዙሪያ የሚገኙት ምግብ ቤቶች ድንቅ የሜታና የጊዮርጊስ ድራፍት ቢራ በ0.85 ሳንቲም ሒሳብ ግጥም አርገን፣ ካስፈለገም የሳሪስ ቀይ ወይን ጠጅ ጨምረንበት፤ አለያም የመምሩን ጠጅ እኔ ነኝ ካለ ግሩም የጐድን ጥብስ ጋር ሲጥ አድርገን ተዝናንተን እንገባ ነበር፡፡

ረብሻም ሁካታም ሳይፈጠር ተከባብረን፣ ተፋቅረን ለምንደግፈው ክለብ እስከ ጨዋታ ማብቂያ ጮኸን ተጯጩኸን እንወጣ ነበር፡፡ እነሆ ዛሬ መጠጥ እንዳይሸጡ ገደብ ሊጣልባቸው ዳር ዳር የተባሉት መዝናኛ ቤቶች ከቶ በምን መስፈርት ይሆን መጠጥ እንዳትሸጡ የሚል ሕግ ሊጣልባቸው የተነሳው? ረብሻንና ሁካታን የሚፈልግ፣ ግብረ ገብ የጎደለው ሰው እኮ ከስታዲየም ዙሪያ በቅርብ ርቀት ከሚገኙ መዝናኛ ቤቶች ጥግብ ብሎ ጠጥቶ ከስታዲየሙ በመገኘት ለመረበሽ ማን ከልክሎት?

 በሠለጠኑት አገሮች ውስጥ ራሴ የፈጸምኩትን ልናገር፡፡ ጠንካራ የክለብ ጨዋታ ለመመልከት ወደ ስታዲየም ስንዘልቅ፣ በስታዲየሙ ግቢ ውስጥ ካሉ ምግብ ቤቶች በፕላስቲክ ብርጭቆ የተሞሉና የአልኮል መጠናቸው ከ4.5 እስከ ስድስት በመቶ የሆኑ ቢራዎችን ተጎንጭተን፣ ካስፈለገንም ተጨማሪ ቢራ ገዝተን በመግባት ጨዋታ እንኮመኩማለን፡፡ እንዲያውም ለስታዲየሙ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገቡት በዚያው ስታዲየም ዙሪያ የሚገኙ ልዩ ልዩ የንግድ ቤቶች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

እነዚህ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ከመዝናኛ ቦታዎች መካከል የሚመደቡ ናቸው፡፡ ለሰዓታት ተቀምጦ በስፖርት ውድድሮች ሲዝናና የሚውለውን ሰው ሁሉ ባዶ ሆድህን፣ ጥማትህን ችለህ ቁጭ በል ማለት ቅጣት ይመስለኛል፡፡

አለመታደል ሆኖ በአገሬ ከሥልጣን እርካብ ላይ ጉብ የሚሉ አብዛኞቹ ሰዎች ማለት ይቻላል ‹‹በዚህ ማለፍ ክልክል ነው!››፣ ‹‹መቆም ክልክል ነው!››፣ ‹‹ፎቶ ግራፍ ማነሳት ክልክል ነው!››፣ ‹‹መጻፍ ክልክል ነው!›› ወዘተ የሚሉ የክልከላ አዋጆችን ያበዛሉ፡፡ ይኸው ዛሬ ደግሞ ‹‹መጠጣት ክልክል ነው!›› ይሉናል፡፡ ገፋ ሲልማ ‹‹ሀብታሞች ፎቅ ሊሠሩ ነውና እዚህ አካባቢ መኖር ክልክል ነው!›› የሚል መመርያ ለማውጣት አይጣደፉ ይሆን? በአንፃሩ ለአካባቢው ነዋሪ አንዲት የቆሻሻ መጣያ ገንዳ ለማኖር ዓመት ከመንፈቅ ሲመላለሱ  ቢክርሙ እንኳ ቀና ምላሽ ሊገኙ ለዓይን እንኳ የሚጸየፉ ሹመኞች አይታጡም፡፡

እውን በስታዲየሙ ዙሪያ ያሉ ምግብ ቤቶች ድራፍትና ቢራ እንዳትሸጡ በመባላቸው የስታዲየሙ ሁካታ ይወገዳል? ከዚህ የለየለት ስሜታዊ ውሳኔ ወጥተን የኳስ ደጋፊውን የሁካታ ምንጭ በሠለጠነና በሰከነ ህሊና እናስብ፡፡ መፍትሔው በእጃችን ነው፡፡ ቸር ያገናኘን፡፡

(ቧዘ ነኝ፣ ከስዊድን ስቶክሆልም)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...