Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊበእግር እየተጓዙ የማስተማር መርህ

  በእግር እየተጓዙ የማስተማር መርህ

  ቀን:

  እንደወትሯቸው ማልደው ተነስተው ቤተ ክርስቲያን ለመሳለም ተያይዘው ወጥተዋል፡፡ ልጆቻቸውም እነሱን ተከትለው በየፊናቸው ተሰማርተዋል፡፡ ዕለቱን በዚህ መልኩ በተለመደው ሁኔታ የጀመሩት ቢሆንም ፍጻሜው ግን ልብ የሚሰብር ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለመሳለም የወጡት ጥንዶች ፀሎታቸውን አድርሰው ፈጣሪያቸውን አመስግነው ሳያበቁ ያልተጠበቀ አደጋ ደረሰባቸው፡፡

  አንድ ሰው መኪና አቁሞ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ገባ፡፡ መኪናውን ሲያቆም ተገቢውን ጥንቃቄ አላደረገም ነበረና ድንገት መኪናዋ ቁልቁል ወደ ቤተክርስቲያኑ ነጎደች፡፡ ሁሉ ነገር በፍጥነት ነበርና ማንም ማንንም የማዳን ጊዜ አልነበረውም፡፡ ቁልቁል የወረደችው መኪናዋ ቤተ ክርስቲያኑ ደጃፍ ሆነው ፀሎት ሲያደርሱ በነበሩት ባለትዳሮች ላይ ወጣች፡፡ ክፉኛ ጎድቷቸው ስለነበር ሆስፒታል ሳይደርሱ ሕይወታቸው አለፈ፡፡ ይህ የተከሰተው የዛሬ አራት አመት አካባቢ ነው፡፡

  አጋጣሚው ለሟቾቹ ልጅ አማኑኤል ኪዳነሣህለ፣ ወላጆቹን እንደወጡ ስላስቀራቸው የትራፊክ አደጋ ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እንዲሠራ አነሳሳው፡፡ 33 ዓመቱ ሲሆን፣ ተወልዶ ያደገው መቐለ ከተማ ነው፡፡ በወላጆቹ ላይ  ስለደረሰው አደጋ እሱና ሁለት ታናናሽ ወንድሞቹ የሰሙት በስልክ እንደነበር ይናገራል፡፡

  ባልተጠበቀ አጋጣሚ ወላጆቹን ያሳጣው የትራፊክ አደጋ በቸልተኝነት የተከሰተ መሆኑ ሁሌም እንዲያዝን አድርጎታል፡፡ ይሁንና ከመቆጨት ባለፈ ተመሳሳይ አደጋዎች እንዳይከሰቱ በኤችአይቪ ዙሪያ ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ከሚሠራ ጓደኛው ጋር በመሆን ስለትራፊክ ደህንነት በማስተማር የበኩሉን እያደረገ ይገኛል፡፡ ስራውን የሚሰሩት ከቦታ ቦታ ከክልል ክልል የእግር ጉዞ በማድረግ ነው፡፡

   አብረውት በመሥራት ላይ የሚገኙት ዳንኤል የማነና ሀፍቶም ገብረጊዮርጊስ  የተባሉት ጓደኞቹ ናቸው፡፡ ዳንኤል ተወልዶ ያደገው አክሱም ከተማ ነው፡፡ ኤርትራ ይኖሩ የነበሩ ወላጅ እናቱ ጋርም የተወሰነ ጊዜ ኖሯል፡፡ ኢትዮጵያ ገብተው መኖር የሚችሉበት አጋጣሚ ሲፈጠር፣ ከእናቱ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡ ይሁንና በወላጆቹ መካከል ስምምነት ባለመኖሩ  እናትና አባቱ ይኖሩ የነበሩት ተለያይተው ነበር፡፡ እሱም ያደገው በአያቶቹ እጅ ነው፡፡

  በወቅቱ ገና ልጅ ስለነበር የወላጆቹ ተለያይቶ መኖር ይህንን ያህል አላሳሰበውም፡፡ ሙሉ ትኩረቱም የነበረው በሚያስደስተው የኪነ ጥበብ ሥራ ላይ ነበር፡፡ በአካባቢው የተለያዩ ኪነጥበባዊ ስራዎችን ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ይሰራ ነበር፡፡ ‹‹ንግሥተ ሣባ የሚባል ክበብ አቋቁመን ነበር፡፡ በወቅቱ የተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮችና ኤችአይቪ ኤድስ ላይ ድራማዎችና ሙዚቃ በማቅረብ ሕዝቡን እናስተምር ነበር›› ሲል ጅምሩ እንዴት እንደበር ያስታውሳል፡፡

  እንደ ዝንባሌ ይቆጥረው፣ በትርፍ ጊዜ ይሰራ የነበረው ስራ ህይወቱ እንደሚሆን የገባው ግን ቆይቶ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት አዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩት ወላጅ አባቱ ወደ ትግራይ በመሄድ ልጃቸው ዳንኤልን ያገኙታል፡፡ አዲስ አበባ አምጥተው እንደሚያስተምሩትና የአባትነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ ቃል ገብተውለት ተለያዩ፡፡

  በሐሳባቸው ተስማምቶ ስለጉዳዩ ለእናቱ ለመንገር አክሱም ተመለሰ፡፡ አክሱም ሲደርስ ግን ፈፅሞ ያልጠበቀው ነገር አጋጠመው፡፡ ያሳደጉት አያቶቹ ቤት መግቢያ ላይ ድንኳን ተጥሎ ይለቀሳል፡፡ ፈጽሞ ያልጠበቀው ነገር ቢሆንም ድንኳኑን ሲያይ በዕድሜ የገፉት አያቱ አልፈው እንደሆነ ገመተ፡፡ ወደ ውስጥ ሲገባ ግን አያቶቹም ሆነ ወላጅ እናቱ በህይወት መኖራቸውን አረጋገጠ፡፡

  ሁኔታው ግራ አጋብቶት ሳለ ከቀናት በፊት አግኝቷቸው የነበሩት አባቱ እንደሞቱ ተነገረው፡፡ ማመን እስኪያቅተው ተደናገጠ፡፡ ‹‹ስልክ አልነበረም ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ መረጃዎችን ማወቅ የሚቻለው በደብዳቤ አልያም በአካል በመሄድ ነው›› ሲል በመካከል የተፈጠረውን ክፍተት ያስረዳል፡፡

  አያቶቹ፣ አባቱ በሦስት ቀን በሽታ እንደሞቱ ቢነግሩትም ቆይቶ ግን ኤችአይቪ መሆኑን ሰማ፡፡ ‹‹ሳገኘው የሕመም ምልክት አይቼበት ነበር፡፡ ይሁንና ኤችአይቪ ይሆናል ብዬ አልጠረጠርኩም ነበር፤›› ይላል፡፡ የአባቱ ህልፈት ሳይወጣለት በዓመቱ እናቱም ተደገሙ፡፡ ከፈጣሪ የመጣ ቁጣ ያህል ተሰማው፡፡ በኤችአይቪ ምክንያት መሞታቸውን ከሐኪማቸው ሲሰማ ደግሞ ይበልጥ አዘነ፡፡

  ‹‹ለማኅበረሰቡ ስለ ኤችአይቪ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ስሠራ ቆይቼ ቤት ውስጥ የነበረውን ነገር ሳላውቅ በመቅረቴ ወላጆቼን አጣሁ፡፡ በጣም ነበር ያዘንኩት፡፡ በወቅቱ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት አልተጀመረም፡፡ ቢሆንም ግን ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ ሕይወታቸውን ማቆየት እችል ነበር፤›› በማለት ሙሉ ትኩረቱን በኤችአይቪ ላይ አድርጎ እንዲሠራ ያደረገውንና ከጓደኞቹ ጋር ተጣምሮ እንዲሰራ ያነሳሳውን አጋጣሚ ያስታውሳል፡፡

  ለጉዳዩ የበለጠ ትኩረት በመስጠት ከአክሱም እስከ አዲስ አበባ በእግር እየተጓዘ ስለ ኤችአይቪ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ለመሥራት ወሰነ፡፡ ‹‹በእግር እየተጓዝኩ ለመሥራት ያሰብኩት ማኅበረሰቡ ለጉዳዩ ክብደት ሰጥቶ እንዲሰማኝ ለማድረግ ነው›› ይላል፡፡

  ጓደኞቹ ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁና አብረውት እንዲሠሩ አደረገ፡፡ እነዚህ ጓደኞቹ አማኑኤልና ሌላኛው አብሯቸው የሚሠራው ሀፍቶም ገብረጊዮርጊስ ነው፡፡ በኤች አይቪ በመሥራት ላይ ሳሉ ነበር በአማኑኤል ወላጆች ላይ የደረሰውን የትራፊክ አደጋ ተከትሎ የትራፊክ ደኅንነት ጉዳይ አካትተው መሥራት የጀመሩት፡፡

  እስካሁን በአገሪቱ በተለያየ አቅጣጫ ጉዞ በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ እንደዋነኛ ሥራቸው አድርገው መሥራት ከጀመሩ ሦስት ዓመታትን ያስቆጠሩ ሲሆን፣ እስካሁን ከ200 በላይ የሚሆኑ ከተሞችን አዳርሰዋል፡፡ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው የእግር ጉዞ ሲያደርጉ ባንዲራ ለብሰው ነው፡፡ ‹‹በእግር እየተጓዙ ማስተማር መርሀችን ነው›› የሚለው ዳንኤል፣ ከቦታ ቦታ በሚዘዋወሩበት ወቅት ምንም ዓይነት የትራንስፖርት አገልግሎት እንደማይጠቀሙ ይናገራል፡፡

   ለአንድ ጉዞ ቢያንስ እስከ 10,000 ብር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይሁንና ይህንን ያህል ገንዘብ ለማግኘት ብዙ ይቸገራሉ፡፡ የተወሰነ ዕርዳታ የሚያደርጉላቸው አንዳንድ ድርጅቶችና ግለሰቦች ቢኖሩም፣ ወቅቱን ጠብቆ የሚገኝ ባለመሆኑ የሚንቀሳቀሱበትና ለአልጋ የሚከፍሉት አጥተው የተቸገሩባቸው ቀናት ብዙ መሆናቸውን አማኑኤል ይገልጻል፡፡ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ሲጓዙ የተለያዩ ገጠመኞችም ያስተናግዳሉ፡፡ እስከዛሬ ከገጠማቸው መካከል አንዳንዶቹን አስታውሰዋል፡፡

  በቀን 35 ኪሎ ሜትር ያህል የመጓዝ ልምድ አላቸው፡፡ ከደጀን እስከ ጎኃፅዮን ደርሶ መልስ 42 ኪሎ ሜትር ያህል መንገድ በአንድ ቀን ተጉዘዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ረዥም መንገዶችን ሲጓዙ የተለያዩ አውሬዎች ያጋጥሟቸዋል፡፡ በአንድ ወቅት የገጠማቸውንም አንዲህ ያስታውሳሉ፡፡

  ወደ ጎንደር መስመር በመጓዝ ላይ ሳሉ በአቋራጭ መንገድ መሄድ ይጀምራሉ፡፡ የክረምት ወቅት ነበረና መንገድ ላይ ደራሽ ጎርፍ ይዟቸው የሞት ሽረት ትግል አድርገው መትረፍ ቻሉ፡፡ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ፀጉረ ልውጦች ብለው በጥርጣሬ የሚመለከቷቸውም ብዙ ናቸው፡፡ ሲጓዙ የኢትዮጽያን እንዲሁም ሰላምና ኤችአይቪን የሚያመለክት ባንዲራ ይይዛሉ፡፡ በመንገዳቸው ባንዲራው ምንድነው ብለው የሚያፋጥጧቸው ያጋጥሟቸዋል፡፡

   ‹‹አንደኛው ሰውዬ አንዱ የኢትዮጵያ ባንዲራ ነው፣ ሌሎቹ ግን አዲስ የሚመጣው መንግሥት ባንዲራ ነው ብሎ አዋክቦናል›› ይላል፡፡ ሌቦች ናቸው ተብለው በዱላ ተደብድበውም ያውቃሉ፡፡ መንገድ አሳብረው ኪሎ ሜትሮችን ከተጓዙ በኋላ ወደ የትም ሊያደርሳቸው የማይችል የተራራ ጫፍ የደረሱበት ጊዜም አለ፡፡ ‹‹ወደ ኋላ መመለስ አንችልም ብዙ ኪሎ ሜትር ተጉዘናል፡፡ ከተራራው ጫፍ ላይ ለመውረድ የሚመች አይደለም፡፡ የምናደርገው ነገር ቢጠፋ የያዝናቸውን ዕቃዎች ወደ መሬት ወርውረን ከተራራው ለይ እየተንከባለልን ወረድን፡፡ ተራራው አፈርማ ስለነበር ከአንዱ ጓደኛችን በቀር ሳንጎዳ መንገዱን ጨርሰናል›› ሲል አማኑኤል የማይረሳቸውን የጉዞ ታሪክ ተናግሯል፡፡

  ሌላኛው የቡድኑ አባል ሀፍቶም ነው፡፡ በዚህ ተግባር ለመሰማራት እንደ ዳንኤልና አማኑኤል የተለየ ምክንያት ባይኖረውም፣ አብሯቸው መሥራት ከጀመረ ቆይቷል፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን በትግርኛና በአማርኛ ይሰጣሉ፡፡ ሀፍቶም ግን በኦሮሚኛ ቋንቋ ለማስተማር እንዲችል ኦሮሚች ቋንቋ እየተማረ ይገኛል፡፡

  በአሁኑ ወቅት የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት በመኖሩ ታማሚዎች እንደ በፊቱ አይሰቃዩም፡፡ ቤተሰብም አያስቸግሩም፡፡ እንደማንኛውም ሰው መድኃኒቱን እየተጠቀሙ ይኖራሉ፡፡ ይህ ኤችአይቪ ጠፍቷል የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ በኅብረተሰቡ ዘንድ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ‹‹ሞት ነው እንጂ የቀነሰው የቫይረሱ ሥርጭት አሁንም አለ›› የሚለው ዳንኤል፣ የመዘናጋት ነገር መኖሩንና ይናገራል፡፡ በትራፊክ አደጋ ላይም የግንዛቤ ችግር መኖሩንና ትኩረት ተደርጎበት ሊሠራበት እንደሚባ ገልጿል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...